(ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ የጥቅምት 2 እትም)
“አርቢትሩ ሁሉንም ነው የነካው የሚፈረድበት
መሆኑ አይቀርም”
አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው የኮሚቴው ሰብሳቢ
“በተናገርኩት የምቀጣው ህግና መንግስት
ከሌለ ብቻ ነው”
- ማሰታውቂያ -
አርቢትር ሃ/የሱስ ባዘዘው
“ዳኛን ካሁን በኋላ አንድም ቃል እንዳትተነፍስ
ማለት አይቻልም”
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የኮሚቴው አባል
“ታዛዥ ባለመሆኔ ነው እርምጃ የተወሰደብኝ
የሚለው ለመታዘዝም እንኳ መቻል ይጠይቃል”
ይድነቃቸው ዘውገ /ቦቸራ/ የዳኞች ኮሚቴ አባል
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሄራዊ
የዳኞች ኮሚቴ ኢንተርናሽናል አርቢትር
ኃይለየሱስ ባዘዘው ላይ የ50 ሺህ ብር ቅጣትና
የ2 ዓመት የእገዳ ውሳኔ ሊያስተላልፍ ነው
መባሉ የዳኝነቱን አለም ትኩሳት እንዳባባሰው
ታወቀ፡፡
ባለፈው ሳምንት ለንባብ በበቃው ጋዜጣችን
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዳኞች ኮሚቴ
ከፍተኛ በደል እንደደረሰበት፣ ተደጋጋሚ
የምደባ ቅነሳ እንደተፈፀመበትና ዳኝነቱ አካባቢ
አሉባልታ እንዳለ መናገሩ የዳኞች ኮሚቴን ቁጣ
መቀስቀሱ ታውቋል፡፡ ካሜሩንና አልጄሪያን
በኮሚሽነርነት ለመምራት ባለፈው ሃሙስ
ወደ ያውንዴ ከማቅናታቸው በፊት የኮሚቴው
ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው አርቢትር
ኃይለየሱስ ባዘዘው በሰጠው ቃለ-ምልልስ ዙርያ
በተለይ ለሀትሪክ እንደገለፁት “ኮሚቴዎቹ
በእርሱ ላይ ርምጃ ወስደህ ካላሳየኸን ስራውን
ማቆም አለብን እያሉ ነው፤ ሁሉንም ነው
የነካነው የሚፈረድበት መሆኑ አይቀርም” ሲሉ
ገልፀዋል፡፡
ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ ኮሚቴው በጉዳዩ
ዙሪያ ከተወያየ በኋላ በዲሲፕሊን መመሪያው
አንቀፅ 68 ተራ ቁጥር 4 በመገናኛ ብዙሃን
የፌደሬሽኑን ስም ያጎደፈ ወይም
የፌደሬሽኑን አመራር በግልም
ሆነ በጋራ የተሳደበ ወይም
የዘለፈ ወይም ያዋረደ ወይም
ስለ አሰራራቸውም ሆነ ስለ
አመራረጣቸውም በሃሰት ላይ
የተመሰረተና አግባብ ያልሆነ
መግለጫና ትችት የሰጠና
የስፖርት ቤተሰቡን ተገቢ
ያልሆነ አቅጣጫ እንዲይዝ
ለማድረግ የሞከረ ከብር 40 ሺህ
እስከ 200 ሺህ ብር ይቀጣል፡
፡ በተጨማሪም ከ2 ወር ያላነሰ
ከ2 ዓመት ያልበለጠ እገዳ
ይጣልበታል የሚለውን ህግ
ጠቅሰው የ2 ዓመት እገዳና የ50 ሺህ ብር
ቅጣት በማስተላለፍ ሰብሳቢው ከካሜሩን
እስኪመጡ እየተጠበቁ መሆኑ ታውቋል፡፡
ውሳኔውን ማረጋገጥ ባንችልም አቶ ልዑልሰገድ
በጋሻው ከትላንት በስቲያ (እሁድ) ምሽት አ/አ
መግባታቸው ታውቋል፡፡
ስለ ፌደሬሽኑ የዲሲፕሊን ህግ የሚያውቁ
የህግ ባለሙያዎች በበኩላቸው ሜዳ ላይ
ያሉ የቴክኒክ ችግሮችን ከጨዋታው በፊትና
በኃላ በዳኝነቱ ዙርያ የተሰጠ ቃለ-ምልልስ
ካልሆነ በስተቀር በተጠቀሰው አንቀፅ ጉዳዩን
ማየት የሚገባው የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሆኖ ሳለ
የአርቢትር ኮሚቴ ውሳኔ በህገ ወጥና በማን
አለብኝነት የተወሰደ በመሆኑ የፌደሬሽኑ
አመራሮች ለፍትህ መቆማቸውን በማሳየት
የኮሚቴውን ድርጊት እንዲያስቆሙ እየጠየቁ
ነው፡፡ እስከአሁን ስለመቀጣቱ የሚገልፅ
ደብዳቤ ያልደረሰውና ስለቅጣቱ በወሬ
የሰማው ኢንተርናሽናል አርቢትር ኃይለየሱስ
ባዘዘው በበኩሉ “ከምመራው ጨዋታ
ውጪ የተሰማኝን የመናገር መብት አለኝ፤ በተናገርኩት የምቀመጠው ህግና መንግስት
ከሌለ ብቻ ነው” ሲል ተናግሯል፡፡ “ይግባኝ
የማለት መብት አለኝ ፤የማይመለከተው ኮሜቴ
ሊወስንብኝ አይገባም” ያለው አርቢትሩ “ሃሳብን
የመግለፅና የመናገር መብቴ ህገ መንግስታዊ
ነው”ካለ በኃላ የስራ አስፈፃሚውንና ኮሚቴውን
በችግሬ ዙርያ ለማናገር መጥቼ ለማየትም
ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የአሰራር ክፍተቱን
ተችቻለሁ፤ወደ ስቴዲየም እንዳይመጣ፣ የስራ
አስፈፃሚ ኮሚቴውን እንዳላናግር መባሌ
መስመሩን እንደጣሰ በመረዳት ችግሬን
ለህብረተሰቡ ለመግለፅ ተገድጃለሁ” ሲል
ተናግሯል፡፡
አርቢትሮች ቋንቋ አይችሉም ማለትህ
ቅሬታ አስነስቷል በሚል የተጠየቀው አርቢትር
ኃይለየሱስ ባዘዘው “እኔ የምናገረው ይጋነናል፤
ሁሌ የሚገርመኝ ይህ ነው፤ መፅሃፍ ሲታተምኮ
ሁሉንም አንባቢ አያረካም፤ ጋሽ ስብሃት ገ/
እግዚአብሄር መፅሃፍ ሲፅፍኮ በሁሉም አንባቢ
ሊወደድም ሊጠላ ይችላል መፅሃፉም ሁሉንም
እንዲያረካ አይጠበቅም፤ ቃለ-ምልልስ ስሰጥም
በዚህ መልኩ መታየት አለበት፤ ለሙያችን
እንቁም፤ ለገንዘብ ሳይሆን ለሙያ እንኑር፤
ያኔ ገንዘብ ይመጣል ማለቴ እውነት ነው።
በቋንቋ ጉዳይ ሁለቱ እንጂ ሌሎች ዳኞች ቅር
መሰኘታቸው ተገቢ አይደለም፤ በወቅቱ ስሜቴ
ስለተነካ የተናገርኩትን ተናግሬያለሁ፤ ይሄ ነው
እውነቱ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ የአርቢትር
ኮሚቴው ውሳኔውን አስተላለፈ ቢባልም ጉዳዩን
የማያውቅ የኮሚቴ አባል ተገኝቷል፡፡ ስሙን
መጥቀስ ያልፈለገው የዳኞች ኮሚቴ አባል
ለሀትሪክ እንደገለፀው “አንድ ዳኛ ባጫወተው
ጨዋታ ዙሪያ መናገር አይችልም፤ ከዚህ ውጪ
ያለው ሁኔታ የሚመራው ግን በህገ መንግስቱ
ነው፤ በግሌ ግን ስለተቀጣው ቅጣት የማውቀው
ነገር የለም፤ የዳኛ ኮሚቴ የሚቀጣው አርቢትሩ
ተጠይቆ መልስ ሰጥቶ እንጂ ድንገት ተነስቶ
አይደለም፤ የተባለው ውሳኔም ተቀባይነት
የለውም” ሲል ተናሯል፡፡ “የተቋሙን አሰራር
መቃወም ይቻላል፤ ትችቱ እውነት ከሆነ
ወደ ቅጣት ምን ያስኬዳል ፤በዚህች አገር ላይ
የመናገር ነፃነት የተከበረ ነው፤ ይህን በመናገሩ
ቀጥቼዋለሁ የሚል አካል ካለ ትክክለኛው
ውሳኔ አይመስለኝም” ያለ ሲሆን “የዳኞች
ኮሚቴ ሰብሳቢውን ለምን ኃይለየሱስን ቅጣው
አለበለዚያ ከስራው ራሳችንን እናገልላለን” በሚል
በማስከተል ለቀረበው ጥያቄ ስሙን መጥቀስ
ያልፈለገው የዳኞች ኮሚቴ አባል “ፈፅሞ
እንዲህ የተናገረ የለም፤ ተናግረዋል ከተባለ
መረጃው ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከዚህ የተለየ ምንም
መናገር አልፈልግም፤ ማስመር የምፈልገው
ተቋምና ግለሰብን መሳደብና አሰራርን መተቸት
ግን ይለያያል፤ ዳኛን ካሁን በኋላ አንድም ቃል
እንዳትተነፍስ ማለት ግን አይቻልም፤ ከወር
በኋላ ምን እንደሚፈጠርም አይታወቅም” ሲል
አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የዳኞች ኮሚቴ አባል የሆነው ይድነቃቸው
ዘውገ /ቦቸራ/ በበኩሉ የኢንተርናሽናል አርቢትር
ኃይለየሱስ ባዘዘውን አስተያየት ተችቷል፡፡
“አርቢትሩ የሰጠው አስተያየት ተገቢ አይደለም፤
ታዛዥ ባለመሆኔ ነው ርምጃ የተወሰደብኝ የሚለው ለመታዘዝም እኮ መቻልን ይጠይቃል፤
የሚችል ሰው እኮ ነው የሚታዘዘው፤ የሚከበር
የሚታመን ሲኮን እኮ ነው ኃላፊነት የሚሰጠው፡
፡ እንኳን የአሁን ዳኛ እኛም አላደረግነውም፤
የአሁኑ ዳኛ የሚሰራውን የማያውቅ በ90 ደቂቃ
ውስጥ አራት አይነት ጥፋት አይቶ አራት
አይነት ውጤት የሚሰጥ ፈፅሞ አልታዘዝም”
ሲል ተናግሯል፡፡ ቦቸራ ለሀትሪክ እንደገለፀው
“በግሌ ዘመናዊ ለመሆን ሞክር ብዬዋለው፤
ከሰው ጋር ለመቀራረብና አራዳ ለመሆን
ሞክር ብዬም መክሬዋለሁ፤ከዳኞቻችን ጋር
አይግባባምኮ” ሲል ኃይለየሱስ ባዘዘው ላይ
ያለውን ቅሬታ አስረድቷል፡፡
ከሀትሪክ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ
በኃይለየሱስ ባዘዘው ላይ ከተከፉት አርቢትሮች
መካከል ኢንተርሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ
ምትኩ አንዱ ነው፡፡አርቢትር ቴዎድሮስ
ለሀትሪክ እንደገለፀው “ኃይለየሱስ በዳኝነት
ዙሪያ አሉባልታ በዝቷል ማለቱ አበሳጭቶኛል፤
ይህን መናገር አልነበረበትም፤ ራሱንና
ቤተሰቡንም ነው አሳልፎ የሰጠው፡፡ አሉባልታ
አለ ላለው እራሱም አሉባልተኛ ነበር ማለት
ነው፤ ዳኞች ስንገናኝ በፍቅር ነው፤ አሉባልታ
አለ ላለው አይዋጥልኝም፤ በቃ ተሳስቷል” ሲል
አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
አርቢትር ኃይለየሱስ ባዘዘው የሰጠውን
ቃለ-ምልልስ በአንዳንድ ዳኞች ከፍተኛ ውግዘት
ቢቀርብበትም በተቃራኒው በርካቶች ግን
ኃይለየሱስ ባዘዘው ለሀትሪክ የሰጠው ቃለ-
ምልልስ ድፍረት የተሞላበት፤ የአርቢትሮችን
የልብ ትርታ የገለፀ፣በኮሚቴው ብልሹ አሰራር
ላይ የተቃጣ ጀግንነት ነው በማለት እያሞገሱት
ይገኛል፡፡