አትሌት ሞስነት ገረመው በፖርቹጋል ሊዝበን ማራቶን በአስገራሚ የአጨራረስ ብቃት 59 ደቂቃ ከ37 ሴኮንድ በመግባት ማሸነፉን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።
ሞስነት ትናንት የገባበት ጊዜ በርቀቱ ሁለተኛ ምርጥ ሰአቱ ሲሆን እ.አ.አ በ2014 በህንድ ኒው ዴልሂ የግማሽ ማራቶን 59 ደቂቃ ከ 11 ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱን ያስመዘገበት ውድድር ነበር።
“ጥሩ ብቃት ላይ አልነበርኩኝም በፈለኩት ደረጃም አልሮጥኩም ያም ቢሆን በውጤቱ ደስተኛ ነኝ ያስመዘገብኩት ውጤት በሚያዚያ ወር በሚካሄደው የለንደን ማራቶን የተሻለ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበኝ የሚያሳይ ነው” ብሏል አትሌት ሞስነት ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያያት።
ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ብርሃኑ ወንድሙ በመጀመሪያ የግማሽ ማራቶን ውድድሩ 59 ደቂቃ ከ 42 ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱን ያስመዘገበ ሲሆን ኬንያዊው ኢሳክ ኪፕሳንግ 59 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
በሴቶቹ ውድድር አትሌት ዘይነባ ይመር 1 ሰአት ከ 8 ደቂቃ ከ 7 ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥታለች።
ኬንያዊቷ አትሌት ቪቪያን ቼሮይት 1 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ34 ሴኮንድ እ.አ.አ በ2015 በሌላኛዋ ኬንያዊ ሮዝ ቼሊሞ ተይዞ የነበረውን የቦታውን ክብረ ወሰን በ1 ደቂቃ 48 ሴኮንድ በማሻሻል የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።
ሌላኛዋ ኬንያዊ ሳንድራ ቱዌይ ፌሊስ 1 ሰአት ከ 8 ደቂቃ ከ 14 ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥታለች።
በሌላ በኩል ትናንት በአሜሪካ ኒው ዮርክ የግማሽ ማራቶን በወንዶች አትሌት በላይ ጥላሁን 1 ሰአት ከ2 ደቂቃ ከ10 ሴኮንድ ያሸነፈ ሲሆን ኤርትራዊው አትሌት ዳንኤል መስፍን 1 ሰአት ከ2 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥቷል።
በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነው ፖል ቼሊሞ 1 ሰአት ከ2 ደቂቃ ከ19 ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥቷል።
በሴቶች ጆይስሊን ጄፕኮስካይ 1 ሰአት ከ10 ደቂቃ ከ 7 ሴኮንድ አሸናፊ ሆናለች።
ኬንያዊቷ አትሌት ማሪ ንጉጊና አትሌት ቡዜ ድሪባ በውድድሩ 1 ሰአት ከ 11 ደቂቃ ከ7 ሴኮንድ በሆነ ተመሳሳይ ጊዜ ቢገቡም በመለያ ቴክኖሎጂ (ፎቶፊኒሺንግ) ኬንያዊቷ አትሌት ማሪ ንጉጊ ከአትሌት ቡዜ ቀድማ በመግባቷ ሁለተኛ ስትወጣ አትሌት ቡዜ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።
በተያያዘ ዜና ትናንት በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ማራቶን በሴቶች አትሌት ሂሩት ጥበቡ 2 ሰአት ከ 24 ደቂቃ ከ 10 ሴኮንድ ሁለተኛ የወጣች ሲሆን በውድድሩ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነችው አትሌት ደሲ ጂሳ አሸናፊ ሆናለች።
ኬንያዊቷ አትሌት ሴልስቲን ቼፕቺርቺር ሶስተኛ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ዝናሽ መኮንን አራተኛ ወጥታለች።
በወንዶች ኬንያውያኖቹ አትሌቶች ቶማስ ኪፕላጋት፣ ኤሊሻ ኪፕቺርቺር እና ማይክ ኪፕቱም ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።
አትሌት ፍቅሬ በቀለና አትሌት ጸጋዬ ከበደ በቅደም ተከትል አራተኛና ስድስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በተጨማሪም ትናንት በታይዋን ‘ኒው ታይፔ ሲቲ ዋን ጂን ሺ’ ማራቶን በሴቶች አትሌት መሰረት ሲሳይ 2 ሰአት ከ 34 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ ሁለተኛ የወጣች ሲሆን ኬንያዊቷ አትሌት ናኦሚ ጄፕኮጄይ አሸናፊ ስትሆን ሌላኛዋ ኬንያዊቷ ኤድናህ ሙክዋና ሶስተኛ ወጥታለች።
በወንዶች ኬንያውያኖቹ ማቲው ኪፕሳት፣ ፍሊፕ ቼሮይትና አሌክስ ቼፕክዊክ ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት በበላይነት አጠናቀዋል።