ትግራይ ስታድየም ላይ የተካሄደው የወልዋሎ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ተጠናቋል። ወልዋሎዎች ከ5ተኛው ሳምንት የደርቢ ጨዋታ አይናለም ሃይሉን በዳዊት ወርቁ፣ካርሎስ ዳምጠውን በሰመረ ሀፍታይ፣አብዱላዚዝ ኬይታን በጃፋር ደሊል ሲቀይሩ ሀዋሳዎች በበኩላቸው በሲዳማ ቡና ከተሸነፈው ስብስብ 6 ተጨዋቾችን ቀይረው ወደ ማዳ ገብተዋል።ሀብቴ ከድር፣ወንድማገኝ ማዕረግ፣የተሻው ግዛው፣አክሊሉ ተፈራ፣ዘላለም ኢሳያስ፣ብርሀኑ በቀለ ወጥተው ቢሊንጌ ኢኖህ፣መሳይ ፓውሎስ፣መስፍን ታፈሰ፣ተስፋዬ መላኩ፣ሄኖክ ድልቢ፣ዳንኤል ደርቤ ገብተዋል።
ትላንትና ህይወቱን በድንገተኛ አደጋ ላጣው የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊ የህሊና ፀሎት በማካሄድ በተጀመረው የመጀመርያ አጋማሽ ሳቢ ጨዋታ ያልታየበት፣የተቆራረጡ ና አድራሻ የሌላቸው ረጃጅም ኳሶች የታዩበት ነበር።በ4-2-3-1 የጨዋታ ስልት ወደ ሜዳ የገቡት ወልዋሎዎች ከመስመር እየተነሱ በጁንያስ ናንጂቦ፣ኢታሙና ኩሜይኒ አማካኝነት እድሎችን ቢፈጥሩም ኳሱን ከመርበብ ጋር ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።በመጀመርያ 15 ደቂቃዎች ላይ ጥሩ የተንቀሳቀሱት ቢጫ ለሻሾቹ በኢታሙና ኩሜይኒ አማካኝነት ያገኝዋቸውን ሁለት እድሎች ናሚብያዊው አጥቂ ሳይጠቀምባቸው ቀርተዋል።
በተለይ ፍቃዱ ደነቀ መሀል ለመሀል አሾልኮለት በፍፁም ቅጣት ሳጥን በቀኝ በኩል የነበረው ኢታሙና ከቢሊንጋ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርትዋል።መረጋጋት የተሳናቸው የሀዋሳ ተከላካዮች ወልዋሎዎች ከመስመር እና ከመሃል ሚጥልዋቸውን ረጃጅም ኳሶች ለመከላካል ሲቸገሩ ታይቷል።የዚህ ማሳያ ሚሆኑት በተቀራራቢ ደቂቃዎች በሰመረ ሀፍታይ እና በጁንያስ ናንጂቦ የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው።በተለይ ጁንያስ ከመሀል ሜዳ የተላከለትን ኳስ በመጠቀም ሁለት ተጨዋቾን አታልሎ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ከኃላ የሀዋሳ ተከላካዮች ደርሰው ያስጣሉበት ቅጽበት ወልዋሎዎች በጨዋታው ያመከኑት አስቆጪ እድል ነበር።ከደቂቃ ወደ ደቂቃ መረጋጋት የታየባቸው ሀይቆቹ በመስፍን ታፈሰ
እና ብሩክ በየነ አማካኝነት እድሎችን ቢፈጥሩም የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታውን ባደረገው ጀፋር ደሊል ሊመለሱ ችለዋል።በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ላይ ከቀኝ መስመር ዳንኤል ደርቤ አሻምቶት ወጣቱ አጥቂ ብሩክ በየነ ተቆጣጥሮ ለመስፍን ታፈሰ እቀብሎት መስፍን ታፈሰ የመታውና ጃፋር ደሊል የመለሰው ኳስ የሀይቆቹ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።
- ማሰታውቂያ -
በፈጣን የሀዋሳዎች እንቅስቃሴ የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ሙከራዎችን ቢያስተናግድም በሁለቱም በኩል ግብ ሳያስተናግድ ተጠናቋል።ሀዋሳዎች ጨዋታው እንደተጀመረ በመስፍን ታፈሰ የግል ብቃት ያገኙትን እድል በወልዋሎዎች በኩል በጨዋታው ላይ ጥሩ በተንቀሳቀሰው ጃፋር ደሊል ሊመለስ ችሏል።ቀስ ብለው ወደ ጨዋታው የገቡት ወልዋሎዎች ከቀኝ መስመር በኢታሙና ኩሜይኒ ምስጋናው ዮውሃንስ እና ራምኬል ሎክ አማካኝነት በሚያሻግርዋቸው ኳሶች እድሎችን ፈጥረዋል።በሁለት ደቂቃ ልዩነት በጁንያስ ናንጂቦ እና ሰመረ ሀፍታይ የግምባር ኳሶች ያደረጉዋቸው ሙከራዎች የዚህ የመስመር እንቅስቃሴው ውጤት ናቸው።በተለይ ራምኬል ሎክ በግራ እግሩ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ጁንያንስ በግምባሩ ገጭቶት ቢሊንጋ በሚገርም ብቃት አድኖበታል።ጨዋታው እየገፋ በሄደ ቁጥር የመስመር አጨዋወታቸው ተገማች የሆነው የዮውሃንስ ሳህለ ልጆች የላውረንስ ላርቴ እና መሳይ ፓውሎስ ጥምረት መስበር አቅትዋቸው ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል።
የአዲሴ ካሳ ቡድን የሁለተኛው አጋማሽ አብዛኛውን ክፍለ ጊዜ ወደ ኃላ አፈግፍገው በመጫወት ነጥብ ተካፍለው ሊወጡ ችለዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ወልዋሎዎች ለ5ሳምንታት የተቆናጠጡትን የሊጉ መሪነት ወንበርን ለፋሲል ከነማ ሲያስረክቡ ሀይቆቹ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኃላ ነጥብ ማግኘት ችለዋል።