በካሜሮን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2021 አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታውን በባህርዳር ስታድየም ያካሄዱት ዋልያዎቹ በመጀመርያ አጋማሽ ባስቆጠርዋቸው ሁለት ግቦች ታግዘው አሸንፈዋል።
ማዳጋስካርን ከገጠሙት የመጀመርያ ተሰላፊዎች ጋቶች ፓኖም እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን በታፈሰ ሰለሞን ና አዲስ ግደይ ሲቀይሩ ዝሆኖቹ በተመሳሳይ ሁለት ቅያሬዎችን አድርገዋል።ኒጀርን ካሸነፈው ስብስብ የኤስሚላኑን ፍራንክ ኬሲን በማክስዌል ኮርኔት፣ሮጀር አሳሌን በኢዩጌኔ ኮፊ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።ጨዋታው ተጀምሮ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ጨዋታው ለመግባት በሚሞክሩበት ቅጽበት ኮትዲቫሮች ግራ መስመር ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት ግራድል መትቶት ቀዋሚ ብረት ገጭቶ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው ሰርጂ ኦሬር አስቆጥሮ ዝሆኖቹን መሪ ማድረግ ችሏል።ከግቡ መቆጠር በኃላ የአብርሀም መብራህቱ ልጆች ኳሱን በሚይዙበት ጊዜ ኳሱን ከኃላ በማስጀመር ግራ መስመር ላይ ትኩረት አድርገው ተደጋጋሚ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።የዚህም ውጤት ከግቡ በቅርብ ርቀት የተገኘችውን ቅጣት ምት ሱራፋኤል ዳኛቸው በቀጥታ መትቶት በኮትዲቫር ተጨዋቾች ተጨርፎ ቀጥታ ዝሆኖቹ መርበብ ላይ አርፏል።በግባ የተነቃቁት ዋልያዎቹ የጨዋታውን ፍጥነት በመጨመር የከተማዋ አየር ሁኔታ የከበዳቸውን የኮትዲቫር ተጨዋቾችን የበለጠ አንዲዳከሙ ማድረግ ችለዋል።መሀል ላይ ከይሁን እንደሻው ና ታፈሰ ሰለሞን ጋር ጥሩ ጥምረት የነበረው ሽመልስ በቀለ በ24 ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ፍፁም ቅጣት ሳጥን ይዞት በመግባት በጥሩ አጨራረስ ኢትዮጵያ ከመመራት ተነስታ መሪ እንድትሆን ያስቻለ ወሳኝ ግብ ማስቆጠር ችልዋል።ከግቡ መቆጠር በኃላ ኮትዲቫሮች ከተከላካይ ክፍል እንዲሁም ከመሀል ክፍል ወደ መስመር በሚላኩ ረጃጅም ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም በቀላሉ በኢትዮጵያ በተከላካዩ ክፍል በቁጥጥር ስር ሲውሉ ታይቷል።በመጀመርያው አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂው አቤል ማሞን በጉዳት በምንተስኖት አሎ ለመቀየር ተገዷል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ ዋልያዎቹ ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ተቀዛቅዘው የታዩበት በተቃራኒው ኮትዲቫሮች በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩበት ሆኖ አልፏል።በተለይም ዋልያዎቹ በመጀመርያ አጋማሽ ተጫወቱበት የጨዋታ ፍጥነት በሁለተኛ አጋማሽ ላይ ተጨዋቾቹ ከኳስ ውጪ ባለው እንቅስቃሴዎቻቸው ላክ ተፅዕኖ ሲፈጥርባቸውና ለተደጋጋሚ ጉዳቶች ሲያጋልጣቸው ታይቷል።ሆኖም የዝሆኖቹ ተጨዋቾች ለማጥቃት የሞከሩበት መንገድ ያልተጠና ና ዒላማቸውን ባልጠበቁ ረጃጅም ኳሶች ስለነበር በቀላሉ በኢትዮጵያ ተከላካይ ክፍልና ግብ ጠባቂ ሲመለሱ ታይቷል።
በዚህም መሰረት ዋልያዎቹ በምድብ ማጣሪያው ሁለተኛ ጨዋታቸው የከዋክብቶች ስብስብ የሆነችውን አይቮሪኮስትን ከኃላ ተነስተው በማሸነፍ የምድቡ ሁለተኛ ደረጃነትን ኒጀርን በሰፊ የግብ ልዩነት ያሸነፈችውን ማዳጋስካርን በመከተል መያዝ ችለዋል።ቀጣይ ጨዋታቸውም ከዘጠኝ ወር በኃላ ከሜዳቸው ውጪ ከኒጀር ጋር ያደርጋሉ።