በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት የዕለተ ቅዳሜ የመጨረሻ ጨዋታ መከላከያ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክን አገናኝቶ በመከላከያ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው 8ኛ ደቂቃ ላይ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ ከቀኝ በኩል ያሻገረለትን ኳስ የተሻ ግዛው ከግቡ ጋር ፊትለፊት ተገናኝቶ ያገኘውን ኳስ ሞክሮት የግቡ አግዳሚ ገጭቶበታል። ይህ አጋጣሚ መከላከያን ቀዳሚ ማድረግ የሚችል እና በመከላከያ በኩል እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በዚህ ጨዋታ ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጨዋታውን ለማሸነፍ የታየባቸው ተነሳሽነት በግልፅ የሚደነቅ ነበር። በተለይ አሰልጣኝ ስዩም ከበደን የቀጠረው መከላከያ በየተሻ ግዛው፣ ምንይሉ ወንድሙ እና ሳሙኤል ሳሊሶ የፊት መስመር መሪነት የኢትዮ-ኤሌክትሪክን የግብ ክልል ለመድፈር ተደጋጋሚ ጥረትን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ለዚህ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ደግሞ በዝውውር መስኮቱ ከፋሲል ከተማ መከላከያን የተቀላቀለው አማካዩ ዳዊት እስጢፋኖስ ትልቁን ሚና መጫወት ችሏል።
15ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ሳሙኤል ሳሊሶ ለየተሻ ግዛው በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ በቀጥታ ወደግብ ሞክሮት የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሌማን አቡ በቀላሉ ይዞታል። 25ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ሄኖክ ካሳሁን ከሳጥን ውጪ አግኝቶ የሞከረው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ 4ደቂቃዎች በኋላ 29ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ሳሙኤል ሳሊሶ ከሳጥን ውጪ አግኝቶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። ከዚህ በኋላ ግን ጨዋታው እንደአጀማመሩ መሆን ሳይችል ቀርቶ በመሀል ሜዳ ሽኩቻ፣ ቶሎ ቶሎ ኳስ በመቀማማት እና ፍትጊያ የበዛበት ሆኖ ተስተውሏል። ሆኖም 42ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ዳዊት እስጢፋኖስ በቀጥታ ወደግብ ሞክሮት የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሌማን አቡ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። ከ1ደቂቃ በኋላ 43ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ የኢትዮ-ኤሌክትሪክን ተከላካዮች መዘናጋት ተጠቅሞ ከመሀከላቸው በመሹለክ ያገኘውን ኳስ ወደግብነት ቀይሮት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በዚህም ውጤት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው መቅረብ የቻሉት ኢትዮ-ኤሌክትሪኮች የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ይህንንም ተከትሎ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ 46ኛው ደቂቃ ላይ በዚህ የዝውውር መስኮት አዳማ ከተማን ለቆ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን የተቀላቀለው አንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ከቀኝ ክንፍ በኩል በቀጥታ ወደግብ የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ የመከላከያውን ግብ ጠባቂ መትቶ ወደውጭ በመውጣት የማዕዘን ምት መሆን ችሏል። ከዚህ ሙከራ 5ደቂቃዎች በኋላ 51ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ተክሉ ተስፋዬ በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ አዲሱ ፈራሚ ታፈሰ ተስፋዬ በግሩም ሁኔታ ወደግብነት ቀይሮት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር። ሆኖም የኢትዮ-ኤሌክትሪክ አቻነት መዝለቅ የቻለው ለ5ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 56ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ ትንሽ አለፍ ብሎ የተገኘውን ቅጣት ምት የመከላከያው አምበል ሽመልስ ተገኝ በቀጥታ ወደግብ መቶት በማስቆጠር መከላከያን ዳግም ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከዚህም በኋላ መከላከያዎች ቅድሚያ ይዘውት የገቡትን የ4-4-2 ዳይመንድ የጨዋታ ስልት ወደ 4-2-3-1 በመቀየር ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥንቃቄ ያለው ጨዋታን ለመጫወት መርጠዋል። 62ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ ያመሸው ታፈሰ ተስፋዬ ከመሀል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ በድንቅ ሁኔታ ወደግብ ቢሞክረውም የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ በቀላሉ ይዞታል። ከዚህች ሙከራም በኋላ ይሄ ነው የሚባል ሙከራ እና ተመልካችን የሚስብ ጨዋታ ያልተስተዋለ ሲሆን ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5ደቂቃዎች ሲቀሩት 85ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደሜዳ የገባው የመከላከያው ማራኪ ወርቁ ከተከላካዮች መሀል ሾልኮ በመውጣት እንዲሁም የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ በፑንት(ቺፕ) በማድረግ ግሩም ግብ አስቆጥሮ መከላከያ ሙሉ 3ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሎታል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ስዩም ከበደ — መከላከያ
- ማሰታውቂያ -
“እንግዲህ የዛሬው ጨዋታ ጥሩ ነበር፤ ለኔም እንደ መነሻ ለልጆቹም መነሳሻ ነው፤ ከዛ ባለፈ ጨዋታው ለኛም ለኢትዮ-ኤሌክትሪክም ወሳኝ ጨዋታ ነበር፤ ከሽንፈት መውጣት ራሱ ጥሩ ነገር ነው፤ ለኛ እንደ 6ነጥብ ነው። በመጀመሪያው ዙር የቡድኑ ድክመት አጨራረስ ነበር እሱን ለመቅረፍ ስራዎችን እየሰራን ነው፤ በቀጣይ ጨዋታዎች ተሻሽለን እንቀርባለን። በአጠቃላይ ግን በልጆቼ በጣም ደስተኛ ነኝ።”
ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ — ኢትዮ-ኤሌክትሪክ
“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ መከላከያ ጥሩ ቡድን ነው ሆኖም ግን በራሳችን ስህተቶች ተሸንፈን ወጥተናል፤ መጫወት የፈለግነው እንደዚህ አልነበረም፤ ስህተቶቻችን ብዙ ነበሩ እነዛን ለማረም እና ለማስተካከል ጠንክረን እንሰራለን።”