ቅዳሜ መደረግ እያለበት ከአ/አ ፖሊስ ኮሚሽን በተላለፈ ትዕዛዝ ሳይደረግ ወደ ዛሬ የተዛወረው እና ዛሬ(ሰኞ) ልክ 09:03 ደቂቃ የጀመረው የመከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ለማስተናገድ የፈጀበት የ1 ደቂቃ እድሜ ነበር። ሀዋሳ ከተማዎች (ሀይቆቹ) በያቡን ዊሊያም አማካኝነት ጎል በማስቆጠር መሪ መሆን ችለው ነበር።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ኳስን ለመጫወት ፍላጎት የታየ ሲሆን በጨዋታው ግን ከ2 እና ከ3 በላይ ቅብብሎችን ማድረግ አልቻሉም፡፡ በዚህም ጨዋታው ቀጥሎ በሀዋሳ መሪነት መዝለቅ የቻለው ለ17 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 18ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ በማስቆጠር አቻ ማድረግ ችሏል፡፡
ከግብዋ መቆጠር በኃላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል፡፡ 40ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያ የተሻለ በመንቀሳቀስ ያገኙትን አጋጣሚ የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ አውጥቶታል። ከ3 ደቂቃዎች በኋላ 43ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማው ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን የመታውን ኳስ የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ መልሶበታል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያ በተወሰነ መልኩ ተሽሎ የታየበት አጀማመር ሲያደርግ በአንጻሩ ሀዋሳ ከተማ በዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ቢያደርግም በእለቱ ጥሩ የነበረው አቤል ማሞ ሊያመክናቸው ችሏል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽም ይህ ነው የሚባል የረባ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡
11:30 ሲል በውጤት ቀውስ ውስጥ ሆነው የተገናኙት ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባጅፋር ሲሆኑ ጨዋታቸውን ያለምንም ግብ 0-0 ማጠናቀቅ ችለዋል። እንደ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሁሉ ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት ይህ ጨዋታ ከአየር ንብረቱም ጋር በተያያዘ ደህና የሚባል እንቅስቃሴ ሳይስተዋልበት ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው መንቀሳቀስ የቻሉት እንግዳዎቹ ጅማ አባጅፋሮች ሲሆኑ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ባለመቻላቸው ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። 45ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ኦኪኪ ግሩም ኳስ ሞክሮ የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ በድንቅ ሁኔታ ያወጣበት ኳስ በጨዋታው ብቸኛ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ከእረፍት መልስም ደህና እንቅስቃሴ ሳይስተዋልበት ጨዋታው ያለምንም ግብ ተጠናቋል። ውጤቱንም ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች እኩል 5 ነጥቦችን በመያዝ ጅማ አባጅፋር 13 እና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 15ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።
ፕሪምየር ሊጉ ነገ (ማክሰኞ) ሲቀጥል በአ/አ ስታዲየም 11:30 ሲል የሸገር ደርቢ በቅ/ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል የሚደረግ ሲሆን ጨዋታውን ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ ይመራዋል ተብሎ ይጠበቃል።