በ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን ኢትዮጵያ ቡና ወልድያን አሸንፈዋል፡፡
Pic-source ፈረሰኞቹ ገጽ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ላይ በተካሄደው ጨዋታ 5 ለ 3 በሆነ ውጤት ነው ያሸነፈው።
- ማሰታውቂያ -
ፈረሰኞቹ የመጀመሪያውን ግማሽ ጨዋታ በመሀሪ መና፣ አዳነ ግርማ እና ሳልሃዲን ሰዒድ ግቦች 3 ለ 0 እየመሩ ለዕረፍት ወጥተው ነበር፡፡
ከዕረፍት መልስ ሳልሃዲን እና ፕሪንስ ሰቨርኒኾ ባስቆጠሯው ተጨማሪ ሁለት ግቦች እስከ 82ኛው ደቂቃ ጊዮርጊስ 5 ለ 0 ሲመራ ነበር፡፡
ለድሬዳዋ ከተማ በ85ኛ ደቂቃ በበረከት ይስሐቅ እንዲሁም 87 እና 92ኛው ደቂቃ ላይ ይሁን እንደሻው ሶስት ግቦችን ቢያስቆጥሩም ከመሸነፍ አልዳነም፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ወልድያ ከተማን በአዲስ አበበ ስታዲያም አስተናግዶ 2 ለ 1 ረቷል፡፡
ቡና በጋቶች ፓኖም እና በሳሙኤል ሳኑሚ ሁለት ግቦች መደበኛውን ጨዋታ 2 ለ 0 ሲመራ ቆይቷል፡፡
የመሃል አልቢትሩ በጨመሩት ደቂቃም ወልድያ ከተማ ሙሉጌታ ረጋሳ በ93ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ባሳረፋት ግብ ከባዶ ከመሸነፍ ድኗል፡፡
ТУРИСТИЧЕСКИЙ ОНЛАЙН-СПРАВОЧНИК
ትናንት በ9 ሰዓት ላይ በተደረጉ ጨዋታዎችም አዲስ አበባ ላይ መከላከያ እና ንግድ ባንክን ያገናኘ የመጀመርያ ጨዋታ በመከላከያ 3 ለ1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን የጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም ክለቦች የነበረው እንቅስቃሴ አጥጋቢ ባይሆነው መከላከያዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ያገኟትን ፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ ወደ ግብ ቀይሯት 1 ለ 0 መርተው ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ 61ኛው ደቂቃ ጥላሁን ወልዴ ከመአዝን የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ቀይሮ ክለቡ አቻ ማድረግ ቢችልም ቴድሮስ በ67ኛ ደቂቃ ባስቆጠራት ግሩም ቅጣት ምት እና 76ኛ ደቂቃ ላይ ምንይሉ በጨዋታ ባስቆጠራት ጎል 3 ለ1 መረታት ችሏል፡፡
ፋሲል ከነማ በሜዳው አዲስ አበባ ከተማን ያስተናደገ ሲሆን፥ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
pic source -fasil kenema fb page
በጨዋታው ላይም ሀይሌ እሸቱ በ61ኛው ደቂቃ ለአዲስ አበባ ከተማ የማሸነፊያ ጎሉን ከመረብ አሳርፏል።
ወላይታ ድቻ በሜዳው ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደ ሲሆን፥ ጨዋታውም በባለሜዳው ወላይታ ድቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የወላይታ ድቻው አብዱልሰመድ አሊ በ45ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻን የማሸነፊያ ጎል በማስቆጠር ክለቡ በሜዳው ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።
ሲዳማ ቡና ከጅማ አባቡና ጋር ያደረጉት ጨዋታም በሲዳማ ቡና 1ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ሲዳማ ቡና በሜዳው ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችሏል።
በጨዋታው ላይ ፀጋዬ ባልቻ ለሲዳማ ቡና መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ለመጠናቀቅ ሶስት ደቂቃ ሲቀሩ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል።
9 ሰዓት ላይ የተደረገ ሌላ ጨዋታ አዳማ ላይ አዳማ ከተማን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቷል።
ጨዋታውም በአዳማ ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ አዲስ ህንፃ በ72ኛው ደቂቃ እንዲሁም ቡልቻ ሹራ በ52ኛው ደቂቃ የአዳማን የማሸነፊያ ጎሎች ከመረብ አሳርፈዋል።
ደደቢት ከአርባ ምንጭ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሌላ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ 10:30 ደደቢት አርባምንጭን አስተናግዷል፡፡
በዚህ ጨዋታ ለተከታታይ ሁለት ሳምንት ሽንፈት ያስተናገደው አርባምንጭ ከነማ በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ጨዋታ እና ሙከራ ማድረግ ችሏል፡፡ በተለይ እንዳለ ከበደ እና አስጨናቂ ፀጋዬ ከበረኛ ጋር ተገናኝተው ያመከኗቸው ኳሶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ኤፍሬም አሻሞ አስቀምጠው ሽመክት ጉግሳ ይዘው የገቡ ደደቢቶች መጠነኛ ለወጥ ሲያመጡ 49ኛ ደቂቃ ላይ ሰለሞን ሐብቴ ወጥቶ ዳዊት ፍቃዱ ከገባ በኀላ ተጭነው መጫወት ችለዋል፡፡
በተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ ደደቢቶች 65ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል ያገኟትን ቅጣት ምት ብርሀኑ ቦጋለ ወደ ግብ ሲቀይራት ብዙም ሳይቆዩ 67ኛ ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከመሀል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ በሚገባ ተጠቅሞ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል በዚህም ወቅት የአርባ ምንጭን መለያ ያጠለቁ ደጋፊዎች ድንጋይ ወደሜዳ በመወርወራቸው ጨዋታው ተቋርጦ ነበር፡፡
የአጥቂ መስመር ችግራቸው በደምብ የተገነዘቡ አርባምንጮች 75ኛው ደቂቃ ላይ ቀይረው ያስገቡት ወንድምነው 78ኛ ደቂቃ ላይ ተስፋ ሰጪ ጎል በማስቆጨር ቡድኑን አነቃቅቷል፡፡
ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ አርባምንጮች መደበኛ የጨዋታ ጊዜ አልቆ በመጨረሻ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ያገኟት ቅጣት ምት ተመስገን ካስትሮ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ጎል በመቀየር ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አድርጓቸዋል፡፡
በሽርፍራፊ ሰከንድ ሀለት ነጥባቸው የተነጠቁት ደደቢቶች በውጤቱ የተከፉ ሲሆን ጌታነህ ከበደ ወደመልበሻ ክፍል ሲያመራ መለያውን በፍጥነት ለማውለቀ ሞክሮ ስላልተሳካለት እላዩ ላይ እንዳለ ቀዳዶ ከመጣሉ ውጪ ቤንች ላይ ያሉ ያሉ አመራሮች ላይ ሀይለ ቃላትን በብስጭት ሲናገር የተመለከቱ ታዳሚዎች ከጨዋታው የበለጠ በድርጊቱ አዝነው ሲወያዩበት ነበር፡፡
ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ43 ነጥብ ሲመራ ሲዳማ ቡና በ42 ደደቢት በ41 ነጥቦች ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ይከተላሉ፡፡
ጅማ አባቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ግርጌ ይገኛሉ፡፡
የደረጃ ሰንጠረዥ
# | ክለብ | ተጫ | ልዩ | ነጥብ |
---|---|---|---|---|
1 | ቅዱስ ጊዮርጊስ | 23 | 21 | 43 |
2 | ሲዳማ ቡና | 24 | 7 | 42 |
3 | ደደቢት | 24 | 14 | 41 |
4 | ኢትዮጵያ ቡና | 24 | 10 | 39 |
5 | አዳማ ከተማ | 24 | 6 | 39 |
6 | ፋሲል ከተማ | 23 | 1 | 35 |
7 | ሀዋሳ ከተማ | 24 | 2 | 31 |
8 | ወልዲያ ከተማ |
24 | -1 | 30 |
9 | አርባምንጭ ከተማ |
24 | -2 | 30 |
10 | መከላከያ | 24 | -10 | 30 |
11 | ድሬዳዋ ከተማ |
24 | -6 | 28 |
12 | ኢትዮ ኤሌክትሪክ |
24 | -1 | 27 |
13 | ወላይታ ድቻ | 24 | -10 | 26 |
14 | ጅማ አባቡና |
24 | -5 | 24 |
15 | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ |
24 | -15 | 20 |
16 | አዲስ አበባ ከተማ | 24 | -12 | 19 |