የሓራምቤ ከዋክብት መሪ ፈረንሳያዊው ሴባስቲያን ሚኜ ለኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመጨረሻ የደሞዜ ይከፈለኝ ጥያቄ አስገብተዋል፡፡ የሃገሪቱ ፌዴሬሽን ጥያቄያቸውን ሰምቶ እስከ ጥቅምት አምስት ካልከፈላቸው ከኢትዮጵያ የደርሶ መልስ ጨዋታ ማግስት ኃላፊነታቸው ሊለቁ እንደሚችሉ ተናግረዋል::
ከዚህ በፊት ሃትሪክ ስፖርት እንደዘገበችው አሰልጣኙ ቡድኑን በኃላፊነት ከተረከቡ አምስት ወራት ብቻ ቢሆናቸውም እስካሁን የተከፈላቸው የሁለት ወራት ደሞዝ ብቻ ነው፡፡ የሓምሌ፣ የነሓሴና የመስከረም ወራት ደሞዛቸው እንዲሁም የማላዊና የጋናን ብሔራዊ ቡድኖች ያሸነፉበት ማበረታቻ ያልተከፈላቸው ሚስተር ሚኜ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አሰራር መንገፍገፋቸውንና ከኢትዮጵያ ቡድን የደርሶ መልስ ግጥሚያ በኋላ መልቀቅ እንደሚፈልጉ እየተነገረ ነው፡፡
የኬንያ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ሃላፊ ኒክ ምዌንድዋ አሰልጣኙ ኮስተር ያለ የይከፈለኝ ጥያቄ በይፋ ማስገባታቸውን አምነው ፌዴሬሽኑ ከመንግስት ጋር በመነጋገር የሳቸውንና የአሰልጣኞች ስታፍ ኣባላትን ደሞዝ ከኢትዮጵያ ጨዋታ በፊት ለመክፈል የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ሚስተር ምዌንድዋ ከኢትዮጵያጋ የሚያደርጉትን ጨዋታ አስመልክቶ በተጠራ ፕሬስ ኮንፈረንስ ላይ እንዳሉት “ከአምስቱ ወራት የከፈልናቸው የሁለት ወራት ደሞዛቸውን ብቻ ነው፡፡ ከነቤተሰባቸው በጥሩ ሆቴል ውስጥ እንዲኖሩ ማድረግ ብንችልም የሓምሌ፣ የነሐሴና የመስከረም ወራት ደሞዝ አልተከፈላቸውም፤ ይህንንም ተከትሎ እስከጥቅምት አምስት ድረስ እንድንከፍለው ጠይቆናል፡፡”
የፌዴሬሽን አለቃው “ጥያቄውን በጽሁፍ ነው ያስገባው፡፡ የክፍያው መዘግየት የአሰልጣኙ መነሳሳት ላይ ችግር ያስከትልበታል ብዬ አላስብም እሱ ሁሌም ከቡድኑ ጋር ውጤታማ መሆንን ትኩረት አድርጎ ይሰራል ይሁን እንጂ እኛም ግዴታችንን መወጣት አለብን” ብለዋል፡፡
“አሰልጣኙ ምን ለማድረግ እንዳሰበ አልገለጸልንም፤ ጥቄውን ግን አስገብቷል፡፡ ጥያቄው ምን ማለት እንደሆነ በደንብ እንረዳለን፤ ከዚህ በፊት በዊሊያምሰንና በአምሩሽ ደርሶብናል አሁን ደሞ በሚኜ እንዲደርስብን አንፈልግም ስለዚህም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል ገብቶልናል፤ ቀነ ገደቡ ከማለቁ በፊት መፍትሔ ያገኝለታል ብለን እንጠብቃለን፡፡”
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አያይዘውም የአሰልጣኙን፣ የረዳታቸውንና የቪዲዮ አሲሰታንታቸውን ደሞዝ የሚከፍለው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጋናን በሜዳዋ ያሸነፈችው ኬንያ የሴራሌኦን ቅጣት የሚጸና ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር በደርሶ መልስ ተጫውታ የምታስመዘግበው ውጤት የቡድኑን ወደዓለም ዋንጫ ማለፍ ወይም አለማለፍ የሚወስን ይሆናል፡፡ በምድቡ ውስጥ ጋና፣ ኬንያ፣ ቦትስዋናና ኢትዮጵያ የተመደቡ ሲሆን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ አራቱም ብሔራዊ ቡድኖች በሁለት ጨዋታ እኩል ሶስት ነጥብና እኩል የማለፍ እድል ይዘዋል፡፡
የኢትዮጵያና የኬንያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በባህር ዳር እሮብ መስከረም 30 ና በናይሮቢ ሰኞ ጥቅምት 4 ይደረጋሉ፡፡