የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ(መጋቢት 15 እና 16 2010ዓ.ም) አ/አ ላይ እና በክልል ስታዲየሞች ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ጅማሬውን የሚያደርግ ይሆናል።
ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል እሁድ በብቸኝነት የሚስተናገደው የወላይታ ድቻ እና የደደቢት ጨዋታ ተጠቃሽ ነው። በዚህም ጨዋታ ላይ በቅጣት ለ3 ጨዋታዎች ከሜዳ ርቆ የነበረው ጌታነህ ከበደ ወደሜዳ የሚመለስ ይሆናል። ጌታነህ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር 13ኛ ሳምንት ላይ ክለቡ ደደቢት ጅማ አባጅፋርን አስተናግዶ 2-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ ከጨዋታ ውጪ የተጋጣሚን ተጫዋች በክርኑ በመማታት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶ የ4ጨዋታዎች ቅጣት ተጥሎበት እንደነበር የሚታወስ ነው። ሆኖም ክለቡ ደደቢት ተጫዋቹ 3ጨዋታዎች መቀጣቱን በማስታወስ አራተኛው ጨዋታ ቅጣት እንዲነሳለት ይግባኝ አስገብቶ ይግባኙ በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት በማግኘቱ ቅጣቱ ተነስቶለት ለዕሁዱ ጨዋታ የመጫወት ፈቃድ አግኝቷል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 3ጨዋታዎችን የተቀጣው ጌታነህ ከበደ ከጅማ አባጅፋሩ ኦኪኪ አፎላቢ ጋር የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት በ9 ግቦች በጋራ እየመራ ይገኛል።