“ኦሎምፒክ ኮሚቴ አሁን ያለንበት ቁመና ከመንግሥት ገንዘብ የሚያስጠይቀን አይደለም።”
“የነበረው የአየር ሁኔታ አመቺ ስላልነበረ ኮንሰርቱን አራዝመነዋል።”
“ከበቂ በላይ ዝግጅት አድርገናል።”
ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የፓሪስ ኦሎምፒክ የመጨረሻ ዝግጅቶች ፣ የጉዞ ሁኔታ እና የተዘጋጁ አልባሳትን በተመለከተ በማርዮት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በተለይም የኮሚቴው ፕሬዚዳንት በሆኑት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አማካይነት በዝግጅት ዙሪያ ማብራሪያዎች የተሰጡ ሲሆን ለውድድሩ ከበቂ በላይ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።
አመቱን ሙሉ ህዝቡን አሳታፊ ያደረገ ንቅናቄ መደረጉን ያነሱት ፕሬዚዳንት አሸብር ውጤታማ ስራዎች አመቱን ሙሉ ስለመሰራታቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የሚወከለው የመጀመሪያው የልዑክ ቡድን በመጪው ረቡዕ ለሊት ወደ ፓሪስ ያቀናልም ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ባሉት መልኩ ከዋና ተመራጭ አትሌቶች በተጨማሪም ተጠባባቂ አትሌቶችም ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ሲገልፁ ምክንያቱንም እንደሚከተለው በማብራራት ነው።
“አንድም የመክፈቻው ዕለት ሳስተን እንዳንታይ ሁለት ምናልባት በጤና እክል የማይሰለፉ አትሌቶች ቢኖሩ እነሱን ተክቶ የመሮጥ ዕድል ያጋጥማል። ስለዚህ በተጠባባቂነት የተያዙት ሁሉም አትሌቶች ይጓዛሉ።”
በተጨማሪም በሚጓዘው ልዑክ 18 አሰልጣኞች እና 10 የህክምና ቡድን አባላት ይገኙበታል።
ወደ ፓሪስ ከሚያቀኑ አካላት ጋር በተያያዘ በተለይም ከክልል ስፖርት ቢሮ ሀላፊዎች ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ ዶክተር አሸብር ጠንከር ባለ ንግግር ተከታዩን ተናግረዋል።
“ኦሎምፒክ ሲደርስ ሰዎች ሲሔዱ ጥላቻ አለ። ለምን እንደሚጠሉ ግን አይገባኝም። አቅም ካለ ለምን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አይሔድም? ምንድነው ችግሩ ? አይደለም ክልሎች የኦሎምፒክ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ሀላፊዎች ፤ ወጣቶች ላይ የሚሰሩ ከስፖርቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሙያተኞች መሔዳቸው ምንድነው ችግሩ? ለምን ሔዱ ነው? ምንድነው? እውነቴን ነው ተገቢ አይደለም። በጣም ቀና ሆነን በጎ አሳቢ ሆነን እንየው።”
ዶክተር አሸብር አክለውም ማንም ከዚህ ጋር ተያያዥነት የሌለው ፣ በስራው ያልተሳተፈ ፣ ግንኙነት የሌለው ሰው አይሔድም ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
በትናንትናው ዕለት በመስቀል አደባባይ ይደረጋል ተብሎ ስለነበረው እና ሳይካሄድ ስለቀረው ኦሎምፒክ ኮንሰርትም ዶክተር አሸብር ተራዘመ እንጂ አልተሰረዘም ብለዋል።
“የተሰረዘ ኮንሰርት የለም። ትናንት በነበረው ሁኔታ ያለው የአየር ሁኔታ ምቹ ስላልነበረ አራዝመነዋል። አይተን እንደ አመቺነቱ እናደርጋለን።”
መንግስት በገንዘብ ዙሪያ በተገቢው ልክ አግዟችኋል ወይ ለተባሉት ደግሞ ተቋማቸው በገንዘብ አቅም ራሱን የቻለ መሆኑን በመጥቀስ በሀገር ገንዘብም ሆነ በውጪ ምንዛሪ ከበቂ በላይ ገንዘብ አለን ብለዋል ዶክተር አሸብር
“መንግስት እኛ ጠይቀን የከለከለው ነገር የለም። ግን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አሁን ያለንበት ቁመና ገንዘብ ከመንግሥት የሚያስጠይቀን አይደለም። ከበቂ በላይ ገንዘብ አለን። ራሳችንን የቻልን ነን።”
ገቢ በማሰባሰብ ረገድ እጅግ በተሻለ መልኩ ገንዘብ መሰብሰቡን የጠቀሱ ሲሆን ህዝቡን ከማሳተፍ አኳያ በተለይም በቴሌብር ላይ ከአንድ ብር ጀምሮ ብዙ ሰዎች እየተሳተፉ ነው ብለዋል።
በዚሁ በቴሌብር የገቢ ማሰባሰቢያ ከ43 ሚሊዮን በላይ ሰው እየተሳተፈ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አትሌቶች ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል። ከነዛም መካከል አንዱ የሆነው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ እንዲወዳደር ቢመረጥም በመጨረሻ በ10 ሺህ ብቻ እንዲወዳደር ተወስኗል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አትሌቱ ያለ አግባብ ተቀንሻለሁ ብሎ መናገሩ የሚታወስ ሲሆን የኦሎምፒክ ኮሚቴው ግን በፕሬዚዳንቱ አማካይነት በ5 ሺህ መወዳደር ፍላጎት የለኝም በማለቱ ነው የተቀነሰው የሚል መልስ ሰጥቷል።
“ከዮሚፍ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የውስጥ ንግግሮች ስለነበሩ ነው። ዮሚፍ ብቁ ነው ምንም ጥያቄ የለውም። ግን ከደረሰን ሪፖርት አኳያ 5 ሺህ ላይ የመሮጥ ፍላጎት እንዳልነበረው በቀረበው ሪፖርት ላይ ተንተርሶ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ መወሰኑን ነው የሰማነው። ስለዚህ ዮሚፍ ላይ የአቋም ችግር የብቃት ችግር ኖሮ ሳይሆን ከርሱ ወጣ የተባለው ጥያቄ ተከትሎ የመጣ ውሳኔ ይመስለኛል።”
በመክፈቻው ስነስርዓት ላይ በESPN የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምርጡ አፍሪካዊ ስፖርተኛ የተባለው ቀነኒሳ በቀለ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እንዲይዝ ተፈልጎ እሱም ፈቃደኛ ቢሆንም በአሰልጣኞቹ ሙያዊ አስተያየት ሳይሆን መቅረቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
“እኛ ፈልገን የነበረው ቀነኒሳ በቀለ እንዲይዝ ነው የነበረው ቀነኒሳ በቀለ ተጠይቆ እምቢ የሚለው ነገር የለውም ትልቅነቱ ፤ ምንም ነገር ቢጠየቅ እምቢ አይልም። እሺ ነው ያለው ግን ሙያተኞቹ በኋላ ጉዞ ላይ ረጅም ስለሚቀመጥ እግሩ ቢያሳብጥ ድካም ቢመጣበት ደርሶ መልስም ከባድ ይሆንበታል እና የሚል ሀሳብ አለ። የሱ ካልሆነ ሁለተኛ እቅድ አለ። እያሰብን ያለነው እነ በሪሁም ስላሉ አትሌቶች አሉ ከነሱ አንዱን ጀግና አትሌት መርጠን ሰንደቅ አላማችንን እንዲይዝ እናደርጋለን።”
ኦሎምፒክ ኮሚቴው በስካይ ላይት ሆቴል ከፍ ባለ መልኩ ሽኝት አድርጓል ያሉት ዶክተር አሸብር ኢትዮ ቴሌኮም ዛሬ ቱሪዝም ሚኒስቴር ማክሰኞ ይሸኛሉ ያሉ ሲሆን በርካታ የሽኝት መርሐግብሮች ቢኖሩም ታጥፈው ለአቀባበል እንዲሆን ከስምምነት ደርሰናል ብለዋል።
የፌዴራል መንግስትም በነገው ዕለት ከ10:00 ጀምሮ ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ በተገኙበት በብሔራዊ ቤተመንግስ ደማቅ ሽኝት ለኦሎምፒክ ቡድኑ ያደርጋል።