ኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ሲቀጥሉ ነገ(ቅዳሜ) 2 ጨዋታዎች ሲከናወኑ እሁድ ደግሞ 6 ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል።
ቅዳሜ 09:00 ሰዓት ሲል አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በውጤት ቀውስ ውስጥ ያሉት ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባጅፋር የሚገናኙ ይሆናል። ካደረጋቸው 4 ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቶ በሁለቱ የተሸነፈው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 4ነጥቦችን ብቻ ሰብስቦ በሊጉ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ በአንፃሩ 5 ጨዋታዎችን አድርጎ በተመሳሳይ 4 ነጥቦችን የሰበሰበው ጅማ አባጅፋር በግብ ክፍያ በመብለጥ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
11፡30 ሲል እዚሁ አ/አ ላይ የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው መከላከያ በዘንድሮው የውድድር አመት ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነውን ሐዋሳ ከተማን ይገጥማል። በመከላከያ በኩል ምንም አይነት አዲስ ጉዳትም ሆነ ቅጣት የሌለ ሲሆን በሐዋሳ በኩል ዳንኤል ደርቤ አና ላውረንስ ላርቴ በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ ይሆናል።
- ማሰታውቂያ -
እሁድ ውድድሩ ሲቀጥል ከሚደረጉት 6 ጨዋታዎች 4ቱ በተመሳሳይ 9፡00 የሚደረጉ ሲሆን 2ቱ ደግሞ በተመሳሳይ 10:00 ላይ የሚደረጉ ይሆናል።
እሁድ 10:00 ሲሆን አዲስ አበባ ላይ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ የሸገር ደርቢ በኢትዮጵያ ቡና እና ቅ/ጊዮርጊስ መካከል የሚካሄድ ይሆናል። የብዙ ደጋፊዎች ባለቤት የሆኑት እና ጠንካራ ተፎካካሪዎች የሆኑት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁሉም እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ እጅግ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ ነው። ካደረጋቸው 4 ጨዋታዎች 2 አሸንፎ 1 አቻ ተለያይቶ 1 ጨዋታ የተሸነፈው እና 7ነጥቦችን መሰብሰብ የቻለው ኢትዮጵያ ቡና 1 ቀሪ ጨዋታ እየቀረው 4ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ 3 ጨዋታዎችን አከናውኖ 2 በማሸነፍ እንዲሁም 1 አቻ በመውጣት 7ነጥቦችን ሰብስቦ ከኢትዮጵያ ቡና በ1 የግብ ክፍያ መብለጥ የቻለው ቅ/ጊዮርጊስ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
9፡00 ሲል ከሚጀመሩት ጨዋታዎች መካከል ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ወልድያ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠቀሳል። እንደ ሐዋሳ ከተማ ሁሉ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው ሲዳማ ቡና ማግኘት ከሚገባው 12 ነጥብ 3ቱን ብቻ አሳክቶ 15ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ወልድያ ከተማ በአንፃሩ 5 ነጥቦችን ሰብስቦ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የሲዳማ ቡናዎቹ ፈቱዲን ጀማል እና መሳይ አያኖ በቅጣት ምክንያት በእሁዱ ጨዋታ ለክለባቸው ግልጋሎት የማይሰጡ ይሆናል።
በተመሳሳይ 9ሰዓት ሲል አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ(አዞዎቹ) ሊጉን በ9 ነጥብ እየመራ የሚገኘውን ወልዋሎ አ.ዩ. የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል። በአርባምንጭ በኩል ከመከላከያ ጋር ሲጫወቱ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠማቸው ላኪ ሳኒ እና አሌክስ አሙዙ ከጉዳታቸው በማገገማቸው ለእሁዱ ጨዋታ ይደርሳሉ ተብሏል፡፡ ለብዙ ወራት ከሜዳ ርቀው የነበሩት አምበሉ አማኑኤል ጎበና ና ተሾመ(ክሮች) ለብቻቸው ቀለል ያለ ልምምድ ማድረግ ችለዋል፡፡
ወንደሰን ሚሊኪያስ ግን በጉዳት ምክንያት በእሁዱ ጨዋታ የማይኖር ይሆናል። ከወልዋሎ አዲግራት በኩል ብሩክ አየለ እና እዮብ ወልደማርያም በጉዳት የቀሩ ሲሆኑ አፍወርቅ ሃይሉ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወቱ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም ወደ አርባምንጭ ከቡድኑ ጋር ተጉዟል። ሆኖም ግን እስካሁን ልምምድ እየሰራ ባለመሆኑ የመሰለፉ ጉዳይ 50/50 ነው።
በሌላ የ 9ሰዓት ጨዋታ ጎንደር ላይ 6ነጥቦችን መሰብሰብ የቻለው ፋሲል ከተማ እንደ አጀማመሩ መዝለቅ ያልቻለው እና በ5 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻን የሚያስተናግድ ይሆናል። በወላይታ ድቻ በኩል ተክሉ ታፈሰ እና አብዱልሰመድ አሊ በጉዳት ምክንያት በጨዋታው ላይ የማይሳተፉ ሲሆን ይህ ቅድመ ዳሰሳ እስከ ተጠናቀረበት ሰአት ድረስ ከፋሲል ከተማ በኩል ምንም የተሰማ የጉዳት ዜና የለም።
መቐለ ላይ መቐለ ከተማ ደደቢትን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በጉጉት ከሚጠበቁ ጨዋታዎች መካከል ተጠቃሽ ነው። በሊጉ ደደቢት 5 ጨዋታዎችን አድርጎ 7 ነጥቦችን በመሰብሰብ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መቐለ ከተማ ደግሞ 4 ጨዋታዎችን አድርጎ ከደደቢት በ1 ነጥብ ዝቅ ብሎ በ6 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በደደቢት በኩል ብርሃኑ ቦጋለ (ፋዲጋ) ክለቡ ከፋሲል ከተማ ጋር ሲጫወት ተጎድቶ የነበረ ሲሆን እሁድ የመግባቱም ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። በመቐለ በኩል አዲስ ጉዳት የሌለ ሲሆን ከጉዳት የተመለሱት ቢስማርክ አቦሜንግ እና ሀብታሙ ተከስተ ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ ለረጅም ግዜ ጉዳት ላይ የቆየው ዮሴፍ ሃይሉ (ጆሲ) አሁንም ከጉዳቱ አለማገገሙን የቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ጎይቶኦም ሃይለ (ጎጄ) አስታውቋል። ከደደቢት አቤል ያለው እና ተክለማርያም ሻንቆ ከመቐለ ደግሞ አማኑኤል ገብረሚካኤል ለሴካፋ መመረጣቸውን ተከትሎ ለየክለቦቻቸው ግልጋሎት የማይሰጡ ይሆናል።
በሌላ ጨዋታ 10:00 ሲል ድሬ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል። ድሬዳዋ ከተማ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 6ነጥቦችን ይዞ ከመቐለ ከተማ እኩል 7ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ አዳማ ከተማ ደግሞ በ2 ነጥቦች ከፍ ብሎ 8ነጥቦችን በመያዝ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በአዳማ ከተማ በኩል ታፈሰ ተስፋዬ እና ደሳለኝ ደባሽ በጉዳት የማይገቡ ሲሆን ጀማል ጣሰው ከድሬዳዋ ከተማ በኩል በህመም ምክንያት የማይኖር ይሆናል።
ሊጉን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ9 ነጥብ እና 3የግብ ክፍያ ሲመራ መከላከያ በ2 ነጥቦች እና በ4 የግብ እዳ የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል።