በይስሀቅ በላይ ከለንደን
ድል ለኢትዮጵያ፤ ወርቅ ለኢትዮጵያ፤ ፍፁም የማይታመን ፤የሆነውን ሁሉ አምኖ ለመቀበል የሚክበድ፤ በምድር ላይ ያሉት ቃላቶች ሁሉ በትክክል ለመግለፅ የሚቸገሩበት አንፀባራቂ ድል፤ ትናንት ምሽት ከወርቅም በላይ በሆነችው አልማዝ ተመዘገበ። አትሌት ጥሩነሽ ዲባባም ከወርቅ የማይተናነስ የብር ሜዳሊያ በማስመዝገብ ኢትዮጵያውያኖች በለንደን ሰማይ ስር ደምቀው እንዲያበሩ አደረገች።
የ25 ዓመታ የዓለም የኦሎምፒክ ሪከርድ ባለቤት የሆነችው አልማዝ አያና ዓለምን ሁሉ ባስደመመ ፍፁም የሆነ የአጨራረስ ብቃት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገርዋ አስገኝታለች።
በለንደን በኩዊን ኤልዛቤት ኦሎምፒክ ስታዲየም በተካሄደው የ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሁለተኛ ቀን የ10ሺ ሜትር ውድድር አልማዝ አያና ከፍተኛ ፍጥነትን በያዘ የአጨራረስ ብቃት በማሸነፍዋ ውድድሩን በአካል በስታዲየም ተገኝተውና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በተከታተሉት ሁሉ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝታለች።
በተለይ በኦሎምፒክ ስታዲየም በእያንዳንዱ ዙር ከተመልካቹ ሲሰጣት የነበረው ድጋፍ ፍፁም ልዩ ነበር።በተሻለ ፍጥነት እንድታሸንፍም ረድታታል።
አልማዝ አያና የመጨረሻዎቹን 3 ኪሎሜትሮች በ8.33 በሆነ የሠዓት ፍጥነት መሮጣ ከብዙዎች አድናቆት ኦንዲጎርፍላት አድርጓል።
አስገራሚ በሆነ አጨራረስ ሌሎች ተፎካካሪዎቻን በመደረብ ከ300 ሜትር በላይ በሆነ ርቀት የ10ሺ ሜትሩን ሩጫ 30:16:32 በሆነ ሠዓት ያሸነፈችው የኦሎምፒክ ሪከርድ ባለቤትዋ አልማዝ አያና ድሉ ከእዛሬዎቹ ድሎችዋ ሁሉ የተለየ ደስታን እንደፈጠረባት ተናግራለች።
ላለፍት 11 ወራት በጉዳት ምክንያት ከውድድር ርቃ የቆየችው የኦሎምፒክ እና የአለም ዋንጫ አሸናፊዋ አትሌት አልማዝ ከድሉ በኃላ ሀትሪክ ጋዚጣና ሀትሪክ ድረ-ገፅን ጨምሮ ለንደን ለተገኙ ከመላው ዓለም ለተውጣጡ የሚዲያ አካላት የሰጠችው መግለጫ ከዚህ በታች ያለውን ይመስላል።
ድሉን በተመለከተ ስለተሰማት ስሜት …
የተለየ የደስታ ስሜት ተሰምቶኛል፤ሪዮ ኦሎምፒክ ላይ ሪከርድ ሰብሬ ያሸነፍኩት ግን እጅግ በጣም የተደሰትኩት ዛሬ ነው።
አንድ ዓመት ሙሉ በጉዳት ሰለመቆየትዋ…
ደስታዬንም ልዩ ያደረገው ይሄ ነው፤አንድ ዓመት አካባቢ ማለትም ከሪዮ ኦሎምፒክ በኃላ በጉዳት ምክንያት አንድም ውድድር አላደረኩም፤በዚህ ችግር ውስጥ ሆኜ ማሸነፌ አስደስቶኛል።
ለኦሎምፒክ ብላ ውድድር ሰለመሰረዝዋ.,.
ለለንደን ኦለም ዋንጫ ልዩ ትኩረት ነው የሰጠሁት ምክንያቱም አለም ሻምፒዮና ልዩ ታሪክ ነው።ለአለም ሻምፒዮና ብዬ ሞናኮ እና ሮም ያሉብኝን ውድድሮች የሰረዝኩትም ለዚህ ብዬ ነው በውሳኔዬም በጣም ደስተኛ ነኝ።
የለንደንን የአየር ሁኔታ በተመለከተ…
ወደ ለንደን እንደመጣን የነበረው የአየር ሁኔታ አገራችን ላይ ስንዘጋጅ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ቀዝቃዛ ላይ ሰርተን ቀዝቃዛ ላይ መሮጥ ከባድ ነበር ፤ዛሬ ግን ቀኑ በጣም ጥሩ ሰለነበር አየሩ አላስቸገረኝም።
ከኃላ ሰለሚከተላት አትሌቶችና ርቀቱን እንዴት እንደምትከታተለው …
ዕውነት ለመናገር ከኃላዬ እነማን እንዳሉ በስክሪኑ ጭምር እከታተላለሁ፤በምን ያህል ርቀት እንዳሉ ነው ማወቅ ያልቻልኩት እንጂ እከታተላቸው ነበር ።
በቀጣይ ስለምታደርገው የ5ሺሜ ሩጫን በተመለከተ …
ለውድድሩ ትንሽ ቀን አለው ከውድድሩ በፊት እንደዚህ አደርጋለሁ ባልልም ከሌሎች ጋደኞቼ ጋር በመሆን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት አደርጋለሁ።