የኢትዮጵያ ኘሪሚየር ሊግ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ በክልል እና በአ/አ ስታዲየም ተደርገዋል። በክልል ጎንደር ላይ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከ ቅ/ጊዮርጊስ ተገናኝተው እንግዳው ቅ/ጊዮርጊስ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ጣፋጭ 3ነጥቦችን ይዞ መመለስ ችሏል። ለቅ/ጊዮርጊስ ግቦቹን በኀይሉ አሰፋ በ1ኛው ደቂቃ እንዲሁም 58ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ማስቆጠር ችለዋል። ይህንንም ተከትሎ ፋሲል ከተማ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል። ቅ/ጊዮርጊስ ዛሬ ድል ማድረጉ ዕሁድ ከደደቢት ጋር ላለበት ወሳኝ ጨዋታ ጥሩ መነቃቃትን እንደሚፈጥርለት ይጠበቃል።
በሌላ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ አ/አ ስታዲየም ላይ ወልድያ ስፖርት ክለብ ከ መቐለ ከተማ ጋር ተገናኝተው መቐለ ከተማ አንተነህ ገ/ክርስቶስ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ አሸንፎ መውጣት ችሏል። ይህ ጨዋታ በሊጉ 5ኛ ሳምንት ላይ መደረግ የነበረበት ቢሆንም በዕለቱ ወልድያ ላይ በተከሰተ የደጋፊዎች ፀብ እና ስርዓት አልበኝነት ምክንያት ሳይደረግ በመቅረቱ ለዛሬ ተላልፎ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በዛሬው ጨዋታ በወልዲያ ስፖርት ክለብ በኩል በ4-4-2 አሰላለፍ ሲገቡ ተገጣሚያቸው መቐለ ከተማ በበኩሉ 4-5-1 አሰላለፍን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ወደ ጎል በመድረሱ ረገድ ወልዲያ ስፖርት ክለቦች የተሻሉ ነበሩ።
8ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ሀሰን ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ የሞከራት ኳስ በመቐለ ከተማው ግብ ጠባቂ ፍሊፕ አቮኖ ጥረት ወጥታለች፡፡
- ማሰታውቂያ -
በሁለቱም ቡድኖች የመሀል ክፍል በሁለት ተከላካይ አማካይ የሚጠቀሙ መሆኑ ኳስ ቶሎ ቶሎ ወደ አጥቂ ክፍል በማድረሱ በኩል እምብዛም ነበሩ። በ33ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረለትን ኳስ የቀድሞ የባንክ የግራ ኮሪደር ተከላካይ አንተነህ ገ/ክርስቶስ አስቆጥሮ መቐለ ከተማዎች 1-0 የሚመሩበትን አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኀላ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ሁለቱ ቡድኖች 42ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ ከተማው ያሬድ ከበደ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ የሞከራትን ኳስ የወልድያው ግብ ጠባቂ ቢሊንጌ ኤኖህ በድንቅ ብቃት አድኗታል፡፡ ከዚህ ሙከራ በኋላ የረባ ሙከራ ሳይደረግበት ጨዋታው በዚሁ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያ ከተማዎች የአጥቂ አማካይ ቁጥራቸውን በማብዛት ጎል ለማስቆጠር ተጭነው ቢጫወቱም አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ተሸንፈው ወጥተዋል፡፡
53ኛው ደቂቃ ላይ የወልዲያው ተከላካይ ብርሀኔ አንሌይ ከመሀል ሜዳ አለፍ ብሎ አክርሮ የመታት ኳስ በመቐለ የግብ ብረት ታካ የወጣችው ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ከታዩት ሙከራዎች ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች፡፡ ከዚህች ሙከራ 7ደቂቃዎች በኋላ 60ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ ከተማው ድንቅ አጥቂ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግሩም ሁኔታ ተከላካይ አልፎ ወደ ግብ የሞከራት ኳስ በግብ ጠባቂው ቢሊንጌ ኤኖህ ድንቅ ብቃት ከሽፏል፡፡ 75ኛው ደቂቃ ላይ ወልዲያ ከተማ ያገኙትን የግብ ማግባት አጋጣሚ ኤዶም ኮዶዞ የመታውን ኳስ ፍሊፕ አቮኖ ሲተፋው ፍፁም ገ/ማርያም በድጋሚ ያገኛትን አጋጣሚ የመቐለ ከተማ ተጫዋቾች ተረባርበው ጎል ከመሆን አድነዋታል። 84ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በራሱ ጥረት ከመሐል ይዞ በመግባት የሞከራት ኳስ ዒላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ውጪ ወጥታለች ይህች አጋጣሚ ለመቐለ ከተማ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። ከዚህች ሙከራ በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት መቐለ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ እንዳያስቆጥሩ የወልዲያው ግብ ጠባቂ ቢሊንጌ ኤኖህ ጥረት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡
በእለቱ በመቐለ ከተማ በኩል የቀድሞ የአርባምንጭ ከተማ ተጨዋች ዐመለ ሚኪያስ ቡድኑ 3ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ትልቁን አስተዋጽኦ ያበረከተ ተጫዋች ሇኗል፡፡
በዚህም መልኩ ጨዋታው በመቐለ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
የመቐለ ከተማ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ
“እኛ የምንፈልገውን ውጤት ይዘን ወጥተናል፤ ያንን ነበር የምንፈልገው፤ ትንሽ ጨዋታው ሀይል የተቀላቀለበት ነበር፤ ከዛ ውጪ ግን እኛ ማግኘት የሚገባንን ውጤት ይዘን ወጥተናል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የወልዲያ ስፖርት ክለብ ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ
“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ አጀማመራችን ላይ ኳስ ይዘን ለመጫወት ሞክረናል፤ ነገር ግን ኳሶቹ ይሄዱ የነበሩት ወደጎን ነበር እና እንደዛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በነበረን ሰዓት ወደፊት ጫና ፈጥረን መጫወት ብንችል ኖሮ ምናልባት ውጤቱን መቀየር እንችል ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ወደፊት ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል፤ ብዙ የግብ ዕድሎችንም ፈጥረናል፤ ነገር ግን ግብ ባለማስቆጠራችን ተሸንፈን ወጥተናል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።