”በቅ/ጊዮርጊስ የአንድ ዓመት ቆይታዬ ከክለቡ ጋር ሶስት ዋንጫዎችን ማግኘት መቻሌ
ቢያስደስተኝም 4ኛዋን ዋንጫ በቡና ተሸንፈን ማጣታችን በጣም ቆጭቶኛል”
- ማሰታውቂያ -
ወንድምና እህትስ አለ፡- “የተወለድኩትና
ያደግኩት በጅማ አጋሮ ከተማ ውስጥ ነው፤
በቤታችንም ውስጥ 3 ወንድሞችና 4 እህቶች
አሉኝ”፡፡
–ስለ እግር ኳስ አጀማመሩና ከእሱ ውጪ
በቤተሰባቸው ውስጥ ስፖርተኛ ስለመኖሩ፡-
“የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት እንደ
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተጨዋቾች ልጅ
ሆኜ በተወለድኩበት የአጋሮ ከተማ ውስጥ
የጨርቅ ኳስን በማንከባለል ነው፤ ያን ወቅት
ላይ በተለይ በክፍል ሀገር ሜዳዎችን እንደልብ
ማግኘት ይቻል ነበርና በጣም ደስተኛ ሆኜ
ነው ኳሱን ተጫውቼ ያደግኩት፤ በቤተሰባችን
ውስጥ ከእኔ ውጪ ኳስ ተጨዋችም ሆነ
ስፖርተኛ ማንም የለም፤እኔ ብቻም ነኝ የቤቱ
ስፖርተኛ”፡፡
-የእግር ኳስን በልጅነት ዕድሜው
ሲጫወት ተምሣሌቱና /ሞዴሉ/ ማን
እንደነበር፡- “የእኔ ተምሣሌት የነበረው
ተጨዋች ለማ አበበ የተባለ የአጋሮ ልጅና
ተወላጅ ነው፤ በመልኩ ጥቁርና ብራዚላዊውን
ፔሌ እንዲሁም ኢትዮጵያዊውን ንጉሴ ገብሬን
በአጨዋወቱም፣ በቁመናውም፣ በመልኩም
ይመስል ነበርና ያኔ ለእኔ እንደ ብርቅዬ
ቆጥሬው ነው እሱን በማድነቅ ተምሳሌቴ
ላደርገው የቻልኩት”፡፡
-የእግር ኳስን ለመጫወት በመቻልህ
በቤተሰቦችህ አካባቢ ተፅዕኖ ተደርጎብህ ነበር?፡
– “ብዙም ተፅዕኖ አልነበረብኝም፤ በትምህርቴ
ላይ ግን በተለይ በሀይስኩል ደረጃ ስማር ከ1-
5ኛ ባለው ደረጃ ስለምወጣና ጎበዝ ተማሪም
ስለነበርኩ ከፍተኛ ትኩረት እንዳደርግ ነበር
በቤተሰቦቼ አካባቢ ይፈልግ የነበረው፡፡”
–ጎላ ብርሃኑ የእግር ኳስ ተጨዋች
ባይሆን ኖሮስ፡- “የእግር ኳስ ተጨዋች መሆን
የልጅነቴ ህልሜ ነበርና በእዚያው ቀጥዬ
ነው ኳስ ተጨዋች ለመሆን የቻልኩት፤
ምናልባት ግን ያኔ በኳሱ ባይሳካልኝ ኖሮ
ሌላ ልሆን የምችልበት ሙያ ነበረኝ፣ ከላይ
እንደገለፅኩትም በትምህርቴ ጥሩ ስለነበርኩ
በእዛው ተመርቄ ወይ አስተማሪ እሆን ነበር
ያለዚያ ደግሞ በአንድ የመንግሥት መስሪያ
ቤት /ድርጅት/ ውስጥ ተቀጥሬ በመስራት ስራ
አላጣም ነበር”፡፡
–ስለመጀመሪያ ክለቡና እንዴት ወደ
ቡድኑ እንደገባ፡- “የእግር ኳስን በጨዋታ
ዘመኔ ተጫውቼ ሳሳልፍ የመጀመሪያ
ክለቤ ጅማ ሕንፃ ኮንስትራክሽን ነው፤ ወደ
ቡድኑ የገባሁትም በጊዜው የአጋሮ ከተማ
ላይ የአውራጃዎች ውድድር ይደረግ ነበርና
አጋሮን ወክዬ ስጫወት ባሳየሁት ጥሩ የሆነ
የኳስ ብቃትና እንቅስቃሴዬ ነው፤ ያኔ የክለቡ
አሰልጣኝ የነበረው ሀብታሙም በውድድሩ
ላይ እኔን ጨምሮ ጥሩ ጥሩ የሆነውን ልጆች
ከየጨዋታዎቹ በመመልመል ወደ ቡድኑ
እንድንገባ ስላደረገን በጊዜው ጥሩ የሆነ
የደስታ ስሜት ሊሰማኝ ችሏል”፡፡
–በእግር ኳሱ ለመጀመሪያ ጊዜ
ስለተከፈለው ደመወዝና ብሩን ምን ላይ
እንዳዋለው፡- “የመጀመሪያው ደመወዜ
ለጅማው ሕንፃ ኮንስትራክሽን ክለብ ስጫወት
8 ብር ከአምስት ሳንቲም ነው የተከፈለኝ፤ ይሄ
ብርም በጊዜው ለነበሩት የድርጅቱ ግንበኞችና
አናፂዎች ይከፈል የነበረም ነውና ያቺን ብር
ለቡድኑ ስጫወት በካምፕ ውስጥ እየኖርኩ
ምግብ ከራሳችን እንድንችልም ይደረግ ስለነበር
አብቃቅቼያት ነው እጠቀምባት የነበረው”፡፡
–ለጅማ ሕንፃ ኮንስትራክሽን ስትጫወት
ያገኘኸው ስኬት አለ፡- “አዎን፤ ከቡድኑ ጋር
ቆይታ ሳደረግ ሻምፒዮና መሆን ችያለው፤
ያኔ ለቡድኑ ስጫወትም አሸናፊ የሆንበት
ሁኔታ በጣም ይገርመኛል፡፡ ምግብ ራሳችን
እየቻልንና በካምፕ ውስጥ የምንኖርበት ዘመን
ላይም ስለነበር በእዚህ ሁኔታ ላይ ተጫውተን
በአንድ በተዘጋጀ የ8 ክለቦች ውድድር ላይ
ማለትም ደቡብ እርሻ፣ ጅማ ከተማ፣ ጅማ
ውሃ ልማት፣ ጅማ ፖሊስና ጅማ ጤና ሳይንስ
የመሳሰሉ ክለቦች የተሳተፉበት ውድድር ላይ
እኛ ጨዋታዎቹን አሸንፈን ክለባችን ወርቅ
የሸለመንና የሽልማቱንም ትልቅነት በጊዜው
ሳስበው በጣም ነው ሊገርመኝ የቻለው”፡፡
-በአንድ ወቅት የእግር ኳስን ሲጫወት
ከዳኛ ጋር በመጣላቱና በቀይ ካርድ በመውጣቱ
ከኳስ ተጨዋችነት እድሜ ልክ ስለታገደበት
ሁኔታ፡- “አዎን፤ ያንን ጊዜ ፈፅሞ
አልረሳውም፤ አጋሮ ላይ በቀበሌና በአውራጃ
ደረጃ ስንጫወት ነው ዳኛው ጥፋትን ፈፅመሀል
ብሎ በቀይ ካስወጣኝ በኋላ ከውጪ ሆኜ
የቡድናችንን ግጥሚያ ስከታተልና በእኛ ቡድን
ላይም እኔ ከወጣው በኋላ ሁለት እና ሶስት
ተከታታይ ግቦች ሲቆጠርብን ጊዜ በንዴት
ወደ ሜዳ ገብቼና ከዳኛውም ጋር በመጣላቴ
ቅጣቱ የተጣለብኝ፤ በጊዜው ቡድኑ ውስጥ
በጣም ጥሩ ተጨዋች የነበርኩት እኔ ነኝ፤
የእኔ በቀይ መውጣት ቡድናችንን ምን ያህል
እንደጎዳውም አይቼ ነው በጊዜው ስሜታዊ
በመሆን ጭምር በቀይ ከወጣሁ በኋላ እኔን
ጨምሮ የሚወዱኝ ደጋፊዎችም ጭምር
ወደ ሜዳ ተከትለውኝ ገብተው ጨዋታው
ሊቋረጥ ችሎ በኋላ ላይ ቅጣቱ የተጣለብኝ፤
በጊዜው እኔ ለጅማ ሕንፃ ኮንስትራክሽን
ለመጫወት ተነጋግሬ የጨረስኩበት ጊዜም
ነበርና ጎላ ወደ ሌላ ቡድን ለማምራት ብሎ
የአካባቢውን ስፖርት ሊያዳክም ፈልጎ ነው
ጥፋቱን የፈፀመው በሚልም ነበር የእድሜ
ልክ ቅጣቱም የተጣለብኝና በኋላ ላይ ግን
ቅጣቱ ከ4 ወር ቆይታ በኋላ ተነስቶልኝ በኳስ
ተጨዋችነቴ ልቀጥል ቻልኩ”፡፡
-የኢትዮጵያ የክልሎች ሻምፒዮና ላይ
ተጫውቶ ስለማለፉና መጫወቱ ስላስገኘለት
ጥቅም፡- “የኢትዮጵያ የክልሎች ውድድር
ላይ ወደ አዲስ አበባ ከጅማ ምርጥ
በመምጣት ለከፋ ክፍለ ሀገር ምርጥ ቡድን
የተጫወትኩበት አጋጣሚው ያኔ ነበረኝ፤ በእዛ
ውድድር ላይ በመጫወቴም ተጠቅሜያለው፤
የወሎ ምርጥ፣ የአስመራ ምርጥና ሌሎችም
ክልሎች በተሳተፉበት ውድድር ላይ እኔም
ጥሩ ብቃቴን ስላሳየው ነበር በእዚያ ውድድር
ላይ ስጫወት የተመለከተኝ ወንድሜ ጊዮን
ኢሳያስ አዲስ አበባ ይኖር ነበርና በእዚሁ
ክለብ ሞክር ይሳካልሃልም ብሎኝ እሱ
የሚያውቃቸው ሰዎች ነበሩና ለአየር ኃይል
ቡድን ደብረዘይት ካምፕ ሄጄ የምሞክርበትን
እድል ስላመቻቸልኝና በሙከራውም ወቅት
የክለቡ ዋና አሰልጣኝ የነበሩት ማስተር
ቴክኒሽያን ሀጎስ ደስታም ነበሩና በ1 ምርጫ
ነው በፍጥነት ተመልክተውኝ ለክለቡ
እንድፈርምና እዛው አልጋ ተሰጥቶኝም ነው
መኖር የጀመርኩትና በእዚህ መልኩ ነው
ወደ አየር ኃይል የገባሁት፤ በጊዜው ወደ
አየር ኃይል እንድገባ ለክልሌ መጫወቴና
ጥሩ ብቃቴን በውድድሩ ላይ ማሳየቴም
የጥርጊያውን በር ሊከፍትልኝ ችሏል”፡፡
-የአየር ኃይል ክለብ ውስጥ ገብቶ ስላደረገው
የመጀመሪያ ጨዋታና ስለተፈጠረበት ስሜት፡
– “የመጀመሪያ ጨዋታዬ ከም/ጦር ጋር
የተደረገው ነው፤ ተቀይሬ የገባሁበትና
የአዲስ አበባ አጥቂሆኜም ነው፡፡ 3ለ1
ስናሸንፍ የተጨዋትኩት ጎልም ለመጀመያ
ጊዜ በእዚያን ጊዜ ስጫወት የህዝቡ ብዛት
የጨዋትው የፉክክር ስሜት አየሩና ሁሉም
ነገር በጣም እንድትደሰትኩትም ያደርግሃልና
በእዚያ ጨዋታ ውስጥ በማማለፌ ራሴን እንደ
እድለኛም ቆጥሬዋለሁ”፡፡
የአየር ኃይል ክለብ ውስጥ ስለነበረው
የዓመታት ቆይታና በተጨዋችነት ሲያሳልፍ
ሲቭል ወይንስ ሚኒቴሪ ሆኖ ስለመጫወቱ፡
– “የአየር ኃይል ክለብ ውስጥ የቆየሁት
ለ3 ዓመታት ያህል ነው፤ በሲቪል ደረጃም
ነው ለቡድኑ የተጫወትኩት፤ እዚያ በነበረኝ
ቆይታም መጀመሪያ ስፈርም አጥቂ ሆኜም
ነበር በቦታው ተጠባባቂ ሆኜ የተጫወትኩት፤
በእዚያ ስፍራ ስጫወትም ለአሰልጣኛችን
ማስተር ጋሽ ሐጎስ ደስታ እንደሚፈልገው
ልሆንለት ስላልቻልኩ ወደ ተከላካይ ቦታ
ወስዶ አጫወተኝ፤ በእዚያም ቦታ ላይም
ጥሩ ስሆንለት ወደደኝና ከእዚያን ጊዜ ጀምሮ
የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ሆኜ በመቀጠል
ከክለቡ ጋር ጥሩ ጊዜንና በምርጥ ብቃትም
ላይ ተገኝቼ ላሳልፍ ቻልኩ፤ የአየር ኃይል
ቡድን ውስጥ በቆየሁባቸው ጊዜያቶች ከኳሱ
ውጪ ብዙ ነገሮችን ማለትም ቡድኑ ምንም
እንኳን የሚኒቴሪ ክለብ ቢሆንም ስርዓትን፣
ጥሩ ጥሩ እውቀቶችን አለሸነፍ ባይነትንና
ጠንከር ያሉ ልምምዶችን መስራትም ምን
ያህል ለችሎታህ ጠቃሚ መሆኑን ልማርበትና
የራስ መተማመንም እንዲኖርኝ አድርጓል፤
ከዛ ውጪ ኑሮንም እንዴት ቀለል አድርጌ
መኖር እንዳለብኝም የተማርኩበት ጊዜም
ነበርና የአየር ኃይል ክለብ ውስጥ ተጫውቼ
ማለፌ ለእኔ ትልቅ ኩራትም እንዲሰማኝ
አድርጓል”፡፡
–የአየር ኃይል ክለብ ውስጥ በአጥቂው
ስፍራ ብዙም ለመጫወት ሳይችል መቅረቱና
በተከላካይ ስፍራው ግን የተዋጣለት ተጨዋች
ሆኖ ስለማሳለፉ፡- “የአየር ኃይል ቡድን ውስጥ
ስገባ በአጥቂው ስፍራ ብዙም ለመጫወት
ያልቻልኩት ገና ወጣት ተጨዋች ከመሆኔ
ባሻገር በቦታው በጊዜው ልምድ ያላቸው
በርካታ ተጨዋቾች ክለቡ ውስጥ ስላሉና
የአጥቂው መስመር ላይም የሚበልጡኝ
ተጨዋቾች ስለነበሩ ነው፤ በእዚያ ላይ
በቦታው እንዴት መጫወት እንዳልብህም ብዙ
ነገር ማወቅ አለብህ፤ የአጥቂው መስመር
ላይም ያኔ አሰልጣኜ ጋሽ ሐጎስ ደስታም
ስላልረኩብኝም ነበር ያኔ እሳቸው በተከላካይ
ስፍራው ብጫወት በኳሱ ትልቅ ደረጃ
እንደምደርስ ስላወቁ ነው በቦታው ከእነ መሰለ
አካለወልድ ጋር ያጫወቱኝ፤ መሰለም በጊዜው
ከእኔ አጠገብ ጋር ሆኖ ሲጫወትም በጣም
ስለወደደኝም በእዚህ ቦታ ላይ እስከመጨረሻው
የክለቡ ቆይታዬም ላይ ሆነ ወደ ቅዱስ
ጊዮርጊስም ስገባ በቦታው ልጫወት ቻልኩ”፡፡
-የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ምርጡ
አሰልጣኝ፡- “ብዙ አሰልጣኞችን በተጨዋችነት
ዘመኔ ላይ አይቻለው፤ አሰልጣኞቹን በማድነቅ
የማስቀድማቸውም በሁለት ነገሮች ነው፤
አገራችን ውስጥ መጀመሪያ ያደነቅኳቸው
አሰልጣኝ ማስተር ቴክኒሽያን ሐጎስ ደስታን
ነው፤ እሳቸው አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆኑ ጥሩ
አባትም ናቸው፡፡ በጊዜውም ከእሣቸው ጋር ብዙ
ነገርንም አሳልፌያለው፤ እሳቸው በሙያቸው
ቆይታ እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹን ልጆችም
ያሳደጉ ናቸው፡፡ ጋሽ ሐጎስ ለሙከራ የሚመጡ
ተጨዋቾችን ቢሳካላቸውም ባይሳካላቸውም
ወዲያው ጠርተውና ትሪት አድርገው ነው
የሚያቀርቡት፤ በሙከራ የማይሳካላቸውን
ተጨዋቾች ደግሞ እዚህ አልተሳካልክም
ማለት ሌላ ጋር አይሳካልክም ማለት አይደለም
በሚልም ለተጨዋቾች
ምን ምን ማሻሻል
እ ን ደ ሚ ኖ ር ባ ቸ ው ም
የሚነግሩም ናቸውና
በእዚህ እሣቸውን ነው
በጣም የማደንቀው፤
ከጋሽ ሐጎስ ውጪ
ሌላ የማደንቀው
አሰልጣኝ ለብሔራዊ
ቡድን ለመጀመሪያ
ጊዜ የመረጠኝን
ኢንስትራክተር ካሳሁን
ተካን ነው፤ እሱ ጎበዝና
የሚሰጠው ስልጠናም
ጥሩ ስለነበር ነው
የማደንቀው”፡፡
-የእግር ኳስ
ጨዋታ ዘመንህ
ምርጡ ተጨዋች፡
– “ለእኔ ምርጡና
በጣም የማደንቀው
ተጨዋች የቅ/ጊዮርጊስና
የኢትዮጵያ ብሔራዊ
ቡድን ተጨዋች
የነበረውን ሙሉጌታ ከበደን ነው፤ ያን ጊዜ
እሱ በነበረው ችሎታም እንደአስማተኛም
ነበር የማያውና ከፍተኛ አድናቆት ነው
ያለኝ፤ ከእሱ ውጪ ሌላ የማደንቃቸው
ተጨዋቾች ልዩ ታለንት የነበረውን ኤልያስ
ጁሀርንና ለረጅም ጊዜያት በግብ ጠባቂነት
የተጫወተውን ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስን ነው፡፡”
–ከአንተ አጠገብ ሆኖ ሲጫወት በጣም
የሚስማማሃና ምቾት የሚሰጥህ ተጨዋች፡
– “ከፀጋዬ ባቲ ጋር በወጣትም በብሔራዊ
ቡድንም ደረጃ የተከላካይ ስፍራው ላይ
አብሬው ስለተጫወትኩና ጥሩ ብቃትን
ስላየሁበትም እሱ ነበር ከአጠገቤ ሆኖ
ሲጫወት በጣም የሚስማማኝ”፡፡
–በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
ከአጠገብህ አብሮ ባለመጫወቱ የሚቆጭህ
ተጨዋች፡- “ከብዙዎቹና በጊዜው ታዋቂና
ስመጥር ከነበሩት የሀገራችን ተጨዋች ጋር
አብሬያቸው የተጫወትኩ ቢሆንም አብሬው
ባለመጫወቴ የሚቆጨኝ ተጨዋች አለ፤
እርሱም የእርሻ ሰብሉ አፈወርቅ ከበደ (ካቻ)
በዋናነት ሲሆን ከእሱ ሌላ ደግሞ ምርጥ
ታለንት እንዳለው የምመሰክርለት ዳንኤል
ክፍሌና በጊዜው እኛ ስንጫወት ባይደርስም
አሜሪካ ሀገር ላይ ሲጫወት የተመለከትኩት
ዳዊት መብራቱም እንደሜሲ አይነት ብቃት
ስላለው ከእሱም ጋር አለመጫወቴ ነው
የሚቆጨኝ፤ እነ ዳዊትን አሜሪካ ሀገር ላይ
ስመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጥ ክህሎት
እንዳለና ብዙ ተጨዋቾችም እይታ እንዳጡም
ልገነዘብም ችያለው”፡፡
–በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ላይ
የተቃራኒ ቡድን ተጨዋች ሆኖ በጣም
ያስቸገረክና የከበደህ ተጨዋች፡-‘‘የተከላካይ
ስፍራ ተጨዋች እንደመሆኔ ብዙ ጊዜ
ያስቸግረኝ የነበረው ተጨዋች ኤልያስ
ጅሃር ነው፤ እሱ ጥሩ ችሎታና ፍጥነትም
ስላለው ብዙ ጊዜ ለማቆም እቸገር ነበር፤
አሰልጣኛችን ሀጎስ እንደውም ኤልያስ ሲመጣ
በጣም ፍጥነት ስላለው ዘው ብለህ አትግባም
ይለኝ ነበርና፤ ኤልያስን በእዚሁ አጋጣሚ
አደንቀዋለው”፡፡
–በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
በጣም የተደሰትክበት ቀን፡- “ለመጀመሪያ ጊዜ
የተደሰትኩበት ቀን ለወጣት ብሔራዊ ቡድን
ተመርጬ ወደ ውጪ ሀገር የሄድኩበትን
ጊዜ ሲሆን ሌላው ደስታዬ ደግሞ ወደ ቅዱስ
ጊዮርጊስ ከገባውና ለአንድ ዓመትም ቆይታ
ካደረግኩ በኋላ ሶስት ያህል ዋንጫዎችን
ያነሳንባቸው ቀናቶች የተደስትኩባቸው
ናቸው”፡፡
–በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ በጣም
ያዘንክበትና ልብህ የተሰበረበት ቀን፡-‘‘ብዙም
የተደሰትኩባቸው እንጂ ያዘንኩባቸው ጊዜያቶች
ባይኖሩም አንዴ ግን ከማዘኔ በተጨማሪ
ልቤ የተሰበረበት ቀን አለ፤ ይህውም የአየር
ኃይል ቡድን ውስጥ ስጫወት ልዩ ፍቅሩና
ክብሩም ኖሮን በህዝቡም እየተረዳን ጭምር
ተጫውተን አልፈን ያን የመሰለ ቡድን የአሁን
ሰዓት ላይ አለመኖሩና ያኔ ክለቡም የአቅም
ውስንነት ሊፈጠርበት መቻሉ የሚያሳዝነኝ
ነው”፡፡
–በአየር ኃይል ክለብ ቆይታው
መቼም የማይረሳውና ከፍተኛ አግራሞትን
የፈጠረበት ትውስታው፡- ‘‘ለአየር ኃይል ክለብ
በምጫወትበት የእዚያን ሰዓት ላይ ያጋጠመኝ
ያ ትዝታ አሁንም ድረስ ከውስጤ ያልጠፋ
ነው፤ የአየር ኃይል ቡድን በጊዜው ለስፖርቱ
ይሰጥ የነበረውን ከፍተኛ ትኩረትም
ያመላከተን ነገርም ነበር በአመራሮቻችን ላይ
ልመለከትም የቻልኩት፤ የቡድኑ ቆይታዬ ላይ
ለእኔም ሆነ ለብዙዎቻችን ተጨዋቾች በጊዜው
ከፍተኛ አግራሞትን ከፈጠሩብን ጉዳዮች
መካከል ልጠቅሰው የምፈልገው ለዝግጅት
በክረምት ወራት ላይ ወደ ሐዋሳ ከተማ
ባመራንበትና በሐዋሳና በዲላ ከተማ መካከል
በሚገኝ የጫካ ስፍራ ውስጥ በአንድ መሰንቀላ
በሚባል የገበሬ አዳራሽ ውስጥ መብራት
ሳይኖር በጄኔሬተር በመጠቀም እየኖርን
ልምምዳችንን ስንሰራ የክለባችን የበላይ ጠባቂ
የነበሩትና የአየር ኃይል የኮንስትራክሽን ዋና
ኃላፊ የነበሩት ጄኔራል ሰለሞን በሳምንት
አንድ ቀን ለሁለት ወራት ያህል በኢሊኮፕተር
በመምጣት ልምምዳችንን እና የወዳጅነት
ጨዋታም ስናደርግ ይመለከቱንና ያበረታቱንም
ስለነበር ለቡድኑ ይሰጥ የነበረውን ግምት ዛሬ
ላይ ሆኜ ሳነሳው በጣም ነው ደስ የሚለኝ”፡፡
–ከአየር ኃይል ወደ ቅ/ጊዮርጊስ
ስላመራበት መንገድ፡- ‘‘የቅዱስ ጊዮርጊስ
ክለብን በጊዜው የተቀላቀልኩት የአዲስ
አበባ ብዙ ቡድኖችና እኛ ተጨዋቾችም አየር
ኃይልን ከመፍረስ ለማዳን ጥረትን እያደረግን
በነበረበት ሰዓት ያ ሊሳካልን ባለመቻሉ ነው፤
ያኔም እኔን የቅዱስ ጊዮርጊስና የኤሌክትሪክ
ክለቦችን ጨምሮ ሌሎችም በጥብቅ ይፈልጉኝ
ስለነበር ምርጫዬን ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ላደርግ
ችያለው፤ ቅ/ጊዮርጊስን የመረጥኩትም
በጊዜው ቡድኑ ውስጥ እንደእነ ሙሉጌታ
ከበደ፣ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስና በአየር ኃይል
ክለብ ውስጥ ስጫወትም ከአንድ ዓመት
በፊት አብሮኝ የነበረው ተስፋዬ ኦርጌቾም
ነበርና እነሱ ጓደኞቼ ስለሆኑና ክለቡ በጠየቀኝ
ጊዜም አብሬያቸው እንድጫወት ስለፈለጉና
ቡድኑም ትልቅ ክለብ ስለነበርም ነው ወደ
ቡድኑ የገባሁት”፡፡
-የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ስለነበረው
ቆይታና መቼም ቢሆን ስለማይረሳው
ትዝታ፡- ‘‘የቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ የነበረኝ
ቆይታ ምንም እንኳን ለአንድ ዓመት ያህል
የዘለቀ ቢሆንም በአብዛኛው ጥሩ ጊዜን ነው
ከቡድኑ ጋር ያሳለፍኩት፤ የቡድኑ ቆይታህ
ላይ ኳስን ስትጫወት ክለቡ ትልቅና በብዙ
ደጋፊዎችም ታጅቦ የሚጫወት ስለሆነ
ኳስን በጥንቃቄ የምትጫወትበት ሁኔታ ነው
ያለው፤ ያኔ ጥሩ ስትጫወት ሙገሳ እንዳለህ
ሁሉ ስህተት ስትሰራም ነገሮች ይጎሉብሃል፤
ደጋፊውም ስታጠፋ ይቆጣሀልና እኔ በብዙ
ነገሮች ተጠንቅቄና ስራዬንም ጠንክሬ
በመስራቴም ነው ከክለቡ ጋር በፍጥነት
ለመላመድና ብዙ ሳልቸገርም ለመጫወት
የቻልኩት፤ ያኔ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ
ሶስት ዋንጫዎችን ከቡድኑ ጋር ለማግኘት
በመቻሌ ለእኔ አስደሳች ጊዜን ሊፈጥርልኝ
ቢችልም ሌላ የማይረሳኝና የምቆጭበት
ትዝታም አለኝ፤ ይኸውም ቅ/ጊዮርጊስ
የእዚያው ዓመት ላይ አራተኛ ዋንጫውን
የሚያነሳበት እድሉ እያለው ከቡና ጋር
የነበረን ጨዋታ ላይ ግጥሚያው ሊጠናቀቅ
አንድ ደቂቃ እየቀረው እኔ የተከላካይ
ስፍራው ላይ ሆኜ ስጫወት ከቡናው አጥቂ
ሚሊዮን በጋሻው ጋር ብቻ ለብቻ አንድ
ለአንድ ከተገናኘን በኋላ ኳሷን በግምባሩ
ገጭቶ ከወሰደ በኋላ እሱ ባስቆጠረው ግብ
ተሸንፈን ዋንጫ ያጣንበትንና ደጋፊዎቻችንም
በሽንፈቱ በጣም የተቆጩበትንና በመበሳጨት
ስሜት ላይ እያሉም እነሱን ስመለከታቸው
በጣም በመደናገጤ እኔን የክለቡ የቡድን
መሪ አሰፋ ክፍሌና አሰልጣኛችን አስራት
ኃይሌ በመኪና ይዘውኝ የሄዱበትን ወቅት
አልረሳውምና የቡድኑ ትውስታዎቼ እነዚህን
እነዚህን ነው የሚመስሉት”፡፡
-ለብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ መች
ተመረጥክ?፤ ስትመረጥስ ምን ተሰማህ?፡-
‘‘ጊዜውን አሁን ላይ ባላስታውስም ለመጀመሪያ
ጊዜ የተመረጥኩት ለወጣት ብሔራዊ ቡድን
በአሰልጣኝ ስዩም አባተ አማካኝነት ነበር፤
ከቶጎ ጋር ለነበረን የደርሶ መልስ ጨዋታም
ነው ልመረጥ የቻልኩትና ያኔም እድሉን ሳገኝ
በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ለሀገርህ ቡድን በተለይ
ደግሞ የክፍለ ሀገር ልጅ ሆነህ ስትመረጥ
መመረጥህን እንደማስትሬት እንዳገኘ ሰው
ስለምትመለከተውና ስለምትቆጥረው ደስታዬ
ያኔ ልዩ ነበር፤ በተለይ ከተመረጥክ በኋላ
የሀገርህን ህዝብ መዝሙር አንተም
ሆንክ የስፖርት አፍቃሪው እየዘመረ
የምትጫወትበትም ሁኔታም ስላለ ልዩ
ኩራትም ነው የሚሰማህ፤ ከወጣት ብሔራዊ
ቡድን በኋላም በቀጣይነት በፍጥነት
የተመረጥኩት በኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ
አማካኝነት ለብሔራዊ ቡድን ነበር፤ እሳቸው
ልምምድ ላይ ካዩኝ በኋላም ነው በታንዛኒያ
አስተናጋጅነት ተደርጎ ለነበረው የሴካፋ
ውድድር ሊመርጡኝ የቻሉትና በሁለቱ
አሰልጣኞች መመረጥ መቻሌም ልዩ የሆነ
ስሜት እንዲሰማኝም ነው ያደረገኝ”፡፡
-የእግር ኳስ ተጨዋች ሆነህ በማለፍህ
ምን ይሰማሃል? ጥቅምስ አስገኝቶልሃል…
የገንዘብ? የመኪና? ወይንም ? የሌላ ነገር?፡
-‘‘የእግር ኳስ ተጨዋች ሆኜ ማለፌ በጣም
ነው ያስደሰተኝ፤ ተጫውቼ ማለፌምደስታንና አድናቆትን ነው፤ ከሀብትና
ገንዘብ በላይም ትልቁም ነገር ይሄን ክብር
ማግኘትም ነው የሚበልጠው፤ ኳስ መጫወቴ
ሌላው ያስገኘልኝ አሁን ለምገኝበት ህይወቴ
መንገዱን የከፈተልኝ መሆኑና ቤተሰብም
እንድመሰርትም ስላደረገኝ ያ ሊያስደስተኝ
ችሏል”፡፡
-ከሀገር ከወጣህና ወደ አሜሪካ ከተጓዝክ
ምን ያህል ዓመት ሆነህ? ከእዚህ በፊትስ
ተመልሰህ መጥተህ ታውቃለህ፡- ‘ከኢትዮጵያ
የወጣሁት ከ23 ዓመት በፊት ነው፤ ያ ሆኖ
ሳለ ግን ከእዚህ በፊት በመሀል በተደጋጋሚ
ወደ ሀገር ቤት በመምጣት የምወዳቸውንና
የሚናፍቁኝን ቤተሰቦች እንደዚሁም ጓደኞቼን
የጠየቅኳቸው ጊዜያቶች አለ”፡፡
–ከኢትዮጵያ በመውጣት ያኔ ወደ
አሜሪካ የተጓዝከው እንዴትና በምን መልኩ
ነበር?፡- ‘‘በእዚያን ወቅት ከሀገር የወጣሁት
በአሜሪካ ከሚገኘው የአላባማ ዩንቨርስቲ
የስኮላር ሺፕ እድልን በማግኘቴ ነው፤
ይህንንም የስኮላር ሺፕ እድልንም በወቅቱ
ጥሩ እንጫወት ለነበርነው ለእኔ፣ ለመድኑ
አብዲ ሰይድ፣ ለኤሌክትሪኩ አስራትና ለባንኩ
ግብ ጠባቂ ቻላቸው ያመቻቹልንም አሰልጣኝ
ሳላ የሚባሉ ሀገር ወዳድ ሰው ነበሩ፤
ያኔ የእሳቸው ምክትል አሰልጣኝ የነበረው
ደግሞ አሰልጣኝ ዩሃነስ ሳህሌ ነበርና በኋላ
ላይ አራታችንም ተመርጠን ሄድን፤ እዚያም
ኳሱን እየተጫወትን በመቆየት ኑሮአችንን
በእዚያው አደረግን”፡፡
–ወደ አሜረካ ከሶስቱ ተጨዋቾች
አንተ ዘግይተህ ነበር የተጓዝከው፤ ለምን
ነበር? እዚሁ ለመቅረት ፈልገህም ነበር
ይባላል፡-‘‘ከአሜሪካ የስኮላር ሺፕ እድሉን
ሳገኝ የእውነትም ስለሀገሪቷ ምንም ነገር
ስለማላውቅ፣ እዛ የማውቀው ሰው ስለሌለኝና
እዚህ ሀገሬ ላይ ደግሞ የእግር ኳሱን ገና
ጠግቤ ያልተጫወትኩም ስለሆንኩ እዚሁ
ለመቅረት ወስኜ ስለነበር በጊዜው ከእነሱ
ጋር ወደ ስፍራው አልተጓዝኩም ነበር፤
ያኔ ታዲያ እኔ በክለብ ደረጃ የምጫወተው
ለቅዱስ ጊዮርጊስ ነበርና የሚወዱኝ ደጋፊዎቹ
የእኔን አለመሄዴን ሲያዩ በመቆጣት ጭምር
ለእኔ አስበው ያገኘከውን እድል ተጠቀምበት
ሲሉኝ ጊዜ መለስ ብዬ በማሰቤና በተለይ
ደግሞ ብዙ ነገሮችን ወደ አሜሪካ አስቀድሞ
ሄዶ የነበረው አብዲ ሰይድ የትምህርት
መረጃዎቼንና ዶክመንቶቼን በማሰባሰብ
ስላመቻቸልኝ በኋላ ላይ ከሶስት ሳምንታት
ቆይታ በኋላ ወደ ስፍራው አመራውኝ፤ ያኔ
እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው አብዲ ሰይድ ብዙ
ነገሮችን ባያመቻችልኝ ኖሮ ወደ አሜረካ
አልሄድም ነበርና ያ ወቅት ትዝ ይለኛል”፡፡
–ወደ አላባማ ዩንቨርስቲ ከገባህ በኋላ የነበረ
ቆይታህ ምን ይመስላል፡- ‘‘በአሜሪካ የኮሌጅ
ላይፉ ላይ ብዙ ስላልቆየው ብዙ የምለው ነገር
የለኝም፤ በኋላ ላይ ዩንቨርስቲውን ቶሎ
ጥዬ በመውጣትም ነው ብዙ ኢትዮጵያውያን
ኳስ ተጨዋቾች ወደሚገኙበት የአትላንታ
ከተማም ያመራሁትና እዛም ነው ኑሮዬን
ያደረግኩት”፡፡
–በአሜሪካ ቆይታህ እግር ኳስን በክለብ
ደረጃ የመጫወት ዕድል አግኝተሃል?፡-
‘‘አዎን፤ ወደ አትላንታ ከተጓዝኩና ኑሮዬንም
እዛ ካደረግኩ በኋላ የ2ኛ ሊግ ላይ ለሚሳተፍ
ራከርስ ለሚባል አንድ የፕሮፌሽናል ክለብ
ውስጥ ገብቼ ኳስን ለመጫወት ችያለው”፡፡
–የራከርስ ክለብ ውስጥ ያኔ ገብተህ
ልትጫወት የቻልከው እንዴትና በምን መልኩ
ነው?፡- ‘‘በአሜሪካ የአትላንታ ከተማ ውስጥ
ለሚገኘው የራከርስ ቡድን በጊዜው ገብቼ
ለመጫወት የቻልኩት ክለቡ የሰጠውን
የሙከራ እድል ለማለፍ በመቻሌ ነው፤ ያኔ
ይሄ ቡድን ምርጫ እንደሚያደርግም አላውቅም
ነበርና ከአላባማ ዩንቨርስቲ የመጡ ተጨዋቾች
ናቸው ክለቡ ምርጫ እንደሚያደርግ ነግረውኝና
የምርጫ ቦታውንም እነሱ ስለማያውቁት እኔ
እንዳሳያቸው ጠይቀውኝ እኔስ ለምን ለክለቡ
አልሞክርም በሚል ወደ ቦታው ይዣቸው
ልሄድ የቻልኩት፤ እዛም እንደደረስን ከየት
ነው ሲሉኝ አመጣጤንና የኢትዮጵያ
ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች መሆኔንም
ነገርኳቸው፤ ሌሎቹ ሲጠየቁም የተጫወቱም
ያልተጫወቱም ሁሉም የብሔራዊ ተጨዋቾች
እንደሆኑ ይናገሩ ነበርና አሰልጣኙ ላይ
የመገረም ምልክትን አየሁኝ በኋላ ላይ እኔን
በተመለከተ እዛ የሚገኝ አሰልጣኝ እኔን
በሚገባ ያውቀኝ ስለነበር ከአሰልጣኙ ጋር
በደንብ አስተዋውቆኝ የተሰጠኝን የሙከራ
እድል በማለፌ ነው ወደ ክለቡ የገባሁት፤
ያኔ ወደ ክለቡ ከገባነው 8 ተጨዋቾች ውስጥ
በታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተጫወቱ
የብራዚልና የናይጄሪያ ተጨዋቾችም ካሉበት
ቦታ በቀጥታ ወደ ቡድኑ ተመርጠው የገቡበት
ሁኔታም ነበርና የእዚያን ጊዜ የቡድኑ አገባቤ
ይሄን ነበር የሚመስለው”፡፡
–በአሜረካው ክለብ ቆይታ ላይ ጥሩ
ጊዜን አሳለፍክ?፤ ምንስ ትዝ ይልሃል…፡
– ‘‘ አዎን፤ የራከርስ ክለብ ውስጥ የነበረኝ
የሁለት ዓመታት ቆይታ ጥሩ የሚባል ነበር፤
በተከላካይ ቦታው ላይ በቋሚነትና በጥሩ
ሁኔታም ተጫውቼ በማሳለፍ በእንቅስቃሴ
ደረጃ የኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ብቃት
የቱን ያህል እንደሆነ በችሎታዬ ላሳያቸውና
በእኛ ተጨዋቾችም እንደነብራዚልና የሌሎች
ሀገር ተጨዋቾችም እንዲገረሙብን፣ ኳስን
እንዲያውቁትና ከማንም እንደማናንስም
ለማመላከት ችያለውና ያን በጊዜው ማሳየቴ
ያስደስተኛል”፡፡
–የእግር ኳስ ጫማውን ስለሰቀለበት
ምክንያት፡- ‘‘የእግር ኳስን ለአንዴና ለመጨረሻ
ጊዜ በአሜሪካ ከተጫወትኩ በኋላ ጫማዬን
የሰቀልኩት የግራ እግር ጉልበቴን በመጎዳቴ
ነው፤ ያኔ ባልጎዳ ኖሮ ወደ አሜሪካ ዋናው
ሊግ ገብቼ የምጫወትበትም እድሉ ነበረኝና
ጉዳት ከኳሱ ጋር አለያይቶኛል”
-የእግር ኳስን ተጫውቶ ካበቃ በኋላ
ስለተሰማራበት ሙያ፡- ‘‘የአሜሪካን ሀገር
ላይ የእግር ኳስን ተጫውቼ ካበቃው በኋላ
የተሰማራሁበት ሙያ በትራንስፖርቴሽን
ቢዝነስ ላይ ባተኮረ ስራ ነው፤ እሱን ነው
የአሁን ሰዓት ላይ በመስራት ቤተሰቦቼን
የማስተዳድረውና ኑሮዬንም እየመራው
ያለሁት”፡፡
–ከባህር ማዶ ክለቦች የሚደግፈው፡
– ‘‘የውጪ ኳስ ብዙ ጊዜ ባላይም ሪያል
ማድሪዶች ግን ደስ ይሉኛል”፡፡
–ከባህር ማዶ ተጨዋቾች የሚያደንቀው፡
– “የሁልጊዜም የእኔ ምርጡ ተጨዋች ዲያጎ
አርማንዶ ማራዶና ነው”፡፡
–በአሰለጣጠን ብቃቱ ከውጪዎቹ
የሚያደንቀው አሰልጣኝ፡- ‘‘አርሰን ቬንገር፤
ስለእሳቸው የምሰማቸው ነገሮች ሁሌም
ያስደስተኛል”፡፡
–ከውጪ ሀገር ብሔራዊ ቡድኖች
የሚደግፈው፡- ‘‘የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድንን
ነው የምደግፈው”፡፡
-ጎላ ራሱን በ3 በተመረጡ ቃላቶች
ሲገልፅ፡- ‘‘ረጋ ያለ፣ ለሰው የሚያስብና
ተግባቢም ነው”፡፡
–ከኢትዮጵያ የቀድሞ ተጨዋቾች ውስጥ
የጎላ ድሪም ቲም ፡- ‘‘የ3-5-2 ፎርሜሽንን ነው
የምጠቀመው፤ ግብ ጠባቂ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ
ተከላካዮች እኔ፣ ፀጋዬ ባቲ፣ ዳኛቸው ደምሴ፣
አማካዬች ተስፋዬ ኦርጌቾ፣ ክፍሉ መብራቱ፣
አብርሃም ብስራት፣ ዳንኤል ክፍሌና ኤልያስ
ጁሃር፣ አጥቂዎች ሙሉጌታ ከበደና ጌቱ ከበደ
ሲሆኑ የእነሱ ተጠባባቂ ቅጣው ሙሉ፣
ዮሴፍ /ቡላ/፣ ዘሪሁን ሸንገታ፣ ገነነ መክብብ፣
አብዲ ሰይድ አፈወርቅ ከበደ /ካቻና/ ሙሉጌታ
ወ/የስ ናቸው”፡፡
–ስለትዳር አመሰራርቱ፣ ህይወቱና
ስለልጆቹ፡- “ከባለቤቴ ቤዛ አለባቸው ጋር የትዳር
ሕይወትን የመሰረትኩት ኑሮዬን ባደረግኩበት
የአሜሪካ ሀገር ነው፡፡ እዚያም ገብቼ ከ5
አመት በኋላም ነው በጌት ቱጌዘር መልኩ
የኢትዮጵያውያንን በሚመስል አይነት ጋብቻ
ልንጋባ የቻልነውና ያ የሚያስደስተኝ ሆኖ
አልፏል፤ ጋብቻዬን ከፈፀምኩ በኋላ ኑሮዬን
በጥሩ ሁኔታ እየመራሁ ነው የምገኘው፤
በውጪ ሀገር ስትኖር በተለይ ህይወትን
በከባድ ሁኔታም ነው የምትመራውና በእዚያ
በኩል ባለቤቴ ትልቁን እገዛ እያደረገችልኝ
ነው የምትገኘው፤ ከባለቤቴ ጋር በመሰረትነው
ትዳር ሁለት ልጆችን አፍርተናል፤ እነሱም
የ12 ዓመቱን አሁን የያዘው ያፌት ጎላና
የ8 ዓመት ዕድሜ ያለው ሄኖክ ጎላ ይባላል፤
ከቤተሰቦቼ ጋር አሁን ስኖር በጣም ደስተኛ
ነኝ፤ በተለይ ባለቤቴ ከአጠገቤ ስላለች ብዙ
ነገሮችን ለእኔ አቅልሎልኛልምና በእዚህ
አጋጣሚ ላመሰግናት እፈልጋለው”፡፡
–ባለቤቱን ሲገልፃት፡- “በጣም ትሁትና
ጥሩ የትዳር ሰው ናት፤ ከሰዎች ጋር
ትግባባለች፤ በአሜሪካ ሀገር ያለን የቀድሞ
ተጨዋቾች አንድአንዴ በምንፈላለግበት
ሰዓት እኔ ቤት የምንሰባሰብበት ጊዜ ስላለ
ያኔ እንግዶቼን እንደእኔ ሁሉ የምትቀበልበት
መንገድም በጣም ደስ ስለሚል በጥሩነቷ ነው
እሷን እኔ የምገልፃት”፡፡
–በመጨረሻ…..‘‘የእግር ኳስ ተጨዋችነት
ዘመኔ ላይ ለእኔ ጥሩ ደረጃ መድረስ ብዙ
ሰዎች ከጎኔ በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ
አድርገውልኛል፤ መጀመሪያ ፈጣሪዬ ሲቀጥል
ቤተሰቦቼ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በጅማ ያሰለጠነኝ
ሀብታሙ በአየር ኃይል ያሰለጠነኝ ሀጎስ ደስታ
ወንድሜ ጊዮን የአጋሮ ነዋሪና ጓደኞቼንና
ሲያደንቁኝ የነበሩትን መላውን የስፖርት
ቤተሰቦች ማመስገን እፈልጋለውኝ”፡፡