በ 24ኛው ሳምንት የ ኢትዮጽያ ፕሪመርሊግ በግዙፉ ትግራይ ስታድየም ሃዋሳን ያስተናገደው መቐለ ከተማ በጋናዊው ፎስይኒ ኑሁ ብቸኛ ግብ ታግዞ ማሸነፍ ችሏል። መቐለዎች ኣዳማን ከገጠመው ቡድን ግብ ጠባቂውን ፊሊፕ ኦቮኖ በብሄራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት በሶፋንያስ ሰይፈ ሲቀየር ኣመለ ሚኪያስን በቅጣት ምክንያት በሃብታሙ ተከስተ ቀይሮ ገብቷል። ሃዋሳዎችም ፋሲልን ካሸነፈው ቡድን እስራኤል እሸቱን በጉዳት በዳዊት ፍቃዱ በመቀየር ጨዋታውን ጀምሯል።
የመጀመርያው 45 ደቂቃ ብዙ ሙከራ ያልታየበት ሃዋሳዎች መሃል ሜዳ ላይ በሚደረጉ ቅብብሎች እንዲሁም መቐለ ወደ ፊት በሚላኩ ረጃጅም ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይቷል። በተለይ ሃዋሳ ከኋላ ኳስ በመመስረት የኳስ ብልጫውን መውሰድ ችሏል። ለዚህ የኳስ ብልጫ መገኘት የመሃል ተከላካዮቹ መሳይ ፓውሎስና እና ላውረንስ ላርቴ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል። በረኛው ሶሆሆ ሜንሳህ የመልስ ሚት በሚያስጀምርበት ጊዜ ሁለቱም ተከላካዮች ወደ ጎን በመለጠጥ ለሙሉኣለም ረገሳ እና ለኣስጨናቂ ሉቃስ ክፍት ቦታ መፍጠር ችሏል። ሆኖም ግን የኳስ ብልጫ የወሰዱትን ያህል የግል ሙከራ ማድረግ ኣልቻሉም። ለዚህ ችግር ዋነኛው ምክንያት የመጨረሳ ኣጥቂ የተሰለፈው ዳዊት ፍቃዱ ከኣጥቂ ጀርባ በተለምዶ ኣስር ቁጥር ብለን በምንጠራው ቦታ ላይ ከተሰለፈው ታፈሰ ሰለሞን ጋር ሊግባቡ ኣለመቻላቸው ነው።
መቐለዎች በበኩላቸው የሃዋሳ ተከላካዮችን ወደ መሃል ሜዳ ተጠግቶ የመጫወት ታክቲክን ለመጠቀም ከመሃል ሜዳ ረጃጅም ኳሶች ቢጥልም ኳሶቹ የተመጠኑ ባለመሆናቸው በቀላሉ በሃዋሳው በረኛ ሲያዙ ተስተውለዋል። የጨዋታው የመጀመርያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በ 37ኛው ደቂቃ በግምት 30 ሜትር ኣካባቢ መቐለ ያገኙትን ቅጣት ምት ጋናዊው ፎስዩኒ ኑሁ ቢሞክርም በቀላሉ በረኛው ሊቆጣጠረው ችሏል። በተመሳሳይ ሃዋሳዎች የመጀመርያ ሙከራቸውን በቀኝ ተመላላሽ ቦታ ሲጫወት የነበረው ኣዲስኣለም ተስፋዬ ከርቀት ኣክርሮ የመታው ኳስ በዓመቱ ሁለተኛ ጨዋታውን ያደረገው ሶፋንያስ ኣድኖበታል።
ሁለተኛው ኣጋማሽ ላይ ዮውሃንስ ሳህሌ የሃዋሳን የመሃል ሚዳ ብልጫ ለማስቆም ሚኪኤለ ደስታን በካርሎስ ዳምጠው በመቀየር መሃል ሜዳውን በማጥበብ ሃዋሳዎች ኳስ እንዳይቀባበሉ ማድረግ ችለዋል። የዚህም ውጤት በ 49ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ከበደ በቀኝ መስመር ወደ ፔናሊቲ ሳጥን ሰብሮ በመግባት ያሻማውን ኳስ ፎስይኒ ኑሁ በግራ እግሩ ኣክርሮ በመምታት የጨዋታውን የመጀመርያና የመጨረሻ ጎል ማስቆጠር ችሏል።
ከጎሉ በኋላ ሃዋሳዎች የኣቻነት ጎል ለማግኘት ባልተለመደ ሁኔታ ረጃጅም ኳሶችና የቆሙ ኳሶችን ለመጠቀም ሲሞክሩ ታይቷል። በዚህም በ 53ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰሎሞን( ጣቁሩ) ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት የቀኝ ተመላላሹ ኣዲስኣለም ቢመታውም የጎል ብረት መልሶበታል። ሃዋሳዎች ሙሉ ሃይላቸውን በማጥቃት ላይ ባደረጉበት ሰዓት ያሬድ ከበደ ከቀኝ መስመር ለኣማኑኤል የሾለከለትን ኳስ ኣማኑኤል በቀኝ እግሩ ኣክርሮ ቢመታውም በረኛው ሶሆሆ ሜንሳህ ኣድኖበታል። ሃዋሳዎች የማጥቃት ሙሉ ዒላማቸውን በግራ መስመር ሲጫወት በነበረው ፍሬው ሰለሞን በመድረግ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ፍሪያማ መሆን ኣልቻሉም።
የሃዋሳው ኣሰልጣኝ ዉበቱ ኣባተ የመሃል ሜዳቸውን ለማጠናከር ኣስጨናቂ ሉቃስን በ ጅብሪል ኣህመድ ቢቀይሩም የ መቐለን የተደራጀና ክፍተት የማይሰጠውን የተከላካይ ክፍል መስበር ኣልቻሉም። በተደጋጋሚ ከመሃል እና ከግራ መስመር የሚጥሏቸው ረጃጅም ኳሶች የበረኛውና የተከላካዮቹ ሲሳይ ሲሆኑ ውለዋል።
በዚህም ጨዋታው ሌላ ጎል ሳያስተናግድ በመቐለ ከተማ ኣንድ ለ ዜሮ ኣሸናፊነት ተጠናቋል። ሶስት ነጥቡም የመቐለ ከተማን የዋንጫ ግስጋሴ ሲያጠናክር የሃዋሳ ከተማ ከሜዳ ውጪ ያለማሸነፍ መጥፎ ክብረወሰን ኣስቀጥሏል።
የሁለቱ ቡድን ኣሰልጣኞች ኣስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት በ ፀጥታ ሃይሎች ምክንያት ማቅረብ ኣልቻልንም።