የ2018ቱ የቶታል ካፍ ኮንፌደሬሺን ካፕ የሁለተኛ ዙር ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ትናንት ሲጀምር ዛሬ ቀጥለው በሚካሄዱ 8 ጨዋታዎች ወደ ቀጣዩ ዙር አላፊ ክለቦች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ መድረክ በካፍ ኮንፌደሬሺን ካፕ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያው ወላይታ ድቻ ከሜዳ ውጭ ከዛማሌክ ጋር የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ምሺት 1:00 በካይሮ አልሰላም ስታዲዬም ያደርጋል፡፡በዚህ ታሪካዊው ጨዋታ በግብፅ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያን በስታዲየም በመገኘት የጦና ንቦቹን እንደሚያበረታቷቸው ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያው ወላይታ ዲቻ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሳተፉበት የካፍ ኮንፌዴሬሺን ካፕ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የዛንዚባሩን ዚማሞቶ በድምር ውጤት 2ለ1 በመርታት ከዛማሌክ ጋር ያገናኘውን ውጤት ሲያስመዘግብ፡ዛማሌክ ባለፈው አመት ከተሳተፈበት የአፍሪካ ሻምፒዬንስ ሊግ በመውረድ ምንም ጨዋታ ሳያደርግ በኮንፌዴሬሽን ካኙ ከዲቻ ጋር ተገናኝቷል፡፡
የሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያው ጨዋታ በወላይታ ድቻ ሜዳ በሀዋሳ አለምአቀፍ ስታዲዬም የተደረገ ሲሆን በጨዋታው በርካታ ታላላቅ አለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከጨዋታው መጠናቀቅ በሇላ ያልተጠበቀው የኢትዮጵያው ወላይታ ድቻ በሜዳው ሃያሉን ዛማሌክ አሸነፈው በማለት ሲዘግቡ የግብፅ ጋዜጦች ጭምር ሽፋን ሰተው የዛማሌክን መሸነፍ ፅፈዋል፡፡በጨዋታው ወላይታ ዲቻ በሜዳው በዛብህ መለዬና ያሬድ ዳዊት ባስቆጠሯቸው ጎሎች የ5ጊዜ የአፍሪካ ቻምፒዬንስ ሊግ ሻምፒዬኑን የግብፁን ዛማሌክ ከተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጋር 2ለ1 ማሸነፋቸው አለምን አነጋግሯል፡፡
የወላይታ ድቻና ዛማሌክ ጨዋታ ዛሬም ቢሆን የበርካታ አለም አቅፍ ሚዲያዎችን ትኩረት ስቧል፡፡ዲቻ በሜዳው ዛማሌክን ማሸነፍ ቢችልም የዛሬውን የመልስ ጨዋታ ዛማሌክን በሜዳው እንዴት ሊቋቋመው ይችላል ካይሮ ላይ ውጤቱን ያስጠብቃል ወይ የሚለው ገና ምላሺ የሚያስፈልገው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ በሌላ በኩል ዛማሌክስ ቢሆን በሜዳው ውጤቱን ቀልብሶ ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፋል ወይ የሚለው በሁለት ጎራዎች እያከራከረ ነው፡፡
የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ “ዘነበ ፍስሀ” ጨዋታውን አስመልክቶ ከሀትሪክ ስፖርት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዛሬ ከሜዳችን ውጭ ብንጫዎትም አጥቅተን በመጫዎት ዛማሌክን ጫና ውስጥ በመክተት ቀድመን ግብ ለማስቆጠር እንጫዎታለን ሲሉ አክለውም ወደ ሜዳ የሚገቡት ለመከላከል እንዳልሆና ውጤቱን አስጠብቀው እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡የባለሜዳዎቹ ዛማሌኮች አሰልጣኝ “ኢላል ጋላል” GhanamanSport ከተባለ ድረገፅ ጋር ባደረጉት ቆይታ በእርግጠኛነት እመኑኝ በሜዳችን ውጤቱን ቀልብሰን ወደ ቀጣዩ ዙር እናልፋለን ለዚህም ተጨዋቾቸ ይህን ለማድረግ ዝግጁ ናቸው በማለት ተናግረዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
የወላይታ ድቻ 42 የልዑካን ቡድን አባላት ሀሙስ ምሽቱን ወደ ስፍራው ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን ማረፊያቸውን በኖፋ ሆቴል በማድረግ የሁለት ቀን ቀለል ያለ ልምምድ ጨዋታው በሚካሄድበት ሜዳና ሰዓት የሰሩ ሲሆን ተጨዋቾቹ እስካሁን በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡
የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ክለባቸውን ለመደገፍ ከሶዶ ሀዋሳ እና ከአዲስ አበባ ወደ ካይሮ የተጓዙ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በስታዲየም በመገኘት ድምቀት ከመሆናቸውም ባሻገር ለንቦቹ ሌላ ሞራል ይሆኗቸዋል፡፡
ጨዋታው ዛሬ ምሺት 1:00 በካይሮ አልሰላም ስታዲዬም የሚደረግ ሲሆን ጨዋታውን የኬንያውያን ዳኞች እሚመሩት ይሆናል።