ሽረ አንዳስላሰ ስታድየም እድሳት ላይ መሆኑን ተከትሎ የ2012 የመጀመርያ ጨዋታቸውን በትግራይ ስታድየም ያካሄዱት ስሑል ሽረዎች በመጀመርያው አጋማሽ በዲድዬ ሌብሪ አማካኝነት ባስቆጠሩት ግብ ታግዘው የዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታቸውን በድል ጀምረዋል።ስሑል ሽረዎች አዳዲስ ፈራሚዎቻቸውን ምንተስኖት አሎ፣በረከት ተሰማ፣አብዱልለጢፍ መሀመድ፣ዲድዬ ሌብሪ፣አክሊሉ ዋለልኝን ቀዋሚ 11 ውስጥ ሲያካትቱ በካሳዬ አራጌ ሚመሩ ቡናዎች በበኩላቸው አዲስ አበባ ዋንጫ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከገጠመው ቀዋሚ 11 አማኑኤል ዮውሃንስን በአህመድ ረሺድ፣ታፈሰ ሰለሞን በአላዛር ሽመልስ በመቀየር ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ቡና የተቆራረጡ ቅብብሎች የስሁል ሽረ ፈጣን የማጥቃት ሽግግርና ተደጋጋሚ ሙከራዎች መጀመርያ አጋማሽ ላይ የታዩ የሁለቱም ቡድኖች እንቅስቃሴዎች ነበሩ።ቡናዎች ኳስን ከኃላ በሚጀምሩበት ጊዜ የስሁል ሽረ ተጨዋቾች ሰው በሰው በመጫን(pressing) ተደጋጋሚ ስህተቶች እንዲሰሩና ስህተቶችን በመጠቀም እድሎችን ለመፍጠር ያደረጉት ሙከራ ተሳክቶላቸው በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።በ4-2-3-1 አሰላለፍ ፊት ላይ በተጣመሩት በሁለቱም መስመር የተሰለፋት ዲድዬ ሌብሪና አብዱልለጢፍ መሀመድ ትኩረት ያደረገው የሽረዎች ፈጣን ማጥቃት እንቅስቃሴ በ2ኛው ደቂቃ በሳሊፍ ፎፎና ሙከራ ጅማሬውን አድርጓል።በተለይ በግራ መስመር የተሰለፈው አብዱልለጢፍ ሚያሻማቸው ኳሶች የቡና ተከላካይ ክፍልን ሲያስቸግር ታይቷል።የዚህም ውጤት በ21ኛው ደቂቃ አብዱልለጢፍ ከግራ መስመር ያሻማው ኳስ ሳሊፍ ፎፎና በጥሩ ሁኔታ ለዲድዬ ሌብሪ አቀብሎት ዲድዬ በጥሩ አጨራረስ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።ኢትዮጵያ ቡናዎች ከግቡ መቆጠር በኃላም በተመሳሳይ መንገድ በአጭር ቅብብል ለማለፍ ሚያደርጉት ሙከራ ቢያስቀጥሉም ሽግግር ላይ በነበራቸው ክፍተት የጠሩ የግብ እድሎች እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል።ስሑል ሽረዎች በተቃራኒው ከቡና ተጨዋቾች እግር በሚነጥቅዋቸው ኳሶችን በመጠቀም በያሰር ሙገርዋ፣ሄኖክ ዋለልኝ አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጨዋታው ላይ ጥሩ በተንቀሳቀሰው ተክለማርያም ሻንቆ ተመልሶባቸዋል።
- ማሰታውቂያ -
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደ መጀመርያው አጋማሽ በተመሳሳይ መልኩ ኳሱን ከራሳቸው ክፍል በአጭር ቅብብል ለመውጣት ቢሞክሩም በሜዳው የመጨረሻ ክፍል ሲደርሱ የነበራቸው አለመግባባት የስሁል ሽረን ተከላካይ ክፍልን እንዳያስከፍቱ እንቅፋት ሆኗቸው ታይቷል። መሀል ላይ የተሰለፋት ፍቅረየሱስ ተክለብርሀን፣አለም አንተ ካሳ ከአጥቂው እና ከተከላካይ ክፍል የነበራቸው ቅንጅት ጥሩ ሚባል አለመሆኑ ቡናዎች በቀላሉ በስሁል ሽረ የጨዋታ እቅድ ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ አድርጓቸዋል።ስሁላውያን በፈጣን መልሶ ማጥቃት በሁለተኛው አጋማሽ በዲድዬ ሌብሪ፣ሳሊፍ ፎፎና ና አብዱልለጢፍ አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል።