በትግራይ ስታድየም ፋሲል ከነማን ያስተናገዱት ስሑል ሽረዎች በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች በሳሊፍ ፎፎና ና አብዱልለጢፍ መሐመድ አማካኝነት ባስቆጠርዋቸው ሁለት ግቦች ታግዘው ወሳኝ ሥስት ነጥብ አግኝተዋል።ስሑል ሽረዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ ወላይታ ድቻን ካሸነፈው ስብስብ ሸዊት ዮውሀንስን በአብዱልለጢፍ መሐመድ፣ክብሮም ብርሀነን በአዳም ማሳላቺ ሲቀይሩ እንግዶቹ ፋሲላውያን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፈው ቡድን ምንም ቅያሬ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
የስሑላውያን የበላይነት በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ በሚታወቁበት የመስመር አጨዋወት በርካታ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።በአንፃሩ ፋሲሎች ኳስን ከኃላ በመመስረት በአጫጭር ቅብብሎች ለመውጣት በሚሞክሩበት ጊዜ በሚሳሳትዋቸው ቅብብሎች ለበርካታ አደገኛ ሙከራዎች ሊጋለጡ ችለዋል።ለዚህም ማሳያ በጨዋታው የመጀመርያ 20 ደቂቃዎች ላይ የተደረጉ ሙከራዎችን ማየት ይቻላል።
- ማሰታውቂያ -
አምሳሉ ጥላሁን መሀል ላይ በሰራው ስህተት የተገኘውን ኳስ ያሰር ሙገርዋ አግኝቶት ከሳሊፍ ጋር አንድ ሁለት በመጫወት ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሳትን ገብቶ የመታው ኳስ የግቡ ቀዋሚ ብረት መልሶበታል፤አሁንም ብዙ ሳይቆይ ፋሲሎች ከኃላ የሚሰሩት ስህተት በመጠቀም ያሰር ሙገርዋ ከግራ መስመር መሬት ለመሬት ያሻገረው ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሳሊፍ ፎፎና መትቶት ከግቡ ወደ ጎን ለትንሽ ወጥቷል።
የመስመር ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ስሑላውያን ዲዲዬ ሌብሪ ከቀኝ መስመር ያሻገረው አደገኛ ኳስ ለግቡ ቅርብ የነበረው መሐመድ ለጢፍ ሳያገኘው ቀርቶ ወደ ውጭ ወጥቷል።
የስሑል ሽረን የተደራጀ ና ከመሀል ሜዳ በቂ ሽፋን ሚያገኘው ተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት የተቸገሩት ፋሲል ከነማዎች በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ላይ ዓለምብርሀን ይግዛው ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሰብሮ በመግባት የሙጂብን እንቅስቃሴ አይቶ ያሾለከው ኳስ ሙጂብ ቃሲም መትቶት የግቡ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቷል።
እንደ መጀመርያው አጋማሽ በተመሳሳይ በባለሜዳዎቹ በላይነት የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ፤ በመጀመርያ 10 ደቂቃዎች የስሑል ሽረዎች ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን አሳይትዋል።
በግራ መስመር ከረመዳን የሱፍ ጋር ጥሩ ጥምረት የነበረው መሐመድ ለጢፍ ሁለት ተጨዋቾችን ቀንሶ በማለፍ አሻምቶት የተገኘውን ኳስ ጨዋታው ላይ በርካታ እድሎችን ሲያመክን የነበረው ሳሊፍ ፎፎና ሳይጠቀምበት ቀርትዋል።በተጨማሪ ዲድዬ ሌብሪ ከያሰር ሙገርዋ የተቀበለውን ኳስ ከአጥቂው ጋር በጥሩ ቅብብል የሜዳው 16 ከ50 ላይ ሆኖ ሲሞክረው ሚካኤል ሳማኪ አድኖበታል፤በተመሳሳይ መሀል ላይ ጥሩ የነበረው ያሰር ሙገርዋ በፍፁም ቅጣት ሳጥን በግራ በኩል ለነበረው ረመዳን የሱፍ ያቀበለው ጥሩ ኳስ የግራ መስመር ተከላካዩ ሲመታው ማሊያዊው ግብ ጠባቂ በጥሩ ሁኔታ አድኖበታል።
65ኛው ደቂቃ ላይ በተደረጉ ቅያሬዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱት ፋሲሎች ዓለምብርሀን ግዛው ከቀኝ መስመር ባሻማው ኳስ የተገኘውን እድል ሙጂብ ቃሲም በግምባሩ ለመግጨት ቢሞክርም ኳሱን ሳያገኘው ቀርቷል።
ጨዋታው ላይ ከመስመር እየተነሳ በርካታ እድሎችን የፈጠረው መሐመድ ለጢፍ 70 ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ሰብሮ በመግባት ያሻማው ኳስ ዲድዬ ሌብሪ ቢመታውም ከግቡ አናት ወደ ላይ ወጥቷል።
ጨዋታው እየገፋ ሲሄድ መረጋጋት የተስተዋለባቸው ፋሲሎች ከመስመር በሚጣሉ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል።መደበኛው ጨዋታ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ጨዋታውን የቀየረ ክስተት ሊከሰት ችሏል።ከቀኝ መስመር ዓወት ገብረሚካኤል ያሻማው ኳስ ሚካኤል ሳማኪ ለመያዝ በሚሞክርበት ጊዜ በፈጠረው ስህተት የተገኘውን ኳስ ኮትዲቫራዊው ሳሊፍ ፎፎና አስቆጥሮ ስሑል ሽረን መሪ ማድረግ ችሏል።
ጨዋታው ተጠናቅቆ ዳኛው በጨመሩት 4 የባከኑ ደቂቃዎች ላይ ፋሲሎች አቻ ሚያደርጋቸውን ግብ ለማግኘት በሚሞክሩበት ጊዜ ጨዋታው ላይ ድንቅ የነበረው መሐመድ ለጢፍ ከያሰር ሙገርዋ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ የስሑል ሽረን አሸናፊነት ማረጋገጥ ችልዋል።
ጨዋታውን ተከትሎ ስሑል ሽረዎች ሁለተኛ ደረጃነትን ከፋሲል ከነማ መረከብ ችለዋል።