የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ሲሆን ዛሬ (አርብ) አንድ ጨዋታ የተደረገ ሲሆን ነገ (ቅዳሜ) ደግሞ ሰባት ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። በነገው እለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና
የጨዋታ ቀን: ቅዳሜ ጥር 09/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደራል አርቢትር አሸብር ሰቦቃ
የጨዋታ ቦታ: አዲስ አበባ ስታዲየም
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ዙርም በውድድር አመቱ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳናቸውን ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡናን የሚያገናኝ ይሆናል። የዘንድሮው ኢትዮጵያ ቡና በሜዳው ብዙ ጎል የሚያስቆጥር እና ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ የተቸገረ ሆኖ እየተመለከትን ነው። በኢ/ር ካሳዬ አራጌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና ከሜዳው ውጭ እስካሁን ምንም አይነት ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። የአሁኑ የኢትዮጵያ ቡና ቡድን ትልቁ ጥንካሬ በሜዳው ጎሎችን ማስቆጠር የማይቸገር ቡድን መሆኑ ይጠቀሳል። በካሳዬ አራጌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮው የውድድር ዓመት ኳስን ይዞ ለመጫዎት ሲሞክር ተስተውሏል። ይህም በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ውጤት ሲያስገኝለት ታይቷል። ተጋጣሚው ሲዳማ ቡናም ቢሆን ከሜዳው ውጪ ያን ያህል ደካማ ውጤት እያስመዘገበ ነው ለማለት አያስደፍርም። ያለፉትን 3ተከታታይ ጨዋታዎች ቢሸነፍም የተከላካይ ክፍሉን የሚያርም ከሆነ በነገው ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡና በቀላሉ እጁን ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም። በሲዳማ በኩል የአዲስ ግደይ፣ ዳዊት ተፈራ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለ አስደናቂ ጥምረት ለኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ለሲዳማ ቡና የተከላካይ መስመር ክፍል እንደ መልካም ዜና ሊጠቀስ የሚችለው ነገር የኢትዮጵያ ቡናው ወሳኝ አጥቂ አቡበከር ነስሩ በጉዳት አለመሰለፍ ይሆናል።
- ማሰታውቂያ -
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ቡና ካደረጋቸው 8ጨዋታዎች 3ጨዋታዎችን በሜዳው ሲያደርግ በሁለቱ ጨዋታዎች አሸንፎ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይቶ ምንም ጨዋታ ሳይሸነፍ 9ግቦችን አስቆጥሮ 1ግቦ ብቻ ሊቆጠርበት ችሏል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 8ጨዋታዎች ደግሞ በ2ጨዋታዎች አሸንፎ በ3ጨዋታዎች ተሸንፎ በ3ጨዋታ ደግሞ አቻ ወጥቶ ማግኘት ከሚገባው 24 ነጥቦች 9 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በ3ነጥቦች ብቻ አንሶ በሊጉ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 4ቱን ከሜዳው ውጪ ያደረገ ሲሆን ከነዚህ 4ጨዋታዎች ጅማ አባጅፋርን እና ሀዋሳ ከተማን ሲያሸንፍ በወላይታ ድቻ እና በሀድያ ሆሳዕና ሊሸነፍ ችሏል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 8ጨዋታዎች 4ቱን ሲያሸንፍ በ4 ሽንፈት በማስተናገድ በሊጉ አቻ ያልተለያየ ብቸኛው ክለብ መሆን ችሏል። ሲዳማ ቡና የሊጉ አናት ላይ ከሚገኘው ከመቐለ 70 እ. በ4ነጥቦች ዝቅ ብሎ በ12ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ነገ በሚካሄደው እና ፌደራል አርቢትር አሸብር ሰቦቃ በሚመሩት ጨዋታ ሲዳማ ቡና የሚያሸንፍ ከሆነ የሌሎቹን ቡድኖች ውጤት ተንተርሶ የሊጉ ሁለተኛ መሆን ሲችል በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡና ድል የሚቀናው ከሆነ ከሲዳማ ቡና ጋር በነጥብ ተስተካክሎ በግብ ክፍያ በመብለጥ ከተጋጣሚው በላይ መቀመጥ ያስችለዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል በፋሲል ከነማው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው ወሳኙ አጥቂ አቡበከር ናስር በጉዳት እንዲሁም በባህርዳሩ ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው አቤል ከበደ በቅጣት የማይሰለፉ ይሆናል። በሲዳማ ቡናዎች በኩል ሚለዮን ሰለሞን፣ ሙሉቀን ታሪኩ እና ወንድሜነህ ዓይናለም በጉዳት ምክንያት ግልጋሎት የማይሰጡ ሲሆን የተከላካዩ ዮናታን ፍሰሃ መግባትም አጠራጣሪ ነው።