በ19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዬር ሊግ በአዲስ አበባ ስታዲዬም የሊጉ መሪ ደደቢት በሜዳው ድሬድዋ ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ ያለ ግብ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
ባለሜዳው የሊጉ መሪ ደደቢት ባለፈው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ተሸንፈው ለጨዋታው ሲቀርቡ እንግዳዎቹ ድሬዎች ወልዲያን በሜዳቸው አሸንፈው ለጨዋታው ቀርበዋል፡፡በጨዋታው ባለሜዳዎቹ በሰለሞን ሀብቴና አቤል ያለው ምትክ ስዩም ተስፋየ እና አቤል እንዳለን በመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች ሲያስገቡ እንግዳዎቹ ድሬድዋ ከተማዎች ኢማኑኤል ላሪያን በመጀመሪያ አሰላለፍ አካተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
በጨዋታው ሂደት ግልፅ የማግባት ሙከራ ለማድረግ በርካታ ደቂቃዎች በጠበቅንበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ያን ያህል በተጋጣሚው ቡድን ድሬድዋ ከተማ ላይ አደጋ የሚፈጥር አልነበረም፡፡ባለሜዳዎቹ የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ለማድረግ 20 ደቂቃ የወሰደባቸው ሲሆን በዚሁ ደቂቃ ተጨራርፎ ያገኘውን ኳስ የአብስራ ተስፋዬ ወደ ግብ ቢሞከረውም በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው የድሬድዋው ሳምሶን አምክኖበታል፡፡
በ26ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ በግንባሩ ወደ ግብ የሞከረውን በድጋሚ ሳምሶን አውጥቶበታል፡፡ድሬድዋ ከተማዎች በመከላከሉ በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ወደ ፊት በሚሄዱበትና የተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ሲገቡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ሲጋቡ በቀላሉ ኳስ ሲነጠቁ አምሽተዋል፡፡በደደቢት በኩል በዚሁ የጨዋታ አጋማሽ ረጃጂም ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል የግብ ዕድል ለማግኘት ሲጫዎቱ በድሬዳዋ ከተማ በኩል የሚነሳው በመከላከሉ የነበራቸው ጠንካራ ጎን ነበር፡፡
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የሁለተኛው አጋማሽ በተመልካቹ ሁለቱም ቡድኖች የነበረባቸውን ክፍተት አርመው ወደ ሜዳ በመግባት ጥሩ ኳስን ግብ ሊቆጠር እንደሚችል ቢጠበቅም ሜዳ ላይ የነበረው ውሎ ይሄ አልነበረም፡፡በዚሁ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ ግብ ለማግኘት ቢንቀሳቀሱም የተቀናጀና የተጠና አልነበረም፡፡በድሬድዋ ከተማ በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ያለቀለት የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው መጠናቀቁ አስገራሚም አነጋጋሪም ነበር፡፡በጨዋታው መጠናቀቂያ ሰዓት ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች የማሸነፊያ ግብ ለማግኘት ቢቀሳቀሱም የተጋጣሚያቸው የመከላከል አቅም ጠንካራ ቢሆንም በአጨራረስ በኩል የነበረባቸው ክፍተት ይህን እንዳያደርጉ ገድቧቸው ውሏል፡
ድሬዎች በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ግብ ከማስቆጠር ይልቅ ይህንኑ አስጠብቀው ነጥብ መጋራትን በመምረጥ ወደ ሇላ ተመልሰው ተከላክለው ሲጫዎቱ ይህም ተሳክቶላቸው ከሜዳቸው ውጭ ከሊጉ መሪ ደደቢት ላይ 1 ነጥብ ይዘው ወጥተዋል፡፡
በዚህም የሊጉ መሪ ደደቢት ከተከታዬቹ ያለውን የነጥብ ልዩነትወደ 3 የሚያሰፋበትን ዕድል አምክኖ በ33 ነጥብ ሊጉን ሲመራ፡፡ ድሬድዋ ከተማ በ1ነጥብም ቢሆን ተጠቃሚ በመሆን በ18 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ በመሆን ወራጂ ቀጠና ላይ ቆይተዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞ደደቢት-ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ
ጨዋታው በሜዳችን እንደመሆኑ አጥቅተን በተጋጣሚያችን ላይ ጫና ለመፍጠርና ግብ ለማስቆጠር ተጫውተናል፡፡ነገር ግን በነበሩብን ክፍተቶች ምክንያት ግብ ሳናስቆጥር ነጥብ ለመጋራት ተገደናል፡፡በቀጣይ ስህተቶቻችን አርመን እንመጣለን፡፡
☞ድሬድዋ ከተማ-ስምዖን አባይ
በአጠቃላይ በጨዋታው ሜዳ ላይ የነበረን እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጭ ነበር፡፡በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻልን ነበርን፡፡ጎል አላስቆጠርንም፡ግብም አልተቆጠረብንም ፡ካለንበት የደረጃ ሰንጠረዥ አንፃር ከሜዳችን ውጭ ከሊጉ መሪ ጋር ነጥብ በመጋራታችን ደስተኛ ነኝ፡፡