የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ዙርም በውድድር አመቱ ድል ማስመዝገብ ተስኖት የቆየው ሀዲያ ሆሳዕና በሜዳው አቢዮ አርሳሞ ስታዲየም ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤት እየራቀው የመጣውን ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ በማሸነፍ በሊጉ የመጀመሪያውን ድል ማስመዝገብ ችሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ሀዲያ ሆሳዕና ከተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በተሻለ ሁኔታ በኳስ ቁጥጥር እና ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ ብልጫ ወስዷል። በተለይም ሱራፌል ዳንኤል ወደ ጎል አክርሮ የመታው ኳስ በሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ እጅ ላይ አርፋለች ከዚያ በኋላ ሀዲያ ሆሳዕና በደስታ ጊቻሞ እና በይሁን እንደሻው አማካኝነት ያደረጉት የጎል ሙከራ አስደንጋጭ ነበር። ብልጫ ወስደው የተጫወቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ37ኛው ደቂቃ ላይ ቢስማርክ አፒያ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ሱራፌል ዳንኤል በግንባሩ በመግጨት በመጀመሪያው አጋማሽ ሀዲያ ሆሳዕና መሪ የሆነበትን ጎል አስቆጥሯል።
ከጎሏ መቆጠር በኋላም ሀዲያ ሆሳዕና ይበልጥ ጫና ፈጥሮ ተጫውቷል።
ከእረፍት መልስ በመሃል ሜዳው ብልጫ ወስደው የተንቀሳቁሱት ሲዳማ ቡናዎች በይበልጥ ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል። ባደረጉት የጎል ሙከራም ተቀይሮ የገባው አማኑኤል እንዳለ ከረጅሙ አክርሮ የመታው ኳስ በሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች ተነክታ የግብ ጠባቂውን ታሪክ ጌትነት አቅጣጫ በመቀየር 67ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ላይ በማሳረፍ 1-1 መሆን ችለው ነበር ብዙም ሳይቆይ ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል በተደጋጋሚ መቅረብ የቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ቢስማርክ ኦፖንግ የመታት ኳስ ከመረብ ላይ በማረፍ ሀዲያ ሆሳዕና ውጤቱን ወደ 2- 1 መሪነት መቀየር ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ የተጫወቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ትዕግስቱ አበራንና ፍራሆል መንግስቱን ቀይረው በማስገባት ውጤቱን አስጠብቀው ወጥተዋል።
ጨዋታው በሀዲያ ሆሳዕና 2- 1 በሆነ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና በሜዳው ካደረጋቸው ጨዋታዎች የመጀመሪያውን 3 ነጥብ በማስመዝገብ ነጥቡን ወደ አምስት ከፍ በማድረግ ተስፋውን አለምልሟል።
ሊጉን ወልዋሎ አ.ዩ. በ14 ነጥቦች ሲመራ መቐለ 70 እ. እና ፋሲል ከተማ በቅደም ተከተል በ13 እና በ12 ነጥቦች 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የኮከብ ግብ አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ7 ግቦች ቀዳሚ ሲሆን የባህርዳር ከነማው ፍፁም ዓለሙ በ6 እንዲሁም የመቐለ 70 እ. አማኑኤል ገ/ሚካኤል በ5ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
ፎቶ ምንጭ ሆሳዕና ስፖርት