5ተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዳሜ በሚካሄዱ 6 ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል።በትግራይ ስታድየም ሚካሄደው የስሁል ሽረ ና የአዳማ ከተማ ጨዋታን እንዴት ሊመስል እንደሚችል በዚህ መልኩ አቅርበንላችኃል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋርተው የተመለሱት ስሁል ሽረዎች ነገ በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ ተከላካያቸው ዮናስ ግርማይ በቅጣት ከማጣታቸው በስተቀር ሙሉ ቡድናቸውን ይዘው ወደ ሜዳ ይገባሉ።በ4ተኛው ሳምንት ከደሞዝ በወቅቱ አለመከፈል ጋር ተያይዞ ከቡድኑ ጋር ወደ አዲስ አበባ ያልተጓዙት አክሊሉ ዋለልኝ፣ያሰር ሙገርዋ፣ሳሊፍ ፎፎና ና ዲድዬ ሌብሪ ወደ ቡድኑ የተመለሱ ሲሆን በጉዳት ፈረሰኞቹን ያልገጠመው ምንተስኖት አሎም ከጉዳቱ አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።ከመስመር በሚነሱ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ሚሞክሩት ስሁል ሽረዎች እስካሁን በተካሄዱት 5 ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስተናገደውን የአዳማ ተከላካይ ክፍልን ሰብሮ ለመግባት መሀል ላይ የአጥቂ አማካዮቻቸውን ቁጥር አብዝተው ሊገቡ አንደሚችሉ ይገመታል።
አዳማዎች በበኩላቸው በክረምቱ ያስፈረሙት አጥቂያቸው ሚኪኤለ ጆርጅን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ የመሀል አማካዮቻቸው አመለ ሚልክያስ እና አማኑኤል ጎበና ግልጋሎት ማያገኙ ይሆናል።ፊት ላይ በሚያሰልፏቸው ዳዋ ሆቴሳ፣በረከት ደስታ እና ቡልቻ ሹራ ጥምረት ላይ ጥገኛ የሆነው የአዳማ ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ደካማ ተከላካይ ክፍልን ለያዘው ስሁል ሽረ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።