በይስሀቅ በላይ
ስለ ኳስ አጀማመሩ የት ጀምሮ የት
ጨረሰ?የተወለድኩት በተለምዶ ጨፌ ሜዳ
- ማሰታውቂያ -
ተብሎ በሚጠራው አካባበቢ ሲሆን ዕድገቴና
የኳስ ህይወቴ የተጀመረውና የተጠናቀቀው
ኮተቤ አካባቢ ነው፤ ጨፌ ተወልጄ የልጅነት
ጊዜዬን ያሳለፍኩት አሁንም የምኖረው
በዚህ አካባቢ ነው፡፡ የእግር ኳስ ህይወቴን
በተመለከተ ብዙ ሰዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቢ
ቡድን ወደ ዋናው እንዳደግኩ ያህል ነው
የሚሰማቸው፤ቅ.ጊዮርጊስ ቢ ከመግባቴ በፊት
በ1989 ዓ.ም አካባቢ ለመብራት ኃይል ቢ
ቡድን አንድ ዓመት ተይዤ ነበር፡፡ ከዚያ
በዓመቱ ጊዮርጊስ ቢ ቡድን ምርጫ አለ ሲባል
እዚያ ሄጄ ተመርጪ በመቀጠል በአሰልጣኝ
አስራት ኃይሌ አማካይነት ወደ ዋናው ቡድን
የማደግ እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ በብርቱካናማው
ማልያ በአጠቃላይ ለ6 ዓመታት በመጫወት
የማይዘነጉ ጣፋጭና ውጤታማ ዓመታትን
አሳልፌያለሁ፡፡
–በትውልድ አካባቢው የሚያደንቃቸው
ሞዴል የሆኑት ተጫዋቾች ይኖሩ
ይሆን?ብዙም ባይባሉም ከእኛ አካባቢ የወጡ
ተጫዋቾች አሉ፤ ከሁሉም ግን ስሙ ከፍ
ብሎ የሚነሳው በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ትልቅ
ታሪክ ያለው ገብረኪዳን ነጋሽ (ጋምብሬ)
የእኛ አካባቢ የላምበረት ልጅ ነው፤ ከእሱ
ሌላ ለትራንስና ለወንጂ ቡድኖች ተጫውቶ
ያለፈ ኤርሚያስ ታደሰ የሚባል ልጅ አለ፡፡
ከዚህ ውጪ ሌላ ሰው ባላስታውስም እነሱ
የሰፈራችን መጠሪያ ነበሩ፡፡
–ሰለሞን ታዋቂ ተጫዋች ከመሆኑ በፊት
በልጅነቱ ማንን እያደነቀ፤ እንደ እሱ ለመሆን
እየተመኘ ነው ያደገው?“በልጅነቴ በዚህ ደረጃ
እያደነኩትና እሱን ለመሆን እየተመኘሁ
ያደኩት ተጫዋች አለ ለማለት ይቸግረኛል፤
ለዚህ ደግሞ ምክንያቴ በልጅነቴ ያለሁበት
ሰፈር ከስቴዲየም ራቅ ያለ በመሆኑ ስቴዲየም
ለመግባትና ተጫዋቾችን እያደንኩ ለማደግ
እድሉን አልፈጠረልኝም፡፡ በወሬ ከምሰማውና
አልፎ አልፎ ስቴዲየም በመግባት ከማየው
ውጪ ተከታትዬ ወይም አድንቄው ወደፊት
እሱን እሆናለሁ ብዬ የተመኘሁት ተጨዋች
የለም”
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስለተገናኘበት
የመጀመሪያ አጋጣሚ፦“ በ1989 ዓ.ም
መብራት ሃይል ቢ ቡድን ውስጥ ለአንድ
ዓመት ተይዤ ነበር፤ ቅድስ ጊዮርጊስ የአገሪቱ
ሃያልና ውጤታማ ቡድን መሆኑን እሰማ
ነበር፤ ጊዮርጊሶች ለቢ ተጫዋች ይመርጣሉ
ሲሉኝ ለአፍታም ሳላመነታ ለምርጫ ሄድኩኝ፡
፡ በወቅቱ የቢ ቡድን አሰልጣኘ የነበረው ስዩም
ከበደ ነበር፤ ለቢ ቡድን ተያዝኩኝ፤ አሰልጣኝ
አስራት ኃይሌ ደግሞ ወደ ዋናው ቡድን
የማደግ ዕድሉን ሰጥቶኝ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር
መቼም ቢሆን የማይዘነጉና የማይረሱ አስደሳች
ጊዜያትን የማሳለፍ ዕድልን አግኝቻለሁ”
–በእግር ኳስ በጣም የተደሰተበትና በልዩ
ምርጥ ቀንነት የሚያነሰው፦“በጨዋታ ዘመኔ
በጣም ብዙ ደስ የሚሉ የማይዘነጉ ጊዜያትን
አሳልፌያለሁ፤ በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከቢ
ወደ ዋናው ቡድን ካደኩ በኋላ በ1994ዓ.ም
ከመብራት ሃይል ጋር ስንጫወት 2-1
እየተመራን ባለቀ ሰዓት በካታንጋ አካባቢ
የተገኘችውን ቅጣት ምት በቀጥታ ወደ
ግብነት ቀይሬ 2ለ2 የወጣንበት ጨዋታ በጣም
የተደሰትኩበት ጨዋታ ነው፡፡”
–በጨዋታ ዘመኑ ልቡ የተሰበረበትና
የደማበት ክፉ አጋጣሚ ብሎ የሚጠራው
ቀን፦“በጣም የሚገርምህ በእግር ኳስ ደስታና
ሃዘን ተነፃፃሪ ወይም ተፈራራቂ ነገሮች
ናቸው፤አብዛኛው የጨዋታ ጊዜዬ በደሰታ
የተሞላ ቢሆንም በ1998 ዓ.ም ኢትዮጵያ
ቡና እያለሁ ለዋንጫ ተፎካካሪ ብቻ ሳይሆን
ዋንጫ የማንሳት አቅም ያለው ቡድን ይዘን
ዓመቱን በዋንጫ አለመዝጋታችን በወቅቱ
በጣም ያዘንኩበት ቀን ሲሆን አጋጣሚውም
የፈጠረው ቁጭትም ዛሬም ድረሰ ከውሰጤ
አልጠፋም”
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጡ አሰልጣኝ፦
“በጨዋታ ዘመኔ በጣም ብዙ ምርጥ
አሰልጣኞች አሰልጥነውኝ አሳልፌያለሁ፤ ለእኔ
የመጀመሪያዬ እንደ አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን
እንደ አባት ኮትኩቶ አሳድጎ ለትልቅ ቁምነገር
ያበቃኝ አስራት ኃይሌ ከሁሉም ቅድሚያውን
ይወስዳል፤ አስራት ኃይሌ የተለየና
ከአሰልጣኝም በላይ ነው ለእኔ፤ ከእሱ ውጪ
በክለብም በብሄራዊ ቡድንም ያሰለጠኑኝና
በጣም የማከብራቸው አሰልጣኞች አሉ፤
ለስዩም ከበደ፣ ለስዩም አባተና ለአብርሃም
መብራቱ የተለየ ቦታ አለኝ”
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ተጫዋች፦“ለእኔ
ቴዎድሮስ በቀለ (ቦኮንዴ) የምንጊዜም ምርጡ
ተጫዋች ነው፤ቴዲ ምርጥነቱ በሜዳ ውስጥ
ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም የሚወደድ
ምርጥ ባህሪ ያለው ተጫዋች ነው፡፡ የቴዲ
የኳስ ችሎታ፣ ውጤታማነቱና መልካም
ባህሪው የጨዋታ ዘመኔ ምርጡ ተጫዋች
ብዬ እንድመርጠው አድርጎኛል”
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ግብ ብሎ
የሚጠራት፦“በጨዋታ ዘመኔ ለማበላለጥ
የሚከብዱኝ ግቦች አሉኝ፤ የግድ አንዱን
ምረጥ ካልከኝ ግን በ1994ዓ.ም ቅድስ
ጊዮርጊስ እያለሁ ኢትዮጵያ ቡና ለይ
ያስቆጠርኳት ግብ ለእኔ ፍፁምና ምርጧ
ግቤ ናት፡፡ በሁለቱ ኃያላን ቡድኖች ጨዋታ
ላይ 1ለ1 እያለን ሙሉ የ90 ደቂቃ የጨዋታ
ክፍለ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ በጭማሪው ሰአት
ማለትም በ92ኛው ደቂቃ ከሩቅ በሹት መትቼ
ያሰቆጠርኳትና 2ለ1 እንድናሸንፍ ያደረገችው
ጎል በህይወቴ የተለየ ቦታ ያላት ምርጥ ጎሌ
ናት”
–የቅዱስ ጊዮርጊስ የዋናው ቡድን
ቆይታው፦“የቅድስ ጊዮርጊስ የዋናው ቡድን
ቆይታዬ በውጤትና በስኬት የታጀበ በመሆኑ
እጅግ አስደሳችና የማይዘነጋ ነው፤ ቅዱስ
ጊዮርጊስ በእኔ የእግር ኳስ ህይወትና ለዛሬው
ማንነቴ ትልቁን አሻራ ያሳረፈ ክለብ ነው፤ዛሬ
ሰለሞን የሚባለው ሰው እንዲታወቅም
ምክንያት የሆነ ክለብ ነው፤ የጨዋታ ዘመኔ
በውጤትና በስኬት የታጀበም ነው፤ በፕርምየር
ሊግ ደረጃ የአገሪቱን 3 ትላልቅ ዋንጫዎችን
ያገኘሁበት፤ በርካታ ኢንተርናሽናል የውድድር
መድረኮች ላይ አገሬን ወክዬ የቀረብኩበት፤
ኬኒያ ላይ በተካሄደው የሴካፋ ሻምዮና
3ኛ ደረጃ በመውጣት ሜዳሊያ ያገኘሁበት
በአጭሩ በስኬት የታጀበ የእግር ኳስ ህይወት
እንዲኖረኝ ያደረገ፤ ሰለሞን የሚለው ስምም
በስፖርት ቤተሰቡ እንዲታወቅ መነሻ የሆነ
ክለብ ነው ለእኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ”
ስብስብ፦“ቅዱስ ጊዮርጊስ ስብሰቡን በተመለከተ
ሁሌም ልዩነት ፈጣሪ ነው፤ ከሌሎች
ክለቦች የተለየ የሚያደርገው ስብስቡ ሁሌም
ጠንካራና ለምርጫ የሚቸገር መሆኑ ነው፡
፡ በየክለቡ አሉ የተባሉ ምርጥ ምርጥ
ተጫዋቾች በዝውውር የሚመጡበት ክለብም
ነበር፤ በእኔ የጨዋታ ዘመንም ስብስቡ በዚህ
መልኩ የተዋቀረ በመሆኑ በዚህ ስብስብ
ውስጥ የቋሚ ተሰላፊነት ቦታን ማግኘት
በጣም ፈታኝ የሆነበት ክለብም ነው፡፡ አሸናፊ
ሲሳይ፣ብርሃኑ ፈየራ፣ፋሲል ተካልኝ፣ዘሪሁን
ሸንገታና ከፍያለው ተስፋዬ(ዲላን )የመሳሰሉ
ምርጥ ተጫዋቾች የተሰባሰቡበት ቡድን ነበር፤
በዚህ ቡድን ውስጥ ለመሰለፍ አንተም ጥረት
እንድታደርግ ያደርግሃል፡፡ ሁልጊዜም ስራ
ላይ ነህ፤ ንቁ ሆነህ ለመሰለፍ ከተሰለፍክም
ቦታህን አሳልፈህ ላለመስጠት ጠንክረህ
እንድትሰራም ያደርግሃል” በዚህ መሃልም
ተጠቃሚ ትሆናለህ።
–የኢትዮጵያ ቡና ቆይታውን
በተመለከተ፦“ልክ እንደ ቅዱሰ ጊዮርጊስ
ሁሉ በኢትዮጵያ ቡናም ጣፋጭና የማይረሱ
የጨዋታ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ፤ ስለ እግር
ኳስ ተጫዋችነቴ ሳስብ ቅዱስ ጊዮርጊስም
ኢት.ቡና ውስጥም መጫወቴ ታሪኬን በጣም
የተለየ ያደርገዋል፡፡ በኢት.ቡና 4 ጣፋጭ
ዓመታትን ተጫውቼ ባሳልፍም የአራት ዓመቱ
ቆይታዬ በዋንጫ ድል የታጀበ ባለመሆኑ
ከመቆጨት ውጪ በነበረኝ ቆይታ ግን በጣም
ደስተኛ ነበርኩ፡፡ በኢት.ቡና ቆይታዬ በተለይ
በ1998 ዓ.ም ጥሩ የቡድን ስብስብም ጥሩ
ውጤት ይዘን ሊጉን እየመራን በወቅቱ
በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት የፕሪምየር
ሊጉን ዋነጫ አለማንሳታችን በኢት.ቡና
የነበረኝ ቆይታ በዋንጫ የታጀበ እንዳይሆን
አድርጎብኛል፡፡ በ1998 ዓ.ም የነበረው ቡድን
ለዋንጫ የተሰራ ቡድን ስለነበር ዓመቱን
በዋንጫ መዝጋት ነበረብን፡፡
የቡና ቆይታዬን ከዚህ ቁጭት በስተቀር በጣም ጥሩ ነበር፤
ስብስባችንም ጨዋታችንም በጣም ምርጥ
የሚባል ነበር”
–ለሁለቱ የአገሪቱ ኃያላን ክለቦች
መጫወቱን ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስበው ምን
ይሰማዋል?“በእርግጥ የአገራችን ተጫዋቾች
ወደ ፊት የት መጫወት እንደሚፈልጉ
ስትጠይቃቸው የመጀመሪያ ምርጫቸው
እነዚህ ኃያላንና ታላላቅ ክለቦች ውስጥ
መጫወትን ነው የሚያስቀድሙት፤ እኔ
ደግሞ እንደ ዕድል ሆኖ የሁለቱን ታላላቅ
ክለቦች ታሪካዊ ማሊያ በተለያየ ጊዜ ለብሼ
የመጫወት እድልን አግኝቻለሁ፡፡ በዚህም
የተለየ የኩራት ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡
ብዙ ተጫዋቾች ከሁለት አንዱ ጋር እንጂ
ሁለቱም ጋር የመጫወት እድል ሲያገኙ
ስለማታይ ራሴን እንደ ልዩ እድለኛ ተጫዋች
ነው የማየው፤ ከታሪካቸው ከውጤታቸውና
ከደጋፊዎቻቸው አንፃር ስታየው ለሁለቱም
ቡድኖች መጫወት ለእኔ መታደልም ነው”
–በቅዱስ ጊዮርጊስና በኢትዮጵያ ቡና
በነበረው ቆይታ ከማን ጋር ሲጫወት ወይም
ሲጣመር ይመቸዋል?“በሁለቱም ታላላቅ
ክለቦች አሉ ከተባሉ ታላላቅ ተጫዋቾች
ጋር የመጫወት እድል አግኝቻለሁ፤ቅዱስ
ጊዮርጊስ እያለሁ ከቴዎድሮስ በቀለ (ቦካንዴ)
ጋር ስጫወት በጣም ይመቸኛል፡፡ ነገሮችም
ይቀልሉኛል፡፡ ቴዲ ምን እንደምፈልግ
ምን እንዳለኝ ጠንቅቆ ያውቃል፤ እሱንም
በተመሳሳይ እኔ ስለማውቀው ከእሱ ጋር
ስጣመር እግር ኳስ ይቀለኛል፡፡ ኢትዮጵያ
ቡና እያለሁም ከብዙዎች ጋር ስጫወት
ይመቸኛል፤ ግሩም ከተባለው ተከላካይ፣
ከዕድሉ ደረጀና ከደብሮም ሐጎስ ጋር ተጣምሬ
ስጫወት እንዲሁ ይመቸኛል”
–አብሮት ባለመጫወቱ የሚቆጨውና
አንድ ቀን አብሬው ብጫወት ብሎ
የሚመኘው፦“እንዲህ አይነቱ ምኞቴ በእኔ
ዘመን ከነበሩት ተጫዋቾች ጋር ሳይሆን
ከእኔ በፊት ከነበሩት ጋር ነው፤ በስም
የምንሰማቸው ትልቅ ችሎታ አላቸው የሚባሉ
ተጫዋቾችና በእኔ የጨዋታ ዘመንም ኖረው
አብሬያቸው ብጫወት ብዬ ከምመኛቸው
ተጫዋቾች ውስጥ ገብረኪዳን ነጋሽ (ጋምብሬ)
ይጠቀሳል።ጋምብሬ ሲኒየራችንም ነው፤
ከነበረው ስምና ችሎታ አንፃር አብሬው
ብጫወት ብዬ እመኛለሁ”
–በጨዋታ ዘመኑ የቅጣት ምት
ኤክስፐርት ነው ስለመባሉና የቅጣት ምቶችን
ወደ ግብነት የመቀየሩ ምስጢር፦“እውነት ነው
ቅጣት ምቶችን ወደ ጎል የመቀየር ለየት ያለ
ተሰጥኦ ነበረኝ፤ ሰዎችም በዚህ ላይ የቅጣት
ምት ጥሩ መቺ እንደነበርኩ ሲመሰክሩልኝም
እሰማለሁ፡፡ የቅጣት ምቶችን ወደ ግብ
የመቀየሬ የተለየ ምስጢር የለውም፤ ጎሉንና
መረቡን ጠንቅቄ ማወቄ ብቻ ይመስለኛል
ምስጢሩ”
–በዚህ በኩል የተለየ የቅጣት ምት
ልምምድ ያደርግ ይሆን? በቅጣት ምትስ
እንደ ሞዴል የሚቆጥረው ተጫዋችስ
አለ?“እውነት ነው በቅጣት ምትን ወደ
ግብ ለመቀየር የሚረዳኝ የተለየ ልምምድ
አደርጋለሁ፤በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለሁ
እንደ አጋጣሚ ካምፓችን ውስጥ ሜዳ አለች
እዛች ሜዳ ላይ ከመደበኛ ልምምዴ ውጪ ወደ
11 ሰአት አከባቢ ብቻዬን ኳስ ይዤ እየወጣሁ
አንድ ኳስ የሚያቀብለኝ ሰው መድቤ የቅጣት
ምት ልምምድ እሰራ ነበር፤ ይሄንን ማድረጌ
በቅጣት ምት የተሻለ ነገር እንዲኖረኝም
ያገዘኝ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ውጪ በቅጣት
ምት እንደ ሮል ሞዴል የምወስደው የዴቪድ
ቤካምን የቅጣት ምት አመታት በልዩ ትኩረት
መከታተሌና በልምምድ ወቅት እሱ ያደረገውን
ለማድረግ መሞከሬ ረድቶኛል ብዬ አስባለሁ”
–ጊዜው ረጅም ቢሆንም “ኤክስፐርት”
የሚል ስያሜ ባሰጠህ የቅጣት ምት ስንት
ግቦች እንዳሉህ ታስታውሳለህ?“ብዛታቸውን
አላስታውስም፤ ግን እኔም ሆንኩ የስፖርት
ቤተሰቡ ቀላል የማይባሉ የቅጣት ምት ጎሎች
እንዳሉኝ የሚያስታውሱ ይመስለኛል”
–በቅጣት ምት ግብ ማስቆጠር የሚቀናህ
ማን ላይ ነው?“ምክንያቱን በትክክል
ባላውቀውም መብራት ኃይልና ግብ ጠባቂው
ደያስ አዱኛ ላይ በተደጋጋሚ በቅጣት ምት
አስቆጥር ነበር”
-ለመጀመሪያ ጊዜ በእግር ኳስ
ተጫዋችነት ያገኘው ትልቁ ደሞዝ፦“መብራት
ኃይል ቢ እያለሁ 60 ብር በወር ደሞዝ ተብሎ
የተከፈለኝ ሲሆን በዓመቱ ግን ቅዱሰ ጊዮርጊስ
ቢ ስገባ ደሞዜ በጣም አድጎ 100 ብር
ያገኘሁት የመጀመሪያው ትልቁ ደሞዜ ነው”
–ዛሬ የአንድ ተጫዋች ወርሃዊ ደሞዝ
200 ሺህ ብር ገብቷል፤ ይሄንን ክፍያ
ከእናንተ ዘመን ጋር ስታነፃፅረው ምን
ይሰማሃል? ምነው በዚህ ዘመን በኖርኩ
ብለህ ትመኛለህ?“ሁሉም ነገር በጊዜው ነው
የሚሆነው፤እኛ በነበርንበት ጊዜ ሲከፈለን
የነበረው ደሞዝ በወቅቱ ትልቁ ደሞዝ ነው
ተብሎ የሚነገር ነበር፡፡ በተለይ በወቅቱ
ሲከፈለን የነበረው ደሞዝ ከእኛ በፊት ከነበሩት
ጋር ሲነፃፀር በጣም ብዙና ትልቅ ነበር
የሚባለው፤ የአሁኖቹም ከእኛ ጋር ሲነፃፀር
ያለው ነገር ተመሰሳይ ነው፡፡ አሁን ደግሞ
ጊዜው ፈቅዶ አሁን ያሉት ተጫዋቾች ከፍተኛ
ተከፋይ ናቸው፤ ይሄንን ነገር ጊዜው ነው
እንዲሆን ያደረገው፤ አሁን ያሉት ተጨዋቾች
ገና ለገና ከፍተኛ ገንዘብ ተከፈላቸው ብዬ
ምነው በዚህ ዘመን ተጨዋች በሆንኩ ብዬ
አልመኝም፤ እንደዚህ ማሰብ ጤነኝነትም
አይደለም፡፡ ተጨዋቾች ከዚህ በላይ ተጠቃሚ
ቢሆኑ ደስተኛ ነኝ”
–በተጨዋችነት ዘመንህ የፊርማ ገንዘብ
ተከፍሎህ ያውቃል?“ኢት.ቡና ስገባም
አግኝቻለሁ፤ ትልቁ ያገኘሁት የፊርማ ክፍያ
30 ሺህ ብር ነው፡፡”
–ከዋናው ስምህና ከአባትህ ስም ይልቅ
“ልምጭ” በሚለው ስም ነው ተለይተህ
የምትጠራው፤ “ልምጭ” ለምን ተባልክ?
ስሙን ያወጣልህስ ማነው?“ልምጭ”
የተባልኩት በቅጥነቴ ይመስለኛል፤ ስሙን
ያወጣልኝ ደግሞ ሰፈር ውስጥ ስንጫወት
አንዱ ውጪ ሆኖ ጨዋታችንን የሚከታተል
ሰው ቅጥነቴን አይቶ ይሄ “ልምጭ” ነው
በማለት ዳቦ ሳይቆረስ ስሙን አወጣልኝ፤
በዚያው ፀደቀ፡፡ ዛሬም ድረስ የአባቴ ስም
ያህል መጠሪያዬ ሆኖ ቀርቷል”
–ከውጪ የማን ደጋፊ ነህ?“የማንቸስተር
ዩናይትድ”
–ከውጪ አሰልጣኞችስ? በውጤታማነቱ
የምታደንቀው አሰልጣኝ?“የማን.ዩናይትድ
ደጋፊ በመሆኔ የውጤታማውና ምትክ
አልባው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን
አድናቂ ነኝ”
–ከውጪ ተጨዋቾችስ? “ከላይ
አንስቼልሃለሁ የዴቪድ ቤካም”
–ከውጪ ብሄራዊ ቡድኖችስ?“ከውጪ
የሁለት አገር ብሄራዊ ቡድኖች ደጋፊ ነኝ፤
የጀርመንና የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን”
-ሰለሞን እግር ኳስ ተጨዋች ባይሆን
ኖሮ በምን ሙያ ላይ ይገኝ ነበር? “ይሄንን
አስቤው አላውቅም፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ኳስ
ነበር የምጫወተው፤ ያንን የምፈልገውን ነገር
ከልጅነቴ ጀምሮ ስላገኘሁ ነው መሰለኝ ሌላ
ነገር ስለመሆን አስቤ አላውቅም”
–ሰለሞን ራሱን በ3 የተመረጡ ቃላቶች
ግለፅ ቢባል እንዴት ይገልፃል?“ራሱን በራሱ
አንደበት መግለፅ ከባድ ነው፤ ታጋሽ ዝምተኛ
ነኝ፡፡ ከሰው ጋር ለመቀራረብ ጊዜ የሚወስድብኝ
ከተግባባሁ ግን ቶሎ የማልላቀቅና የተረጋጋሁ
ሰው ነኝ ብዬ አስባለሁ”
–ሰለሞን የስሙን ያህል፤ ታላላቅ ክለቦች
ውስጥ የመጫወቱን ያህል ለብሄራዊ ቡድን
አልተጫወተም ስለመባሉ?“እውነት ነው
ቅዱስ ጊዮርጊስና ቡናን ለመሰሉ ታላላቅ
ክለቦች እንድተጫወት ሰው ካየኸው ለአገሬ
የመጫወት እድሉ አልነበረኝም፡፡ ግን በጣም
የሚገርምህ ለወጣትም ይሁን ለዋናው
ብሄራዊ ቡድን የመሰለፍ እድል ባላገኝም
ከምርጫ ግን ተዘልዬ አላውቅም፡፡ በጉዳት
ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሁሌም ለብሄራዊ
ቡድን እመረጣለሁ፡፡ ግን እንደመመረጤ
አልተጫወትኩም፡፡ ይሄ ለምን ሆነ? መልሱን
የሚያውቁት በወቅቱ የነበሩት አሰልጣኞች
ናቸው”
–የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት እድል
ስለማግኘቱ?“እዚሁ ቅርባችን የመን ቢሆንም
በፕሮፌሽናልነት ከአገር ውጪ የመጫወት
እድልን አግኝቻለሁ፤ በየመን ሊግ ውስጥ
ለሁለት አመት ያህል የመጫወት እድሉን
አግኝቻለሁ፡፡ ይሄንን እድል እንዳገኘ የተባበረኝ
ዮርዳኖስ አባይ ነው፡፡ እድሉ የተገኘው እንዴት
መሰለህ ክረምት ላይ እረፍት ሲሆን 22
አካባቢ ያለ አንድ ጅምናዝየም አለ፤ ሁሌም
በክረምት እዛ እንሰራለን፡፡ እነ መርከብ ሲሳይ
/ውሮ/ በአጠቃላይ የእዛ አካባቢ ልጆች እዚህ
ጂም ውስጥ የመስራት ልምዱ አለን፡፡ አንድ
ቀን ከመርከብ ጋር ስንሰራ የእነ ዮርዳኖስ
ክለብ አንድ ሚፊድፊልደር ይፈልጋሉ ለምን
ዮርዳኖስን አታነጋገርውም ይለኛል፡፡ ከዚያም
እሺ ስልኩን ስጠኝና ላናግረው አልኩት ሰጠኝ፡
፡ እኔም ለዮርዳኖስ ደወልኩለት፡፡ ዮርዳኖስም
በእርግጥ ሚድፊልደር እንፈልጋለን፤ ግን
በዚህ ጉዳይ ላይ ከሐዋሳው ሙሉጌታ
ምህረት ጋር አውርተናል፡፡
ውሉ ስላላለቀና ከመልቀቅያ ጋር ያስጨረሰው
ነገር ስላለ የእሱ ካልተሳካ 0ከአንተ ጋር
እንጨርሳለን አለኝ እንደተፈራው የሙልጌታ
ነገር ሳይሳካ ቀረ ከዮርዳኖስ ጋር በተነጋገርነው
መሰረት ወደ የመን ሄድኩ፡፡ በየመን በነበረኝ
የሁለት አመት ቆይታም ጥሩ ጊዜያትን
አሳልፌያለሁ፡፡ በጨዋታውም በቅጣት ምትም
ለክለቤ ጎሎችን በማስቆጠር ጥሩ ለመጫወት
ሞክሬያለሁ”
–ከጨዋታ ዘመንህ በኋላ ያለውን እግር
ኳስ እንዴት አገኝኸው? ብዙዎች ገንዘቡ እንጁ
ኳሱ አላደገም ይላሉ አንተስ?“ይሄ የሚታይ
ነገር በመሆኑ መካድ አይቻልም፤ እግር ኳሱ
ላለማደጉ ውጤቱም እቅስቃሴውም ምስክር
ነው፡፡ ደጋፊው ለሊት ተሰልፎ፣ ተጋፍቶ
ሜዳ ገብቶ የሚያየው እንቅስቃሴ ወረድ የለ
ነው፤ የስፖርት ቤተሰቡ የሚፈልገውና ሜዳ
ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ አይመጣጠንም፤
ይሄንን ደግሞ ሁሉም ሰው የሚስማማበት
ነው”
–ስለ ትዳር ህይወቱ?“ከባለቤቴ ሳምራዊት
ግርማ ጋር ትዳር መስርተን በአንድ ጣሪያ
ስር መኖር ጀምረናል፤ ለቤታችን ድምቀት
የሆነች ህያብ ሰለሞን የምትባል የዘጠኝ ወር
እድሜን ብቻ ያስቆጠረች ሴት ልጅ አለችን፡
፡ ከዛሬዋ ባለቤቴ ጋ ኢት.ቡና እያለሁ በ2000
ዓ.ም የጀመርነው የፍቅር ግንኙነት አድጎ ነው
ለትዳር የበቃነው፤ ባለቤቴ ለእግር ኳስ በጣም
ቅርብ ሆና ስቴዲየም ባትገባም በወቅቱ ግን
ተጫዋች መሆኔን ታውቅ ነበር፤ መቀራረባችን
አድጎ ለዙህ በቅተናል።”
–ከስፖርቱ አካባቢ በጣም ርቀሃል
ተደብቀሃል፤ምክንያቱ ምነድነው? አሁንስ
በምን ሙያ ላይ ትገኛለህ? የወደፊት
እቅድህስ?“እውነት ነው ከስፖርቱ አካባቢ ርቄ
ነበር፤እንዳልከው ተደብቄም ነበር፡፡ ከስፖርቱ
ይልቅ በሌላ ሙያ የተሰማራሁበት አጋጣሚም
ነበር፤ አሁን ግን ከስፖርቱ ጨክኖ መራቅ
ስለማይቻል ወደ ስፖርቱ እየተመለስኩ
ነው፤ በተለይ በስልጠና ሙያ የመግፋት
ትልቅ ህልም አለኝ፤ የመጀመሪያ ደረጃ
የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስጃለሁ፤በቅርቡ የሲ
ላይሰንስ ስልጠናን ለመውሰድ እየተዘጋጀሁ
ነው፡፡ ቀጣይ እቅዴ በስልጠና ሙያ በመግፋት
ውጤታማ አሰልጣኝ የመሆን ትልቅ ህልም
አለኝ፡፡ በተጫዋችነቴ ትላልቅና ከፍ ያለ
ታሪክና ውጤት ባላቸው ክለቦች ውስጥ
ተጫውቼ በማለፌ ፤ በታላላቅና ስመ-ጥር
በሆኑ አሰልጣኞች ስር ሰልጥኜ በማለፌ
ያገኘሁትን ልምድና እውቀት ተጠቅሜ
ይሄንን በስልጠና ይበልጥ በማሰደግ ጥሩና
ውጤታማ አሰልጣኝ የመሆን ትልቅ ህልም
አለኝ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋርም አሳካዋለሁ”
-በመጨረሻ…“እዚህ ደረጃ እንድደርስ
አሻራቸውን ያሳረፉትን በቅድሚያ ፈጣሪዬን፣
በመቀጠል ቤተሰቦቼንና ባለቤቶን ከልብ
ማመስገን ብቻ ነው የምፈልገው”