በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት 1ጨዋታ ዛሬ(ቅዳሜ) ተደርጓል። በአ/አ ስታዲየም በተካሄደው በዚህ ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከ አዳማ ከተማ ተጫውተው በእንግዳው ቡድን 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቀዝቃዝ ብሎ በጀመረው የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከተከላካዩ ግርማ በቀለ ጀምሮ ኳስ በማደራጀት ወደፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ለዚህ ጨዋታ መሳካትም የካሉሻ አልሀሰን ሚና እጅግ ከፍተኛ ነበር። አዳማ ከተማ በአንፃሩ ረጃጅም ኳሶችን ተጠቅሞ ወደግብ ለመድረስ ያደረጉት ጥረት ብዙም ሳይሳካላቸው አጥቂዎቹ ዳዋ ሁጤሳ እና ታፈሰ ተስፋዬ ሲባክኑ ውለዋል። 17ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ካሉሻ አልሀሰን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል። 29ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው አጥቂ ዳዋ ሁጤሳ ከግብ ጠበቂው ጋር ተገናኝቶ የሞከረው ኳስ ሱሌማን አቡ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል።
33ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ካሳሁን ያሻገረውን ቅጣት ምት ካሉሻ አልሀሰን በግንባሩ ሞክሮት ወደውጭ ወጥቷል። ከ3 ደቂቃዎች በኋላ 36ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ምንያህል ይመር ከርቀት የሞከረው ኳስ ወደውጭ ወጥቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ በኢትዮ-ኤሌክትሪክ ፍፁም ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት አዳማ ከተማዎች አልፎ አልፎ በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ 41ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው ሱሌማን አሚድ ያገኘውን ጥሩ ኳስ አሻምቶት ወደውጭ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ ከ2 ደቂቃዎች በኋላ 43ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ አዲስ ነጋሽ ወደ ግብነት ቀይሯት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር። ከግቡ መቆጠርም በኋላ ጥሩ የተንቀሳቀሱት ኢትዮ-ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካለት ቀርቷል። የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪው 2ኛ ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ሄኖክ ካሳሁን ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዞ ይዞታል። ይህ ሙከራም የመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ተቃራኒ የሆነ ጨዋታ የተስተዋለ ሲሆን አዳማ ከተማ እጅግ ተሻሽሎ ሲቀርብ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በበኩሉ ፍፁም ተዳክሞ ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ ብልጫ ተወስዶበታል። በአዳማ ከተማ በኩል ግብ አስቆጥሮ ውጤቱን ለመቀልበስ አጥቅተው ሲጫወቱ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ደግሞ በጥንቃቄ ወደኋላ አፈግፍጎ በተገኘ አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ሲጫወት ተስተውሏል። ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ 50ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሁጤሳ በግሩም ሁኔታ ተከላካዮችን አታሎ የሞከረው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቷል።
በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት አዳማ ከተማዎች ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል። ይህንንም ተከትሎ 61ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ጥላሁን ወልዴ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሁጤሳ አስቆጥሮት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር። ከግቡ መቆጠር 1ደቂቃ በኋላ 62ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲየር ሊብሬ የአዳማ ከተማ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ ሞክሮት ወደውጭ የወጣበት አጋጣሚ እጅግ የሚያስቆጭ እና ውጤቱን መቀየር የሚያስችል ነበር። 70ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሁጤሳ ያሻገረውን ቅጣት ምት እስማኤል ሳንጋሪ በግንባሩ ገጭቶት ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። 73ኛው በሁለተኛው አጋማሽ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የዋለው ዳዋ ሁጤሳ በግሩም ሁኔታ ተከላካዮችን አታሎ የመታው ኳስ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከ4ደቂቃዎች በኋላ 77ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሁጤሳ በግሩም ሁኔታ በረኛውን አታሎ የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቷል።
79ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው በረከት ደስታ ከረጅም ርቀት የሞከረውን ኳስ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሌማን አቡ እንደምንም አውጥቶታል።
87ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የአዳማ ከተማው ቡልቻ ሹራ 3ኛ ጎል አስቆጥሮ አዳማ ከተማን ባለድል ማድረግ ችሏል። ጨዋታው ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ 93ኛው የአዳማ ከተማው አንዳርጋቸው ይላቅ ኳስ በእጁ በመንካቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ጋናዊው ካሉሻ አልሀሰን አስቆጥሮ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
የአሰልጣኞች አስተያየት
የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ቅጣው
“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበርን፤ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አልተጠቀምንባቸውም፤ በራሳችን ጥቃቅን ስህተቶች ተሸንፈናል። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ብንጠቀም ውጤቱ ይቀየር ነበር። ለወደፊቱ ስህተታችንን አርመን እንመጣለን።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የአዲሱ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በቦታቸው ላይ አለመገኘታቸውን ተከትሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አሰልጣኙ ሲመልሱ “ሁሉንም ነገር ጨርሰዋል፤ ነገር ግን ከፌዴሬሽኑ ጋር ያላለቀ ነገር ስላለ ነው፤ ከሰኞ ጀምሮ ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ ይጀምራሉ።” በማለት አስተያየታቸውን አጠናቀዋል።
የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ
“በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ጥሩ ነበሩ፤ ኳሱን ተቆጣጥረውት ነበር። እኛ ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት ስንሞክር ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠብን፣ እሱ ለኛ ጥሩ አልነበረም። ሆኖም ግን በሁለተኛው አጋማሽ ጫና በመፍጠር ለመጫወት ችለናል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።