የኢትዮጵያ ብሔራዊ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከዛምቢያ አቻቸው ጋር ነገ ቅዳሜ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደርጋሉ።
ዋልያዎቹ ኬንያ ለምታስተናግደው የ2018ቱ የቻን ዋንጫ እንዲረዳቸው ነው ከዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያካሄዱት።
የወዳጅነት ጨዋታው ነገ ቅዳሜ በዛምቢያ ሉሳካ የሚካሄድ ይሆናል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ እንደተናገሩት የወዳጅነት ጨዋታው ዋልያዎቹ ከሱዳን ጋር ላለባቸው የቻን ዋንጫ ማጣሪያ አቋማቸው የሚፈትሹበት ነው።
- ማሰታውቂያ -
በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ በአዳማ ልምምድ የሰራ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ትናንት ማለደ ወደ ስፍራው አቅንቷል፡፡
ዋልያዎቹ በያዝነው ዓመት ግንቦት ላይ ከኡጋንዳ አቻቸው ጋር ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ያለምንም ግብ መለያየታቸው አይዘነጋም።
ዋልያዎቹ የመጀመሪያ የቻን ዋንጫ ማጣሪያ ከጁቡቲ ጋር ተጫውቶ 5 ለ1 ማሸናፈቸው ይታወሳል።
በአዲስ አበባ ሊካሄድ ፕሮግራም ወጥቶለት የነበረው የመልሱ ጨዋታ የጁቡቲ ብሔራዊ ቡድን እንደማይመጣ በማሳወቁ ምክንያት ካፍ ለኢትዮጵያ ፎርፌ በመስጠቱ ኢትዮጵያ በድምር ውጤት 8ለ1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችላለች።
የሱዳን እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ ቡሩንዲን በድምር ውጤት አንድ ለ ባዶ በማሸነፍ ነው ቀጣዩን ዙር መቀላቀል የቻለው።
ነሀሴ 7 በሀዋሳ እስታዲየም ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደረጉ ይሆናል።
ኢትዮጵያና ሱዳን በሚያደርጉት ጨዋታ በድምር ውጤት አሸናፊው አገር በቀጥታ ወደ ቻን ዋንጫ አላፊ ይሆናል።
በአገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚካፈሉበት የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ውድድር በ2018 በኬንያ አስተናጋጅነት ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል።