የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ በየሳምንቱ
ማክሰኞ ለንባብ ስትበቃ ይዛ ከምትወጣው
ዘገባ መካከል የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾችን
በምናስታውስበት የOLDIES BUT
GOODIES አምዷ በዛሬ እትሟ ይዛሎት
የምትቀርበው በተጨዋችነት ዘመኑ ኳስን
በግብ ጠባቂነት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን
ብሎም ለተለያዩ የሀገሪቱ ክለቦች ለረጅም
ዓመታት የተጫወተውን አክሮባትቲስቱን/
ግብ ጠባቂ ጥላሁን እሸቱን ነው፤ ይህን
የቀድሞ ግብ ጠባቂ ብዙዎቹ የስፖርት
አፍቃሪዎችም የሚያስታውሱት በአየር ላይ
ተወርውሮ በሚይዛቸው ኳሶችን በተለይ
ደግሞ የሚጫወትበት ቡድን ሲያሸንፍም
አቻ ሲወጣም በአየር ላይ በመገለባበጥ
በሚያሳየውም ትርሂት ነው፤ ጥላሁን በእዚህ
ዙሪያ አስተያየቱን ሲሰጥ ‘‘በአየር ላይ ያኔ እኔ
እገለባበጥ የነበረው የስፖርት ቤተሰቡ በኳሱ
ብቻ ሳይሆን በእኔም አክሮባት ሊደሰትና
ሊዝናናም ይገባል የሚል እሳቤ ስለነበረኝ ነው፤
እኔም ደግሞ ከልጅነቴ አንስቶ ጅምናስቲክም
እሰራ ስለነበር በእዚያ ደረጃ ደስታዬን
ስገልፅ ደስ ይለኝም ስለነበር ለእዚያም ነው
የምገለባበጠው ሲልም ተናግሯል”፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞው
ግብ ጠባቂ ጥላሁን እሸቱ የእግር ኳሱን
ካቆመ በኋላ በአሁን ሰዓት ላይ በቀድሞ
የኒያላ እና የአየር መንገድ ግብ ጠባቂ
በነበረው አንድነት በቀለ /ቀዬ/ በከፈተው
የመስታወት መቁረጫ ድርጅት ውስጥ
ተቀጥሮ በመስራትና ኑሮውንም በመምራት
ላይ ሲሆን ይህንን የቀድሞ ግብ ጠባቂ
የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ
/G.BOYS/ በኳስ ህይወቱ ዙሪያ አናግሮት
ምላሹን እንደሚከተለው ሰጥቷል፡፡
-ስለትውልድ ስፍራህ አስተዳደግህና
የእግር ኳስ ጨዋታ አጀማመርህ፡-
‘‘የተወለድኩትና ያደግኩት ለኤርትራ ቅርብ
በሆነችው በሀሰብ አካባቢ ነው፤ እዛም ነው
የእግር ኳስን ልጅ ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር
በመጫወት የጀመርኩት”፡፡
-ከቤተሰባችሁ ውስጥ የእግር ኳስን
የምትጫወተው አንተ ብቻ ነህ? ስንት
ወንድምና እህትስ አለ?፡- “በቤታችን ውስጥ
ሁለት እህቶችና አንድ ወንድም ነው ያለኝ፤
ከቤቱም የእግር ኳስን የምጫወተውም
ስፖርተኛውም እኔ ብቻ ነኝ”፡፡
-የልጅነት ዕድሜክ ላይ የእግር ኳስን
ስትጫወት የቤተሰብ ተፅህኖ ነበረብህ፡
-‘‘በፍፁም፤ ያኔ ከኳሱ ውጪ አክሮባትና
ጅምናስቲክንም የምሰራበት ጊዜ ስለነበር
የአሁን ሰዓት ላይ በወሎ ክፍለ ሀገር
ኮምቦልቻ ከተማ ላይ የሚኖሩት ቤተሰቦቼ
በስፖርተኝነቴ ሁሉም ነገሬ ደስ ስለሚላቸው
በጊዜው እንደውም ያበረታቱኝም ነው የነበረው
እንጂ ምንም አይነት ተፅህኖን አይፈጥሩብኝም
ነበር፤ በእዚህ አጋጣሚ ያኔ እነሱ ያደርጉልኝ
የነበረው ድጋፍም እንክብካቤም መበረታታትን
እንዳገኝና ለበርካታ ክለቦችና በብሔራዊ
ቡድን ደረጃም እንድመረጥና የቡድኑም አባል
እንድሆን ስላደረጉኝ በእዚሁ አጋጣሚ እነሱን
ለማመሰገንና ያለኝንም ከፍተኛ ክብር መግለፅ
እፈልጋለው”፡፡
-በብዙዎች ዘንድ የምትታወቀው በግብ
ጠባቂነት ነው፤ በኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
ከእዚህ ስፍራ ውጪ ተጫውተህ ታውቃለህ?
እንዴትስ ግብ ጠባቂ ሆንክ፡-‘‘አዎን፤ የልጅነት
ዕድሜዬ ላይ ኳስን በሰፈር ደረጃ ላቋቋምነው
ዊንስተን ለሚባለው ቡድን ስጫወትም ሆነ
በትምህርት ቤት ደረጃ መጫወት ስጀምር
በቅድሚያ የግራ ተከላካይ /የስቶፐር/
ስፍራ ተጨዋች ነበርኩ፤ በኋላ ላይ የግብ
ጠባቂ የሆንኩት በአንድ ወቅት ላይ ለእዚህ
ቡድን እየተጫወትኩ ሳለው የእኛ በረኛ
የነበረው አደም በስራው ፍቶ አንሺ ነበርና
እሱ ይቀርብናል፤ በጊዜውም በእሱ ቦታ እኔ
በረኛ ሆኜ እንድጫወትላቸው የቡድናችን
ተጨዋቾች ስለጠየቁኝና ግባልንም ሲሉኝ
እሺ አልኩና በረኛ ገባው፤ በኋላም በእዚያው
ግብ ጠባቂ ሆንኩ፤ ቀጥሎም በእዚሁ ቦታ
ላይ እኔን የተመለከተኝ አማኑኤል ማቲዎስ
የተባለ የሀሰብ ከነማ ቡድን አሰልጣኝ ወደ
ክለቡ በማምጣት ሊያጫውተኝ ቻለ”፡፡
-ስለመጀመሪያ ክለቡና ወደ ቡድኑ ሲገባ
ስለተፈጠረበት ስሜት፡-‘‘ለመጀመሪያ ጊዜ
የእግር ኳስ ተጨዋች ሆኜ ያሳለፍኩበት
ክለቤ ሀሰብ ከነማ ነው፤ በእዚሁ ቡድን
ውስጥም ኳስን ከ1978-1979 ዓ/ም መጨረሻ
ድረስ ልጫወት ችያለው፤ ወደ ቡድኑ
የገባሁትም በአሰልጣኝ አማኑኤል ማቲዎስ
በሰፈር ደረጃና በትምህርት ቤት ውድድር ላይ
ስጫወት ተመርጬም ነውና ያኔ ወደ ቡድኑ
ስገባ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ነው በውስጤ
ሊፈጠርብኝ የቻለው”፡፡
-በእግር ኳሱ ሌሎች የተጫወትክባቸው
ክለቦችስ ማን ማን ይባላሉ፡-‘‘የእግር ኳስን
ለሀሰብ ከነማ ከተጫወትኩ በኋላ ቀጥዬ
የተጫወትኩባቸው ክለቦች ብዙ ናቸው፤
በቅደም ተከተልም ላስቀምጣቸው፤ በ1980
ለሕንፃ ኮንስትራክሽን፤ በመቀጠል በ1981
ለሀሰብ ነዳጅ ድርጅት፣ በ1982 በባህር
ዳር መምህራን ኮሌጅ እየተማርኩ ለባህር
ዳር ዩንቨርስቲና ለጎጃም ምርጥ ቡድን
ከተጫወትኩኝ በኋላ በትምህርቱ ከውጤት
አኳያም ብዙም ሳልቀጥል ቀርቼ ወደ ሀሰብ
ከተመለስኩና እዛው ከቆየው በኋላ ከ1984
ዓ/ም አንስቶ ለመድን አራት ዓመት፣
ለቡና አምስት ወር፣ ለኒያላ አንድ ዓመት፣
ለጉና አራት ዓመት፣ ለሐዋሳ ከነማ አንድ
ዓመትና፣ ለትራንስ ኢትዮጵያ ሁለት ዓመት
ከተጫወትኩኝ በኋላ ነው ኳስን ላቆም
የቻልኩት”፡፡
-ወደ አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ
ስትመጣ ለሕንፃ ኮንስትራክስን ክለብ ነበር
የተጫወትከው፤ ያኔ ግን ከክለቡ ጋር ብዙም
ሳትዘልቅ ለቀክ፤ ምክንያቱ ምን ነበር? ሕንፃን
ያኔ በምን መልኩስ ነበር የምትገልፀው?፡
-‘‘የሕንፃ ኮንስትራክሽን ክለብ ውስጥ ስገባ
ከቡድኑ ጋር የረጅም ጊዜ ቆይታ ይኖረኛል
ብዬ ነበር የጠበቅኩት፤ እነሱ በጊዜው ከሀሰብ
ከነማ ቡድን ያመጡኝም ያኔ የ11ኛ ክፍል
ተማሪ ነበርኩና ወደ 12ኛ ባለፍኩ ጊዜ
እናስተምርካለን ብለውም ነበርና ቡድኑን
ተቀላቀልኩ፤ በጊዜውም የነበረኝ የክለቡ
ቆይታ እነ ማቲያስ ሀብተማሪያም፣ ቢተው
አብሬና ጳውሎስ ጌታቸው /ማንጎን/ የመሳሰሉ
ተጨዋቾችን በያዘው ምርጥ ቡድን ውስጥ
ነበር የተጫወትኩትና የነበረኝን ቆይታዬን
በጥሩ መልኩ ነው የምገልፀው፤ ሕንፃ ጥሩ
ቡድን ነበር በክለቡ ውስጥ ተጫውቼ ማለፌም
ያስደስተኛል”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈለህን ደመወዝ
ታስታውሳለህ፤ ስንት ነበር? ምንስ
አደረግክበት?፡- ‘‘በእኛ ጊዜ ኳስን ስንጫወት
ደመወዝ አልነበረንም፤ ደመወዛችንም
ላወጣነው ከፍተኛ ላብ መተኪያ የሚሆንልንን
ምግብ በደንብ አድርገን እንመገብ ነበርና አንዱ
ደመወዝ ይሄ ነበር፤ ሌላው ኳሱንም ያኔ
ለፍቅር ስንል ብቻ እንጫወተውም ስለነበር
የሁላችንም የጊዜው ሁለተኛው ደመወዛችን
ኳሱን ተጫውተን የምናገኘው ደስታም
ጭምር ነውና ያ ልዩ ትዝታን ይጭርብኛል”፡፡
-ከእግር ኳሱ ውጪ ትምህርቱስ ላይ
እንዴት ነበርክ?፡-‘‘በትምህርቱም የምታማ
አልነበርኩም፤ በ1981 ዓ/ም ለሀሰቡ ነዳጅ
ድርጅት ቡድን ስጫወት የሀይስኩል ተማሪነበርኩና በሁለተኛው ደረጃ ትምህርቴ
2.8 በማምጣት ወደ ባህር ዳር መምራህን
ኮሌጅ አምርቼ ነበርና እዛም ተማርኩ፤
እየተማርኩም ነው ኳስን ለባህር ዳር
ዩንቨርስቲ ክለብ እጫወት የነበርኩትና በኋላ
ላይ ብዙም ባልቀጥልም ጊዜውን መቼም
ቢሆን አልረሳውም”፡፡
-በ1984 ዓ/ም ከሀሰብ በመፈናቀል ወደ
አዲስ አበባ መምጣትህ ይነገራልና ያን ወቅት
እስኪ አስታውሰን፡-‘‘አዎ፤ በጊዜው ወደ አዲስ
አበባ የመጣሁት በፖለቲካው ሳቢያ ኢአህዲግ
ሀገሪቷን የተቆጣጠረበትና ጦርነትም የነበረበት
ወቅት ስለሆነ እኔ ከምኖርበት ሀሰብ ነው
ከእነ ቤተሰቦቼ ተፈናቅለን ወደ አዲስ አበባ
የገባነው፤ አዲስ አበባ እንደመጣንም ጃንሜዳ
ላይ ነው መጠለያ ተሰጥቶን እንኖር የነበረውና
ያ ሰዓት የማይረሳ ታሪክ ሆኖ አልፏል”፡፡
-ከሀሰብ ተፈናቅለህ ከመጣ በኋላ
ሕይወት ምን ትመስል ነበር?፡-‘‘ያኔ
ተፈናቅዬ የመጣሁት ከእነ ቤተሰቦቼም ነበርና
መጀመሪያ አካባቢ ትንሽም ቢሆን በህይወቴ
ተቸግሬያለው፤ ከጃንሜዳም በኋላ በሀሰብ
የማውቃቸው ጓደኞቼ አዲስ አበባ ነበሩና
እነሱ ቤት ሄጄ መሬት ላይ ፍራሽ እያነጠፍን
በጋራ አድርና አብረንም እንኖር ነበርና ያ ጊዜ
የሚገርም ነበር፤ ያኔ የጓደኞቼ እናትና አባት
የነበሩት አቶ አባይ አድጎና አሁን ላይ በህይወት
የሌሉት ነብሳቸውን ፈጣሪ ይማረውና ወ/ሮ
እምባአፍራሽን ከእነ ልጆቻቸው ጥሩ ነገርን
አድርገውልኛልና እነሱን በጣም ለማመሰገን
እፈልጋለው፤ በእዚያ ጊዜ የሕይወት
ቆይታዬም በመቀጠል የግድ ራሴንም
ቤተሰቦቼንም መርዳት ስለነበረብኝም ባለኝ
የግብ ጠባቂነት ሙያ ክለብ ማፈላለግ አለብኝ
በሚል ጉዞዬን ወደ ተለያዩ ክለቦች አደረግኩ፤
ወደ ፖሊስ፣ አየር ኃይል፣ ኪቤአድና ወደ
መሳሰሉት ብዙዎቹ ክለቦችም ጋር ሙከራን
ባደርግም ልያዝ አልቻልኩም፤ በኋላ ላይ ግን
ለመድን በምሞክርበት ሰዓት አሰልጣኝ ስዩም
አባተ እኔን ለክለቡ 3ኛ ግብ ጠባቂ አድርጎ
ሲመርጠኝ በጣም ተደሰትኩ፤ ያም ሆኖ ግን
ለመድን ልያዝ ብችልም ቡድኑ ወዳረፈበት
ብሉ ናይል ሆቴል ያልገባው ስለሆንኩ
በየጊዜው ተፈናቅለን ከምንኖርበት ጃንሜዳ
ልምምድ ሜዳ ድረስ እየተመላለስኩ ስሰራ
የትራንስፖርት ብርና ምግብ የምመገብበትም
ገንዘቤ ሲያልቅ ጊዜ ለስዩም በመጠራጠር
ሄድኩና ለቡድኑ ይዘከኛል ወይንስ
አልያዝከኝም የሚል ጥያቄ ሳቀርብለት እንዴ
አንተንማ ይዤካለው ለምን ሆቴል አትገባም
ሲለኝና የሁለት ወር ደመወዝም 600 ብር
ሲያሰጠኝ ጊዜ መረጋጋት የቻልኩበትንና
በኋላም ላይ እኛ የምንኖርበት ካምፕም
እንድንገባበት ተሰርቶም ተጠናቆም ነበርና
በእዚሁ በ1984 ዓ/ም የመድን ተጨዋች
የሆንኩበትን ጊዜ አልረሳውም”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
ትልቁን እውቅና ያገኘህበት ክለብ ማን ነው?
ስኬታማ የሆንክበትስ…፡-‘‘ስላሳወቀኝ ክለብማ
ምን ይጠየቃል! መድን ነዋ! መድን ለእኔ
ቤቴ፣ ቤተሰቤና ሁሉ ነገሬ ነው፤ ያሳደገኝ፤
ለጥሩ ደረጃ ያበቃኝና ለከፍተኛ እውቅናም
ሊያደርሰኝ ስለቻለ የነበረኝን ጣፋጭ የሆነ
የ4 ዓመታት ቆይታዬን መቼም ቢሆን
የምረሳውም አይደለም፤ በክለቡ ስሰለጥን
በጥሩ አሰልጣኞች ስዩም አባተና ነብሱን
ይማረው ገዘኸኝ ማንያዘዋል ስር መሰልጠኔና
ከእነ ጉልማ፣ በላያ ብሩክና ተክሌም ጋር አብሬ
በመጫወቴ ደስ የሚል ጊዜን እንዳሳለፍበትም
ነው ያደረገኝ፤ ከመድን ውጪም በጉና ንግድ
ቡድን የአራት ዓመታት ቆይታዬ ጥሩ ጊዜን
ለማሳለፍና በአፍሪካ ክለቦች የውድድር
ተሳትፎም ላይ ቡድኑ እንዲካፈል ጥረትን
አድርጌያለው፤ ሌላው ከሐዋሳ ከተማ ጋር
የተቀዳጀሁት የሊግ ዋንጫም አለና በእነዚህ
ክለቦች ውስጥ ነው መድንን ጨምሮ የስኬት
ጊዜን ለማሳለፍ የቻልኩት”፡፡
-ለመድን ያደረግከውን የመጀመሪያ
ጨዋታ ታስታውሳለህ፡-‘‘በወዳጅነት ጨዋታ
ችን ከሆነ አዎ አስታውሳለው፤ ያኔ የጋዜጠኞች
ማህበር ያዘጋጀው አንድ ጨዋታ ነበርና
እኛና ባንክ ለፍፃሜ ተጫወተን ስናሸንፋቸው
በጊዜው ወደ ሜዳ ገብቼ ተጫውቻለው፤
በመደበኛ ውድድር ከሆነ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ
ያደረግኩትን ግጥሚያ ከማን ጋር እንደሆነ
ባላስታውስም ተቀይሬ ገብቼ ተጫውቻለው፤
በመድን የእዚያን ጊዜ ተጨዋችነቴም ተቀይሬ
ወደ ሜዳ የገባሁት ይልማ ከበደ /ጃሬ/ ጥሩ
ችሎታ ስለነበረውና እሱንም ማስቀመጥ ከባድ
ስለነበርም ነው”፡፡
-የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
ምርጡ አሰልጣኝ፡-‘‘ስዩም አባተ ነዋ! እሱ
በማሰልጠን ብቃቱ ልዩ ሰው ነው፤ ለብዙ
ወጣት ተጨዋቾች የመጫወት እድሉን
በመስጠት ለእውቅና ያበቃና በችሎታክ
ብቻም ተመርኩዞ የሚመርጥክና ብቃትክንም
በየጊዜው እንድታሳድግም ማድረግ የሚችል
ነውና እሱን ነው የቅድሚያ ደረጃ ሰጥቼው
የማደንቀው፤ ከስዩም በመቀጠል የማደንቀው
ደግሞ አሁን ኢንስትራክተር የሆነውን
የቀድሞ የጉና ንግድ አሰልጣኜን አብርሃም
ተክለሃይማኖትን በስልጠናው አሁን ላይ
በጣም የተሸሻለና ከፍተኛ እውቀትንም
የያዘበት ጊዜ ስለሆነ እሱን አደንቀዋለው”፡፡
-የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
ምርጡ ተጨዋች፡-‘‘ለእኔ የመጀመሪያው
ተጨዋች ነብሱን ይማረውና አሰግድ ተስፋዬ
/ጂረስ/ ሲሆን ቀጥዬ ደግሞ የማደንቃቸው
ተጨዋቾች አብዲ ሰይድንና ተክሌ ብርሃኔን
ነው፤ ሶስቱም በአንድ ወቅት የመጡና
በችሎታቸውም ቀልብን ይስቡ ስለነበርም ነው
በጣም ላደንቃቸው የቻልኩት”፡፡
-እንደ ግብ ጠባቂነትህ በእግር ኳሱ
ከአንተ ፊት አብረውክ ከተጫወቱ ውስጥ
በጣም የተስማማክና ያደነቅከው ተጨዋች፡
-‘‘ይሄ ተጨዋች ተከላካይ ሲሆን በመድን
ውስጥ አብሮኝ ተጫውቷል፤ ስሙም ዳንኤል
አስግዶም /ቦዬ/ ይባላል፤ የእሱ የኳስ ችሎታ
ልዩ ነው፤ በጣም ብልጥና ኳስን ከተቃራኒ
ቡድን ላይ እንዴት መንጠቅ እንዳለበትም
በሚገባ የሚያውቅ ነበርና ለእሱ ነው የተለየ
አድናቆት ያለኝ”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
አብረከው ባለመጫወትህ የሚቆጭህ
ተጨዋች አለ፡- ‘‘ከብዙዎቹ ጋር በተደጋጋሚ
የተጫወትኩበት አጋጣሚ ስላለ አብሬው
ባለመጫወቴ የሚቆጨኝ ተጨዋች ማንም
የለም”፡፡
-የእግር ኳሱ ላይ የአንተ ተቃራኒ
ሆነው በመጫወት በጣም ያስቸግሩክ የነበሩት
ተጨዋቾች፡- ‘‘ሁለት ናቸው፤ እነሱን
መያዝም ይከብዳልና በአስቸጋሪ አጥቂነታቸው
የምጠቅሳቸው ሙሉጌታ ከበደንና ኤልያስ
ጁአርን ነው”፡፡
-ከጥላሁን ውጪ አክሮባትቲስቱ
እንደምትባል እናውቃለን፤ ከእዚያስ ሌላ
የምትጠራበት ስያሜ አለህ…?፡-‘‘አዎን፤
በሀሰብ እያለው የምጠራበት ስም ነበር፤
ጓደኞቼም ጥላሁን ጆርጅም ነበር የሚሉኝ፤
ይህን ስም ጓደኞቼ ያወጡልኝ አንዴ የጥቁር
ፊልም ካዩ በኋላ አክተሩም ጥቁር ስለነበርና
ሁሉም ነገሩም አንተን ይመስላልም በሚል
ነው በስሙ የሚጠሩኝ የነበሩት”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ በጣም
የተደሰትክበት ቀን፡-‘‘ለኢትዮጵያ ብሔራዊ
ቡድን በአሰልጣኝ ጌታሁን ወልደ ጊዮርጊስ
የኃላፊነት ዘመን ስመረጥና ወደ ኡጋንዳም
በተጓዝንበት ወቅት ያኔ በጣም ነበር ደስ
ያለኝ፤ የአንድ እግር ኳስ ተጨዋች ትልቁ
እልምም ለብሔራዊ ቡድን መመረጥም
ስለነበር ያኔ ደስታዬ በጣም ከፍ ሊልም
ችሏል፤ ሌላው የተደሰትኩበት ቀን ለመድን
ክለብ ለመጀመሪያ ጊዜ ስመረጥ ነው፤ መድን
ምርጥና ተወዳጅ ቡድን ስለነበርም ነው
እነዚያን ሁለት የደስታዬ ቀናቶቼን ፈፅሞ
የምረሳቸውም አይደለም”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
በጣም ያዘንከውና ልብህ የተሰበረበት ቀን፡
-‘‘የመጀመሪያውና ትልቁ ሀዘኔ በመድን
አብሮኝ የተጫወተው ተከላካያችን ወንድማገኝ
/ፔሌ/ እንደ እኔ ሁሉ ያኔ የወባ ሕመም ይዞት
ነበርና እሱን በሞት ሳጣው ልቤ ነው በሀዘን
የተሰበረው፤ እኔና ፔሌ በጊዜው ሕመሙ
በያዘን ጊዜ ቀበና አካባቢ በሚገኘው ሰናይ
ክሊኒክ አጠገብ ለአጠገብ ነበር የተኛነውና
የእሱን ማረፍ ስሰማ በጣም ነው ላዝን
የቻልኩት፤ ሌላው ሀዘኔ ምርጥ ቆይታ
ካሳለፍኩበት የመድን ክለብ በ1989 ላይ
ስቀነስና ከሐዋሳ ከተማም ጋር የፕሪምየር
ሊጉን ዋንጫ በ1996 ዓ/ም አግኝቼ ወዲያው
ከቡድኑ የተቀነስኩበት አካሄድ ተገቢ
አልነበረምና ያ ስሜትን የሚጎዳ ሆኖ ነው
ያገኘሁት”፡፡
-የመድን ክለብ ውስጥ ስትጫወቱ
ደስታን ይፈጥርላችሁ የነበረውና ጥርሳችሁን
የማያስከድናችሁ ተጨዋች ማን ነበር? አንድ
ቀልድስ ጣል ብታደርግብን፡-‘‘ያኔ ብዙዎቹ
ተጨዋቾች አስቂኞች ቢሆኑም ብሩክ
እስጢፋኖስ /ካንቶና/ ግን የተለየ ነበር፤ አንዴ
ምን ሆነህ መሰለህ እሱን ጨምሮ የቡድናችን
ተጨዋቾች ውስጥ እንግሊዘኛ የሚችል
ተጨዋች የለም፤ ከዛም ብሩክ አንድ የውጪ
ዜጋን ሲያገኝ ጊዜ ያልተፃፈበት ነጭ ወረቀት
ስጠኝ ለማለት ፈልጎ ለፈረንጁ ‘‘ኖ ራይት”
ሲለውና ፈረንጁም ስላልገባው ዋት? ካለው
በኋላ እኛም ምን ለማለት ፈልገህ ነው ስንለው
እኔና እሱ ተግባብተናል ካለን በኋላ ፈረንጁም
በኋላ ላይ ነጭ ወረቀት አምጥቶ የሰጠውን
ሁኔታ ስናይ በሁላችንም ዘንድ በኋላ ላይ
የደስታ ሳቅ ተፈጥሮብን ነበርና ብሩክ በብዙ
ነገሮቹ ለእኛ አዝናኛችን ነበር”፡፡
-የመድን ተጨዋቾች በአንድ ወቅት
የኢትዮጵያን ባንዲራ የሚገልፅ ባነር
እጅህ ላይ አስረህ አንተንስ የኮመኩክ ነገር
ምን ነበር፡- “ሳቅ ካለ በኋላ የመድን ቡድን
በጊዜው ለኢንተርናሽናል ጨዋታ ወደ ሩዋንዳ
ያመራበት ጊዜ ነበር፤ ያኔ እዛ ከሄድን
በኋላም የቡድናችን ተጨዋቾች በእኔ እጅ ላይ
የታሰረውን የሀገራችንን ባንዲራ ሲያዩ በአንተ
ቤት ከእነሱ ተለይተህ ሞተሃል፤ የሩዋንዳም
ባንዲራ እኮ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው፤ አንተም
እነሱን ነው የምትመስለው ያሉኝ በጣም ያሳቀኝና ፈፅሞም የማልረሳውም ነው”፡፡
-ኢትዮጵያ መድንን ከለቀክህ በኋላ ቡናንም
ተቀላቅለህ ነበር፤ የቡና ቆይታህስ ምን ይመስል
ነበር..ከክለቡስ እንዴት ለቀቅህ?፡-‘‘የቡና ቆይታዬ
የወራቶች ያህል ማለትም የአምስት ወር ስለነበር
ያንን ያህል ብዙ ትዝታው የለኝም፤ ያም ሆኖ
ግን ክለቡ የሀገሪቱ ትልቁና ተወዳጁም ስለነበር
ወደ ቡድኑ ለመግባት ስለቻልኩና ለጥቂት
ጊዜም ቢሆን ስለተጫወትኩ በእዚያ ደስተኛ
ነኝ፤ ከቡና የወጣሁት በመድን በነበረኝ ቆይታ
ከስዩም ጋር አንድ አንዴ ስትሰራ ላትግባባ
የምትችልባቸው ጊዜያቶች አሉና እንደ ሰው
ደግሞ አንድ አንዴ ላትግባባም የምትችልባቸው
ሁኔታዎች ስላሉ ያ ጉዳይ ነው ቡና ውስጥ
መጥቶ እኔ ክለቡን እንድለቅ ያስቻለኝ፤ ይኸውም ምንድን ነው መሰለህ ከስዩም ጋር
በመድን እያለው ከሁላችንም ተጨዋቾች ጋር
ቡድኑ ውጤት እያጣ ነበርና ያለመግባባት ነገር
ከእኛ ጋር ነበረው፤ በጊዜው ታዲያ ከሀሰን
በሽር በስተቀር ሁላችንም እሱ እንዲለቅ ለክለቡ
አመለከትንና ፈርመንም ደብዳቤ ስናስገባ እሱ
ለካ ቀድሞን ቡድኑን ለቅቆ ወጥቷልና በጊዜው
የተፈጠረው ጥሩ ያልሆነው ግንኙነታችን ነው
እሱም እኔም ወደ ቡና ከመጣን በኋላ ለእኔ
መውጣቴ ምክንያት የሆነኝ፤ በጊዜው ከስየም
ጋር ባንስማማም ለእኔ ግን ሁሌም ምርጡ
አሰልጣኝ እሱ ነው እወደዋለው፤ ስዩም
በአሰልጣኝነት ህይወቱ አንድን ግጥሚያ ዛሬ
1-0 አሸንፈን እንወጣለን ካለ ያሸንፋል፤ ሲሰራ
የሚያስበውን በደንብ ያውቃል፤ ይህ ሁሉ ነገር
ኖሮት ግን ከተጨዋቾች ጋርና ከኮሚቴ ጋር
በጥቂት ነገሮች ጭምር የሚጣለበት ሁኔታና
ባህሪው ሁሌም ለእኔ ይገርመኛል”፡፡
-የእግር ኳስ ተጨዋች ሆነህ በማለፍህ
ምን ትርፍ አግኝተሃል፤ ገንዘብ..? ወርቅ…?
ወይንስ መኪና?፡- ‘‘በዋናነት የሰው ፍቅሩን፣
ደጋፊንና የሚያበረታታክን ሰው ሳገኝበት ከእዛ
ውጪም ተጨዋች እያለው በክለብ ደረጃ
ከሐዋሳ ከተማ ጋር የሊጉን ዋንጫ ማንሳቴን
ተከትሎ እንደዚሁም ደግሞ በሩዋንዳው
የአሰልጣኝ አስራት ኃይሌና የሰውነት
ቢሻው ቡድን ስብስብ ውስጥ የሴካፋን
ዋንጫ በማግኘታችን ለሁለት ጊዜ
የመሬት ስጦታን ስላገኘው እነዚህ ልዩ
ትርፎቼ ሆነው ነው ያለፉት”፡፡
-የጥላሁን ድሪም ቲም ራሱን አካቶ
እነማን ናቸው፡- ‘‘በ3-5-2 አጨዋወት
ውስጥ ግብ ጠባቂ ራሴን ካስቀመጥኩ
በኋላ ተከላካዮች ሳሙኤል ደምሴ /
ኩኩሻ/ ዳንኤል አስግዶም /ቦዬና/ ዳዊት
/ቹቹ/ አማካዮች ተክሌ ብርሃኔ፣ ጉልማ
ጉተማ፣ አድማሱ ነበረኝ፣ ሙሉጌታ
ምህረትና አዳነ ግርማ ሲሆኑ አጥቂዎች
ደግሞ በላይነህ አስቻለው /በላያ/ እና
ነብሱን ይማረው አሰግድ ተስፋዬ ናቸው
የእኔ ምርጫዎቼ”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ
የግብ ጠባቂነት ጓንቱና ለአንዴና ለመጨረሻ
ጊዜ በምን መልኩ ሊያወልቅ እንደቻለ፡
– ‘‘የግብ ጠባቂነትን ለማቆም የቻልኩት
ለትራንስ ከተጫወትኩ በኋላ ነው፤ ለማቆሜ
ምክንያት የሆነኝም ከዛ ከወጣው በኋላ ክለብ
ፈልጎ መግባት ከባድ እየሆነ ስለመጣና በጣም
በመተዋወቅና በመቀራረብ ስለሆነና ራሴው
ፈልገው ሳይሆን በሰዎች አመለካከት ነው፤
በጊዜው ለብዙ ዓመት መጫወት እችል ነበር፤
በድጋሚ ወደ አንድአንድ ክለቦች ለመግባትም
ሙከራ ባደርግም ሊሳካ ስላልቻለና በሰዎች
አመለካከትም ኳሱን ለምን አያቆምም፤
ለወጣቶች ለምን ቦታውን አይለቅም፤
አይበቃውም ወይ የሚሉ ንግግሮች ሲደጋገሙ
ጊዜ ነው በኋላ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ
ጊዜ ያቆምኩት እንጂ ኳሱ በቅቶኝ አይደለም
ያቆምኩት”፡፡
-ወደ አሰልጣኝነት ሙያው የመምጣት
ፍላጎትህ የቱን ያህል ነው?፡- ‘‘ፍላጎቴማ
ከፍተኛ ነው፤ ለእዚያም ነው እኮ ከዚህ በፊት
ጊዜያዊ የስልጠና ኮርስን ልወሰድ የቻልኩት፤
በማሰልጠኑም ሆነ በሌላ ሙያ ሀገሩን በሙያው
ማገልገልስ የማይፈልገው ማን ነው! አሁንም
ድረስ የሚያሰራኝን አካል እየፈለግኩም ነው፤
አሁን ላይ ሪስክ ወስዶ የሚወስድህ ክለብ
የለም፤ ብዙ ቦታም ሄዶ ለመስራት ነገሮች
በጣም በመቀራረብ ሆነና ማንን ሄጄስ ልጠይቅ፤
አሰልጣኝ ለመሆን እፈልጋለው፤ መስራት
እየቻልኩ ባለመስራቴ በጣም ነው የማዝነውና
ይሄ ችግር የሚቃለልበት ሁኔታ ቢፈጠር በጣም
ነው ደስ የሚለኝ”፡፡
-ጥላሁን ራሱን በ3 በተመረጡ ቃላቶች
ሲገልፅ፡- ‘‘ዝምተኛ፣ ደስተኛና ተጨዋች፣
ለሰውም ክፉ ሳያስብ ሰውን በሰውነቱ
የሚያከብር ነው”፡፡
-የእግር ኳሱን ካቆምክ በኋላ አሁን ላይ
በምን ሙያ ተሰማርተህ ትገኛለህ፡- ‘‘የእግር
ኳሱን ካቆምኩ ወደ 11 ዓመታት ቢጠጋኝም
ከእዚያ በኋላ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት
አሳልፌ ቆይቻለው፤ ከዚህ በፊት ዳንኤል
የሚባል ኪክ ቦክሰር የሚያሰለጥን ጓደኛ ነበረኝና
ከእሱ ጋር በጋራ በመስራትና ቀለምም በመቀባት
ሙያ እንሰራ ስለነበር በዛ ሙያ ቆይቻለው፤
ንግድም ሞክሬያለው አልቻልኩም፤ ታክሲም
ነበረኝና እሱንም ብሰራም ታክሲው ሲበላሽ
ሸጥኩትና ከእዚህ በኋላ በነበረኝ ህይወት በካናዳ
ኤምባሲ በጥበቃ ሙያ ላይ ከሰራው በኋላ
ነው የቀድሞው የኒያላና የአየር መንገድ ግብ
ጠባቂ አንድነት በቀለ /ቀዬ/ የእኔን
ያለሁበትን ሁኔታ ካየ በኋላ እሱ
ለቡ አካባቢ በከፈተው የመስተዋት
መቁረጫ ፋብሪካ ውስጥ መጀመሪያ
በጥበቃ እንድሰራ ካደረገኝ በኋላ
ስራዬ ላይ ጥሩ ሆኖ ሲያየኝ
የራሱን ፋብሪካ የራሴ ድርጅት
ነው ብቻ ሳይል አሁን ከእኔ ጋር
በመስራት የተሻለ ሰው ትሆናለህ፤
እንረዳዳለንም፤ ፋብሪካው የእኔ ብቻ
አይደለም፤ በስራ ሁላችንም ነው
ጠንክረን መስራት ያለብን ስንሰራ
እናድጋለን ካልሰራን ደግሞ በጋራ
ሁላችንም እንወድቃለን፤ ጥሩ ስራ
ሰርተን ተያይዘን ነው የምናድገውም
በማለት እራሱን እንደአሰሪ እኛንም
እንደሰሪ ብቻ ሳይመለከት በጋራ
ጥሩ ስራ በመስራት ከእሱ ጋር
የፋብሪካውን ስራ በጋራ እየሰራው
ነው ያለሁትና በእዚህ አጋጣሚ አንድነት
ላደረገልኝ ነገር ሁሉ ከልብ ላመሰግነው ነው
የምወዳው”፡፡
-ስለ ትዳር ሕይወቱና ባለቤቱን ሲገልፃት፡
-‘‘ትዳርን ከ1985 ጀምሮ ከተዋወቋት ፍቅረኛዬ
ጋር በ1989 ዓ/ም ላይ መስርቻለው፤ ባለቤቴም
ወ/ሮ መስከረም በቀለ ትባላለች፤ በመሰረትነው
ትዳርም ከእሷ የ22 ዓመት እድሜ ያለው
ዮሴፍ ጥላሁን የተባለ ልጅና የ18 ዓመት
እድሜ ያላት አባጊያ የተባለች ልጅም አለኝና
በትዳር ሕይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ባለቤቴን
ስገልፃት ምን እንደምላት አላውቅም እሷ እናቴ፣
እህቴና ምርጥ ሚስቴ ናት የእሷ ከፍተኛ
ድጋፍና ፅናትም ነው ቆሜ ለመሄድም አንዱ
ያበቃኝ”፡፡
-ከውጪ ብሔራዊ ቡድኖች የምትደግፈው፡
– ‘‘ሁሌም ጥሩ ለሚጫወት ነው የምደግፈው፤
የብራዚልና የስፔን ብሔራዊ ቡድኖችን
አጨዋወትን ስለማደንቅም የእነሱ ደጋፊ ነኝ”፡፡
-ከባህር ማዶ ክለቦች የምትደግፈውስ፡
– ‘‘አርሰናል ጥሩ ስለሚጫወትና ወጣቶችም
ስለሚበዙበት እነሱም ደስ ይሉኛል”፡፡
-ከባህር ማዶ አሰልጣኞች በአሰለጣጠን
ብቃቱ የምታደንቀውስ፡- ‘‘አርሰን ቬንገርን፤
እሳቸው ጥሩና በወጣቶች ላይ የሚያምኑም
ስለሆነ አደንቃቸዋለው”፡፡
-ከባህር ማዶ ተጨዋቾች የምታደንቀውስ፡-
‘‘ሮናልዲኒሆን፤ አጨዋወቱ ስለሚማርክ የእሱ
አድናቂ ነኝ”፡፡
-በመጨረሻ… ‘‘በእግር ኳስ ተጨዋችነት
ዘመኔ ላይም ሆነ አሁን ላይ ከእኔ ጎን ሆነው
ሕይወቴን በጥሩ ሁኔታ ልመራ እንድችል
የማውቃቸው ሰዎች እየረዱኝ ይገኛል፤ ዛሬ
ለደረስኩበት ደረጃም በመጀመሪያ ፈጣሪዬ
መድኃኒያለም ቅድሚያውን ይወስድና ከእሱ
በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼ፣ የባለቤቴ ቤተሰቦች
ባለቤቴ ራሷ፤ ከስደት ማለትም ከተፈናቀልንበት
ጊዜ ጀምሮ የሀሰብ አብሮ አደግ ጓደኞቼ እና
የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋች የሆነው አድማሱ
ነበረኝና አንድነት በቀለም እኔን ስራ በመቅጠር
እየረዳኝ ነውና እነዚህን እና በአጠቃላይ
የቀድሞ ስፖርት አፍቃሪዎችን ላመሰግን ነው
የምወደው”፡፡