በስድስተ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ በሰበታ ከተማ እና ወላይታ ዲቻ መካከል ተደርጎ ሰበታዎች በፍፁም ገ/ማርያም ብቸኛ ግብ ጣፋጭ ነጥብ ማግኘት ችሏል።
ጨዋታው ከወትሮው በተለየ መልኩ በጥቂት ደጋፊዎች ጅማርዎን ሲያደርግ በጨዋታው ጅማሮ ላይ ወላይታ ዲቻዎች በማጥቃት ሲጀምሩ ያገኙትን የማእዘን ምት አንተነህ ጉግሳ ሲያሻማው ወንድሙ ቸርነት ጉግሳ ያመለጠው ኳስ የጨዋታው ጅማሮ ድምቀት ሊሰጠው ችሏል። በአራተኛው ደቂቃ ሰበታዎች በፍፁም ገ/ማርያም አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ ወላይታ ዲቻዎች ኳስን ከራሳችው የግብ ክልል መስረተው ለመጫወት ሲያሰቡ ይህም ለጥቃት ሲያጋልጣቸው በተደጋጋሚ ተስተውሏል። ሰበታዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን መስኡድ መሀመድ ከመሀል ሜዳ አሾልኮ አቅብሎት የሰበታ ተጫዋቾች ሳይጠቀሙበት የቀረው ተጠቃሹ ነው።
- ማሰታውቂያ -
ሰበታዎች በአሊ ባድራ በቀኝ መስመር በኩል ጨዋታቸውን አድረገው ለመጫወት የፈለጉ ሲሆን ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በእሱ ሲያደርጉ በአንድ አጋጣሚ አክርሮ የመታውን ኳስ የወላይታ ዲቻ ግብ ጠባቂ መኳንንት አሸናፊ ያዳናቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ወላይታ ዲቻ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ በዳንኤል ዳዊት እና በቸርነት ጥሩ ጥምረት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል። በተለይም ደግሞ ዳንኤል ዳዊት ጥሩ የሚባል ኳስ አሾልኮ ቢሰጠውም ቸርነት ጉግሳ መዘናጋቱን ተከትሎ ሳይጠቀምበት የቀረበት አጋጣሚ በወላይታ ዲቻ በኩል የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
በጨዋታው ሂደት ላይ ታደለ መንገሻ ላይ በተሰራ ጥፋት የወላይታው በረከት ወልዴ የመጀመሪያውን የማስጠንቀቂያ ካርድ ሊመለከት ችሏል። ሰበታዎች ኳስን ይዘው መጫወት ቢችሉም ወደ ግብ ለመቀየር ተስኗቸው ታይቷል። ቢሆንም ግን ሰበታዎች በተለይም አስቻለው ግርማ ያደርጋቸው የነበሩ ሙከራዎች በመኳንንት አሸናፊ ሲከሽፉ ተስተውሏል። በአሊ ባድራ ቀኝ መስመሩን በመያዝ ተደጋጋሚ ጫናዎችን ሲፈጥሩ የቆዩት ሰበታዎች ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ኢብራሂም ከድር ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ፍፁም ገ/ ማርያም ወደ ግብ በመቀየር ሶስተኛ ተከታታይ ጎሉን ሲያስቆጥር ሰበታዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ሰበታዎች በአሊ ባድራ ከሳጥን ውጪ አስደንጋጭ ሙከራ ቢያደርግም በእለቱ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው መኳንንት አሸናፊ ወደ ውጪ አውጥቶበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ሰበታዎች በጉዳት ምክንያት ሁለት አስገዳጅ ቅያሪዎችን ለማድረግ ተገደዋል። ለመጀመሪያው ጎል መቆጠር ትልቅ ሚና የነበረው ኢብራሂም ከድርን በዳዊት እስጢፋኖስ እንዲሁም አስቻለው ግርማን በበሀይሉ አሰፋ ለመቀየር ተገደዋል። ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር መከላከል ላይ አተኩረው ውጤት ለማስጠበቅ የገቡት ሰበታዎች አልፎ አልፎም ቢሆን ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስትውሏል።
በተለይም ሀይለ ሚካኤል በግራ መስመር ወደ ሳጥን ኳስን አብዶ ሰርቶ ገብቶ አክርሮ የመታው እና መኳንንት ያወጣበት ሙከራ ተጠቃሽ ነው። በወላይታ ዲቻ በኩል በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ለማስቀየር ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ነቅለው በመውጣት ሲያጠቁ ተስተውለዋል። ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ኢላማውን ሳይጠብቅ እና በሰበታ ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጃይ ሲድንባቸው ታይቷል።
በሀይሉ አሰፋን(ቱሳ) በሁለተኛው አጋማሽ ቀይረው ማስገባት የቻሉት ሰበታዎች በፋሲሉ ጨዋታ ይታይ የነበረውን በቀኝ መስመር ከመስመር የማጥቃት አጨዋወትን ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ብዙ አስደንጋጭ ሙከራዎች ሳይስተዋሉበት ሲጠናቀቀ ሰበታ ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ በስምንት ነጥቦች ሌሎች ክለቦች ጨዋታ እስኪያደርጉ ድረስ በሊጉ የአምስተኛ ደረጃን በመያዝ ለመቀመጥ ችሏል።
ሊጉን ወልዋሎ አ.ዩ. እና መቐለ 70 እንደርታ በእኩል 10 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተለያይተው አንደኛ እና ሁለተኛ ሲሆኑ ሲዳማ ቡና በ9 ነጥቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል። የኮከብ ጎል አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም፣ የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ፣ የባህርዳር ከተማዎቹ ማማዱ ሲዲቤ እና ፍፁም ዓለሙ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነ በእኩል 4 ግቦች ሲመሩ አዲስ ግደይ፣ ዳዋ ሁቴሳ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ይገዙ ቦጋለ እና ሰመረ ሀፍተይ በእኩል 3ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል