THE BIG INTERVIEW : BIYADGELGE ELIAS
በይስሀቅ በላይ
ፍፁም ጭምት፣ አመለ ሸጋ፣ ዝምተኛ፣ ግን ደግሞ በሜዳ ውስጥ ታጋይና የድንቅ ችሎታ ባለቤት፤ በሀገራችን የችሎታቸውን ያህል ካልተዘመረላቸው (Unsong hero) አንዱ ነው፤ የዛሬው እንግዳችን ቢያድግልኝ ኤልያስ፡፡ የእግር ኳስ ህይወቱን በአርባ ምንጭ ዳሽን፣ በሲዳማ ቡና፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በጅማ አባቡናና በወልዲያ አሁን ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ አናት ላይ ለተቀጠው መቐለ 70 እንደርታ በመጫወት ላይ የሚገኘው ቢያድግልኝ ኤልያስ (ባደግ) የችሎታውን ያህል ያልተነገረለት ለችሎታው ተገቢው ክብርና ዕውቅና የተነፈገው ተጨዋቾች ነው፡፡
ተከላካይ ሆኖ ኳስን ከመጠለዝ ይልቅ ኳስ ይዞ በመጫወት ኳስን ለሚወዱ እርካታን የሚሰጠው ቢያድግልኝ በዚህ አጨዋወቱ የሚያደንቁት እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው በመሰለፍ “ያስበላናል፤ ጎል ያስገባብናል” ብለው የተለያዩ ጫናዎችን የሚያሳድሩበት በርካቶች ናቸው “የራሱ አጨዋወት ሰለባ ከሆኑት ተጨዋቾች አንዱ እኔ ነኝ” በማለት የሚናገረው ቢያድግልኝ ኤልያስ “ኳስን ባለመጠለዜና ይዤ በመጫወቴ መመስገን ሲገባኝ ሠለባ ሆኛለሁ” በማለትም ይናገራል፡፡ የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስክዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የመቐለ 70 እንደርታውን የኳሱን ሊቅ ተከላካይ የሊጉ መሪ በሆነው ክለቡ፣ የሊጉን ዋንጫ ስለማንሣት ተስፋቸው፣ ስለ ግል ህይወቱና በዝምተኝነት ስለሞላው ህይወቱ አነጋግሮት ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቀናብሮታል፡፡
…የእግር ኳስ “ሀሁን” ስለጀመረባትና የእድገቱ መነሻ ስለሆነችው የትውልድ ከተማው…
- ማሰታውቂያ -
“በጣም የሚገርምህ እኔ ያደኩበት ቦታ ወንዝ ዳርቻ ነው፤ በመስኖ እርሻ እያረስኩ ዓሳ እያጠመድኩ ነው ያደኩት ፡፡ እኔን ያበቀለችኝ መሬት ወይም ከተማ ደግሞ ልማት ትባላላች፤ እኔ የልማት ከተማ ልጅ ነኝ እዚያ ነው ተወልጄ ያደኩትⵆ ልማት ከተማ ውስጥ ግድብ ሠፈር የሚባል አለ ለመስኖ የሚሆን ውሃ የሚገደብበት በዚያ አካባቢ ነው እርሻውን ኳሱንም ዋናውንም እያጣመርኩ እያዘወተርኩ ያደኩት፡፡ ልማት የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ አቅም ያላቸው ተጨዋቾች መፈለቂያ ናት፤ ኳስን በጣም እንወድ ነበር፡፡ በልጅነታችን እርሻውን፣ ዋና ስንዋኝ ውለን ኳስ ስንጫወት ነበር የምናሳልፈው፤ ስራችንን ሰርተን ወደ ኳስ ነበር ሩጫችንⵆ ያ አሁን በእግር ኳስ ህይወታችን ላገኘነው ጥንካሬ በጣም ረድቶናል፡፡ ስለዚህ ልማት ለዛሬው ማንነቴ ትልቁን ውለታ የዋለች ከተማ ናት፡፡”
የአርባ ምንጭ ልጆች ለጥሬ ሥጋ ስላላቸው ፍቅርና ከጨዋታ በፊት ስለመመገባቸው…
“እውነት ነው ጥሬ ስጋ በጣም የሚዘወትር ምግብ ነው፤ በርካታ የአርባ ምንጭ ተወላጅ የሆኑ ተጨዋቾች ከጨዋታ በፊት ሣይቀር ይመገባሉ፤ እኔ ግን ከእነሱ በተቃራኒ ነኝ፡፡ ከጥሬ ሥጋ ጋር ፍቅር የለኝም፤ እንደውም ጥሬ ሥጋ አልመገብም፡፡ ከጥሬ ሥጋ ይልቅ ጥሬ ዓሳን መመገብ ነው ምርጫዬ፤በእርግጥ ብዙ ሰው የአርባ ምንጭ ልጅ እንደሆንኩ አያውቅም፡፡ ቢያድግልኝ የሚለው ስም መታወቅ የጀመረው በዋናነት በሲዳማ ቡና ስለሆነ የሲዳማ አካባቢ ልጅ ነው የምመስላቸው፤ የልጅነት ጊዜዬን ወንዝ አካባቢና ዓሳ እያጠመድኩ ስላደኩ ከጥሬ ሥጋ ይልቅ ጥሬ ዓሳን እየተመገብኩ እንዳድግ አድርጎኛል፡፡ ከጥሬ ዓሳ ሌላ የሥራሥር ምግቦችን አዘወትሬ በመመገብም ነው ያደኩት፡፡”
…በየሄደበት ክለብ በሠራተኛነቱና በዲሲፒሊን ስለመታወቁና ስለመመስገኑ…
“እኔ በየሄድኩበት ክለብ ስራዬን አክብሬ ነው የምሰራው፤ ስራን ደግሞ ወድጄ አክብሬ እንድሰራ በወሬ ሳይሆን በተግባር ሰርቶ ያስተማረኝ ወላጅ አባቴ ነው፡፡ የአባቴ የሥራ ወዳድነት ፍቅር በልጅነት አዕምሮዬ ተጋብቶብኝ አብሮኝ ኖሮ አብሮኝ አድጎ ዛሬም ድረስ አብሮኝ እየኖረ ነው፡፡ የሚገርምህ ገጠር ውስጥ እርሻ እያረስኩ ከብቶችን እየጠበኩ ከአባቴ ሥር ሥር እያልኩ ማደጌ በጣም ጠቅሞኛል፤አባቴ ሥራ ነው ሰውን የሚያስከብረው እያለ ከሚፈጥርብኘ ጫና በላይ ሠርቶ ማሳየቱ ዛሬን በሙያዬ ሥራዬን አክብሬ አፍቅሬ እንድሰራ አደርጎኛል፤ እንዳልከው በገባሁበት ክለብ በሠራተኝነትና በዲሲፒሊን አክባሪነት ነው ስሜ የሚነሣው፤ ከዚህ ውጪ ታምቼ አላውቅም ፤በዚህ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”
…አርባ ምንጭ ላይ ቢያድግልኝ ከሚለው ስሙ ይልቅ “ባደግ” በሚል ቢወጣለት ስም ይበልጥ ስለመታወቁ…
“እግር ጥሎህ ወደ አርባ ምንጭ ሄደህ ቢያድግልኝ የሚባል ኳስ ተጨዋችን ታውቃላችሁ ብትላቸው ብዙዎቹ ግር ይላቸዋል፤ እረ እንደውም አንዳንዶቹ “የቱ ነው ቢያድግልኝ” ብለው ሊያስደነግጡህ ሁሉ ይችላሉ፡፡ አርባ ምንጭ ውስጥ በዋናው ስሜ የሚያውቁኝ ብዙ የሉም፡፡ ቢያድግልኝ ከሚለው ከዋናው መጠሪያ ስሜ ይልቅ ባደግ በሚለው በወጣልኝ ስም ነው የምታወቀው፤ ይሄንን ስም ያወጡልኝ ስጫወት የተመለከቱኝ የአካባቢዬ ሰዎች ናቸው፡፡ ትልቅ ደረጃ ደርሼ ማየትን ከመመኘትና ከመጓጓት የተነሣ ባደገ ምነው ትልቅ ደረጃ በደረሰ ብለው “ባደግ” የሚል ስም አውጥተውልኝ ከዋናው ስሜ ይልቅ መጠሪያዬና መታወቂያዬ ሆኗል፤ እኔም በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”
…ወደ መቐለ 70 እንደርታ ስላደረገው ጉዞው የክለቡ አባል ስለመሆኑ…
“ወደ መቐለ 70 እንደርታ የመጣሁት በቀጥታ ከአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ጋር ተነጋግሬ ነው፤ ወደ ክለቡ የመጣሁት በጣም ደስተኛ ሆኜ ነው፤ አሁንም በክለቡ ጥሩ የሚባል የደስታ ጊዜዬን እየጣጣምኩ ነው፡፡ በእግር ኳስ ደግሞ ይሄ ትልቁና አስፈላጊው ነገር ነው፤ በአሰልጣኙ ታምኖብህ ተፈልገህ ስትመጣ የተለየ ስሜት ይሰማሃል፡፡ የዚህ ስብስብ አካል በመሆኔ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”
…መቐለ 70 እንደርታ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሣት ታሪክ ለማፃፍ እያደረገ ስላለው ግስጋሴና የአሸናፊነት ምስጢሩ…
“ቡድናችን አሁን በሊጉ አናት ላይ ነው፤ አንደኛውን ዙር በመሪነት መጨረሳችን የሊጉን ዋንጫ ለማንሣት ለምናልመው ህልም ትልቅ ጉልበት ሆኖናል። ቡደኑ አሁን ለሚገኝበት ደረጃና ወደ ዋንጫ የሚያደርገው ግስጋሴ ዋናው ምስጢሩ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ቡደኑን እንደ አንድ ማዋቀሩ፣ ተጨዋቾች አንድ ታሪክ ለመስራት ያላቸው ተነሳሽነት፤ ደጋፊውና የክለቡ አመራሮች ለሚመዘገበው ውጤት ትልቅ ኃይል መሆናቸው ተደማምሮ የፈጠረው ነው ብዬ የማምነው፤ ቡድናችን እንደ አንድ በመገንባቱ በተናጠል ይሄ ነው የምትለው ተጨዋች የለም፤እንደ ቡድን ነው የተዋቀረው፡፡ ሁሉም በየቦታው አሰልጣኙ በሚሰጠው ስልጠናና መመሪያ መሠረት ያላቸውን ያለስስት ከልባቸው ይሰጣሉ፤ይሄ ነገር ቡድኑ ሊጉን እንዲመራና ዘንድሮ ክስተት እንዲሆን አድርጎታል ብዬ ነው የማስበው፡፡”
…የመቐለ 70 እንደርታ ሩጫ የት ድረስ…? አዲሱ የሊጉ ሻምፒዮን ይሆናሉ? ስለመባሉ…
“ቡድናችን ገና ሲዋቀር አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ በፕሪሚየር ሊጉ የምንሳተፈው ወይም የምንጫወተው ለዋንጫ እንደሆነ ደጋግሞ ነው የነገረን፤ እያንዳንዱም ተጨዋች የአመቱን ውድድር የጀመረው በዚህ ስሜት ተቃኝቶ ነው፡፡ ህልማችን ለክለባችን አዲስ ታሪክ በማፃፍ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ካነሱ ክለቦች ተርታ መሠለፍ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ሊጉን መራን እንጂ ሻምፒዮን መሆናችን ስላልተረጋገጠ አሁን ባለን ውጤት አንኩራራም፤ልክ ሻምፒዮን የሆንን ያህል የምናስብ ከሆነ አደጋ አለው፡፡ ደግሞም አሁን ስለ ሻምፒዮንነት ለማውራት ጊዜው በጣም ገና ነው፤ አሰልጣኛችን እያዘጋጀን፣ እኛም እየሠራን ያለነው በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነን ነው፡፡ ቡድናችን የተዋቀረው በጣም ልምድና አቅም ባላቸውና ወጣት በሆኑ ተጨዋች ነው፤ በዚያ ደረጃ መዋቀሩን መልካም አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ አሁን ላይ ሆነን ስለ ሻምፒዮንነታችን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ አንድ መናገር የሚቻል ነገር ቢኖር ወደ ሻምፒዮናነት በሚወስደው ትክክለኛው መንገድ ላይ መገኘታችን ነው፡፡ ይሄንን አጠናክረን ከቀጠልንና ያለንበትን ቦታ ካስጠበቅን የምንመኘውን ስለማግኘታችን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ስለ ሻምፒዮንነት ለመናገር በሁለተኛው ዙር የተወሰኑ ጨዋታዎችን ውጤት ማየት ያስፈልጋል፤ ያኔ በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገር ይቻላል፤ አሁን ላይ ግን እንዲህ ነው ብሎ መናገር ከባድ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን እንደ ቡድን መነሻችንን የሊጉ ዋንጫ ላይ አድርገን መስራታችን እንቀጥልበታለን፡፡”
…በርካታ ጨዋታዎችን በሜዳቸው ማድረጋቸው ነው ለመሪነት ያበቃቸው፤ በሁለተኛው ዙር ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ ሊቸገሩ ይችላሉ ስለመባሉ?…
“የሚገርምህ ነገር በአሁን ሰዓት በሜዳና ከሜዳ ውጪ የሚባል ነገር እኛ ሀገር ውስጥ ብቻ ያለ ነው የሚመስለኝ፤ እኛ እንደ ቡድን ስንጫወት በሜዳችንም ከሜዳችንም ውጪ አንድ አይነት አቋም ነው ያለን፡፡ ደግሞም በሊጉ አናት ላይ የተቀመጥነው በሜዳችን ያደረግነውን ጨዋታ ብቻ አሸንፈን ከሜዳችንውጪ እየተሸነፍን አይደለም፤ በሜዳችን ካደረግናቸው ጨዋታዎች ውጪ በሰው ሜዳም ተጫውተን በጣም ትልቅ ዋጋና ውድ የሆኑ ሙሉ ሶስት ነጥቦችን ከተለያየ ቦታ ይዘን መመለሳችን መዘንጋት የለበትም፡፡ በዚህ በኩል በተለይ ከሀዋሳ፣ ከድሬዳዋም ያመጣናቸው ነጥቦች ከሶስት ነጥብ በላይ ናቸው፡፡ በአንደኛው ዙር ስምንት ጨዋታዎችን በሜዳችን ነው ያደረግነው፤ በሁለተኛው ዙርም ከሜዳችን ወጥተን ብንጫወትም በሜዳችን በተመሳሳይ ስምንት ጨዋታዎችን ነው የምናደርገው፡፡ ከዚህ አንፃር በሜዳቸው ስለተጫወቱ ነው መሪ የሆኑት የሚያስብል ነገር የለም፡፡ በሜዳህም እኮ ተጫውተህ ልትሸነፍ ነጥብ ልትጥል ትችላለህ፤ በሜዳህ ማሳካትም ስራን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ መሪ የሆነው በሜዳችን ስለተጫወትን ብቻ ሳይሆን በሜዳችንም ከሜዳችን ውጪም ጠንክረን ስለቀረብን ነው፡፡”
…ለቡድኑ ውጤታማነት የጀርባ አጥንት ስለሆነው የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊ…
“እውነት ለመናገር እድለኞ ነን፤ ለቡደኑ ተጨማሪ ጉልበት የሚሆኑ ለውጤት ይበልጥ የሚያነሣሱ የተለያዩ ደጋፊዎች አሉን፡፡ ክለባችንን ከልብ ነው የሚደግፉት፤ የሚወዱት፡፡ በሜዳችንም ከሜዳችንም ውጪ ስንጫወት ውጤት ቢኖረንም ባይኖረንም የማይለዩን ምርጥ ደጋፊዎች አለን፤ እስከ አሁን ለተመዘገበው ውጤት የደጋፊዎቻችን አስተዋፅኦ ከቃላት በላይ ነው፤ በጣም የሚገርምህ ጨዋታ ከጨረስን በኋላ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ከጎንህ ሆነው ማየት አስገራሚ ነው፡፡ ከጨዋታ በኃላ ለተገኘው ውጤት ለማመሰገንና ለቀጣይ ጨዋታ የሚያሳዩህ አጋርነት የተለየ ነው፡፡ እውነት ለመናገር አሁን ላገኘነው ውጤት ትልቅ ጉልበት ሆነውናልና በዚህ አጋጣሚ በጣም ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡”
…የፕሪሚየር ሊጉ በመቋረጡ ስለተሰማው ስሜት…
“ፕሪሚየር ሊጉ በዚህ የሚንተከተክ የአሸናፊነት ስሜት ውስጥ ሆነነ መቋረጡ እኛን በጣም ጎድቶናል፤ በጥሩ የአሸናፊነት ትራክ ውስጥ ሆነን መቋረጡ ለእኛ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንዲያመዝንብን ነው ያደረገው፡፡ ጨዋታው በመቋረጡ በአሸናፊነት መንፈስ ውስጥ ሆነን ከመቀጠል ይልቅ እንድንወጣ ነው የሚያደርገን፤ከጨዋታ ርቀን አርፈን እንደገና ወደ ጨዋታና ወደ አሸናፊነት መመለስ ከባድ ነው፤ ከልምድ ያየነው ይሄንን ነውና፡፡ ሌላውን ተወውና ተስተካካይ ብለው የተያዙትን ጨዋታዎች መጀመሪያ ብናደርግ ጫና ይቀንስልን ከዚህ የተሻለ ውጤትም እናሳካ ነበር፤በጥሩ የአሸናፊነት መንፈስ (ስፕሪት) ውስጥ ሆነን መቋረጡ ጎድቶናል፡፡”
…ከተከላካይነት ይልቅ በአጥቂነትና አማካይነት እየተጫወተ ስለማደጉ…
“እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ በተከላካይ ተጨዋችነት ተጫውቼ አላውቅም፤በአጥቂነትና በተለይ በአማካይነት እየተጫወትኩ ነው ያደኩት። ሲደማ ቡና እያለሁ በ2001 ዓ.ም በብ/ሊግ፤ በ2002 ደግሞ ፕሪሚየር ሊግ ስንገባ እንኳን በተከላካይነት ሳይሆን በአማካይ ተጫዋችነት ነበር የምታወቀው። እኔን አሁን ወደምጫወትበት ተከላካይነት የመለሰኝ አሰልጣኝ ታረቀኝ (ዳኜ) ነው፡፡ በተከላካይነት ቦታ የሚጫወቱ ተጨዋቾች ለረዥም ጊዜ ለስድስት ወርና ከዚያ በላይ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ የመለየታቸው አጋጣሚ መፈጠሩ ወደ ተከላካይነት እንድመለስ ምክንያት ሆኖኛል እንጂ እኔ ከመነሻው ተከላካይ ተጫዋች አልነበርኩም፡፡
…የትኛው የጨዋታ ሚና ይመቸዋል… ተከላካይ? ወይስ አማካይ?…
“እኔ በታዘዝኩት ቦታ እጫወታለሁ፤ ደግሞም የትኛውም ቦታ ላይ ተጫወት ብባል በብቃት እጫወታለሁ ብዬ ስለማምን ቦታ አልመርጥም፤የታዘዝኩትን መፈፀም ነው የእኔ ድርሻ፤ ምናልባት ግን ጥያቄህ የትኛው ቦታ ላይ ብትጫወት ይበልጥ ይመችሃል? ከሆነ አማካይ ላይ ብጫወት እመርጣለሁ፡፡ ያው ሰው እንዳሰበው ሣይሆን አምላክ እንደፈቀደው ስለሆነ የሆነውን ተቀብያለሁ እንጂ አማካይ ቦታ ላይ ብጫወት ይበልጥ ይቀለኛል፡፡”
…ተከላካይ ተጨዋች ሆኖ ኳስ አለመጠለዙና እንደ አማካይ ኳስ ይዞ ስለመጫወቱ…
“ኳስን በመጠለዝ አላምንም፤ ኳስን ይዞ ተረጋግቶ መጫወትን ነው የማስቀድመው፡፡ ተከላካይ ሆኜ ከመጠለዝ ይልቅ ኳስን ይዤ መጫወት ስራዬን ያቀልልኛል፤በራስ የመተማመን ስሜቴንም በጣም ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ሁለት የተለያየ ስሜትን በብዙዎች ዘንድ ፈጥሯል፡፡እንዴት ኳስ ይይዛል የሚልና ኳስ ይዞ ይጫወት በሚል ሁለት ጎራ። ”
…ኳስን አለመጠለዙና ኳስ ይዞ መጫወቱ ስላደረሰበት ጉዳት…
“እውነት ልንገርህ የራሱ አጨዋወት ሠለባ ከሆኑ ተጨዋቾች አንዱ ነኝ፤ ኳስን ይዤ በመጫወቴ የበለጠ ተጠቃሚና ተፈላጊ መሆን ሲገባኝ አለመጠለዜ ቀላል የማይባል ጉዳት አደርሶብኛል፡፡ በተደጋጋሚ ለብ/ቡድን ተመርጬ ሀገሬን እንዳላገለግልና በምጫወትበት ክለብም በምፈልገው ደረጃ ያለኝን አቅም አውጥቼ እንዳላገለግል የራሱን ከፍተኛ ጫና አሳድሮብኛል፡፡ ኳስን ሳልጠልዝ ይዤ መጫወቴ ከአድናቆት ይልቅ ወቀሳን እንዳተርፍ አድርጎኛል፡፡ በዚህም የተለያዩ የደጋፊዎችና በተለይ የአሰልጣኞች ጫና እንዲያርፍብኝም አድርጎኛል፡ ፡እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ በተከላካይነት ሳይሆን በአማካይነት ተጫውቼ ማሳለፌ ኳስን ከመጠለዝ ይልቅ ይዤ እንድጫወት ምክንያት ሆኖኛል፡፡ እኔንም ክለቤንም የሚጠቅመው ይሄ ሆኖ ሳለ በተለይ በአሰልጣኞች ወይም በክለብ ተጨዋቾችና ደጋፊዎች “እሱ ኳስ ይይዛል፤ ኳስ ይዞ ስለሚጫት ጎል አስገብቶ ያስበላናል“ በሚል የተሳሳተ በሚመስል ስሜት ሀገሬን እንዳላገለግል አቅሜንም አውጥቼ እንዳልጫወት ቀላል የማይባል ጫና እንደፈጠረብኝ አድርጓል፡፡ በዚህም ሰውን ሳይሆን የራሴን አቅም እስከመውቀስም ደርሼያለሁ፤ በአጭሩ ኳስን ከመጠለዝ ይልቅ ይዤ መጫወቴ ሀገሬን በአግባቡ እንዳላገለግል ሰለባ አድርጎኛል።“
…ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስላደረገው ዝውውርና ስለተሰማው የደስታ ስሜት…
“ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንድዛወር ምክንያት የሆነኝ በሲዳማ ቡና ያሳየሁት እንቅስቃሴ ነው፤ሲዳማ ቡናን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አሳድገን በፕሪሚየር ሊጉም በጣም ጥሩ የሚባል ፉክክር በማድረጋችን ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ የበርካታ ክለቦችን ትኩረት ስበን ነበር፡፡ ጊዮርጊሶች እኔን ለማዛወዋር ጥያቄ ያቀረቡት በሲዳማ ቡና ውል እያለኝ በመሆኑ ኮንትራቴን አልጨረስኩም ስላቸው “ችግር የለም እንፈልግሃለን” አሉኝ፡፡ በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያክል ታላቅ ክለብ በዚህ ደረጃ ሲፈልግህ የሚሰማህ የተለየ ስሜትን ነው፤፡ “በጣም እንፈልግሃለን?” ሲሉኝ በጣም ነው የተደሰትኩት፤ ለቅ/ጊዮርጊስ መጫወት ለእኔ ትልቅ ክብር ነው አልኳቸው፡፡ ወዲያው ከአቶ አብነት ገ/መስቀል ጋር እንድገናኝ አደረጉኝ፤ እሳቸውም አነጋገሩኝ፤ በጣም ተደሰትኩ፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀገራችን የደለበ የታሪክና የውጤት ሀብታም የሆነ ክለብ ነው፡፡ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች ያሉበት፣በርካታ ስመ-ጥር ታላላቅ ተጫዋቾች ያለፉበት፣ ጠንካራና ክለቡን የሚወድ አመራሮች ያሉበት ክለብ በመሆኑ ለመጫወት አላመነታሁም፤ ደግሞም ውሳኔዬ በጣም ትክክል ነበር፡፡ ለክለቡ በመጫወት የተለያዩ ክብሮችንና ስኬቶችን ተጎናፅፌያለሁ፤ በኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ላይ በመሳተፍ ትልቅ ልምድም ቀስሜያለሁ፡፡ ከውጪ ከመጡ አሰልጣኞች ጋር በመስራት ትልቅ ቁም ነገር አግኝቻለሁ፤እግር ኳስን ባለኝ እውቀት ላይ ጨምሬ ማወቅ እንዳለብኝ ከእነሱ ተምሬያለሁ፡፡”
.. በቅዱስ ጊዮርጊስ የሚፈልገውን አሳክቷል፤ ራሱንስ በትክክል ገልጾ ወጥቷል በሚል ለቀረበለት ጥያቄ…
“እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ ጥሩ የሚባል ጊዜን ባሳልፉም በሚፈልገው መንገድ አቅሜን ሙሉ በሙሉ አውጥቼ ተጫውቻለሁ፤ ክለቡን መጥቀም በሚገባኝ ደረጃ ጠቅሜያለሁ ለማለት ይቸግረኛል፡፡ ጊዮርጊስ ቤት መጫወት በራሱ በጣም ከባድ ነው፤ የተለያዩ ወገኖች ያለኝን አቅም አውጥቼ እንዳልጫወት አድርገውኛል፤ ተገፍቼያለሁም። በተጨዋቾችና በአንዳንድ ሰዎች አዝኜ ነው ጊዮርጊስ የለቀቅኩት፤ አንተ እየሰራህ እየለፋህ ሌላው መቶ ይጋልብብሃል፡፡ አንተ ጎልተህ እንዳትወጣ የተለያዩ ጫናዎችን ያሳደሩብሃል፡፡ ምክንያቱም ቤቱ ጥቅም የሚገኝበት ቤት ነው ተብሎ ስለሚታመን አንተ ጎልተህ ከወጣህ ያጠፋናል ጥቅም ያሳጣናል የሚሉ ወገኖች ይረባረቡብሃል፤ እኔም የዚህ ሠለባ ነበርኩ፡፡ ዛሬም ድረስ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳስብ ያለኝን አቅሜን አውጥቼ ክለቡን በምፈልገው መጠን ሳልጠቅም ነው የወጣሁት፡፡ ለጊዮርጊስ አራት አመት ነው የተጫወትኩት፤ ከተጫወትኩት አመት በላይ ጊዮርጊስን በደንብ በብቃት መጥቀም፣ የታሪኩ አካል መሆን እየቻልኩ ነው የወጣሁት፡፡ ከላይ በገለፅኩልህ መልኩ አሉታዊ ተፅዕኖ የፈጠሩብኝ ሰዎች ቢኖሩም በደጋፊውና በክለቡ አመራሮች ግን በጣም ደስተኛ ነበርኩ፤ በጣም ጥሩ የሚባሉ ክለቡን የሚወዱ አመራሮችና እውነተኛ ደጋፊዎች ያሉበት ቤት መሆኑን ግን ሳልመሰክር አላልፍም”
…የችሎታውን ያህል የብ/ቡድንን ማልያ ሲለብስ አለመታየቱ…
“የአንድ ተጨዋች ትልቁ ግብ ሀገሩን ህዝቡን መወከል ነው፤ እኔም የዚህ ታላቅ እድል ባለቤት በመሆን የሀገሬን ብ/ቡድን ማልያ ለመልበስ በቅቻለሁ፡፡ በተለይ ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ብ/ቡድን አካል በመሆን ታሪክ አፅፌያሁ፡፡ በዚህ ውድድር በሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ለሀገሬ ተሰልፌ ተጫውቻለሁ፡፡ አሰልጣኝ ባሬቶ በያዙት ጊዜም የመጫወት እድልን አልተነፈግሁም፡፡ ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በኋላ ለብ/ቡድን ያሰበኝ የለም፡፡ ተመርጬ የመጫወት እድል አላገኘሁም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ችሎታዬ ወርዶ ወይም አንሼ ሳይሆን የፈረደበት “ኳስ ይይዛል፤ አይጠለዝም” የሚል ታፔላ ተለጥፎብኝ ነው፡፡ ወደ ብ/ቡድን የመጡ አሰልጣኞች “ተከላካይ ሆኖ ኳስ ይይዛል፤ ኳስ ሲይዝ አስገብቶብን ያስበላናል” በሚል አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት ከምርጫ ውጪ አደርገውኛል፡፡ በአጭሩ ኳስ ከመጠለዝ ይልቅ ይዤ መጫወቴ ሠለባ አድጎኛል፡፡ ኳስ መያዝ ደግሞ አብሮኝ ያደገ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ምክንያት እየተደረደረ ከምርጫ ውጪ ስሆን ቆይቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ ብ/ቡድኑን ማገልገል የምችልበት አቅም ሳላጣ “ኳስ ይይዛል” የሚል ስም እየተሰጠኝ ከምርጫ ውጪ ሆንኩ እንጂ ሀገሬን አሁንም በብቃት ማገልገል የምችልበት አቅሙ አለኝ፡፡ “
…በእግር ኳስ ህይወቱ የማይረሳውና ሁሌም ሲያስታውሰው ስለሚኖረው ቁጭት…
“በእግር ኳስ ህይወቴ በጣም የተቆጨሁበትና ሁሌም በቁጭት ሳነሣው የምኖርው አንድ አጋጣሚ አለ፤ ጅማ አባቡና ስጫወት በተሰራብን የከፋ በደል ቡድናችን እንዲወርድ የተፈረደበትን ግፍ የተሞላበት ፍርድ ሁሌም በቁጭት ሳስታውሰው ነው የምኖረው። ይህ አጋጣሚ እግር ኳስን እስከመጥላትና ከጨዋታ እስከመገለል የሚያደርስ ውሳኔን እስከመወሰን አድርሶኝ እንደነበር ዛሬም በቁጭት ነው የማስታውሰው፡፡ አጋጣሚው አልፎ አሁን በሌላ ክለብና የእግር ኳስ ህይወት ውስጥ ብሆንም ያ ግፍ ግን አሁን የተደረገ ያህል ቁጭቱ አብሮኝ አለ፤ ባሰብኩት ባስታወስኩት ቁጥር በጣም ነው የምንገበገበው፡፡ እኔ ላይ ሁሉ አላስፈላጊ ፋውል ተሰርቶ ቡድናችን እንዲወርድ የተደረገበት የድሬዳዋው ድራማ ግፍ እስከህይወቴ ፍፃሜ ድረስ ቁጭቱ አብሮኝ የሚኖር ነው፡፡”
…በእግር ኳስ በጣም ስለተደሰተበት አጋጣሚ…
“እግር ኳስ ብዙ የደስታ ጊዜያትን ያለስስት ሰጥታኛለች፤በመልካምነት ከማነሣቸው ውስጥ የዛሬው ቢያድግልኝ እንዲታወቅ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ምክንያት የሆነው ሲዳማ ቡና ውስጥ ያሳለፍኩት የደስታ ጊዜ የሚጠቀስ ነው፡፡ ቡድኑን ወደ ሀገሪቱ ትልቅ ሊግ ያሳለፍንበት በሊጉም ደግሞ ባሳየነው ጠንካራ ፉክክር ዋንጫ ማንሣት የሚገባው ቡድን ነው የነበረን፡፡ በወቅቱ ከአንድ እስከ 4 ያለን ቡድኖች ለዋንጫ የሚፎካከሩበት አጋጣሚ ነው የነበረው፤ ይሄ የማልረሳው የተደሰትኩበት አጋጣሚ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዋንጫ ያነሳሁበት፣ ለአፍሪካ ዋንጫ ሀገራችን ከረዥም ጊዜ በኋላ ካሳለፉት ተጨዋቾች አንድ መሆኔ በምፈልገው ደረጃና ርቀት ባይሆንም ለሀገሬ ብ/ቡድን አስተዋፅኦ ማድረጌ የእግር ኳሱ ደስታዎቼ ናቸው፡፡”
…በእግር ኳስ አተረፍኩ ስለሚለው…
“እኔ በማማረር አላምንም፤ በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ ብዙ ትርፍ አትርፌያለሁ፤ ራሴን የምደብቅ ዝምተኛ ሰው በመሆኔ ግርግር ካለበት ቦታ ርቄ በመቀመጤ ራሴን የበለጠ ህዝብ ውስጥ እንዳልከት ቢያደርገኝም የህዝብ ፍቅርን አትርፌያለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የራሴ የሆነ ንብረት እንዲኖረኝ እግር ኳስ አግዞኛል፡፡ ግን ይሄን ስል እግር ኳስ ዝም ብዬ ተቀምጬ ሣይሆን ጥሬ ግሬ ለፍቼ እንዳደረገልኝ መዘንጋትየለበትም፡፡”
…ስለ አሰለጠኑት አሰልጣኞችና ለየትኛው አሰልጣኝ የተለየ ቦታ እንዳለው…
“እኔ እድለኛ ነኝ፤ ወደ ዘጠኝ አመት በሚጠጋ የእግር ኳስ ህይወቴ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ አሰልጣኞች አሰልጥነውኛል፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን ለሁለት አሰልጣኞች በተለይ ለአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌና ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የተለየ ቦታ አለኝ፤ በጣምም ነው የማከብራቸው በጣምም ነው የማደንቃቸው፡፡ ገ/መድህንም ሰውነት ቢሻውም ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ አሰልጣኞች በመሆናቸው ለእነሱ የተለየ ቦታ አለኝ፡፡”
…አብሮት ተጣምሮ ቢጫወት የሚመርጠውና ጨዋታ የሚያቀልለት ተጨዋች…
“ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በክለብ በፕሪሚየር ሊግና በብ/ቡድን ደረጃ ተጫውታለሁ፤ በዚህ ሁሉ አመት ውስጥ ግን በጣም ይፈትነኛል ያስቸግረኛል የምለው አጥቂ አልገጠመኝም፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አስቸግሮኛል ባልልም ከሀገራችን አጥቂዎችና በድንቅ ችሎታው የማደንቀው የተለየ ቦታ የምሰጠው አጥቂ አለ፤ ሳላሀዲን ሰይድ፡፡ ሳላ በጣም ጎበዝ አጥቂ ስለመሆኑ ግን እመሰክራለሁ፡፡”
…በጣም የበዛው የዝምተኘነት ባህሪው የበለጠ ጎልቶ እንዳይወጣና እንዳይታይ ጎድቶታል ስለመባሉ…
“እውነት ነው በባህሪዬ ብዙ ከመናገር ይልቅ ዝምታን ነው የማስቀድመው፤ ይሄ የዝምተኝነት ባህሪዬ የሚነሣው ከአድኩበት አካባቢ ነው፡፡ የአደኩበት አካባቢና ማህበረሰብ በጣም በዝምታ የተረጋጋ ህይወትን የሚኖር ማህበረሰብ ያለበት ነው። አብዛኛውን ጊዜዬን በዝምታ ከሚያወራ ወንዝ ጋር ዓሳ እያጠመድኩ እንዲሁም እርሻ ውስጥ በማሳለፍ ስላደኩ ያ አብሮኝ የኖረ ይመስለኛል፤ይሄ አጋጣሚ አሁን ባለው ዝምተኝነቴ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል፤ ብዙውን ጊዜ ሰው የተሰበሰበበት ቦታ ቆሞ ማውራትን አለመድኩም፤ አሁንም ምርጫዬ ፀጥ ያለ ቦታንና በብቸኝነት ውስጥ ከራሴ ጋር ማውራትንና ሠላምን ነው የምመርጠው፡፡ ይሄ መሆኑ ሁለት አይነት አጋጣሚዎችን ፈጥሮብኛል፡፡ አንደኛው ከሰው ጋር ሳልደርስ ሠላማዊ ህይወትን እንድመራ በተረጋጋ መስመር ውስጥ እንዳልፍ ስለረዳኝ በመልካም ጎኑ ቢነሣም በሌላ ተቃራኒ መልኩ ስታየው ከሰዎች ጋር ሊኖረኝ የሚገባውን የበለጠ መቀራረብ ያንን ተከትሎም በመግባባት የማገኛቸውን እድሎች ትምህርቶች ልምዶችን አሳጥቶኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ በተለይ ችሎታዬን አውጥቼ በመጫወቱ ላይ የራሱን የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረብኝም ይሰማኛል፡፡ በአጠቃላይ ግን ዝምታኝነቴ በገንዘብ የማይተመን ሠላምን ስለሰጠኝ በመልካምነት ማየትን ነው የምመርጠው፡፡”
…ፕሮፌሽናል ተጨዋች ስለመሆን ህልሙ…
“ፕሮፌሽናል ተጨዋች የመሆን ትልቅ ህልም ነበረኝ፤ የመሀል ተከላካይ ሆኜ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ሄጄ የሞከርኩ ብቸኛ ሰው ነኝ፡፡ እንዳልኩህ ዝምተኝነቴ ከሰው ጋር ግንኙነት እንዳይኖረኝ ባይገድብኝ የተሻለ ርቀት ልጓዝ እንደምችል አስባለሁ፡፡ በእርግጠኝነት የምነግርህ ግን ተከላካይ ባልሆንና በልጅነት የጨዋታ ሚናዬ በሆነው በአማካይ (የመሀል ተጨዋችነት) ሚና ብገፍ ኖሮ ከሀገር ወጥቼ ፕሮፌሽናል ሆኜ የመጫወት እድልን አላጣም ነበር፡፡ በእኛ ሀገር ጎል የሚሆን ኳስ ስታድን ሳይሆን ጎል ስታገባ ነው በጣም የምትደነቀውና እይታ ውስጥ የምትገባው፤ ሰውም የሚያይህ፡፡ ተከላካይ ተጨዋች በመሆኔ ባልከፋም አማካይ ብሆን ልደርስበት የሚገባው ርቀት ላይ እንዲሁም የፕሮፌሽናልነት እድል እንዳይኖረኝ አድርጓል ብዬ አስባለሁ፡፡”
…ከየትኛው ቡድን ጋር ሲጫወት ጨዋታ ይቀለዋል? ወይም ጫና ይፈጠርበታል…
“እኔ እንደውም በህይወቴ በጣም ጫና የበዛበትንና ብዙ የተወራለትን ጨዋታ መጫወትን ነው የምመርጠው፤ በዚህ የተነሣ ጫና የፈጠረብኝን ጨዋታ አላስታውሰውም፡፡ ከመክበድ ይልቅ ብዙ የተወራለት ትልቅ የተባለን ጨወታ መጫወት በጣም ይቀለኛል፤ ይመቸኛል፡፡ ከባድ ቡድን ነው ትልቅ ነው ከሚባል ቡድን ጋር ስጫወት የስነ ልቦና ሚና ውስጥ ከመግባት ይልቅ በጣም ይቀለኛል፤ ስለዚህ በዚህ ደረጃ የምመርጠው የለም፡፡”
…ዘጠኝ አመታትን በእግር ኳስ ስ ለማሳለፉ…
“በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በትልቅ ክለብና ሊግ ደረጃ ዘጠኝ አመታትን በመጫወት አሳልፌያለሁ፤ አሁንም በመጫወት ላይ እገኛለሁ፡፡ከሰፈር ወጥቼ የመጀመሪያ ክለቤ ለሆነዉ አርባ ምንጭ ዳሽን፣ ብዙ ስኬትን ላገኘሁበት ለዛሬው ማንነቴ መገለጫ ለሆነው ሲዳማ ቡና፣ የተለያዩ ድሎችንና ኢንተርናሽናል ልምምዶችን ላገኘሁበት ቅ/ጊዮርጊስ ለጅማ አባቡና ለወልዲያና አሁን ደግሞ ለሊጉ መሪ ለመቐለ 70 እንደርታ የሀገሬን ባንዲራ በመወከል በመጫወት ለሀገሬ እግር ኳስ የአቅሜን ጡብ እያስቀመጥኩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በምፈልገውና ባለኝ አቅም ደረጃ እግር ኳስን ተጫውቻለሁ ለማለት ቢቸግረኝም በተሻለ ደረጃ ላይ በመገኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”
…ከዚህ በኋላ እግር ኳስን በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ለስንት አመት ለመጫወት ያስባል…
“አቅሜ እስካለ ከሌላው ተጨዋች አንሼ እስካልተገኘሁ ድረስ ከዚህ በኋላ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ በብቃት እጫወታለሁ ብዬ አስባለሁ፤ ከሰው ይልቅ ራሱ አቅሜ ይበቃሃል እስኪለኝ ድረስ እጫወታለሁ፤ አስረግጬ የምነግርህ ግን እግር ኳስን ችክ ብዬ መጫወት አልፈልግም፤ አሁን ውስጤ የሚነግረኝ ከዚህ በኋላ በወረደ ደረጃ ሣይሆን ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ እግር ኳስን ለበርካታ አመታት መጫወት የሚያስችል አቅም እንዳለኝ ነው፡፡ ከዚህ በመነሣት በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ በምርጥ ቡድን ውስጥ በምርጥ ብቃት ከዚህ በኋላ ለበርካታ አመታት መጫወት እሻለሁኝ፡፡”
…ስለቀጣይ ህልሙ…
“አሁንም እግር ኳሳዊ የሆነ ትልቅ ህልም አለኝ፤ ሀገሬን በምፈልገው ደረጃ አገልግያለሁ ብዬ ስለማላስብ ሀገሬን የማገልገል ረሃቤን ማስታገስ እፈልጋለሁ፡፡ ይሄ ትልቁ የእግር ኳስ ህልሜ ነው፡፡”
…በቀጣይስ ወደ ስልጠና ስለመግባት ያስባል…
“ዛሬ ላይ ሆኜ እንደዚህ ነው ማለት አልችልም፤ በአሰልጣኝነት ሙያ አገለግላለሁ ብዬ ያሰብኩበትን ጊዜ ባላስታውስም በእግር ኳስ ህይወቴ ከበርካታአሰልጣኞች ያገኘሁትን ልምድ አርባ ምንጭ አካባቢ ላሉ ክለብንም ሀገርንም መጥቀም የሚችሉ ልጆች ስላሉ እነሱን ባግዛቸው ግን በጣም ደስ ይለኛል፡፡ በልምድ፣ በአቅሜም በፋይናንስ ጭምር ባግዛቸው በጣም እረካለሁ፡፡ የአባባቢው ልጆች ማወቅ ያለባቸውን እንዲያውቁ እንዲማሩ ስለምፈልግ ያለኝን ማጋራት ነው ምኞቴ፡፡“
…ከባህር ማዶ ስለሚያደንቀው አሰልጣኝ…
“የሊቨርፑሉ የርገን ክሎፕ አድናቂ ነኝ፡፡”
…በአጨዋወቱ ቀልቡን ስለሳበውና ድጋፉን ስለሚሰጠው ብ/ቡድን…
“ከተጨዋቾች ከሮናልዲኒሆ ጎቾ ውጪ ጥራ ብትለኝ አይመጣልኝም፤ እኔን በድንቅ ችሎታው ምርኮኛ ያደረገኝ ብራዚላዊው ጥበበኛ ሮናልንዲሆ ጎቾ ነው፤ ለማግኘት ያደረኩት ጥረት ባይሳካም አዲስ አበባ የመጣ ጊዜ ስታዲየም ገብቼ አይቼዋለሁ፤ ለእሱ ልዩ አድናቆትና ፍቅር አለኝ፡፡ በብ/ቡድን ደረጃ ደግሞ የብራዚል ብ/ቡድንን አስቀድማለሁ፡፡”
…ስለ ግል ህይወቱና ለየት ያለ ስም ስላላት ልጁ…
“ባለትዳር ነኝ፤ ከባለቤቴ… ጋር ከዛሬ ሰባት አመት ጀምሮ ተዋደን ኖረን ከሶስት አመት በፊት በጋብቻ ተሳስረን አብረን በመኖር ገና አንድ አመት ያልሞላት ሆናልያት የምትባል ሴት ልጅ አፍርተን በደስታና በፍቅር የተሞላ ህይወትን እየመራን ነው፡፡ ባለቤቴ የይርጋለም ልጅ ናት፤ሲዳማ ቡና ስጫወት ተዋውቀን ነው ለትልቅ ቁምነገር የበቃነው፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት ስኬት የባለቤቴ ድጋፍ ቀላል አይደለም፤ በሙያዬ ከፍ እንድል ንብረት እንዳፈራ የእሷ ሚና ትልቅ ነው፡፡ ህይወቴ በደስታ እንዲሞላ ሚስትም፣ እህትም፣ እናትም ሆና ነው የምታግዘኝ በዚህ እድለኛ ነኝ፡፡”