በቻይናዋ የወደብ ከተማ ሲያመን በተካሄደው 15 ኛው ሲያመን ኢንተርናሽናል ማራቶን ኢትዮጵያውያኑ ለሚ ብርሀኑ በወንዶች መሰረት መንግስቱ በሴቶች አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በየዓመቱ በአዲስ ዓመት መባቻ በሚካሄደውና ከዚህ ዓመት ጀምሮ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር የወርቅ ደረጃ በተሰጠው ሲያመን ኢንተርናሽናል ማራቶን የዘንድሮ ውድድር ኢትዮጵያውያን እንስት አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ተከታትለው መግባትም ችለዋል፡፡
ከውድድሩ በፊት የአሸናፊነቱን ከፍተኛ የቅድሚያ ግምት አግኝቶ የነበረው ያለፈው ዓመት የቦስተን ማራቶን አሸናፊ ለሚ ብርሀኑ እንደተጠበቀው ሆኖ የተገኘበት የወንዶቹ ፉክክር እንደተጀመረ አስራ አምስት የሚሆኑ አትሌቶች አንድ ላይ በመሮጥ የመጀመሪያዎቹን አስር ኪሎ ሜትሮች በ 30 ደቂቃ ከ 15 ሰከንድ የሸፈኑ ሲሆን ከዛ በኋላ ለሚ ብርሀኑ ወደፊት ብቻውን ተነጥሎ በመውጣት መሮጥን መርጧል፡፡ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ሞስነት ገረመው እና ሹራ ቂጣታ በተወሰነ ርቀት ሲከተሉት የነበረ ቢሆንም ውድድሩ ሲጠናቀቅ ከለሚ ጋር የነበራቸው ልዩነት ሰፊ ነበር፡፡
በዱባይ ማራቶን ላይ ያስመዘገበው 2፡ 04፡33 የሆነ የራሱ ፈጣን ሰዓት ያለው ለሚ 2 ፡06፡19 የሆነውን እና ኬንያዊው ሞሰስ ሞሶፕ በ 2015 ሲያሸንፍ የያዘውን የሲያመን ማራቶን የውድድር ስፍራ እንዲሁም በምድረ ቻይና የተመዘገበ ሪኮርድ የመስበር ዕቅድ ነበረው፡፡ በውድድሩ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ሪኮርዱን ማሻሻል በሚችልበት ፍጥነት ሲሮጥ የነበረ ቢሆንም 25ኛውን ኪሎ ሜትር ካለፈ በኋላ ፍጥነቱ እየቀነሰ በመምጣቱ ያሰበውን ሊያሳካው ሳይችል ቀርቷል፡፡
ውድድሩን በአሸናፊነት ሲጨርስ ያስመዘገበው ሰዓትም 2፡ 08፡27 ሆኗል፡፡ በግማሽ ማራቶን ተወዳዳሪነቱ የሚታወቀው ሞስነት ገረመው እና ባለፈው ዓመት በዚህ ውድድር ላይ ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለው ሹራ ቂጣታ ሲያደርጉት የነበረው ፉክክር 2፡10፡20 በሆነ ሰዓት ቀድሞ በገባው ሞስነት የበላይነት ሲጠናቀቅ ሹራ በ2 ፡10፡ 36 ሶስተኛ ወጥቷል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በ2015 ዓ. ም . የፓሪስ ማራቶን አሸናፊ የሆነችበት 2፡23 ፡25 የራሷ ምርጥ ሰዓት ሆኖ የተመዘገበላት መሰረት ከድሏ በኋላ ለዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ድረ ገፅ ዘጋቢ ቪንሰንትዉ በሰጠችው አስተያየት ‹‹ የራሴን ምርጥ ሰዓት ለማሻሻል አለመቻሌ አበሳጭቶኛል፡፡ የነበረው ሞቃት አየር እና ከውድድሩ አጋማሽ በኋላ የነበረው የመሮጫ መስመር ከባድ ነበር ›› ያለች ሲሆን ቀጣይ የውድድር ዕቅዷ የ 2017 ለንደን ማራቶንእንደሆነም ጨምራ ገልፃለች፡፡
በሲያመን ማራቶን የውድድር ሕግ የሽልማት ገንዘብ መጠኑ በሚመዘገቡ ሰዓቶች ላይም የሚመሰረት ሲሆን በአንደኛነት ለሚያጠናቅቅ አትሌት የተዘጋጀውን 40 ሺህ ዶላር ለማግኘት ወንዶች ሁለት ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ እና ከዛ በታች ሴቶች ሁለት ሰዓት ከሀያ ሰባት ደቂቃ እና ከዛ በታች ማጠናቀቅ ግድ ይላቸዋል፡፡ በዘንድሮው ውድድር ላይ በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ የሆኑት አትሌቶች የጨረሱበት ሰዓት መስፈርቱን ያሟላ በመሆኑ ሁለቱም የ 40 ሺህ ዶላር ተሸላሚ መሆን ችለዋል፡፡ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት አትሌቶችም የ 10 ሺህ እና 8 ሺህ ዶላር ተሸላሚዎች ሲሆኑ እስከ ስምንተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶችም በቅደም ተከተላቸው መሰረት አነስተኛ የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል፡፡
በ2017 ሲያመን ኢንተርናሽናል ማራቶን የገንዘብ ሽልማትየሚያስገኙትን ደረጃዎች ይዘው ለማጠናቀቅ የበቁት አትሌቶች
ወንዶች
1ኛ . ለሚ ብርሀኑ ( ኢትዮጵያ ) 2፡08 ፡27
2ኛ . ሞስነት ገረመው ( ኢትዮጵያ ) 2፡10 ፡20
3ኛ . ሹራ ቂጣታ ( ኢትዮጵያ ) 2፡10 ፡36
4ኛ . ሙሰንዱኪ ሞሐመድ ( ታንዛኒያ) 2፡12 ፡54
5ኛ . ባንታየሁ አዳነ ( ኢትዮጵያ ) 2 ፡13፡ 25
6ኛ . ሀይሌ ሀጃ ( ኢትዮጵያ ) 2፡14 ፡31
7ኛ . አዳሙ ግርማ ( ኢትዮጵያ ) 2፡15 ፡17
8ኛ . ሙንክህባያር ናራንዱላም ( ሞንጎሊያ) 2፡24 ፡34
ሴቶች
1ኛ . መሰረት መንግስቱ ( ኢትዮጵያ ) 2፡25 ፡58
2ኛ . ወርቅነሽ ኢዴሳ ( ኢትዮጵያ ) 2፡26 ፡27
3ኛ . መልካም ግዛው ( ኢትዮጵያ ) 2፡26 ፡47
4ኛ . ጉተኒ ሾኔ ( ኢትዮጵያ ) 2፡ 29፡ 58
5ኛ . መሰረት ለገሰ ( ኢትዮጵያ ) 2፡30 ፡09
6ኛ . ገበያነሽ አየለ ( ኢትዮጵያ ) 2፡ 34፡ 07
7ኛ . ቆንጂት ጥላሁን ( ኢትዮጵያ ) 2፡34 ፡21
8ኛ . የሺመቤት ታደሰ ( ኢትዮጵያ ) 2፡40 ፡31