ዛሬ ሁለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችን ያስተናገደው ትግራይ ዋንጫ ለፍፃሜ ያለፋትን ሁለት ክለቦች ኣሳውቋል።የሁለቱም ጨዋታ ሪፖርት በዚህ መልክ ኣዘጋጅተነዋል።
ሽረ እንዳስላሴ 0(3)-0(4) ድሬዳዋ ከተማ
7:41 ላይ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጥሩ ፋክክር የታየበት ነበር፤በተለይ ድሬዎች ጨዋታው ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል።በ3-4-3 ኣሰላለፍ ወደ ሜዳ የወረዱት ሽሬዎች ከኣዲሱ ኣሰላለፍ ጋር መላመድ ከብድዋቸው ታይቷል።ከኃላ ኳስ መስርተው ለመጫወት ሚሞክሩት በዳንኤል ጸሃየ ሚመሩት ሽሬዎች ኳስ ከኃላ በሚጀምሩበት ጊዜ ድሬዎች ሰው በሰው በመያዝ(man marking) ሙከራቸውን ሲያደናቅፋ ነበር።በመጀመርያው 45 ብልጫ ወስደው የተጫወቱት ድሬዎች በ4-2-3-1(ሲከላከሉ ወደ 4-4-1-1 ሚቀየር) ኣሰላለፍ ቀኝ መስመር ላይ ትኩረት ኣድርገው ሲንቀሳቀሱ ነበር።መሃል ሜዳ ላይ የተሰለፋት ፍሬድ ሙሺንዲና ሚኪያስ ግርማ የሽሬ መሃል ክፍል ኳስ በሚይዝበት ጊዜ ጫና በመፍጠር ኳስን በመንጠቅ ቡድናቸውን ሲመሩ ነበር።ፊት ላይ የተሰለፋት ኢታሙኔ ኮሚኔ ና ራምኬል ሎክ ተደጋጋሚ ዕድሎችን ቢያገኙም ወደ ግብ መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።በተለይ 7ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ያሾለከለትን ኳስ ኮሚኔ ከበረኛው ኣንድ ለኣንድ ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ እንዲሁም የተከላካዩ ዲሜጥሮስ ወ/ስላሴ ስህተት በመጠቀም ራምኬል ከበረኛው ጋር ቢገናኝም ጨዋታው ላይ በርካታ ኳሶችን ያዳነው ሳንደይ ኣድኖበታል።ጣጣቸውን የጨረሱ ኳሶች መፍጠር ላይ ችግር የታየባቸው ሽሬዎች በ5ኛው ደቂቃ ላይ በልደቱ ለማ ኣማካኝነት ካገኙት የግብ ሙከራ ውጭ ይህ ሚባል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ እረፍት ወጥተዋል።
- ማሰታውቂያ -
ሁለተኛው ኣጋማሽ ብዙ ሙከራ ያልታየበት በሁለቱም ቡድን በኩል መሃል ሜዳ ላይ የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ነበር።ሽሬዎች መሃል ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመመለስ ኣሸናፊ እንዳለን በሄኖክ ካሳሁን፣ሰለሞን ገ/ማርያምን በደሳለኝ ደባሽ ቢቀይሩም የተፈለገውን ያህል ለውጥ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።ድሬዎችም በሱላ ኣብዱላሂና ሚኪያስ ግርማ ኣማካኝነት የግብ ሙከራ ቢያደርጉም የሽሬን መርበብ መድፈር ሳይችሉ ቀርቷል።የጨዋታው ኣሸናፊ ለማወቅ በተሰጡት መለያ ምቶች ድሬዳዋ ከተማ 4ለ3 በማሸነፍ ወደ ፍፃሜ ማለፋቸውን ኣረጋግጠዋል።
መቐለ 70 እንደርታ 4-1 ደደቢት
10፡05 ላይ የጀመረው የመቐለ 70 እንደርታና የደደቢት ጨዋታ በምዓም ኣምበሳዎቹ በላይነት ተጠናቋል።ብዙ ደጋፊ የተከታተለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኣምስት ግቦችን ማስተናገድ ችሏል።የመጀመርያው 45 መቐለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ደደቢቶችም በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ ታይቷል።በ4-2-3-1 ኣሰላለፍን የተገበሩት መቐለ 70 እንደርታዎች ጋብርኤል መሃመድ፣ሚኪኤለ ደስታ(ጥልያን) እና ሃይደር ሸረፋ መሃል ላይ የፈጠሩት ጥምረት ቡድኑ ፍሰት ያለው ጨዋታ እንዲጫወት ረድቶታል።ቀኝ መስመር ላይ ያመዘነው የመቐለ ማጥቃት እንቅስቃሴ የመጀመርያው ኣጋማሽ ላይ ብዙ ዕድሎችን በኣማኑኤል ገ/ሚካኤልና በጋብርኤል መሃመድ ኣማካኝነት መፍጠር ችለዋል።ደደቢቶችም በዳንኤል ጌድዮንና በኣለምኣንተ ካሳ ኣማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፤በተለይ በ13ኛው ደቂቃ የመቐለ ተከላካዮችን ወደ መሃል ሜዳ መጠጋትን ተከትሎ ኣለምኣንተ ካሳ መሃል ለመሃል ያሾለከውን ኳስ በቀኝ መስመር የተሰለፈው ዳንኤል ሾልኮ በመውጣት ከሶፈንያስ ጋር ቢገናኝም ኳሱን ወደ ቀኝ ከግቡ ወደቀኝ መትቶ ኣባክኖታል።የመጀመርያ 45 ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ ሲቀረው ከግራ መስመር በጥሩ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ጋናዊው ጋብርኤል መሃመድ በግራ እግሩ ኣክርሮ በመምታት ምዓም ኣምበሳዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
በሁለተኛው ኣጋማሽ ይበልጥ ተጠናክረው የመጡት መቐለ ሁለተኛው ኣጋማሽ በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ላይ ሃይደር ሸረፋ ከግራ መስመር ያሬድ ከበደ ያቀበለውን ኳስ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ ኣሳርፎታል።የማጥቃት ሃይላቸውን ኣጠናክረው የቀጠሉት የገ/መድህን ልጆች በ60ኛው ደቂቃ ኣማኑኤል መትቶት የግቡ ኣግዳሚ መልሶ የመጣውን ኳስ ጨዋታው ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሚኪኤለ ደስታ ኣስቆጥሮ መቐለ 70 እንደርታ 3ለ0 እንዲመራ ኣስችሎታል።ከሁለቱ ግቦቹ በኃላ መረጋጋት የተሳነው የደደቢት ተከላካይ ክፍል ሦስተኛው ግብ ካስተናገደ ከ8 ደቂቃ በኃላ ኣማኑኤል ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ኦሰይ ማውሊ በግምባሩ በመግጨት የመቐለን ግብ ኣራት ማድረስ ችሏል።ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃዎች ሲቀሩት ደደቢቶች ከበባዶ ሽንፈት የገላገለቻቸውን ግብ በኣክዌር ቻም ኣማካኝነት ኣግኝተዋል።
በሁለቱም ጨዋታዎች ውጤት መሰረት መቐለ 70 እንደርታ እና ድሬዳዋ ከተማ ለትግራይ ዋንጫ ፍፃሜ ማለፋቸውን ኣረጋግጠዋል።
እሁድ ጥቅምት 4/2011
መቐለ 70 እንደርታ ከ ድሬዳዋ ከተማ