በ3ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ የተደረጉ ሲሆን አዳማ ላይ ጅማ አባጅፋር ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው ጅማ አባጅፋር የመሪነቷን ግብ ለማግኘት 5ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀበት። 5ኛው ደቂቃ ላይ ኤርምያስ ኃይሉ ግብ አስቆጥሮ ባለ ሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ይህም ግብ ለጅማ አባጅፋር በ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያስቆጠረው የመጀመሪያው ግብ ሆኖ ተመዝግቧል። ከግቧ መቆጠር 2ደቂቃዎች በኋላ 7ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ብሩክ ገ/አብ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ሆኖም የጅማ አባጅፋር መሪነት መዝለቅ የቻለው ለ4 ደቂቃዎች ብቻ ነበር የሲዳማ ቡናው ዳዊት ተፈራ ያሻገረለትን ኳስ ይገዙ ቦጋለ በግንባሩ አስቆጥሮ እንግዳዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል። በፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ በተካሄደው በዚህ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ሲዳማ ቡናዎች ግብ ክልል መድረስ ችለዋል። ይህንንም ተከትሎ 12ኛው ደቂቃ ላይ አምረላ ደልታታ ግሩም ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አልፎ አልፎ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎችም አስደንጋጭ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። 16ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው አጥቂ አዲስ ግደይ ያገኘውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከዚህ ሙከራ 4ደቂቃዎች በኋላም አምረላ ደልታታ ያመለጠው ኳስ ባለሜዳዎቹን የሚያስቆጭ ነበር።
- ማሰታውቂያ -
የአቻነቷን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ መነቃቃት ያሳዩት ሲዳማ ቡናዎች ኳስ ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 39ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ የሞከረው ኳስ በግቡ አግዳሚ ላይ ወጥቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ፈጣን ጨዋታ ቢስተዋልበትም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ቤት ማምራት ችለዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ 47ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ግብ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን በጨዋታው መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር 1ደቂቃ በኋላ ይገዙ ቦጋለ የሲዳማ ቡናን መሪነት ለማጠናከር ግሩም እድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረለትን ኳስ አምረላ ደልታታ በግንባሩ ገጭቶት የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ ወደ ውጭ አውጥቶበታል። በተደጋጋሚ ወደ ጅማ አባጅፋር ግብ ክልል መድረስ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ያገኟቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻሉም። 60ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከግብ ጠባቂው ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። 65ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ ብቻውን ግልፅ እድል አግኝቶ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ኤልያስ አታሮ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል።
ከዚህች ሙከራ በኋላ ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደኋላ አፈግፍገው የተጫወቱ ሲሆን የጅማ አባጅፋሩ አምረላ ደልታታ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 4 ደቂቃዎች ሲቀረው 86ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ብሩክ ገ/አብ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወጥቷል። መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ሰዓት 93ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ከቆቅጣት ምት የሞከረውን ኳስ አምረላ አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም የእለቱ አርቢትር አምረላን ጥፋት ሰረተሀል ብለው ግቡን ሽረውታል። በዚሁም ጨዋታው ተጠናቆ ጅማ አባጅፋር የሊጉ የመጀመሪያውን ሽንፈት አስተናግዷል።
ውጤቱንም ተከትሎ ሲዳማ በ6 ነጥቦች እና በ 1ንጹሕ ግብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ጅማ አባጅፋር በአንፃሩ በ2 ነጥብ እና በ1 የግብ እዳ 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።