የኢትዮጵያ ቡና እና የቅ/ጊዮርጊስ ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ጨዋታ የዳግማዊ ትንሳኤ በዓል በሚከበርበት የፊታችን እሁድ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት
ጀምሮ ይካሄዳል፤ ቅ/ጊዮርጊስ የእርስ በእርሱን የደርቢ ጨዋታ እስከዛሬ በበላይነት በማሸነፍ መሪ ሲሆን ይሄን መላው የእግር ኳስ
አፍቃሪዎች እና የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች በጉጉት የሚጠብቁትን የእሁዱን ጨዋታ አስመልክቶ ግጥሚያው በስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጠናቀቅ
ከቡድኖቹ ተጨዋቾች መካከል የኢትዮጵያ ቡናው እያሱ ታምሩ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሄኖክ አዱኛ “የእሁዱ የሸገር ደርቢ ጨዋታ በሁለታችንም
በኩል ግጥሚያው በስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጠናቀቅ ተዘጋጅተናል፤ የሚመጣውን ማናቸውንም ውጤትም ለመቀበል ተዘጋጅተናል” በማለት
መልህክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን ከእዚህ በታች ደግሞ ሁለቱ የነቀምት ከተማ ተወላጆች ስለ ደርቢው ጨዋታ እና በቡድኖቻቸው ወቅታዊ አቋም ዙሪያ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ሀትሪክ፡-እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሰህ?
ሄኖክ፡– እናንተንም እንኳን አደረሳችሁ፤ በጣም አመሰግናችኋለው፡፡
ሀትሪክ፡- የትንሳኤ በዓልን የት እና በምን መልኩ አሳለፍክ?
- ማሰታውቂያ -
ሄኖክ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ሁሌም ቢሆን የትንሣኤ በዓልንም ሆነ ሌሎች በዓላትን በአብዛኛው የምታሳልፈው የምትጫወትበት ክለብህ
ውድድር ላይ ስለሚሆን ከቡድንህ አባላቶች ጋር ነው፤ የዘንድሮ በዓልንም ከእነዚህ ጓደኞቼ ጋር በጥሩ ሁኔታ ለማሳለፍ ችያለው፡፡
ሀትሪክ፡- የትንሣኤ በዓልን አስመልክተህ እንኳን አደረሳችሁ የምትላቸው ሰዎች ካሉ፤ እድሉን እንስጥህ?
ሄኖክ፡- በጣም ደስ ይለኛል፤ ለመላው የኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ በነቀምት እና በአዲስ አበባ ለሚገኙት ቤተሰቦቼ፣ እንደዚሁም
ደግሞ ለቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እና ለጓደኞቼ እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ በማለት በዓሉ መልካም እና የጤናም
እንዲሆንላችሁ ነው የምመኘው፡፡
ሀትሪክ፡- የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ጨዋታ የፊታችን እሁድ በዳግማዊ ትንሣኤ ቀን ይደረጋል፤ በእዚህ ጨዋታ
ዙሪያ የምትለን ነገር አለ?
ሄኖክ፡- አዎን፤ የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና የሸገር ደርቢ ጨዋታ በታሪክ እንደሰማሁትም ሆነ አሁን ላይ እንደ ተጨዋች ሆኜ ስመለከተው
ሁሌም ቢሆን በጣም አጓጊ እና ልትጫወትበት የምትመኘውም ግጥሚያ ነው፤ የደርቢ ጨዋታ የትም ሀገር ብትሄድም የደርቢ ትንሽ የሌለው እና ከባድ
ግጥሚያም ስለሆነ የእዚህ ጨዋታ ላይ መጫወት መቻልም ታላቅ ደስታንና እርካታን ይሰጣልና የዳግማዊ ትንሳኤውን ቀን ጨዋታ ከወዲሁ በናፍቆትም
እየጠበቅኩት ነው የምገኘው፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ማን የደርቢው ጨዋታ አሸናፊ ይሆናል?
ሄኖክ፡- የኢትዮጵያ ቡናን የምንፋለምበት የእሁዱ የሸገር ደርቢ ጨዋታ በጣም ከባድ እና ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት ቢሆንም በእዚህ
ግጥሚያ ወደ መሪዎቹ ክለቦች በነጥብ ለመጠጋት የግድ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ስላለብን እና ከእዚህ በፊት በተደረጉት የሁለቱ ክለቦች የደርቢ ጨዋታም
ውድድሩን በማሸነፍ የእኛ ክለብ የበላይነትን የያዘም በመሆኑ አሁንም ከሜዳ ሶስት ነጥብን ይዘን ለመውጣት ዝግጁ ሆነናል፤ ኢትዮጵያ ቡናን
አሸንፈንም ደጋፊዎቻችንን የምናስደስትበትም ጨዋታ ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳል? ወይንስ እድሉን አጥቷል?
ሄኖክ፡- የፕሪሚየር ሊጉ ውድድሩ እኮ ገና አላለቀም፤ ከእዚህ መነሻነትም እስካሁን ድረስ የሊጉን ዋንጫ አጥተናል ብለን እያሰብን አይደለም፤
ተስፋም የቆረጥንበትም መንገድ ምንም የለም፤ ስለዚህም እስከመጨረሻ ድረስ ያሉንን ጨዋታዎች በማሸነፍ እና የሌሎች ክለቦችንም ውጤት
በመጠበቅ ዋንጫ የማንሳት እድላችንን በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ላይ እንጠብቃለን፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ በአሰላው አረንጓዴ ስታድየም ከሐዋሳ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ አቻ መለያየቱ ከመሪው ክለብ ጋር ያለውን የነጥብ
ልዩነት እንዳያጠብ አድርጎታል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው?
ሄኖክ፡- የሐዋሳ ከተማ ጋር በነበረን የሊጉ ጨዋታ እድል ከእኛ ጋር ስላልነበር እንጂ ግጥሚያውን ማሸነፍ ይገባን ነበር፤ በጨዋታው ክለባችን
የተሻለ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን እንደ ሳላህዲን፣ ጌታነህ እና አቤልን በጉዳት አለማስገባታችን የአጥቂውን ክፍል ስላሳሳብን እና ንፋስም ስለነበር ጨዋታውን
ሳናሸንፍ ቀርተን ከሜዳ ልንወጣ ችለናል፡፡
ሀትሪክ፡- የቅ/ጊዮርጊስን ባልተለመደ መልኩ ውጤት ማጣት ብዙዎቹን አስገርሟል፤ በዚህ ዙሪያ የዘንድሮ ውጤት ማጣታችሁን እንዴት
ትገልፀዋለህ? የሊጉን ዋንጫ ብታጡስ ስሜታችሁ ምን ይሆናል?
ሄኖክ፡- የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ክለባችን ዘንድሮ ውጤት ያጣባቸው ምክንያቶች ብዙ እና የተለያዩ ናቸው፤ መጀመሪያ ከእኛ
ስንነሳ ቡድናችን አዳዲስ ተጨዋቾችን እና አዲስ አሰልጣኝንም በማምጣት አዲስ ቡድን እየሰራ መሆኑ፤ በተጨዋቾቻችን ላይ ተደጋጋሚ ጉዳቶች የደረሱ
መሆኑ እና ከእዛ በመቀጠል ደግሞ ክልል ላይ ስትጫወት ጨዋታዎቹን ሁሉ ከፖለቲካ ጋር የማያያዝ ነገር ስላለና ለቅ/ጊዮርጊስ ደግሞ ሁሉም ክለብ
ጠንክሮ እና ተዘጋጅቶ ስለሚመጣ በእነዚህ ምክንያቶች ውጤት ልናጣ ችለናል፤ የሊጉን ዋንጫ ብታጡ ላልከው አሁን ላይ አጥተናል ብለን ስላላሰብን
የምለው ነገር ባይኖርም ዋንጫውን ብናጣ በጣም የሚያሳዝኑን ለእኛ ብዙ ነገር የሆኑልን ደጋፊዎቻችን ናቸውና ለእነሱ ስንል የሚቻለንን ሁሉ ከፍተኛ
ጥረትን እንደርጋለን፡፡