በመሸሻ ወልዴ
ቅ/ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በተፋለ መበት ተጠባቂው የሊጉ ጨዋታ
ኢሱፍ ቡርሃና እና አቡበከር ሳኒ ባስቆጠሯቸው
ሁለት ግቦች 2ለ0 አሸንፎ የወጣ ሲሆን ቡድኑ
ያገኘው የድል ውጤትም ከመሪው ክለብ
መቐለ 70 እንደርታ ጋር ያለውን የነጥብ
ልዩነት ወደ 9 እንዲያጠብም አድርጎታል፡
፡ ቅ/ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን ባሸነፈበት ጨዋታ
እና በቡድኑ ወቅታዊ አቋም ዙሪያ ጋዜጠኛ
መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ የእሁዱ ጨዋታ
ላይ ለክለቡ ጎል ያስቆጠረውን አቡበከር ሳኒን
አናግሮት ተጨዋቹ ለጥያቄዎቹ ምላሹን
ሰጥቷል፤ እንደሚከተለውም ይቀርባል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ በፕሪምየር ሊጉ
የእሁዱ ጨዋታ ሲዳማ ቡናን 2ለ0 አሸንፏል፤
ድሉ ይገባችኋል?
አቡበከር፡- አዎን፤ ጥሩ ተጫውተንና
ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችንም ፈጥረን ነው
ጨዋታውን ያሸነፍነው፤ ስለዚህም በሜዳ
ላይ ከነበረን ጥሩ እንቅስቃሴ አንፃር የስኬት
ድሉ ለእኛ ሲያንስብን እንጂ የሚበዛብን
አይደለም፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና
በሜዳ ላይ ያሳዩትን የጨዋታ ፉክክርስ
እንዴት ተመለከትከው? በጨዋታውስ ማን
የተሻለ ነበር?
አቡበከር፡- የቅ/ጊዮርጊስ እና የሲዳማ
ቡና የእሁዱ ጨዋታ ሁለታችንም
ግጥሚያውን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ የገባንበት
ስለነበር ጥሩ ፉክክር ተደርጎበታል፤
ጨዋታው ክፍት እና በማጥቃት
ላይ ያተኮረ ስለነበርም በተለይ በእኛ
ቡድን በኩል ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ
ተደርጎበታል፤ ያም ሆኖ ግን የእለቱ
ጨዋታን ማሸነፍ መቻል ለእኛ ከመሪው
ክለብ መቐለ 70 እንደርታ ጋር ያለንን
የነጥብ ልዩነት የሚያጠብልን ስለሆነ
የእለቱን ጨዋታ ጥሩ በመጫወት
ግጥሚያውን ለማሸነፍ ችለናል፡፡ በሜዳ
ላይ በነበረው እንቅስቃሴ የእኛ ቡድን
ከተጋጣሚው የተሻለ ነበር፤ ለዛም ነው ብዙ
የግብ እድሎችን ልንፈጥርም የቻልነው፡፡
ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ከተገኙት የድል
ጎሎች አንዷን አስቆጥረሃል፤ ስሜቱ ምን
ይመስላል?
አቡበከር፡- የድል ጎሏ ውጤቱ
ስለሚያስፈልገን፣ ለአሸናፊነታችንም ወሳኝ
ከመሆኗ እና ከሊጉ መሪም ጋር ያለንን
የነጥብ ልዩነቱን እንድናጠብ ከማድረጓና
እንደዚሁም ደግሞ ለእኔም ጎሏን ከአንድ
ዓመት በኋላ ያስቆጠርኳት ስለሆነም
በጨዋታው ይቺን ጎል ማስቆጠር መቻሌ
በውስጤ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ነው
የተሰማኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ለመጨረሻ ጊዜ
መች ነበር ጎል ያስቆጠርከው?
አቡበከር፡- በአዳማ ከነማ ላይ ዓምና
ነበር ያስቆጠርኩት፤ ከዛ ወዲያ ጎል
አስቆጥሬ አላውቅም፤ በእሁዱ ጨዋታ
ግን ከብዙ ጊዜያት በኋላ ወደ አጥቂ ስፍራ
መጥቼ በተጫወትኩበት ፍልሚያ ይህን
ጎል ማስቆጠሬ ለወደፊቱ በርካታ ጎሎች
እንዲኖሩኝም በር ይከፍትልኛልና፤ ለእዚያ
የምዘጋጅባቸው ነገሮች ይኖሩኛል፡፡
ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ በባህር
ዳር ከተማ ቢሸነፍም አሁንም ሊጉን
እየመራ ነው፤ እናንተንም በ9 ነጥብ ርቋል፤
ይሄን ስትመለከት ዋንጫ የማንሳት እድላችሁ
የቱን ያህል ነው?
አቡበከር፡- የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ
ገና 10 ጨዋታዎች ይቀሩታል፤ በእነዚህም
ጨዋታዎች አሸናፊ መሆን ከቻልክ 30 ነጥብ
የምታገኝ ይሆናል፤ ይሄን ማሳካት መቻልም
ውጤታማ ያደርግሃልና አሁን ላይ የሊጉን
ዋንጫ የምናነሳበት እድልን እያመቻቸን
ነው የምንገኘው፤ በሊጉ በሲዳማ ቡና ላይ
የተጎናፀፍነው ጣፋጭ ድል አሁንም የሊጉ
ዋንጫ እኛን እንደሚፈልገን የጠቆመንም
ሆኗልና በቀሪዎቹ ግጥሚያዎቻችን ላይ
ጠንክረን እና በርትተን ሰርተን በመቅረብ
የድል ውጤቱን ወደ እኛ ክለብ ለማምጣት
ጥረትን እናደርጋለን፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ከእዚህ ቀደም
ብዙዎች መሪ ሆኖ ያውቁታል፤ ዘንድሮ ግን
ይህን እያሳካ አይደለም፤ የውጤት ማጣት
ችግሩ ምንድን ነው ትላለህ?
አቡበከር፡- አዎን ክለባችን ሁሌም
የሚታወቀው በመሪነቱ እና በሻምፒዮናነቱ
ነው፤ የዘንድሮ የውድድር ተሳትፎአችን
ላይ ግን ባጣናቸው ተደጋጋሚ ውጤቶች
በአሁን ሰዓት መሪ መሆን አልቻልንም፤
መሪ ያልሆንነው እና ውጤት ያጣነው በእኛ
ድክመት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ብዙ ቡድኖች
መጠንከርም ነውና ይሄን ሰው ሊረዳው
ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- የቅ/ጊዮርጊስን የውጤት ማጣት
ተንተርሶ የቡድናችሁ ከፍተኛ አመራሮች
አነጋግረዋችሁ ነበር፤ ቡድኑ ውስጥ የተለያዩ
ነገሮች ተዘርዝረው እዚህ ጋር ችግር አለ?
እዛ ጋርስ? ችግር ካለ ንገሩን ስትባሉ
ሁላችሁም ምንም ችግር የለም ብላችኋል፤
ችግር ከሌለ ታዲያ ቡድናችሁ ውስጥ ውጤት
እንዴት ሊጠፋ ቻለ?
አቡበከር፡- የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ አመራሮች
ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ውጤትን ከመፈለግ
አንፃር እኛን በተረጋጋና ጥሩ በሆነ ስሜት
ሰብስበውን ባናገሩን ወቅት ቡድኑ ውስጥ ምን
ችግር አለ ሲሉን የለም ያልነው የእውነት
ነው፤ ቡድናችን ውጤትን ያጣው ሌሎች
ቡድኖች ጠንክረውበት ስለመጡ ነው፤
ስለዚህም በቀሪዎቹ ጨዋታዎች እሱም እንደ
ሲዳማ ቡናው ቀን ጨዋታ እና ከዛም በላይ
ከእነሱ በተሻለ መልኩ መጠንከር ስላለበት
ወደዛ ለማምራት እየተዘጋጀን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታህ
ላይ ለቡድንህ ሙሉ ብቃቴን አውጥቼ
እየተጫወትኩ ነው ብለህ ታስባለህ?
አቡበከር፡- የቅ/ጊዮርጊስ ቆይታዬ ላይ
በአብዛኛው ስጫወት የነበረው በምፈልግበት
ቦታ ላይ ባይሆንም ሁሌም ግን አሰልጣኞቼ
በሚያሰልፉኝ ቦታ ላይ ለቡድኔ አንድ
ነገርን ሰርቼ ለመውጣት ራሴን ወደ ኋላ
ያደረግኩበት አንድም ቀን አጋጥሞኝ
አያውቅም፤ ለቅ/ጊዮርጊስ ስጫወት ሁሌም
ከቡድኑ ጋር ስኬትንም ለመጎናፀፍ የምፈልግ
አይነት ተጨዋችም ስለሆንኩ በቀጣይ ጊዜ
የቡድኑ ጨዋታዎች ላይም ከእኔ የሚጠበቁ
ብዙ ግልጋሎቶችን ለመስጠትም ዝግጁ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን
ግለፅ? ለእነሱም የምታስተላልፈው መልህክት
ካለህ?
አቡበከር፡-የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎችሁሌምከጎናችንየሆኑናምርጥም
ደጋፊዎች ናቸው፤ እነሱን በቀላል ቃላትም
የምትገልፃቸው አይደለምና ለሚሰጡን
ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናዬን ነው ማቅረብ
የምፈልገው፤ ለቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች አሁን
ላይ የማስተላልፈው መልዕክትም ሊጉ
ሊጠናቀቅ 10 ጨዋታዎች ይቀሩታል፤
በእነዚህ ቀሪ ፍልሚያዎች ላይ ከመሪው ክለብ
ጋር ካለን የነጥብ ልዩነት አንፃር ዋንጫውን
ማንሳት ይቻላልና በትዕግስት እንዲደግፉንም
ነው፤ ያን ሲያደርጉም በጋራ ዋንጫውን
ልናነሳ እንችላለን፡፡