በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት 1ጨዋታ አ/አ ላይ ሲደረግ ቅ/ጊዮርጊስ እና መከላከያ ተገናኝተው ጨዋታቸውን ያለግብ 0-0 በሆነ ውጤት አጠናቀዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ መከላከያ ወደኋላ አፈግፍጎ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ሲያደርግ ቅ/ጊዮርጊስ በአንፃሩ በቀኝ የሜዳው ክፍል በአቡበከር ሳኒ በኩል ያዘነበለ ጨዋታ ለመጫወት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ይህንንም ተከትሎ በተደጋጋሚ በአቡበከር ሳኒ የማጥቃት ሙከራ አድርገዋል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ሙከራ ለማየት 26 ደቂቃዎች ወስዶበታል። 26ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው በሀይሉ ግርማ ከርቀት የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል። ቅ/ጊዮርጊሶች ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ አቡበከር ሳኒ ወደግራ በመውሰድ ጋዲሳ መብራቴን ወደ ቀኝ በማድረግ የመጨረሻዎቹን 15ደቂቃዎች የተሻለ ለመንቀሳቀስ ችለዋል። 31ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ በግራ እግሩ አክርሮ የመታወን ኳስ እንዲሁም 39ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ አቤል ማሞ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶባቸዋል። 42ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ ኢብራሂም ፎፋና በድንቅ ሁኔታ የመከላከያ ተጫዋቾችን አታሎ ወደ ሳጥን ውስጥ ያሻገረውን ኳስ አብዱልከሪም ኒኪማ በመቀስ ምት ሞክሮት በተከላካዮቹ ተጨርፎ ወደውጭ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግበት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽም ቅ/ጊዮርጊሶች የተሻለ ሆነው መቅረብ ችለዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ በግል ብቃቱ ይዞት ሄዶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት በግቡ አናት ወጥቷል። 64ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ማራኪ ወርቁ ያሻገረለትን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ሞክሮት የግቡን ቋሚ ታኮ ወጥቷል። በተደጋጋሚ ወደመከላከያ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉት ቅ/ጊዮርጊሶች ጨራሽ አጥቂ ያለመኖሩ እንደጎዳቸው በግልፅ ታይቷል። አጥቂዎቹ ሳላዲን ሰይድ እና አሜ መሀመድ በጉዳት ማጣቱን ተከትሎ ኢብራሂም ፎፋናን በሀሰተኛ 9 ቁጥር ሚና ለማጫወት ተገዷል። ይህም ቅ/ጊዮርጊሶች የሚፈጥሯቸውን እድሎች በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም።
- ማሰታውቂያ -
የመሀል ሜዳ ሽኩቻ እና ጉሽሚያ በበዛበት በሁለተኛው አጋማሽ 74ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ የመታው ቅጣት ምት ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። ከ3ደቂቃዎች በኋላ 77ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ያሻገረለትን ኳስ ኢብራሂም ፎፋና በግንባሩ ገጭቶት የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። ይህንንም ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታቸውን ያለግብ አጠናቀዋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
የቅ/ጊዮርጊሱ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ
“ወደሜዳ ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው የገባነው። ጨዋታውን ለማሸነፍ ተጫዋቾቹ የሚችሉትን አድርገዋል። ሜዳ ላይ እንዳያችሁት ተጋጣሚያችን መጫወት አልፈለገም። እድሎች አግኝተናል። የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ኳሶቻችን ትክክል አልነበሩም። ተጋጣሚያችን ጨዋታውን እያቀዘቀዘ 1ነጥብ ይዞ ለመውጣት ነው የፈለገው እሱ ደሞ ለኛ ጨዋታውን ከባድ አድርጎብናል። በየጨዋታው ስህተቶች ይኖራሉ እሱን ለማረም ጠንክረን እንሰራለን።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ስለ ሳልሀዲን ሰይድ የተጠየቁት ምክትል አሰልጣኝ ሲመልሱ “በእርግጠኝነት መቼ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ አላወቅንም ነገር ግን አንዳንድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በጂምናዚየም ጀምሯል።” በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።”
የመከላከያው አሰልጣኝ ሻ/ል ምንያምር ፀጋዬ
“ተጋጣሚያችን ብዙ ልምድ ያለው ቡድን ስለሆነ ክብር ሰጥተነው ነው የገባነው። በአብዛኛው ጥንቃቄን መርጠን ነው ለመጫወት የሞከርነው። እነሱ (ቅ/ጊዮርጊስ) በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ነበሩ። በደምብ በተጫወተ ነጥብ አይሰጥም። ስለዚህ ተከላክለን 1 ነጥብ ለማግኘት ተጫውተን እሱንም አሳክተን ወጥተናል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።”