በወርሀ ጥር (ከጥር 4 – ጥር 27) በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቻን(በሀገር በቀል ተጫዋቾች ብቻ የሚጫወቱበት) ውድድር ከሚሳተፉት 16 ሀገሮች አላፊ የሆኑት 15 ሀገሮች የታወቁ ሲሆን ቀሪውን 1 ሀገር ለመወሰን ኢትዮጵያና ሩዋንዳ የሚጫወቱ ይሆናል። ይህንን የቻን ውድድር ለማዘጋጀት ኬንያ ጥያቄ አቅርባ እድሉን በማግኘት ውድድሩን ለማዘጋጀት ሽርጉድ ስትል መክረሟ ይታወሳል።
ሆኖም ግን ካፍ ባደረገው ተደጋጋሚ ጥናት እና ክትትል ሀገሪቷ ውድድሩን ለማዘጋጀት ብቁ አደለችም በማለት የማዘጋጀት መብቷን ነጥቆ ለሞሮኮ ሰጥቷል። ሆኖም ሞሮኮ ቀድማ ለቻን ውድድር ማለፏን ያረጋገጠች በመሆኑ የቀረው 1 ቦታ ለማን ይሰጥ የሚለው ሀሳብ ብዙ ሲያከራክር ቆይቶ በሞሮኮ ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ የሆነችውን ግብፅ ውድድሩ ላይ እንድትሳተፍ ጥሪ ያስተላለፈላት ቢሆንም የግብፅ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ለቻን ውድድር ብዬ የሀገር ውስጥ የሊግ ውድድሬን አላቋርጥም በማለት ውድድሩ ላይ እንደማይሳተፍ አስታውቋል። ከዚህም የተነሳ የአፍሪካ እግርኳስ ፌደሬሽን እድሉን ለምስራቅ አፍሪካ ሰጥቷል። በዚህም ምክንያት በሱዳን ተሸንፋ የወደቀችው ኢትዮጵያ እና በዪጋንዳ ተሸንፋ የወደቀችው ሩዋንዳ በደርሶ መልስ ተጫውተው በድምር ውጤት አሸናፊ የሚሆነው ሀገር ወደ ሞሮኮ የሚጓዝ ይሆናል። የሁለቱ ሀገሮች የመጀመሪያ ጨዋታ ጥቅምት 26 አ/አ ላይ ሲካሄድ የመልሱ ጨዋታ ህዳር 3 ኪጋሊ ላይ የሚደረግ ይሆናል። ይህ ዜና ከተሰማበት ሰዓት ጀምሮ የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ ዝግጅት መጀመሩን ያገኘነው ምንጭ ያስረዳል።
ሱዳን እና ዩጋንዳ ከምስራቅ አፍሪካ
ቡርኪናፋሶ ፣ ኮትዲቯር ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ ፣ ሴኔጋል ፣ ናይጄሪያ እና ካሜሩን ከምዕራብ አፍሪካ
ሞሪታኒያ ፣ ሊቢያ እና አዘጋጇ ሞሮኮ ከሰሜን አፍሪካ
ናሚቢያ አንጎላ እና ዛምቢያ ከደቡብ አፍሪካ
ኮንጎ ከመካከለኛው አፍሪካ ለ2018 ቻን ውድድር ቀድመው ያለፉ ሀገራት ናቸው።