በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታ ወደ ሶዶ ያቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ በወላይታ ድቻ 2-1 በመረታቱ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት አስተናገዶ ለመመለስ ተገዷል። ይህ ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ለማስተናገድ 5ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀበት 5ደቂቃዎች ብቻ ነበር። እንግዳዎቹ ቅ/ጊዮርጊሶች የአጥቂ አማካዩ በኃይሉ አሰፋ ባስቆጠረው ግብ ቀዳሚ መሆን ችለው ነበር። 8ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው ጃኮ አረፋት የፍፁም ቅጣት ምት ክልል መግቢያ ላይ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በቀላሉ ይዞታል። ሆኖም የቅ/ጊዮርጊስ መሪነት መዝለቅ የቻለው ለ5 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 10ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው በዛብህ መለዮ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ይህም ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ7 ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደው ግብ ሆኖ ተመዝግቧል።
በ32ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አበባው ቡጣቆ የፍፁም ቅጣት ምት አካባቢ ላይ ያገኘውን ቅጣት ምት መሬት ለመሬት ቢመታውም ኳሱ በግብ ጠባቂው ተመልሷል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተጠናክረው የገቡ ሲሆን ቅ/ጊዮርጊስ ተጭኖ ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። 54ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ በሃይሉ አሰፋ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ገብቶ አክርሮ የመታው እንዲሁም 55ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ የመታው ቅጣት ምት የግቡን ቋሚ ታክኮ ወጥቷል። 61ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ ሙሉዓለም መስፍን ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ይዞታል። 74ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች ከማዕዘን ምት ያሻገሩትን ኳስ የቅ/ጊዮርጊስ ተከላካዮች ቢመልሱትም ኳሱን ጃኮ አረፋት አግኝቶ በቀጥታ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 1ደቂቃ ሲቀረው 89ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ በዛብህ መለዮ በግንባር በመግጨት ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር ወላይታ ድቻን አሸናፊ ማድረግ ችሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ~ወላይታ ድቻ
- ማሰታውቂያ -
“ተጋጣሚያችን ልምድ ያለውና ጨዋታዎችን መቆጣጠር የሚችል አቅም እንዳለው ስለሚናውቅ በፈጣን እንቅስቃሴና ያገኘነውን አጋጣሚ በመጠቀም አሸናፊ ሆነን ወጥተናል ብለዋል፡፡”
ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ~ቅዱስ ጊዮርጊስ
“በተለይ በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ጊዜ የመረጥነው መከላከልን መሰረት ያደረገ የጨዋታ ዘዴ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡በአጠቃላይ እንቅስቃሴም ቡድናችን አቅሙን በተገቢው አልተጠቀመም ተጋጣሚያችን ያሳየውን የጨዋታ እንቅስቃሴ በመልካም ጎን የሚወሰድ ነው፡፡በማለት አሰተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡”