ላለፉት አራት ዓመታት የአለም ሻምፒዮናና የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያውያን ይዘውት የቆዩትን የትራክ የበላይነት ነጥቆ ለዓመታት የግሉ ያደረገውን ሞ ፋራህን ከትራክ ውድድር በሽንፈት ጡረታ የሚያስወጣው ኢትዮጵያዊ ማነው?የኢትዮጵያዊያንን ቁጭትስ የሚያብሰው ማነው? ዮሚፍ ቀጀልቻ?ሰለሞን ባረጋ?ሐጎስ ገ/ሕይወት?እድሪስ ከድር?ወይስ ሞላ ጌታነህ?የዚህ ጥያቄ ምላሽ ከሰዓታት በኃላ ይገኛል።
በ16ኛው የለንደን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በከፍተኛ የስነልቦና የበላይነትና ብቃት እንዲሁም ከሩጫ ባህል ውጪና ባልተለመደ የአራራጥ ታክቲክ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች አገር አትሌቶችን ከኃላ አሰከትሎ በመግባት የትራፊክ ንጉስነቱን ያስጠበቀው ሞ ፋራህ ዛሬም የ5000ሺ ሜትሩን ውድድር በማሸነፍ ሌላ ወርቃማ ታሪክ እንደሚያፅፍ ከወዲሁ ቅድሚያ ግምት እየተሰጠው ነው።
የ2011፣የ2013እናየ2015 የአለም ሻምፒዮናዎችን በማሸነፍ ታሪክ የሰራው ሞ ፋራህ ለአሸናፊነት ቅድሚያ ግምት ቢሰጠውም ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይ ከዮሚፍ ቀጀልቻና ከሰለሞን ባረጋ ቀላል ፈተና እንደማይጠብቀውና ይልቁንም ከነገሰበት የትራኩ ዓለም በሽንፈት ጡረታ ሊወጣ እንደሚችልና እንደ ዩዜይን ቦልት አጨራረሱ ላያምር እንደሚችል በሌላ ወገን አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል።
የ2017 የምርጥ ሰዓት ባለቤቶች ከሆኑት 10 ምርጥ አትሌቶች መካከል በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚገኙት እነ ሙክታር እድሪስና ሰለሞን ባረጋና ዮሚፍ ለሞ ፋራህ የተለየ ግምት እንደማይሰጡና በሽንፈት ወደ ጡረታው አለም እንደሚያስገቡት እየተናገሩ ነው።
የፌዴሬሽኑ አመራሮችና አሰልጣኞችም ትናንት የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጭምር የአትሌቶቹን አስተየየት የደገፈ የሚመስል ምላሽም መስጠታቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል ሞ ፋራህ የዛሬውን ፍፃሜ አስመልክቶ እንደተናገረው ዩዜይን ቦልት የገጠመውን አይቻለሁ የእሱ ዕጣ ፈንታ አይገጥመኝም ያለ ሲሆን ትኩረቴን የማደርገው ራሴ ላይ ብቻ ነው ብላል።ተወዳዳሪዎቼ በሙሉ የሚሮጡትና የተዘጋጁት እኔን ለማሸነፍ ነው ካለ በኃላ ያም ቢሆን ወርቁን ከመውሰድ የሚያግደኝ የለም፤በእግሬ ላይ ካጋጠመኝ ጉዳትም ሙሉ በሙሉ አገግሜያለ ለውድድሩ ዝግጁ ነኝ ሲልም ተናግራል።
የ2017ቱ የለንደኑ የ5000ሜ የወንዶች ፍፃማ ከደቂቃዎች በኃላ ፍፃሜ ሲያገኝ ማን በርቀቱ ዘውድ ይደፋል?ሞ ፋራህስ በሽንፈት ከትራክ ንግስናው ጡረታ ይወጣ ይሆን?ሲፈለግ የነበረውና ሞ ፋራህን በቃህ የሚለው ኢትዮጵያዊስ ማን ይሆናል?መልሱን አብረን እንጠብቃለን።
የዓለም የምርጥ ሠዓት ባለቤቶች የሆኑ 6 ኢትዮጵያውያን
-ቀነኒሳ በቀለ በ2004 የገባበት 12:37:35
-ኃይሌ ገ/ስላሴ በ1998 የገባበት 12:39:36
-ደጀን ገ/መስቀል በ2013 የገባበት 12:46:81
-ስለሺ ስህን በ2004 የገባበት 12:47:04
-ሐጎስ ገ/ሕይወት በ2012 የገባበት 12:47:53
-የኔው አላምረው በ2012 የገባበት 12:48:77
የ2017 የምርጥ ሰዓት ባለቤቶች የሆኑ 4 ኢትዮጵያውያን
-ሙክታር እድሪስ 12:55:23
-ሰለሞን ባረጋ 12:55:58
-የኔው አላምረው 13:06:81
-ዮሚፍ ከጀልጃ 13:01:21