THE BIG INTERVIEW WITH LOZA ABERA
The Pride Of Ethiopia in Malta
“ኢትዮጵያ በጣም ናፍቃኛለች”
“የሀገሬንም የራሴንም ስም
በማስጠራቴ ኩራት ተሰምቶኛል”
ሎዛ አበራ በተለይ ለሀትሪክ በቀጥታ በስልክ ከማልታ‘
በይስሐቅ በላይ
’Women are no less than the men’’ በእርግጥም ይህንን አባባል በተግባር ተርጉማዋለች፤ምክንያቱም ወንዶች የእግር ኳስ ተጨዋቾች ያላሳኩትን ከዱራሜ አዋራማና ገጠራማ ሜዳ የተገኘችው ሴቷ ሎዛ አበራ አሳክታዋለችና፡፡ በዚህም የመጀመሪያዋ ሴት እግር ኳስ ተጨዋች ብቻ ሳይሆን ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊ ተጨዋች የሚል የክብር ማዕረግም አሰጥቷታል፡፡
ክብርት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የኢ.ፌ.ዴ.ሬ ሴት ፕሬዚዳንት፣ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ ተመራጭ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ የመጀመሪያዋ ሴት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የመጀመሪያዋ ሴት የከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የአሁኗ ታዳጊዋ ሎዛ አበራ ደግሞ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሽናል ተጨዋች በመሆን ከነዚህ ታላላቅ ታሪክ ሰሪዎች ጀርባ ተሰልፋለች፡፡ ከዱራሜ ገጠራማና አቧራማ ሜዳ የተገኘችው ሎዛ አበራ ገና በለጋ እድሜዋ “ከሀገር ወጥቼ እጫወታለሁ” የሚለው ህልም የሚመስለው ምኞቷ ወደ እውነት ተቀይሮ ህልሟን በአውሮፓዊቷ የደሴት ሀገር ማልታ መኖር ጀምራለች፡፡
ሎዛ አበራ ወደ ደሴቲቱ ማልታ ከተጓዘች ገና የአራት ወራት እድሜን ብቻ ብታስቆጥርም ከቆይታዋ ጋር የማይመጣጠን አንፀባራቂ ስኬት በማስመዝገብ የራሷንም የሀገሯንም ስም ከፍ አድርጋ በማስጠራት ላይ ትገኛለች፡፡ በአጭር ጊዜ የማልታን እግር ኳስ በመላመድ “ለካስ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች እግር ኳስ ተጨዋቾች ለታሪክ የተፈጠሩ ናቸው” ብለው ብዙዎች በግርምት እጃቸውን በአፋቸው ላይ እንዲጭኑ በድንቅ ችሎታዋ ያስገደደችው ሎዛ አበራ በአራት ወራት የማልታ ቆይታዋ የሱፐር ካፕ ዋንጫን፣ በአንድ ጨዋታ የክለብ ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበው 7 ጎል በማስቆጠር፣ሁለት ጊዜ የወሩ ምርጥ ተጨዋችነት ክብርን በመጎናፀፍና በ19 ግቦች የማልታን ግብ አግቢዎች ፉክክርን በመምራት ስሟን በወርቅ ቀለም ማፃፏን ቀጥላለች፡፡ በማልታ ሊግም ሆነ የሴቶች እግር ኳስን ለሚከታተሉ ሁሉ ክስተት ሆና ብቅ ያለችው ኢትዮጵያዊቷ ሎዛ አበራ እያስመዘገበችው ያለችውን ድርብ ድርብርብ ታሪክን ሰምቶ ዝም የማለት አቅምን ያጣው የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዴተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የሞባይል ስልኩን አንስቶ “ሄሎ ሎዛ” በማለት ወደ ማልታ በመደወል ስኬታማዋንና ፈር ቀዳጇን ሎዛ አበራን “እንኳን ደስ አለሽ” ማለትን አስቀድሞ ይህ ሁሉ ስኬት፤ ይሄ ሁሉ የጎል ዝናብ ምንድነው?” በማለት ጠይቆ በህትመት ሚዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ የማልታ ህይወቷን ከባህር ማዶ ተጋርቶ ሊያጋራን እንግዳ አድርጎ አቅርቧታል፡፡
በማልታ ሰማይ ስር ደምቃ እያበራች ካለችው ኮከብ ከሎዛ አበራ ጋር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በነበረው ከአንድ ሰዓት የዘለለ የቀጥታ የስልክ ቆይታው የተለያዩ ጉዳዮችን አንስቶ የሰጠችውን ብስለት የተሞላበት ምላሽ ከዚህ በታች ባለው መልኩ አጠናክሮ አቅርቦታል፤ ቆይታችውን አውሱን፡፡
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- …ሄሎ…ሄሎ…ይሰማል…?
ሎዛ፡- …አዎን ይሰማል…?…ማን ልበል…?…ከየት ነው…?…
ሀትሪክ፡- …ከዚህ ከአዲስ አበባ ነው…የምደውለው…ሎዛ ነሽ…አይደል…?
ሎዛ፡- …አዎን ነኝ…?…ማን ልበል…?
ሀትሪክ፡- …ይስሀቅ በላይ እባላለሁ…የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር ነኝ… ባለፈው በቴክስት በተነጋገርነው መሠረት ወኪልሽን ሳምሶንን አስፈቅጄ ከአንቺ ጋር ቃለ-ምልልስ ለማድረግ ነበር ይሄንን ሁሉ ኪሎ ሜትር በስልክ ሞገድ አቋርጬ የምደወልልሽ…ምን አልባት ከፈቀድሽልኝና ይሁንታውን ከሰጠሽኝ ብዬ ነበር.. ሎዛ…?
ሎዛ፡- …ኦው…!…አስታውስኩህ…ምንም ችግር የለም…በጣም ደስተኛ ነኝ…
ሀትሪክ፡-…በነገራችን ላይ ሎዛ እንደዚህ በስኬት ታጅበሽ…የሀገርን ስም በከፍተኛ ሁኔታ እያሰጠራሽ ባለሽበት ወቅት ስላገኘሁሽ…ለቃለ-ምልልሱም መልካም ፍቃድሽን ስለሰጠሽኝ ከልብ አመሰግናለሁ…?
ሎዛ፡- …ኧረ.. ምንም ጣጣ የለውም…እኔም አመሰግናለሁ…ያለሁበት ድረስ ደውላችሁ ከአንባቢ ጋር ለማገናኘት ስለመረ ጣችሁኝ…አንተንም የሀትሪክ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልንም ከልብ አመሰግናለሁ…
ሀትሪክ፡- …ስላከበርሽን ክብረት ይስጥልን…እያልኩ በቀጥታ ወደ ቃለ-ምልልሱ ነው የምገባው…ሎዛ ከሀገር ቤት ወጥተሽ ወደ ማልታ ካቀናሽ ወደ አራት ወር አካባቢ ሆነሽ…ምን ናፈቀሽ…?…ምንስ በናፍቆት ገደለሽ..?
ሎዛ፡- …(ሳቅ)…ኦው…!…በጣም…በጣም የናፈቀችኝ…በናፍቆት እያሰቃየችኝ ያለችው በዋነኛነት ማን እንደሆነች ታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡- ..እኔ ምን አውቃለሁ…ሎዛዬ…አንቺው ንገሪኝ እንጂ…?
ሎዛ፡- …ሀገሬ ኢትዮጵያ ናታ…!…(ሳቅ)…ለካ ሀገርም እንደ ሰው ይናፍቃል የሚባለው እውነት ነው፤በቃ ከምነግርህ በላይ ኢትዮጵያ ሀገሬ በጣም ናፍቃኛለች…ህዝቡ፣አየሩ ሁሉም ነገርዋ በናፍቆት እያሰቃየኝ ነው፡፡ አሁን ከሀገር ቤት ከወጣሁ ወደ አራት ወር ገደማ ነው…ጊዜው አጭር ቢመስልም የኢትዮጵያ ሀገሬን ናፍቆት ግን አልቻልኩም፡፡ አየሩም ሰውም በጣም ይናፍቃል…አሁን በቃል ደረጃ ሳወራው ቀላል ይመስልሃል… ሀገርህ እንደምትናፍቅህ የምታውቀው ከሀገርህ ስትርቅ ነው፤ዕውነቴን ነው የምልህ ኢትዮጵያ በጣም ናፍቃኛለች…
ሀትሪክ፡- …በቃ…?…ሌላስ የናፈቀሽ ነገር የለም…?…ምግቡ…እንጀራው ሽሮ ወጡ፣ ስጋው…ክትፎው ቁርጡ…?
ሎዛ፡- …(ሳቅ)…አረ…በቃህ…!…ምግብማ ምግብ ነው…ሊያምርህ ይችላል እንጂ አይናፍ ቅህም፤… እኔን በናፍቆት ያሰቃየኝ ምግቡ ሣይሆን የሀገሬ ፍቅር ነው…ከምነግርህ በላይ ኢትዮጵያ በጣም ነው የናፈቀችኝ…፡፡…ከዚያ ውጪ ቤተሰቦቼ እናቴ፣አባቴ፣ እህትና ወንድሞቼ፣እጮኛዬም በጣም ናፍቀውኛል…(ሣቅ)…ከዚህ በተረፈ የምግብ ነገር እኔ ድሮም ብዙ አያስጨንቀኝም…ምክንያቱም ትሬይኒንግ ከሰራሁ ወይም ከጨዋታ በኋላ የሚመቸኝንና የሚጠቅመኝን ነው የምመገበው፤…ወደዚህ ወደ ማልታ ከመጣሁ በኋላም ሀገር ቤት የሚገኘውን አላጣሁም፡፡ ደግሞም የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ እዚህ ስላለ የኢትዮጵያ ምግብ ከፈለኩኝ ችግር የለም፡፡
ሀትሪክ፡- …ወደ ማልታ ተጉዘሽ ቢኪርካራን ከተቀላቀልሽ በኋላ ቡድንሽ 17ለ0 ሲያሸንፉ 7 ጎሎችን አስቆጥረሽ በሀገራችን እግር ኳስ አዲስ ታሪክ አፅፈሻል፤ከሀገር ውጭ በዚህ ደረጃ በማስቆጠርሽ የተሰማሽን ደስታ በትዊተር ገፅሽ ላይ እስከማስፈር ደርሰሽ ተመልክቻለሁና እስቲ ሁኔታውን ከአንደበትሽ ልስማው…?
ሎዛ፡- …እውነት ለመናገር በጣም ነው የተደሰትኩት…በሰው ሀገር ሊግ በስሜ ሰባት ጎል ማስመዝገቤና በማልታ ሊግና በክለቡ ታሪክ ውስጥ የእኔም የሀገሬም ስም በመመዝገቡ በጣም ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ፤ይሄንን ደግሞ እንዳልከው በትዊተር ገፄ ላይ ሳይቀር የደስታ ስሜቴን አስፍሬ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት እዚህ ሀገር ቤት እያለሁ በአንድ ጨዋታ ዘጠኝ ጎል ያስቆጠርኩበት የግል ሪከርድ ነው የነበረኝ…አሁን ደግሞ ከሀገር ውጭ ሰባት ጎል አስቆጥሬ የመጀመሪያ ታሪክ ሆኖ መመዝገቡ የደስታዬን መጠን ከፍተኛ አድርጎታል፤በአጠቃላይ እንደ ቡድን 17ለ0 በማሸነፋችን እኔም በግሌ 7 ጎል አስቆጥሬ በመውጣቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ..ሎዛዬ በዚህ ዙሪያ አንድ ነገር ብጠይቅሽ ቅር ይልሽ ይሆን…?
ሎዛ፡- …የምን ቅሬታ ነው…?…ደግሞስ ምን ልትጠይቀኝ ፈልገህ ነው…?
ሀትሪክ፡- …ብዙዎች ቡድንሽ 17ለ0 በማሸነፉ አንቺ ደግሞ 7 ጎል በማስቆጠርሽ ተደስተዋል፤አንዳንዶች ደግሞ በተቃራኒው የጎሉን ብዛት አይተው የማልታ ሊግን ደካማ ሊግ ነው እንዴ?ብለው እንዲያስቡ እያደረጋቸው ነው፤ይሄ ሁሉ የጎል ዝናብ ሊጉም ተጋጣሚያችሁም ደካሞች ስለሆኑ ነው እንዴ? ብዬ ብጠይቅሽ ትመልሽልኛለሽ…?
ሎዛ፡- …(እንደ መሳቅ እያለች)…አንድን ሊግ ጠንካራ ወይም ደካማ የሚያስብለው በሚገባው የግብ ብዛት ወይም በግል በሚቆጠረው ጎል ብቻ ነው እንዴ? ለእኔ አይመስለኝም…ኢትዮጵያ እያለሁ በአንድ ጨዋታ እኮ 15 ጎል ስናገባ 9 ጎል ለብቻዬ አስቆጥሬያለሁ…ያኔ ዘጠኝ ጎል ለብቻዬ በማስቆጠሬ የኢትዮጵያ ሊግ ደካማ ስለሆነ ነው አልተባለም፤ዛሬ በማልታ ሊግ ሰባት ሳገባ በዚህ መንገድ እንዴት እንደታየ አልገባኝም፡፡ የሊጉ ደካማነት ሣይሆን እንደዚህ አይነት አጋጣሚ በእግር ኳሱ ያጋጥማል፤አይደለም በሴቶች ሊግ በወንዶችም እንደዚህ አይነቱ ውጤት ያጋጥማል፡፡ በጎሉ ብዛት ሊጉን ለማሳነስ ከመሞከር ይልቅ አንድ መታየት ያለበት ነገር ሎዛ በሰው ሀገር ሊግ ይሄን በማድረግዋ ማገዝ ማበረታቱ ነው የሚጠቅመው፡፡ እኔ በሰው ሀገር ላይ አሁን ይሄን አድርጌያለሁ ይሄንን አሳይቼያለሁ…ሌላ ሊግ ላይ ደግሞ ምን ላደርግ እንደምችል መጠበቁ ይመረጣል፡፡
ሀትሪክ፡- …እስቲ አሁን ወደ ዋናው ውይይታችን እንግባ…ከዱራሜ ገጠራማና አቧራ ሜዳ የተነሣችው ሎዛ አበራ አሁን አትላንቲክን አቋርጣ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት አውሮፓዊቷ አገር ማልታ አይስላንድ ደርሳለች…አሁን ያለሽበት ደረጃ እንደምትደርሺ ያሰብሽበት ጊዜ ነበር…?
ሎዛ፡- …በእርግጥ በልጅንት አዕምሮዬ ኳስን ለእርካታ ከመጫወት በዘለለ በዚህ ደረጃ አስቤው አላውቅም፤ እንኳን ፕሮፌሽናል ሆኜ ከሀገር ወጥቼ ልጫወት ቀርቶ ክለብ፣ ገብቼ ለብ/ቡድን ተመርጬ የሚለውን እንኳን በዚያ እድሜዬ ማሰብ ቀርቶ በአዕምሮዬም ብቅ ብሎ አያውቅም፡፡ ግን እያደኩኝ ስመጣ ለዞን ምርጥ መጫወት ስጀምር አንድ ሃሣብ በውስጤ ይመላለስ እንደነበር አስታውሳለሁ፤እንደውም ትዝ ይለኛል በዞን ደረጃ በምንጫወትበት ጊዜ ትልቅ ክለብ፣ለብ/ቡድን ስለመጫወት በጣም አስብ ነበር፤በተለይ በክለብ ደረጃ ታቅፌ መጫወት ስጀምር ግን ከኢትዮጵያ ወጥቼ እንደምጫወት ለጓደኞቼ እርግጠኝነት በተሞላበት ስሜት እነግራቸው ነበር…በዚህ ጓደኞቼ በጣም ይገረሙ ነበር፡፡ …በውስጤ አንድ የማላውቀው የእርግጠኝነት ስሜት ነበር፤በጣም እያደኩ፣እየበሰልኩ ስመጣ…ከሀገሬ ሊግ ወጥቼ እንደምጫወት በጣም አወራ ነበር፤ያ ነው የሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ወደ እግር ኳስ እንድትሳቢ እንደ ሞዴል እያየሽ ያደግሽው ተፅዕኖ የፈጠረብሽ ተጨዋች ነበር…?
ሎዛ፡- …ኧ…!…ሁሌም እንደምናገረው የብራዚሊያዊቷ ማርታ በጣም አድናቂ ነኝ፤ ማርታን ማድነቅ የጀመርኩት አሁን ቪዲዮዎቻን እያየሁ ሳይሆን ያኔ ስለ እሷ የሚዘገቡትን ነገሮች በምሰማበት ጊዜ ነው፡፡ በየሚዲያው ማርታ የፊፋ ኮከብ ተጨዋች ተባለች…ማርታ ይሄን ያህል ጎል አገባች…ተሸለመች እየተባለ መዘገቡ እሷን እንዳደንቃት መነሻ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ስኬቶቿ፣በሴቶች እግር ኳስ ጎልታ መወጣትዋ እንዳደንቃት አስገድዶኛል፤በማድነቅ ብቻም አላበቃሁም የእሷ ስኬታማነት በልቤ ውስጥ “እኔም እንደ እሷ መሆን አለብኝ” የሚል መነሳሳትንም ጭሮብኛል፡፡ የእሷ አድናቂ ሆኜ ማደጌ ጎል አግቢ መሆንን እንደመኝ፣እንዳስብ አድርጎኛል።በአጭሩ ማርታን በስኬቷ በጣም ነው የማደንቃት…አሁንም ድረስ በጣም ነው የምወዳት፡፡
ሀትሪክ፡- …ከሀገር ቤት ሴት ተጨዋ ቾችስ…?
ሎዛ፡- …እነሱ ላይ እስከደረስኩበት ድረስ እነ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ፣እነ ሽታዬን፣ እነ ረሂማ ዘርጋውን እያደነኩ ነው አብሬያቸውም እጫወት የነበረው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከዚህ አንፃር የአለማችንን ምርጥ ተጨዋች ጥሪ ብልሽ ከማርታ ውጪ ሌላ አትጠሪም ማለት ነው?
ሎዛ፡- …ይቅርታ አድርግልኝና ለእኔ አሁንም ማርታ በጣም የማደንቃት የምወዳት ተጨዋች ናት፤እንደውም ለማርታ ካለኝ አድናቆትና ፍቅር የተነሣ ውስጤ ምን እንደሚያስብና እንደሚመኝ ታውቃለህ…?…ከእርሷ ጋር አብሮ ስለመጫወት፤ተስፋ አደርጋለሁ አንድ ቀን ምኞቴ እውን ሆኖ አብሬያት የመጫወት ካልሆነም በአካል አግኝቼ አድናቆቴን እንደምገልፅላት።ከማርታ በኋላ የመጡ ምርጥ ምርጥ ተጨዋቾች አሉ እንግሊዝያዊቷ ሉሲ ብሮንዝ፣የአሜሪካ ብ/ቡድን ካፔቴንና አሁን ኮከብ ተብላ የተመረጠችው ሜጋን ራፒኖ እነዚህ የአለማችን ምርጥ ተጨዋቾች ቢሆኑም ማርታ ለእኔ የተለየች ናት፡፡
ሀትሪክ፡- …አሁን የምትጫወቺበት አዲሱ ክለብሽ ቢርኪርካራ በማልታ ሊግ ምን አይነት ታሪክ አለው…?
ሎዛ፡- …እውነት ለመናገር በጣም ትልቅ ታሪክ ያለው…በማልቲስ አንደኛ ዲቪዚዮን የነገሰ ቡድን ነው፤ ቡድኑ ስምንት ጊዜ የማልቲስ አንደኛ ዲቪዚዮን ዋንጫን ያነሣ 15 ጊዜ ደግሞ ካፕ ዊነርስ የሆነ ቡድን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …በዚህ ደረጀ ስኬታማ ለሆነ ቡድን…በእግር ኳስ ብዙም ከማትታወቅ ሀገር አንቺን በፕሮፌሽናልነት ሲያስፈርሙ የነበራቸው ስሜት…እምነት የመጣላቸው ነገር እንዴት ነበር…?
ሎዛ፡- …እውነት ለመናገር መጀመሪያ ላይ በተግባር ሰርተህ እስካላሳየህ ድረስ ሰዎች 100% እምነት አይጥሉብህም…እነሱም ጋ እንደዚህ አይነት ስሜት መኖሩ አይቀሬ ነው፤ይሄ አመለካከት ለምን ኖረ ሣይሆን…ይሄንን አመለካከት በስራህ መቀየርና መስበር ያለብህ አንተ ነህ።በእርግጥ እኔ ወደ ማልታ ከመሄዴ በፊት ስለ እኔ በወኪሌ ሣምሶን በኩል በቂ መረጃ ነበራቸው፤የጨዋታ ቪዲዮቼን ሁሉ ተመልከተው ስለጠበቁኝ የበዛ ስጋት አልነበራቸውም፤የመጀመሪያ ቀን ስንገናኝ ግን ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ…
ሀትሪክ፡- …ምን አሉሽ…?
ሎዛ፡- …አሁን አንቺ የእኛ Official (ይፋዊ) ተጨዋቻችን ሆነሻል…ለክለባችን ምን ልታደርጊ አስበሻል…?…ብለው ነው የጠየቁኝ…
ሀትሪክ፡- …ምን አልሻቸው…?…ሁሉንም ነገር በእኔ ጣሉት…?
ሎዛ፡- …(በጣም ሳቅ)…እንደዛ አላል ኩም… (ሳቅ)…ለጥያቄያቸው የሰጠኋቸው መልስ የክለቡን ታሪክ፣ውጤታማነቱን ለማስጠበቅ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ነው አገር አቋርጬ የመጣሁት፤ በመጀመሪያ ክለቡን ውጤታማ አደርጋለሁ…በመቀጠል በእር ግጠኝነት የማልቲስ ሊግን በኮከብ ግብ አግቢነት ለመጨረስ ነው የማሰበው፤ከቡድኑ ጋርም አዲስ ታሪክ የማፃፍ ህልም ይዤ ነው የመጣሁት አልኳቸው፤በምላሼ በጣም ተደሰቱ…ከጨዋታ ጨዋታ እያዩኝ ሲሄዱ…በጊዜ ሂደት…አመለካከታቸው እየተቀየረ፣ እምነታቸው እየጠነከረ መጣ፤እኔም እንደማምነው…ከእነርሱም ከሚደርሰኝ ምላሽ ስረዳ ገና ስገባ የተናገርኩትን እየተገበርኩ እንደሆነ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ወደ ማልታ ካመራሽ ገና አራት ወርሽ ነው፤የአጨዋወት፣የባህል፣የቋንቋ ልዩነት ወዳለበት ሊግ መጥተሽ ብዙም ሳትቸገሪ ቶሎ የተላመድሽ ይመስለኛል… ተሳሳትኩ…?
ሎዛ፡- …ትክክል ነህ ለመላመድ ብዙም አልተቸገርኩም…፤…ይሄን በተመለከተ እኔ አንድ የማስበው ነገር…እግር ኳስ በባህሪው ሁላችንንም ቶሎ የሚያግባባን አለም አቀፋዊ ቋንቋ ነው፡፡ በእኔ እምነት እግር ኳስ በአለም ላይ ሰዎችን በቀላሉ የማግባቢያ መንገድ እንደሆነ ነው…።ማንኛውም ተጨዋች ከአፍሪካም ይምጣ ከአውሮፓ…ከአሜሪካም ይሁን ከካናዳ…በእግር ኳስ ቋንቋ በደንብ ይግባባል፡፡ ራሱን በደንብ መግለፅ ቢችልም ባይችልም እግር ኳስ በራሱ አለም አቀፋዊ ቋንቋ ስለሆነ ሰዎችን በቀላሉ ያግባባል፤እኔንም በማልታ የገጠመኝ ይሄው ነው፡፡ በዚህ በኩል ችግር ገጥሞኝ ተጨዋቾቹ ያላቸው አጨዋወት ከእኔ ጋር እንዳይግባቡ…ቡድኑንም ሊጉንም እንዳልላመድ አላደረገኝም፤በደንብ መግባባት ችለናል ብዬ ነው የማምነው፤ የእኔም አጨዋወት ለእነሱ እንዳልከበዳቸው ነው የምረዳው፡፡ ከልጆቹ ጋር በዚህ መልኩ መግባባታችን ሊጉን ቶሎ እንደለምደው አግዞኛል፤ የሚገርምህ ግን ይሄ መግባባቴና መላመዴ እግር ኳሱ ላይ ብቻ አይደለም…በአጠቃላይ ከሜዳ ውጪ ያለው ግንኙነታችንም በጣም ጥሩ እንዲሆን አድርጎታል፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ከማልታ ባህል፣በአየርና በቋንቋ በኩልስ የገጠመሽ ችግር የለም…?
ሎዛ፡- …በጣም የሚገርምህ በማልታ ምናልባት ትንሽ የፈተነኝ የከበደኝ ነገር ብዬ የማነሣው የአየር ሁኔታው ነው፡፡የማልታ የአየር ፀባይ እስክትላመደው በጣም ይፈትናል…በጣም ከባድም ነው፡፡ በተለይ ለእንደ እኔ አይነቷ ሞቃታማ የአየር ንብረት ካለበት ሀገር ለሚመጣ ሰው አየሩ ትንሽ ይፈትናል…፤…ማልታ የደሴት ሀገር ናት… አየርዋ በጣም ነፋሽማና…በጣም ቀዝቃዛ ነው…ከዚህ ውጪ ምንም የገጠመኝ ችግር የለም…አሁን አሁን…እንደውም…አየሩን እየተላመድኩት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከክለባችሁ ተጫዋቾች በጣም የምትቀራረቢውና ምስጢርሽን የምታጋሪያት ጓደኛሽ ማናት…?
ሎዛ፡- …እኔ ከሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች አሰልጣኞች ጋር በጣም ቅርብና ጥሩ የሆነ ግንኙነት ነው ያለኝ፤ በዚህ የተነሣ የተለየ ግንኙነት አለኝ ወይም በጣም የቅርብ ጓደኛዬ ናት ብዬ በተናጠል የምጠራት ጓደኛ የለችኝም…ሁሉም የክለቡ ተጨዋቾች ለእኔ ጓደኞቼ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከአንቺ ውጪ ከሌላ ሀገር የመጡ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችስ በክለቡ አሉ… ?
ሎዛ፡- …አዎን አሉ…አንድ እንግሊዛያ ዊት፣ ኮሎምቢያዊትና የሰርቢያ ዜግነት ያላቸት ተጨዋቾችም ቡድናችን ውስጥ አሉ…
ሀትሪክ፡- …አንድ ልማዳዊ አባባል አለ “…የወንድ ልጅ ደሞዙን… የሴት ልጅ እድሜዋ አይጠ የቅም…”…የሚል…እኔ ይሄንን ቀይሬው በ ቢርኪርካራ በወር ምን ያህል ሺ ዩሮ ታገኚያለሽ…ብዬ ብጠይቅሽ አጥጋቢ መልስ አገኛለሁ…?
ሎዛ፡- …(በጣም ሳቅ)…እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችን እኔ መመለስ አልችልም…አዝናለሁ…(አሁንም ሳቅ)…፤…ከእኔ ይልቅ አጥጋቢ መልስ የሚሰጥህ ወኪሌ ሳምሶን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ እኔ ምንም ስለማልልህ ባትደክም ነው የምመርጠው፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን በንፅፅር እዚህ አገር ቤት ከሚከፈልሽ ጋር የተሻለ ክፍያ ነው የሚሰጡሽ…?…በዝርዝር ባይሆን እንኳን በድፍን ንገሪኝ እስቲ…ብዬ ጥያቄዬን ብቀይረውስ…?
ሎዛ፡- …(አሁንም ሳቅ)…አንተ የሰው ደሞዝን ለማወቅ ምነው እንደዚህ ጓጓህ…?…ሆ…!…ሀገር ቤት ካለው የተሻለ ነው ወይ? ላልከው Offcourse(በትክክል) በጣም የተሻለ ነው፤እንደዛማ ባይሆን ለምን ይሄንን ሁሉ ሀገር አቋርጬ እመጣለሁ ብለህ ነው…በእርግጥም በጣም የተሻለ ነገር አለው፤ግን በዚህ ጉዳይ እኔን ተወኝና ከወኪሌ ጋር በደንብ ብታወራ ነው የምመክርህ፡፡
ሀትሪክ፡- …አሁን በማልታ የራስሽንም…የሀገርሽን ስም እያስጠራሽ…ደማቅ ታሪክ በሴቶች እግር ኳስ እያፃፍሽ ነው…፤…በዚህ እኔን ጨምሮ ብዙዎች ከወዲሁ “ጀግናችን” እያልንሽ ነው…አንቺስ ከስኬትሽ የተነሣ ራስሽን እንደ ጀግና ቆጥረሽው ወይም አስበሽው ታውቂያለሽ…?
ሎዛ፡- …በፍፁም…!…እኔ ራሴን እንደ ጀግና ሣይሆን ገና ብዙ እንደሚቀራት ሎዛ ነው የማስበው፤ገና ከፊቴ ብዙ እንደሚቀረኝ ጀግና ለመባል የሚያበቃ በጣም ብዙ ሥራ መስራት እንዳለብኝም ነው ውስጤ የሚያውቀው፡፡ ይሄ የአሁኑ ገና የመጀመሪያዬ መነሻዬ ነው፤ በሠራኋት በጣም ትንሽዬ ሥራ የምኩራራ ወይም በጣም ትልቅ ነገር ሠርቻለሁ ብዬ ራሴን እንደ ጀግና የምቆጥር፣የምኮፈስ አይነት ሰው አይደለሁም፡፡ ምክንያቱም አላማዬ ከዚህ የበለጠ በጣም ሰፊና በጣም ትልቅ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በሠራሁት ነገር ራሴን እንደ ጀግና ወይም እንደ ትልቅ ተጨዋች የምቆጥርበት ደረጃ ላይ አልደረስኩም…ገና የሚጠብቀኝ ረዥም መንገድ ስላለ ማለቴ ነው፡፡ እንደዚህ ብዬ ከማስብ ይልቅ ሎዛ የምትችለውን ከእሷ የሚጠበቀውን ለማድረግ እየሞከረች ነው የሚለውን ብቻ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …የአንቺ በዚህ ደረጃ ወጥቶ መጫወት ብቻ ሣይሆን ስኬታማ መሆን ለሌሎች ተጨዋቾች የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድነው ትያለሽ…?
ሎዛ፡- …እንደ እኔ በጣም ትልቅ መልዕክት አለው ብዬ አስባለሁ…ምክንያቱም የእኔ ወጥቶ መጫወት ኢትዮጵያዊያን ተጨዋች ለካ አቅም አላቸው ብለው ብዙዎች እንዲያስቡ ወደ ሀገራችን ልጆች ትኩረት እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል፤አሁን እኔ ጠንክሬ የምሰራው ለራሴ ብቻ አይደለም…ነገ የአኔን መንገድ ተከትለው ለሚወጡ ተጨዋቾችም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ ጥሩ ስሆን አመለካከታቸው ጥሩ ይሆናል…ስደክም ደግሞ በተቃራኒው ነው…“እኛም ልክ እንደ ሎዛ…ከሀገር አልፈን ወጥተን መጫወት እንችላለን” ብለው እንዲነሳሱ በር ይከፍታል፡፡
ሀትሪክ፡- …አንቺ ወጥተሽ እንዳየሽው…ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ወጥተው መጫ ወት የሚያስችል አቅም አላቸው…?…እውነ ተኛ ምላሽን ስጪኝ እስቲ?
ሎዛ፡- …እውነቴን ነው የምልህ በጣም አላቸው…የእድል ጉዳይና መንገዱን የማጣት ነገር ካልሆነ በስተቀር ወጥተው መጫወት የሚያስችል አቅም ያላቸው ብዙ ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች አሉ፡፡ ግን እነዚህ ተጨዋቾች ብቻቸውን የትም መድረስ አይችሉም፤ድጋፍ በጣም ያስፈልጋቸዋል። በዚህ አጋጣሚ ይሄንን ሁሉ ነገር በግል ጥረቱ ያመቻቸልኝን ወኪሌን ሳምሶን ነስሮን በጣም ነው የማመሰግነው፤ እንደ ሳምሶን ሲርነስ ሶከር ኤጀንሲ አይነት…እና የፌዴሬሽን የሙያተኞች ድጋፍ በጣም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ በኩል ማገዝ፣ርብርቦሽ ማድረግ ከተቻለ ብዙ እህቶቻችን ወጥተው ሲጫወቱ ልንመለከት እንችላለን፡፡ ከተጫዋቾች ችሎታ በተጨማሪ የዚህ አይነቱ ድጋፍና ርብርቦሽ ነው ወደሚፈልገው መንገድ የሚያደርሰው፡፡ እኔ አሁን ወጥቶ መጫወት እንደሚቻል መንገዱን አሣይቻለሁ፤ሌሎች ተጨዋቾችም ይሄን መንገድ እንዲከተሉ እንደ ወኪሌ ሣምሶን አይነት ብዙ ወኪሎች ያስፈልጉናል…ሁሉም በዚህ በኩል ካገዝን፣ከተባበርን ማሳካት ይቻላል፡፡
ሀትሪክ፡- …ከዚህ ውጪ አንድ ተጨዋች ፕሮፌሽናል መሆን ፈልጋ ምክርሽን ብትጠይቅ ምን ትመክሪያታለሽ?
ሎዛ፡- …እኔ እዚህ ደረጃ ለመድረስ የቻልኩት በዋናነት በእግዚአብሔር እርዳታ ነው፤ ከእግዚአብሔር እርዳታ ቀጥሎ ግን የግል ጥረቴ ማድረግ የምፈልገውን ለማሳካት ቁርጠኛ መሆኔ አግዞኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይሄንን በተመለከተ ለውስጤ ማድረግ መስራት እንደምችል እነግረዋለሁ፤ወጥቼ መጫወት እንደምችል ለውስጤ ስነግረው የነበረው ገና ታች እያለሁ ነው። በየትኛውም ሙያ ብትሆን ፍላጎት፣ ጥረት፣ትጋት ይቀድማል፤ማሳካት መድረስ የምትፈልገው ቦታ ለመድረስ መጀመሪያ ፍላጎት ከዚያ ጥረትና ትጋት የግድ ነው።የምንፈልገው ቦታ መድረስ እንደምንችል ቀደመን ለአዕምሮአችን መንገርና አስረግጠን ማሳመን አለብን፤መሰናክሎች፣ፈተናዎች፣ውጣ ውረዶች ቢበዙም የምንፈልገው ቦታ ለመድረስ መክፈል ያብንን መስዋዕትነት መክፈል አለብን፤አይሳካም ብለን ገና ከመነሻው መሸነፍና እጅ መስጠት የለብንም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች የሚጎድለን ይሄ ነው፤ወጥተን መጫወት እንችላለ ብለን መንገድ አንጀምርም፡፡ ከዚህ ውጪ ግን እውነት ነው የምልህ ኢትዮጵያዊያን እህቶቼ በጣም ይችላሉ…አቅሙም አላቸው፤ሁልጊዜ ግን በፍላጎትና በማድረግ ውስጥ አዕምሮአቸውን ማሰራት አለባቸው፡፡ራሣቸውን በዚህ መንገድ ዝግጁ አድርገው…ሩቅ አልመው ከሰሩ የማይሳካ ነገር እንደሌለ እኔ ራሴ ምስክር ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ..እዚህ አገር ቤት ከደደ ቢትና ከአዳማ ጋር የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አንስተሻል…ወደ ማልታም ተጉዘሽ የማልታ ሊግ የሱፐር ካፕ ድልን በማሳካት ከሀገር ውጭ ተጨማሪ የድል ታሪክ አፅፈሻል ይሄስ ምን ስሜት ፈጠረብሽ?
ሎዛ፡- …እንዳልከው ሻምፒዮን መሆን የሚያስገኘውን የላቀ ደስታ በሀገር ቤት ከደደቢትና ከአዳማ ጋር በማሳካት አጣጥሜ ቀምሻለሁ፤በእነዚህ ድሎቼ በጣም ደስተኛ ነኝ…አሁን ደግም ጉዞዬን ከሀገር ወጭም በማስቀጠል የሱፐር ካፕ ድልን ማግኘቴ የበለጠ ልዩ የደስታ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል፡፡ ከሀገር ውጭ ያገኘሁት የመጀመሪያ ዋንጫዬም ስለሆነ በእግር ኳስ ህይወቴ የተለየ ቦታ ስሰጠው እኖራለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …አሁን በማልታ የሴቶች ሊግ ክለብሽ ቢኪርካራ በደረጃው ሰንጠረዥ አናት ላይ ነው የሚገኘው…ከዚህ ውጤት በመነሣት በደደቢትና በአዳማ ያገኘሽውን የሊግ ሻምፒዮናነት ክብር ከሀገር ውጭም የምታሳኪው ይመስልሻል….?
ሎዛ፡- …ከእግዚአብሔር ጋር አዎን…!…በእርግጥ አሁን ስለ ዋንጫ ለማውራት ጊዜው ገና ቢሆንም…ምኞቴም ፍላጎቴም የማልቲስ የሴቶች ሊግ ዋንጫን ከክለቤ ጋር በማሳካት ሌላ ደማቅ ታሪክ በእግር ኳስ ህይወቴ ማፃፍ ነው ፍላጎቴ፤ደግሞም እናሳካዋለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …በኮከብ ግብ አግቢዎች የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ሎዛ አበራ የሚል ስም በመሪነት ተቀምጧል የኮከብ ግብ አግቢነት ክብሩን በማሳካትስ ሌላ ታሪክ ስለመስራትስ አታልሚም…?
ሎዛ፡- …(ሳቅ)…ለምን አላልምም…በእርግጥ ከግል ክብሬ ይልቅ የቡድኔ ውጤትን ነው የማስቀድመው…አሁን በ19 ጎሎች የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራሁ ነው…በያዝኩት መሪነት ለመጨረስና በማልታ ሊግም የራሴ የሆነ ትልቅ ታሪክ እንዲኖረኝ ነው እየጣርኩ..እየታገልኩ ያለሁት፡፡ይሄንን ታሪክ ለማፃፍ ያለኝን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …በማልታ የእረፍት ጊዜ ሲኖርሽ በምን ዘና ፈታ እያልሽ ነው የምታሳልፊው?
ሎዛ፡- …ወደ ቤተከርስቲያን በመሄድ የእግዚአብሔር ቃል በመስማት ነው የማሳልፈው፤ እዚህ ማልታ ውስጥ የኢትዮጵ ያዊያን ፕሮቴስታንት ቸርች አለ እዛ በመሄድ ለነፍሴ የሚሆን ምግብን እመገባለሁ፡፡ ከዚህ በተ ረፈ ከጓደኞቼ ጋር ወጣ ብለን ሻይ ቡና እየጠጣን ፈታ እንላለን…በጣም ከተመቸኝ ጊዜ ካገኘሁ ደግሞ ፊልም በማየት ለማሳለፍ እሞክራለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ሎዛ ከዱራሜ ገጠራማና አዋራ ሜዳ ተነስታ ማልታ ደርሳለች…፤…በቀጣይስ ህልም አለሽ…?
ሎዛ፡- …ቅድም እንዳልኩህ ነው በልጅነቴ ሳልመው ወይም አደርገዋለሁ ስለው የነበረውን በማልታ ገና ማሳካቴ፣መጀመሬ ነው…እንዳልከው ከዱራሜ ተነስቼ ለዞን፣ ለሐዋሳ፣ ለደደቢ ትና ለአዳማ እንዲሁም የሀገሬን ብ/ቡድን አገልግያለሁ… ከሀገሬ ወጥቼም ማልታ ሊግ ላይ ተጫውቻለሁ፤እነዚህ ሁሉ ነገሮች የመጀመሪያዬ እንጂ የመጨረሻ ስኬቶቼ ባለመሆ ናቸው አሁንም ህልም ማለሜን ቀጥያለሁ፡፡ እንደውም አሁን የማልመው ትላልቅ ህልሞ ችን ነው…ከዚህ ከፍ ብዬ የአለማችን ትላልቅ ሊጎች ውስጥ የመ ጫወት…የራሴን የሀገሬንም ስም የማስጠራት ትልቅ ህልም አለኝ፡፡
በአለማችን ትላልቅ ሊጎች ውሰጥ በመጫወት ራሴን መፈተን እፈልጋለሁ፤ በፈረንሣይ፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣በስውዲንና በአሜሪካ ሊጎች ውስጥ ስጫወት ራሴን የማግኘት ጉጉትና ህልም አለኝ፤ምክንያቱም እነዚህ ሊጎች በአለማችን በሴቶች እግር ኳስ በጣም የሚጠብቀው ናቸው…ስለዚህ እነዚህ ሊጎች ውስጥ ራሴን ስለማግኘት ነው ዘወትር የማስበው፡፡ ግን ይሄ ህልምና ምኞት ብቻውን የምመኘውን አያስገኝም…ስለዚህ ይሄንን ለማሳካት እጥራለሁ…አጠነክራለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ትናንት ከዱራሜ የተነሣ ው የሎዛ የእግር ኳስ ህይወት ስኬት በስኬት እንደሆነ ውጤቱ ይናገራል፤ በግል ህይወትሽ በኩልስ ተለውጠሻል…?
ሎዛ፡- …እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን አዎን በጣም ተለውጬያለሁ…ምክንያቱም ትናንት የነበርኩበት ቦታ ወይም ህይወት ላይ አይደለም አሁን ያለሁት፤በእግር ኳስ ብቻ ሣይሆን በህይወቴም በጣም ያደኩበት፣የተለወጥኩበት በአስተሳሰብም፣በአዕምሮም የተለወጥኩበት ሁኔታ ያለው፤ይሄ ደግሞ የሚቆም አይደለም ገና ይቀጥላል፡፡
ሀትሪክ፡- …እዛ የምታገኚው ስልጠና እዚህ ሀገር ካለው ስልጠና ጋር ያለው አንድነትና ልዩነት ምንድነው? የልምምድስ አሠራራችሁስ?
ሎዛ፡- …የትሬይኒነግ አሰጣጣቸው ከዚ ሀገር ጋር ብዙም ልዩነት አላየሁበትም፤ እንደ እድል ሆኖ ጥሩ ጥሩ አሰልጣኞች በሀገር ቤት አሰልጥነውኛል፡፡ ከሰለጥንኩባቸው አሰልጣኞች በመነሣት ስመዝነው ብዙም የተለየ ነገር አላየሁበትም ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሀትሪክ፡- …የልምምድ አሰራራችሁስ…?
ሎዛ፡- …የትሬይኒግ አሰራራችን በሁለት የተከፈለ ነው…በሜዳና በጅምናዚየም፤ በሣምንት አራት ቀን የሜዳ ላይ ትሬይኒንግ ነው የምንሰራው…ከዚያ ውጭ ያለውን ደግሞ ጅምናዚየም በመግባት እንሰራለን፤በሣምንት አንድ ቀን እሁድ በአብዛኛው እረፍት ይሰጠናል…ጨዋታችን ደግሞ ሁሌም ማክሰኞ ማክሰኞ ነው፡፡ በጂም በኩል ሁሉም ነገር የተሞላ ነው…የተወሰነ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ከሀገራችንን ጋር ብዙም የተለየ ነገር አላየሁም፡፡ ምናባት እግዚአብሔር ረድቶኝ ወደ ሌላ ሊግ ሄጂ ካየሁ በኋላ ልዩነት ካለ የምናወራ ነው የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- …በቢርኪርካራ በሆቴል ነው ወይስ በካምፕ ተይዛችሁ የምትሰሩት…?
ሎዛ፡- …እዛ ካምፕ ብሎ ነገር የለም…ከውጪ የመጣን ተጨዋቾች ብቻ የምንኖረው አፓርትመንት ውስጥ አንድ ላይ ነው፡፡ ከውጪ ከመጣነው ውጪ አብዛኛዎቹ ማልቲሶች የሀገሬው ዜጎች ስለሆኑ በየቤታቸው ነው የሚኖሩት፤ከውጪ የመጣን ተጨዋቾች ግን ክለቡ ያዘጋጀልን አፓርመንት አለ እዚያ ነው በአንድ ላይ የምንኖረው፡፡ በነገራችን ላይ እንደዚህ አይነት አሰራር በወንዶቹም በሴቶቹም እግር ኳስ የተለመደ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ቢኪርካራ ከቤት ውጪ ምን ምን አማልቶልሻል…?…ለምሣሌ መኪናና የመሳሰሉት ነገር…?
ሎዛ፡- …ክለቡ መኖሪያ ቤት ብቻ አይደለም የሰጠን…የሚያስፈልገንን ሁሉ አሟልቶልናል…ሁሉም ነገር ሙሉ ነው፤ መኪናን በተመለከተ በግል የሰጡኝ ነገር ባይኖርም ወደ ልምምድም ይሁን ወደ ጨዋታ ስንሄድ የተዘጋጀልን ሰርቪስ አለ…የትም ቦታ መሄድ ከፈለኩ ክለቡ እንዳልቸገር ያደርጋል፤በአጠቃላይ ሁሉም ነገር የተሟላ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከወንዶች የአንቺ የአለማችን ምርጡ ተጨዋች ማነው…?
ሎዛ፡- …በእርግጥ በአሁን ሰዓት የአለማችን ምርጥ ተጨዋች ተብለው ሁሉም ቀድሞ የሚጠራቸው ሜሲና ሮናልዶን ነው፤እኔም ለእነሱ የተለየ ቦታና ክብር ቢኖረኝም በተለየ የማደንቀው ግን የለም፡፡ እኔ ሁሉንም ተጨዋቾች በትኩረትና በንቃት ነው የምከታተለው፤ጨዋታዎችን በመከታተልም ለእኔ የሚጠቅመኝን እወስዳለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …በክለብ ደረጃስ ድጋፍሽን ያለስስት የምትሰጪው…?
ሎዛ፡- …በድጋፍ ደረጃ የሊቨርፑል ደጋፊ ነኝ፤ ግን ሊቨርፑልን ብደግፍም ማንቸስተር ሲቲ የሚጫወተው ጨዋታን መመልከት ደስ ይለኛል፤ጨዋታቸው ይስበኛል፡፡ እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነቴ እማርበታለሁ በሚል ሁሉንም ጨዋታዎች በትኩረት ነው የምከታተለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከላይ በውይይታችን ላይ ስታነሺ እጮኛሽ እንደናፈቀሽ ገልፀሽልኛል፤ ሎዛዬ ፍቅረኛ አለሽ ማለት ነው…?
ሎዛ፡ …/ሳቅ/…ምነው ተገረምክ? አዎ በጣም የምወደው በጣም…የናፈቀኝ እጮኛ አለኝ /ሳቅ/…ግን አደራ ከዚህ በላይ ብዙ እንዳትጠይቀኝ…/ሳቅ/…
ሀትሪክ፡- …በማልታ ኢትዮጵያዊያው ያኖች አሉ…?
ሎዛ፡- …በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራዊያን…ሶማሊያዊያን ሳይቀር አሉ፤ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲም ማልታ ላይ አለ፡፡
ሀትሪክ፡- ስምሽ ከፍ ብሎ ሲነሳ እንደዚህ ታሪክ ስትሰሪ ሲሰሙ ኢትዮጵያዊያን ምን ይሉሻል?
ሎዛ፡- ኢትዮጵያውያኖችም ኤርትራዊያኖ ችም ሁሉም ደስተኞች ናቸው፤ “አኮራሽን፤ጀግናችን ነሽ” በማለት በፈገግታ የተሞላ ልዩ አድናቆት ነው የሚሰጡኝ በዚህም ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖልኛልና በዚህ አጋጣሚ በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ሎዛ ለጋዜጣችን ክብር ሰጠሽ ለቃለ-ምልልሱ ስለተባበርሽን አመስግኜሽ ከመለያየታችን በፊት ቀረ የምትይው ካለ እድሉን ልስጥሽ?
ሎዛ፡- አንተም በማልታ ያገኘሁትን ድልና ስላለሁበት ሁኔታ ለአንባቢዎች ለማጋራት እዚህ ድረስ ደውለህ ስላነጋገርከኝ በጣም ነው የማመሰግንህ፤ ከዚህ በተረፈ ለእኔ እድገት የደከሙትን፣አሻራቸውን ያሳረፉትን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ የማልታ ዝውውሬ እንዲሳካ በጣም የተባበሩኝን የፌዴሬሽኑንና የአዳማን አመራሮች ከጎኔ በመሆናቸው በጣም ነው የማመሰግናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ የዚህ እድል ባለቤት እንድሆን የደከመልኝን ሳምሶንን የSirNess Soccer Agency ን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ሁላችሁንም እግዚአብሔር ይስጥልኝ፤የሀገሬን ስም በተሻለ ለማስጠራትም እጥራለሁ፡፡