አሴ ከተለየን 40 ቀን ሞላው
የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የመድን እና የድሬው ተጨዋች አሰግድ ተስፋዬ የ40ኛ የመታሰቢያ ቀን በገርጂ ሳህሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን ዛሬ ተከናወነ።
አመለሸጋው አሰግድ ተስፋዬ ዳግም ወደ ዚህች ዓለም ላይመለስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማሸለቡ ግን መራራ ዕውነት ሆናል።
የጨዋታ ዘመኑን የትውልድ አገሩ ክለብ በሆነው ድሬዳዋ ኮካኮላ ክለብ በመጫወት የእግር ኳሱን ዓለም በይፋ የተቀላቀለው አስግድ ተስፋዬ አስደንጋጩ ዜና ዕረፍት የተሰማው ከዛሬ 40ቀን በፊት ሲሆን ሁሌም ዘወትር ቅዳሜ እንደሚያደርገው የጤና ቡድን የእግር ኳስ ጨዋታ (ልምምድ) ካደረገ በኋላ መታጠቢያ ቤት ውስጥ እያለ በድንገት የመውደቅ አደጋ አጋጥሞት በዚህ ምክንያት ህይወቱ እንዳለፈ ነው የታወቀው።
- ማሰታውቂያ -
አሰግድ በድንገት መታጠቢያ ቤት ውስጥ መውደቅን ተከትሎ የገጠመውን አደጋ ለመታደግና ህይወቱን ለማትረፍ ወደ ሀያት ሆስፒታል ቢወሰድም በዚህች ምድር እንዲኖር የተቆረጠለት ቀን በመጠናቀቁ ህይወቱን መታደግ ሳይቻል የሀገር ባለውለተኛ ው አሰግድ ተስፋዬ ትዝታውንና መልካም ስራዎቹን ብቻ ትቶልን በድንገት አሸልቧል።
በትናንትናው ዕለት በጨካኙና በክፉው ሞት በድንገት የተነጠቀው አሰግድ ተሰፋዬ በጨዋታ ዘመኑ የሶስት ኃያላን ክለቦች ማልያን ለብሶ የተጫወተ ሲሆን ለቅ.ጊዮርጊስ አምስት ዓመት፣ለመድን አምስት ዓመት እንዲሁም ለቡና ገበያ ለስድስት ዓመታት በአጠቃላይ ለ16 ዓመታት እግር ኳስን በትላልቅ ክለቦች ደረጃ በመጫወት ድንቅ የሚባልና የማይዘነጋን የእግር ኳስ ጊዜን አሳልፏል።
ጂረስ፣የደሃው አገር ሮማሪዮ በሚሉ ዋና ቅፅል ስሞች የሚጠራው አሰግድ ተስፋዬ በእግር ኳሱ ሲታወስ የሚኖርባቸው በርካታ አንፀባራቂ አጋጣሚዎች እንዳሉ የሚካድ ባይሆንም በተለይ በቀድሞ አጠራር ቡና ገበያ እያለ በአንድ ጨዋታ 5 ጎሎችን የሲሸልሱ ሴንት ሚሼልስ ላይ በኢንተርናሽናል ጨዋታ ላይ ያስቆጠራቸው ግቦች የማይዘነጉ ናቸው።
በ1990ዎቹ በተለይ በቡና ገበያ በሚያደርጋቸው ድንቅ እንቅስቃሴዎቹና በግብ አይምሬነቱ በብዙዎች ልብ ውስጥ መፈቀርንና የማይነቃነቅ ሀውልት ለመትከል የበቃው አሰግድ ተስፋዬ የጨዋታ ዘመኑ ከተጠናቀቀ በኃላም ከእግር ኳሱ ላለመራቅና በሙያው ለሀገሩ መልካም ነገር ሠርቶ ለማለፍ በማሰብ “አሰጌ ስፖርት አካዳሚ”ን በመክፈት የነገ የሀገር ተረካቢ ታዳጊዎችን እስከ ህልፈተ ህይወቱ ድረስ በማሰልጠን በእግር ኳሱ የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
አሰግድ ባለ ትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነበር።
የሀትሪክ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልና የሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ የሀገር ባለውለተኛ ተጫዋች በነበረው በአመለሸጋው አሰግድ ተስፋዬ ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በጋራ እየገለፅን አምላክ ዘላለማዊ ዕረፍትን ለእግር ኳሱ ቤተሰቦች፣ለማች ቤተሰቦች፣ለወዳጆቹና ለጋደኞቹ አምላክ መፅናናትን እንዲሰጥልን ከልብ እንመኛለን።