በ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዮር ሊግ በሜዳው ከወላይታ ድቻ ጋር የተጫዎው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለ ግብ 0-0 በሆነ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ ነጥብ ተጋርተው ዳግም ወደ ወራጂ ቀጠናው ተመልሰው ገብተዋል፡፡
ኤሌክትሪክ ከ ወላይታ ድቻ
ልክ 9:00 ሲል በነፋሻማው የመዲናዋ ምቹ የአየር ፀባይ በጀመረው የኤሌክትሪክና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ባለፈው ሳምንት እዚሁ አዲስ አበባ ስታዲዮም ደደቢትን ከረቱበት የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ዘካሪያስ ቱጂን በማሳረፍ በሀይሉ ተሻገርን ተክተው ሲገቡ ወላይታ ድቻዎች ከሲዳማ ቡና ጋር በሜዳቸው ነጥብ ከተጋሩበት ስብስብ የመጀመሪያ ተመራጭ ከነበሩት ተጨዋቾች የ4 ተጨዋቾችን ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ሲገቡ መሳይ ቦጋለ፡እሸቱ መና፡ፀጋዮ ብርሃኑና፡ዳግም በቀለን በማሳረፍ ለኢማኑኤል ፌቦ፡ተስፉ ኤሊያስ፡ለዮናታን ከበደንና ጃኮ አረፋት ቅድሚ ሰጥተው ገብተዋል፡፡
ገና በጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃ ጫና ፈጥረው ለመጫዎት የሞከሩት ድቻዎች ወዲያውኑ ነበር ኢላማቸውን ያልጠበቁ ግን ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን በጃኮ አረፋት፡አብዱልሰመድ አሊና ፡ እዮብ አለማየሁ አማካኝነት ማድረግ የቻሉት፡፡በተለይም በ2ኛው ደቂቃ ጃኮ አረፋት በኤሌክትሪክ የግብ ክልል ውስጥ ባልተጠበቀበት ሁኔታ ከእዮብ አለማየሁ በቀኝ መስመር በኩል የተላከለትን ኳስ አልተጠቀመበትም እንጂ ምናልባትም ባለሜዳዎቹን ባልጠበቁት ሰዓት ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር፡፡ባለሜዳዎቹ በተጋጣሚያቸው የጦና ንቦች የተሰነዘረባቸውን ጥቃት በጊዜ ለማስቆም የበለጠ ከመከላከል ይልቅ እነሱም ጥቃት መሰንዘርን ነበር የመረጡት፡፡በዚህም በ4ኛው ደቂቃ በሀይሉ ተሻገር ከግብ ክልሉ ወጭ አክሮ የመታው ኳስ የወላይታድቻው ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቦ ኳሷን ጨርፎ በግቡ አናት ወደ ላይ አውጥቷት የማዕዘን ምት የሆነበት ተጠቃሽ ነበር፡፡
- ማሰታውቂያ -
የጫዋታው ግለት በዚሁ መልኩ የተጀመረ ቢሆንም ቀስ በቀስ ሁለቱም ቡድኖች ቅድሚ ለግብ ክልላቸው ደህንነት በመስጠታቸው ሀላፊነት ወስዶ የጠራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረገ አልነበረም፡፡ኤሌክትሪክም ሆኑ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት በረጂሙ ለፊት መስመር ክፍሉ በሚጣሉ ኳሶች የግብ ዕድል ለማግኘት ሲጫዎቱ የሁለቱም ቡድኖች ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ኣላማውን በጠበቁ የግብ ሙከራዎች ባይታጀብም ማራኪ ነበር፡፡በ20ኛው ደቂቃ እዮብ አለማየሁ ከመሃል ሜዳ ጃኮ አረፋት በረጂሙ ያሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት ለትንሽ በግቡ ቋሚ ወደ ውጭ ሲወጣ ፡በ29ኛው ደቂቃ ይሄው ተጨዋች በቀኝ መስመር በኩል ከሳጥኑ ውጭ አክሮ የመታው ኳስ በሱሌማን አሊ ጥረት ኳሷ ወደ ወጭ ወጥታ የማዕዘን ምት ሁኗል፡፡በ39ኛው ደቂቃ ከመሃል ሜዳ በግራ መስመር ከካታንጋ ወደ ሚስማር በረጂሙ የተሻገረለትን ኳስ ብቻውን እየገፋ በኤሌክትሪክ የግብ ክልል ውስጥ ሲገባ ኳሱን በተከላካዮች ሲነጠቅ ጥፋት ተሰርቶብኛል በሚል መውደቅን የመረጠው ጃኮ የቢጫ ካርድ ሰለባ የሆነበት የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ማገባደጃ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሁኗል፡፡
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ መጀመሪያ ተሽለው የቀረቡት ባለሜዳዎቹ በ48ኛው ደቂቃ አልሀሰን ካሉሻ ከመሃል ሜዳ በግቡ ትይዩ መሃል ለመሃል ሰንጥቆ ለሄኖክ ካሳሁን ያቀበለውን ኳስ ሄኖክ ወደ ግብ ሞክሮት በግቡ አናት ወደ ላይ ሲወጣ ፡በ52ኛው ደቂቃ ታፈሰ ተስፋዬ ለግብ የተቃረበ መከራ በግብ ጠባቂው ሲመክን፡ 65ኛው ደቂቃ ላይ ካሉሻ አልሀሰን ከዲዲዮ ለብሪ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቦ ኳሷን በቀላሉ መቆጣጠር ችሏል፡፡
በዚህኛው የጨዋታ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ የበለጠ ኳስን ተቆጣጥረው ጫና በማሳደር ለመጫዎት ሲሞክሩ ድቻዎች ከተከላካይ ክፍሉ ጀምሮ በረጂሙ ለጃኮ በሚጣሉ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም የተጋጣሚያቸው ተከላካዮች ጃኮን ቦታ እንዳያገኝ በማድረግ በቀላሉ ማቆም ችለዋል፡፡ድቻዎች በዚህኛው አጋማሽ በቁጥር አንስተኛ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሲያደርጉ 72ኛው ደቂቃ እዮብ አለማየሁ ከበዛብህ መለዮ የተቀበለውን ኳስ ሞክሮት ግብ ጠባቂው በቀላሉ የያዘበት እና በ90+2 ደቂቃ የኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ ኤማኑኤል ፌቦ ከግብ ክልሉ ወጥቶ ኳስን በእጅ በመንካቱ ከግቡ በግምት 20 ሜትር ርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት ዮናታን ከበደ መቶት በቀላሉ በግብ ጠባቂው ተይዞ ጨዋታው በዚሁ ያለ ግብ 0-0 ተጠናቋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞ ኢትዮኤሌክትሪክ -ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ
የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈን ደረጃችን ለማሻሻል አስበን ነበር ፡፡በርካታ የግብ ሙከራዎችን ብናደርግም ግብ ማስቆጠር አለመቻላችን ዕድለኛ አልነበርንም፡፡በቀጣይ በቀሩት ጨዋታዎች ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረን እንሰራለን፡፡
☞ ወላይታ ድቻ -ዘነበ ፍስሀ
ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ጨዋታ መልስ ውጤት ማጣታችን ተጨዋቾች ጫና ውስጥ ገብተዋል፡፡ለዚህም ነው ኳሶች ይበላሹብን የነበረ፡፡የጨዋታው ውጤቱ ግን ያን ያህል አያስከፋንም፡፡