ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) በአዲስ አበባ የሚያካሂደውን 70ኛው የፊፋ ኮንግረስ ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ዛሬ ጥር 19/2012 ዓ.ም በኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን አዳራሽ ውይይት ተካሄደ፡፡
ውይይቱ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ ፊፋን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ባለድረሻ አካላት ተገኝተውበታል፡፡ የ70ኛው የፊፋ ኮንግረስ ውጤታማ በመሆነ መልኩ ለማስተናገድ የሚያስችል መነሻ ሰነድ የቀረበ ሲሆን በቀረበው ሰንድም ላይ ውይይት ተካሂዷል፤ በመቀጠልም ለ70ኛው የፊፋ ኮንግረስን ለማዘጋጀት ብሄራዊ አብይ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡
የኮሚቴው ስብጥር የሚከተለውን ይመስላል (የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ አዲስ አበባ ፖሊስ፤ የሴቶች ህጻናት እና ወጣጦች ሚኒስቴር፤ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፤ የኢምግሬሽን ጉዳዮች፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት፤ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኢፌዲሪ ገቢዎች እና ጉምሩክ፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፤ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ የብሮድካስት ባለስልጣን፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬት እና የብሄራዊ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ናቸው፡፡ )
70ኛው የፊፋ ኮንግረስን ለማዘጋጀት ብሄራዊ አብይ ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሲሆኑ የኮሚቴው ሰብሳቢ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤሊያስ ሽኩር እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ናቸው፡፡
ስድስት ዋና ዋና ኮሚቴዎች በአብይ ኮሚቴው ስር ተዋቅረዋል፡፡ እነዚህም የጸጥታ ደህንነት ና ቪዛ ኮሚቴ፤ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ኮሚቴ፤ የህክምና ኮሚቴ፤ የመስተንግዶ ዝግጅት እና ትራንስፖርት ኮሚቴ እና የመዝናኛ ና ቱሪዝም ኮሚቴ ናቸው፡፡
የአለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ኮርፖሬት ኤቨንት ማኔጀር የሆኑት ወ/ሮ ካሪን አስተርበርገር የፊፋ ኮንግረስ አዲስ አበባ ሲዘጋጅ ቀደም ብለው መሰራት ያለባቻው የትኞቹ ስራዎች እደሆኑ ገለጻ አድርገዋል፡፡
አዲስ አበባ ለዓለም አቀፍ ትልልቅ ስብሰባዎች አዲስ ባትሆንም የሚከተሉት ወሳኝ ነጥቦች ላይ ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ወ/ሮ ካሪን አስተርበርገር በስብሰባው ለተገኙት የ70ኛው የፊፋ ኮንግረስ አዘጋጅ ብሄራዊ ኮሚቴ አሳውቀዋል፡፡
1ኛ. የፊፋ ኮንግረስ ላይ ከ1400 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የገለጹት ወ/ሮ ካሪን ተጨማሪ 600 ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ እና አፍሪካ ህብረት ውስጥ የሚሰሩ ለስብሰባው እና ለእግር ኳስ ጨዋታ የሚያገለግሉ ግባታዎችን የሚሰሩ ሰዎች እንደሚገኙም ገልተዋል፡፡ በተጨማሪም የፊፋ ኮንግረስ ስራ ውጤታማ ለማድረግ 300 የሚደርሱ የፊፋ ሙያተኞች ከስብሰባው ሁለት ሳምንት በፊት ይገኛሉ፡፡
2. በስብሰባው ተሳታፊ የሚሆኑ የፊፋ አባል ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የትኛውን የቪዛ ዓይነት መጠቀም እንዳለባቸው ተለይቶ ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ (በውይይቱ የኮንፍረንስ ቪዛ መጠቀም እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡)
3. የፊፋ 70ኛ ኮንግረስ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት የህክምና አገልግሎት በምን መልኩ ማግኘት እንዳለባቸው ቅድመ ዝግጅት እንደረግ
4. በ70ኛው የፊፋ ኮንግራስ ወቅት መንገዶች ከትራፊክ ነጻ በምን መልኩ ሊሆኑ ይገባል፤ የመጓጓዣ አማራጮች ምን መሆን እንዳለባቸው ብሎም እያንዳንዱ መጓጓዣ አቅጣጫ አመልካች(ጂፒኤስ) መሳሪያ መገጠም እንዳለብት ለዚህም ቅድመ ዝግጅቶች እንዲጠናቀቁ ሀሳብ ቀርቧል፡፡
5. ከፊፋ ለኮንግረሱ የሚገቡ እቃዎች ከመጋቢት ወር ስለሚጀምሩ የገቢዎች እና ጉምሩክ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዲችሉ መመሪያ እንዲሰጣቸው፡፡
6. ለፊፋ 70ኛ ኮንግረስ የሚመጡ ጋዜጠኞች የሚጠየቁት ቪዛ ምን መሆን አለበት አንዲሁም የሚሳተፉበት ማረጋገጫ ወረቀት በምን መልኩ ማግኘት አለባቸው የሚለው ምላሽ እንዲያገኝ፡፡
7. ለፊፋ ኮንግረስ የቴሌኮም አግልግሎት 400 ሲም ካርዶች፤ 4G ኢንተርኔት አገልግሎት እና የሬዲዮ መገናኛ ዘዴ እንዲዘጋጅ
8. ለፊፋ ስብሰባ የሚመጡ ተሳታፊዎች የደህንነት ዋስትና እንዲሰጥ፡፡ የሚሉ ነጥቦችን የፊፋ ተወካይ አቅርበዋል፡፡