በሽቶ ሚድያ ፕሮዳክሽንና ትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኣዘጋጅነት ለመጀመርያ ጊዜ ዛሬ የተካሄደው ትግራይ ዋንጫ ሁለት ጨዋታዎችን ኣስተናግዷል።ዛሬ የተካሄዱትን ሁለት ጨዋታዎች ሪፖርት በሚከተለው መልኩ አዘጋጅተነዋል።
ወልዋሎ ዓ.ዩኒቨርስቲ ከ ደደቢት
ከተያዘለት ሰዓት 15 ደቂቃ ዘግይቶ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሳቢ ጨዋታ ሳይታይበት በደደቢት ኣሸናፊነት ተጠናቅዋል።
በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት ወልዋሎዎች ኣዲስ ፈራሚዎቹን ኣስራት መገርሳ፣ኣማኑኤል ጎበና፣ደስታ ደሙ፣ዳንኤል ኣድሓኖም፣ብርሃኑ ቦጋለ እና ኤፍሬም ኣሻሞን በቋሚ ተሰላፊነት ይዞ ገብቷል።በ4-2-3-1 አሰላለፍ ከሞላ ጎደል አዲስ ቡድን ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት ደደቢቶች ለሙከራና ኣዲስ የፈረሙ ተጨዋቾቹን ተጠቅምዋል።
- ማሰታውቂያ -
መሃል ሜዳ ላይ በሚቆራረጡ ኳሶች ታጅቦ የተካሄደው የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድን በኩል ብዙ ግልፅ የግብ ሙከራ ያልታየበት ነበር።የሁለቱም ቡድኖች ተከላካይ ክፍል ወደ መሃል ሜዳ ተጠግተው መጫወታቸው በሁለቱም ቡድን በኩል ሚቆራረጡ ቅብብሎች እንዲበዙና ግልፅ የግብ እድሎች እንዳይፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።በወልዋሎ በኩል ሚጠቀሱ ሙከራዎች በጨዋታው መጀመርያ አካባቢ ፕሪንስ ሰርቪንሆ በረዥሙ ከአስራት መገርሳ የተላከለትን ኳስ የግል ብቃቱን በመጠቀም ሁለት ተጨዋቾችን ቀንሶ ቢሞክረውም በጨዋታው ጥሩ የነበረው ረሺድ ሙታወሲ አድኖበታል፣በተመሳሳይ ኦዶንጎ ከግራ መስመር ኤፍሬም አሻሞ ያሻማለትን ኳስ ኦዶንጎ በሚገባ ተቆጣሮ ቢሞክረውም ረሺድ ሙታውሲ ኣድኖበታል።ሰማያዎቹ ደደቢቶች ከርቀት እና ከሚሻሙ ኳሶች በመነሳት የወልዋሎ ግብ ክልልን ሲፈትኑ ነበር በተለይ አለም ኣንተካሳ(ማሪዮ)፣ እና የቀኝ መስመር ተከላካዩ መድሃንየ ብርሃኔ የሞክርዋቸው ኳሶች ተጠቃሽ ናቸው።በቀኝ መስመር የተሰለፈው ዳንኤል ጌድዮን፣ኣቤል እንዳለ እና ኣለም ባንተካሳ በግላቸው ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል።
ሁለተኛው ኣጋማሽ እንደ መጀመርያው አጋማሽ በተመሳሳይ ለኣይን ሚስብ ጨዋታ ያልታየበት ነበር።ደደቢቶች በጥሩ ቅብብል የሜዳው አንድ ሦስተኛ ላይ በተደጋጋሚ ቢደርሱም አጨራረስ ላይ ድክመት ታይቶባቸዋል።ወልዋሎዎችም የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም አጥቂውንና አማካዩን ሚያገናኝ ተጫዋች ማጣታቸው ግልፅ የግብ እድሎችን እንዳይፈጥሩ ምክንያት ሆንዋል።ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደደቢቶች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት አለምአንተ ካሳ ወደ ግብነት ቀይሮት ሥስት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል ።
ድሬዳዋ ከተማ ከ መቐለ ከተማ
10፡25 ላይ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመቐለ ከተማ ኣሸናፊነት ተጠናቋል። በአዳዲስ አሰልጣኞች እየተመሩ የገቡት ሁለቱም ቡድኖች አዳዲስ ፈራሚዎቻቸውን ቋሚ 11 ላይ ተጠቅመዋል።በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት መቐለ ከተማ መሃል ሜዳ ላይ ኳስ ተቆጣረው መጫወት ሚችሉ ተጨዋቾችን በማሰለፍ የኳስ በላይነትን መውሰድ ችለዋል። ድሬዎችም በ4-2-3-1 ተለጥጠው በመጫወት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል።በሁለት ተከላካይ አማካዮች ገናናው ረጋሳ እና ፍሬድ ሙሽንዲ የተጫወተው ድሬዳዋ ጨዋታው ላይ ጥሩ የነበረውን የመቐለን መሃል ክፍል መቆጣጠር ከብድዋቸው ታይቷል።ጨዋታው ላይ ድሬዎች በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ራምኬል ሎክ፣ሃይሌ እሸቱና የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።መቐለዎች በአጭር የኳስ ቅብብል እና የመስመር ተከላካዮችን ባሳተፈ የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።በተለይም ጋናዊው ኦሰይ ማውሊ፣አማኑኤል ገ/ሚካኤል የሞከርዋቸው ኳሶች ተጠቃሽ ናቸው።
ሁለተኛው ኣጋማሽ እንደ መጀመርያው ኣጋማሽ በመቐለ ከተማ የኳስ በላይነት የቀጠለ ሲሆን ድሬዎችም ኣልፎ ኣልፎ ከቀኝ መስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ነበር። 55ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተነሳው ሳሙኤል ሳሊሶ ጨዋታው ላይ ኮከብ ሆኖ ከዋለው ሃይደር ሸረፋ ጋር አንድ ሁለት ተጫውቶ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን በሚገባበት ጊዜ በድሬ ተከላካዮች ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ቢያድግልኝ ኤልያስ አስቆጥሮ መቐለን መሪ ኣድርጓል።ከግቡ መቆጠር በኃላ ድሬዎች ተቀይሮ በገባው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አማረ በቀለ አማካኝነት የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ታይቷል።መቐለዎችም ተቀይረው ወደ ሜዳ በገቡት ዮናስ ገረመውና እንዳለ ከበደ የግብ እድሎችን ቢፈጥሩም ተጨማሪ ግብ ሳያክሉ በቢያድግልኝ ኤልያስ ብቸኛ ጎል አሸንፈው ወጥተዋል።