የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ተስተካካይ አንድ ጨዋታ ዛሬ የሚደረግ ይሆናል። ወልድያ ላይ በሚደረገው የዕለተ ሀሙስ የሊጉ ተስተካካይ ጨዋታ 9፡00 ሲል ወልድያ ስፖርት ክለብ ከ መከላከያ የሚጫወቱ ይሆናል።
በ13ኛ ሳምንት በዕለተ ዕሁድ ጥር 20 2010 ዓ.ም መደረግ የነበረበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወልድያ ላይ በነበሩ አንድ አንድ አለመረጋጋቶች ይህንንም ተከትሎ ተጫዋቾቹ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰብን ነው በማለታቸው ክለቡ ላልተወሰነ ጊዜ በመበተኑ ምክንያት ጨዋታው ሳይደረግ ለዛሬ ተዛውሯል።
ዛሬ የሚያደርጉት ይህ ጨዋታ ለመከላከያ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻው ሲሆን ለወልድያ ደግሞ 13ኛው ይሆናል። ይህም ማለት ደግሞ ወልድያ ስፖርት ክለብ የዛሬውን ጨዋታ ጨምሮ 3ቀሪ ጨዋታዎች ይቀሩታል ማለት ነው።
በዘንድሮው የሊጉ ጉዞ መከላከያ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ግቦች 6ብቻ ሲሆኑ ይህም ቡድኑ በአጥቂ ክፍሉ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ነው። ካስቆጠራቸው 6 ግቦች 5ቱን ምንይሉ ወንድሙ ለብቻው ማስቆጠሩ ደግሞ ቡድኑ አማራጭ አጥቂዎች እንደሌሉት እና በአንድ ሰው ትከሻ ላይ እንደወደቀ ያሳያል። በወልድያ በኩል ስንመለከት ደግሞ በሊጉ በሜዳው በቀላሉ ግብ የማይቆጠርበት እንደሆነ ማስመስከር ችሏል። እስካሁንም በሜዳው 1ግብ ብቻ ማስተናገዱ ለተጋጣሚው መከላከያ ጨዋታውን ፈታኝ ያደርግበታል።
ወልድያ በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ ዕለት በ7ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ሜዳው ላይ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን አስተናግዶ እንግዳዎቹ በዲዲየር ሊብሬ ግብ መምራት ቢችሉም አንዷለም ንጉሴ(አቤጋ) ባስቆጠራት ግብ ነጥብ ሊጋራ ችሏል። መከላከያ በአንፃሩ በደደቢት ከደረሰበት የ4-0 ሽንፈት አገግሞ በ7ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ሜዳው ላይ መቐለ ከተማን ገጥሞ በምንይሉ ወንድሙ ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በአጠቃላይ በሊጉ ወልድያ 12ጨዋታዎችን ያከናወነ ሲሆን ከነዚህ 12 ጨዋታዎች መካከል በ3 አሸንፎ በ3 አቻ ተለያይቶ እንዲሁም በ6 ተሸንፎ በ12 ነጥቦች የሊጉ ግርጌ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። መከላከያ በአንፃሩ 14 ጨዋታዎችን አድርጎ 3ቱን አሸንፎ በ6ቱ አቻ ተለያይቶ በቀሪዎቹ በ5ቱ ተሸንፎ ከተጋጣሚው ወልድያ ስፖርት ክለብ በ3ነጥቦች ብቻ ከፍ ብሎ በ15 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ(ሀሙስ) ልክ 9:00 ሲል ወልድያ ላይ በሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም የሚጀመር ይሆናል።