በይስሐቅ በላይ
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ
የዋልያዎቹ አዲሱ አለቃ ሆኖ በይፋ ከተሾመ
ሳምንት አስቆጥሯል፡፡ የፊታችን ጳጉሜን 4
ከሴራሊዮን ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ሶስቱን
ረዳቶቹንና 34 ተጨዋቾችን ይፋ አድርጓል፡
መቀመጫውን በሐዋሳ ሮሪ ሆቴል
አድርጎ ዝግጅቱን ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በወር 125ሺህ ብር ደሞዝ የሚቆረጥለት ኢንስትራክተር
አብርሃም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመሆን
በይፋ ከተሾመ በኋላ የመጀመሪያ የሆነውን ቃለ
ምልልስ በተለይ ለሀትሪክ ሰጥቷል፡፡ የሀትሪክ
ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ
በኢትዮጵያ ሆቴል ከአሰልጣኙ ጋር በነበረው
ቆይታ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን እየወረወረ
በመሀል ሻይ በሎሚውን ፉት እያለ የ1 ሰዓት
20 ደቂቃ ቆይታ አድርጎ ኢንስትራክተር
አብርሃም መብራቱም ለቀረቡለት ኮርኳሪ
ጥያቄዎች ከዚህ በታች ያለውን አጥጋቢ
ምላሽ ሰጥቶታል፡፡ ተከታተሉት፡-
ምን ማድረግ ያስደስተዋል?
“በሰብአዊነት ተግባር ላይ መሳተፉ
በጣም ያስደስተኛል፣ በተለይ ለወገኔ ካለኝ
ላይ ቆርሼ ማካፈል ከምንም ነገር በላይ
ያስደስተኛል፡፡ ከራሴ ይልቅ ለሰዎች መኖርን
እመርጣለሁ፤ በሀገር ቤትም በተለይ በሰው
ሀገር ያሉ ወገኖቼ ተቸግረው ተርበው፣
ታርዘውና ታስረው ማየት የአዕምሮ ሠላሜን
ይነጥቀኛል፤ አይቼ ማለፍን ህሊናዬ
አይፈቅድልኝም፡፡ በተለይ በየመን በነበረኝ
ቆይታይ ሳደረገው የነበረው ይሄንኑ ነው፡፡”
ከሰብአዊነት ጋር በተያያዘ በተለይ
- ማሰታውቂያ -
በየመን ምን ምን ተግባራትን አከናውኗል?
“ይሄን ይሄን ሰርቻለሁ ብዬ
ስለራሴመናገርይከብደኛል፤ የአቅሜን
ለወገኔ ለማድረግ ግን ሞክሬያለሁ፡
፡ በዚህ በኩል በተለይ በየመን የሚገኙ
ኢትዮጵያዊያን በራሣቸው በሀገራቸው ቋንቋ
የሚማሩበትን እግር መንገድም ስለ ባህላቸው
የሚያውቁበትንና የሚማሩበትን ትምህርት
ቤት በትምህርት ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢነቴ
ከሌሎች ወገኖቼ ጋር በመሆን አሰርቻለሁ፡
፡ ከዚህ ውጪ በስደት በሰው ሀገር የሚኖር
ስደተኛ ሁሉንም ነገር የሚነግረው ለፈጣሪው
ነው፤ደስታውንም ብሶቱንም ሀዘኑንና
መከራውን ለማካፈል ደግሞ ቤተክርስቲያን
ያስፈልገዋል፡፡ እንደሚታወቀው የመን
የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚበዙባት
ሀገር እንደመሆንዋ የክርስትና እምነት
ተከታዮች አምላካቸውን የሚያመሰግኑበት
ብሶታቸውንም ልመናቸውን የሚያሰሙበት
ቤተክርስቲያን እንዲገነባ የራሣቸው የእምነት
ቦታ እንዲያገኙ የምችለው ሁሉ አድርጌያለሁ፤
በዚህም ተሳክቶልኝ ተደስቻለሁ።፡፡ ከዚህ ሁሉ
በተጨማሪ ከሙያዬ ጋር በተያያዘ የሀገሪቱን
ከፍተኛ ባለስልጠናት በማግኘበት ጊዜ
በውጤቱ በሠራሃቸው ስራዎች ተደስተው
ምን እናድርግልህ?” ብለው ሲጠይቁኝ ቪላ
ቤት ስጡኝ ከማለት ይልቅ አለአግባብ የታሰሩ
በየእስር ቤቱ የሚሰቃዩ ወገኖቼን ፍቱልኝ
በማለት ወገኖቼ ፍትህን እንዲያገኙ ነፃ
እንዲወጡ ያለውን ሁሉ አጋጣሚ በመጠቀም
አጋርነቴን ለማሳየት መሞከሬ በመልካምነት
የማነሣቸው ናቸው፡፡ እነዚህ እንግዲህ
በግልም በተናጠልም ከማደርጋቸው ተግባራት
በዘለለ የምሳተፍባቸው የሰብዓዊነት ተግባራት
ናቸው፡፡ ነፍሴም ይሄን እንዳደረግ ሁሌም
ታስገድደኛለች፡፡”
የግል ህይወቱስ ምን ይመስላል?
“እውነት ለመናገር እስከ አሁን ትዳር
መስርቼ በአንድ ጣሪያ ሥር ከትዳር አጋሬ
ጋር መኖር አልጀመርኩም፡፡ ከዚህ ይልቅ
ሙያዬ ትዳሬ ነው ብዬ ከሙያዬ ጋር ብቻ
ጋብቻ የፈፀምኩ ይመስል ሙያዬን አፍቅሬ
ኖሬያለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ እናትና
አባታችንን በሞት በመነጠቃችን ወንድም
እህቶቼን የማሳደግና የመንከባከብ ኃላፊነት
ስለነበረብኝ ወደ ኋላ ስገፋው ቆይቻለሁ፡፡
አሁን ግን ትክክለኛው ሰዓት በመሆኑ ወደ
ትዳር አለም በሚወስደው መንገድ ላይ ነኝ፡፡”
ምን አይነት መኪናስ ያሽከረክራል
“በጣም ቅንጡ የሆኑ መኪናዎች
የማሽከረክርሰው ሰው አይደሁም፤ የመን
በነበርኩበት ሰዓት የማሽከረክራት ቪታራ
መኪና ነበረች፡፡ ኳታር እያለሁ ደግሞ
የማሽከረክራት ቶዮታ ኮሮላ ናት፤ እንደሌሎች
የአውሮፓ ወይም የአረብ ሀገራት አሰልጣኞች
ፌራሪ ወይም ቤንትሌ ይነዳል ብለህ ጠብቀህ
ከሆነ አልተሳካልህም (ሣቅ)፤ እዚህም ሀገር
ቤትም ከቶዮታ ኮሮላ ጋር አልተላቀኩም፡፡
እሱን ነው የማሽከረክረው፡፡”
የምግብ ምርጫው…?
“ምግብን በተመለተ ምናልባት
የመጀመሪያ ምርጫው ክትፎ ወይም ጥሬ
ሥጋ ነው ብለህ አስበህ ከሆነ አሁንም
አልተሳካልህም፤ የእኔ የምግብ ምርጫ ብዙ
ሰው የሚያውቀው ነው፤ የፓስታ ዘሮችን ነው
በጣም የምወደውና የማስቀድመው”
ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስወጣው?
“ለሚዲያ ፍጆታ ወይም ለመናገር ሥል
ብቻ አይደለም በርካታ ገንዘብ የማወጣውና
ገንዘቤን የምጨርሰው ሰብዓዊነት ላይ
በማድረገው ተሳትፎ ነው፤ በሰብዓዊነት
ጉዳይ ላይ እጄ እሺ ስለማይለኝ ከሌሎች
ሀገሮች በበለጠ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ገንዘብ
አወጣለሁ”
አዘውትሮ የሚለብሰው?
አለባበሴ ላይ ጠንቃቃ ብቻ ሣይሆን
ወቅትን የጠበቀ ነው ማለቱ ይቀለኛል፤
አስፈላጊ በሆነ ቦታ አስፈላጊ የሆነ አለባበስን
ብጠቀምም ሸሚዝ በጅንስ መልበስን ግን
አዘወትሬ እጠቀማለሁ፡፡”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን
ስለማሰልጠን የዘመናት ህልሙ?
“የዚህችን የታላቅ ታሪክና የኩሩ ህዝብ
ባለቤት የሆነችው ሀገር የ100 ሚሊዮን ህዝብ
ውክልናን የያዘውን ብ/ቡድን ለማሰልጠን
እድል ማግኘቴ ሁለት የተለያዩ ስሜቶችን
በውስጤ ፈጥሮብኛል፤ አንደኛው ኃላፊነቱ
ከሸክም የከበደ ትልቅ ኃላፊነት ሲሆን
ሁለተኛው ደግሞ ለዚህ እድል መታጨት
ኩራትም ክብርም መሆኑ ነው፡፡ እውነት
ለመናገር የሀገሬን ብ/ቡድን ከማሰልጠን ጋር
በተያያዘ ለዘመናት በውስጤ ሲብሰለሰል
የነበረ ትልቅ ህልም ነበር፡፡ ነገር ግን ይሄ
ጥያቄ እንዲህ በፈጠነ ሁኔታ ይቀርብልኛል
ብዬ አልጠበኩም፡፡ ግን የእግዚብሔር ፈቃድ
ሆኖ ሀገሬ ለትልቅ ኃላፊነት ጠራችኝ፤ ምንም
እንኳን የየመን ብ/ቡድንን በማሰልጠን ላይ
በምገኝበት ሰዓት ቢሆንም ሀገሬ ድምጿን
ከፍ አድርጋ “ና ልጄ የሀገርህን እግር ኳስ
በሙያህ አግዝ” ብላ ስትጠራኝ ሁለት ጊዜ
ማሰብ አልፈለኩም፡፡ የሀገር ጥሪ፣ የሀገር
ፍቅር በልጦብኝ ወዲያውኑ ነው እሺታዬን
በመግለፅ የ100 ሚሊዮን ህዝብን ወክልና
የያዘውን ብ/ቡድን ተረክቤያለሁ፤ በዚህም
ደስታም፤ ኩራትም፣ ድካም ተሰምቶኛል፡፡”
ከየመን ብ/ቡድን ጋር ለመለያየት
ስለነበረው ችግርና በኳታር የኢትዮጵያ
አምባሳደር ስለሰጡት ድጋፍ?
“እንዳልኩህ
የ100 ሚሊዮን ህዝብን ውክልና የያዘን ብ/
ቡድን እንዳሰለጥን ሀገሬ ጥሪ ስታደርግልኝ
ደግሜ ማሰብ ባልፈልግም ለ10 አመት ያህል
የቆየሁበትና የቤቴ ያህል ከማያቸው የመኖች
ጋር እንዴት ነው በሠላም የምለያየው በጣም
አስጨንቆኝ እንደነበር መደበቅ አልፈልግም፡
፡ በየመን ረዥም ዓመት ያስቆጠረ ቆይታዬ
የኦሎምፒክ ብ/ቡድን በማሰልጠን በቴክኒክ
ዳይሬክትርነትና በመጨረሻም የዋናው ብ/
ቡድን አሰልጣኝነትን በመደረብ በጣም
ፍሬያማ የሚባል ሥራን ሠርቻለሁ፡
፡ በተለይ ደግም የየመን ብ/ቡድን በሀገሪቱ
እግር ኳስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኤሽያ
ዋንጫ ባለፈበት፣ ወርቃማ የእግር ኳስ
ታሪክ ባፃፈበት ወቅት ይሄ ሀገራዊ ጥሪ
መቅረቡ በሁለታችንም ወገን እንዴት ነው
የሚሆነው? የሚለው አስጨንቆን ነበር፡
፡ ምክንያቱም የነበረው ግንኙነት በቀላሉ
የሚበጠስ አልነበረም፡፡ ያን ያህል አመት
የቆየሁበትን ቤት ድንገት ጥለኸው መሄድ
የማይቻል በመሆኑ የመጨረሻውን ውሳኔዬን
ልቤ ቢያውቀውም መጨነቄ አልቀረም፡
፡ በመጨረሻ ግን የሀገር ፍቅር ስሜትና
የሀገር ጥሪ ሚዛን ደፋና ደፍሬ ነገርኳቸው፤
በየመኖች በኩል ከሀገር የሚበልጥ ነገር
እንደሌለ ያለእስረጅ ቢገባቸውም ውሳኔው
ምንም ያህል እውነትነት ያለው ቢሆንም
አምነው ለመቀበል ግን አልፈለጉም፡
፡ በውሳኔዬም ደስተኛ አልሆኑም፡፡ በዚህ
ሁኔታ ውስጥ እያለን በኳታር የኢትዮጵያ
አምባሳደር የሆኑት ክብርት አምባሳደር
መታሰቢያ ጣልቃ ገቡና “ይሄ የሀገር ጥሪ
ነው፤ የመንና ኢትዮጵያ ያላቸው ግንኙነት
ጥንታዊና ወንድማማችነትን መሠረት
ያደረገ ነው፤ ይሄንን መሠረት አድርጋችሁ
ብትለቁት መልካም ነው፡፡ ነገ ኢትዮጵያ
ውስጥ ያለ የመናዊ ሀገሩ ብትጠራው
ኢትዮጵያ የምትከለከለው ይመስላችኋል?
አትከለክለውም፤ ስለዚህ እናንተም ሀገሩ
ፈልጋዋለች ልቀቁት” በማለት ጣልቃ ገብተው
አሳመኗቸው፤ የመኖችም ልቤ ወደ ሀገር ቤት
መሸፈቱን ሲረዱ የክብርት አምባሳደርዋን
ጥያቅው አክብረው “ይቅናህ፤ መልካሙን
ሁሉ እንመኝልሃለን” ብለው ሸኙኝ ፡፡”
125 ሺህ ብር ወርሐዊ ደሞዝ ከሸክም
አይከብድም? የተሻለ ደሞዝ ስለቀረበለት ነው
የመጣው በሚል ለቀረበለት ጥያቄ…?
“… በጣም ሳቅ… የመን እያለሁ ከዚህ
በላይ ገንዘብ እሸከም ስለነበር ይከብዳል ለማለት
ይቸግረኛል፤ ቁም ነገሩም የገንዘቡ መክበድና
መቆለልም አይደለም፤ ሀገር እምነት ጥላ
መጥራትዋና ለጥሪዋም በጎ ምላሽ መስጠቱ
ላይ ነው፡፡” በየመን ብ/ቡድን ብሎ የሀገሬን
ብ/ቡድን ለማሰልጠን የመጣሁት ከሀገሬ
የሚበልጥብኝ ምንም ነገር ስለሌለና ሀገርህ
ለምታደርግልህ ጥሪ ሁለቴ ማሰብ አሰፈላጊ
ስላልሆነ ነው፡፡ በደሞዝ በኩል ከሄድን እውነት
ለመናገር የመኖች ሲከፍሉኝ ከነበረው ገንዘብ
ቀንሼ ነው ለሀገሬ ጥሪ ምላሽ የሰጠሁት፡
፡ ግልፁን ንገረኝ ካልከኝ በየመን ቆይታዬ
ከቤት፣ ከመኪና፣ ከነዳጅና ከስልክ ውጪ
በወር 5,500 የአሜሪካን ዶላር ይከፍሉኛል፡
፡ ከዚህ ውጪ ስታሸንፍ፣ ለጨዋታ ወደ
ውጪ ስትሄድ አበልና ማነቃቂያ በዶላር ነው
የሚሰጥህ፡፡ ይሄ ሁሉ ትልቅ ጥቅም ነው፡
፡ አንዳንድ ጊዜ ከሚከፈልህ ክፍያ ይልቅ
ውስጥህ ለሚጠይቅህ ጥያቄ መልስ መስጠት
ግድ ይልሃል፤ ለምንድነው የምሰራው?
ለማን ነው…. የምሰራው? የሚለውን ማየት
ትርጉም አለው፡፡ ለምንድነው የምሰራው…?
ለማን ነው…. የምሰራው የሚለውን ቁልፍ
ጥያቄ በአግባቡ በመፈተሽ ለሀገሬ እንኳን
መሰረታዊ ነገር በደሃ አቅሟ አሟልታልኝ
በነፃ ሥራ ብትለኝም መስራት አለብኝ ከሚል
ስሜት ነው ደሞዜንም ጥቅሙንም ሚዛን ላይ
ሳላስቀምጥ የወሰንኩት፡፡ እንዳልኩህ የመኖች
ብዙ ጥቅም ይሰጡኛል፤እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች
ለሀገሬ ከመስራት በላይ እውነተኛውን እርካታ
ስለማይሰጡኝ ትቼ መጥቻለሁ፤ ደግሞም
ትክክለኛ ውሳኔ ነው፡፡
ምን አይነት የቡድን ስብስብና ምን አይነት
አሰልጣኝ (ማናጀር) ለመሆን አስቧል?
“በአብዛኛው በወጣቶችና በጥቂት ልምድ
ባላቸው ተጨዋቾች የተገነባ ቡድን ለመስራት
ነው ሃሣቤ፤ ምክንያቱም ከዘላቂ ጥቅምና
ከራዕያችን አንፃር ይሄን ማዕከል ያደረገ
ቡድን ነው መገንባት የምፈልገው፡፡ ከዚህ
በተረፈ ኳስን ሣያባክን በጥንቃቄ በማጥቃትና
በመከላከል የሚጫወት ብ/ቡድን ነው
መገንባት የምፈልገው፤ ከዚህም በላይ ግን
ለረዥም ጊዜ ኳስን ብዙ ሣያባክን የሚጫወት
ውጤታማ ብ/ቡድን የሚገነባ ማናጀር መሆን
ነው የምፈልገው”
አጭር ኳስ ወይም ረዥም ኳስ
ላይ መጫወትን መሠረት ያደረገ ቡድን
እንዲኖረው ነው የሚፈልገው? የትኛው
አጨዋወት ነው ምርጫው?
“ሙሉ ለሙሉ አጭር ኳስ ላይ
መሠረት ያደረገ ወይም ረዥም ኳስን
በአብዛኛው የሚጫወት ቡድን እንዲኖረኝ
ነው የምፈልገው በማለት ለይቼ መናገር
አልችለም፤ እንደተጋጣሚያችን አጭሩንም
ረጅም ኳስንም እንደአስፈላጊነቱ የሚጫወት
ቡድን ቢኖረኝ ነው የማስበው፡፡
በአካል ብቃት ወይስ በቴክኒክ ላይ
ያተኮረ ተጨዋች? የቱ ነው ምርጫው?
“በአብዛኛው ቴክኒካሉ ላይ ስኪላቸው
ከፍተኛ የሆኑ ተጨዋቾች፤ እግር
ኳስን በአእምሯቸው ሊጫወቱ የሚችሉ
ተጨዋቾችን ነው የማስቀድመው፤ የዘመኑ
እግር ኳስም የሚጠይቀው ይሄንኑ ነው፡
፡ ይሄንን ስልህ ግን እግር ኳሱን ካለ
አካል ብቃትም ማሰብ ከባድ ነው፤ የአካል
ብቃት ስል ግን ግዝፈትን ወይም የሰማይ
ስባሪ ማከልን ማለቴ አይደለም፡፡ 90 ደቂቃ
ሳይደክሙ መጫወት የሚችሎ ወጣቶችን ነው
መያዝ የማስቀድመው… በአእምሯቸው ኳስ
ሳያባክኑ የሚጫወቱ በእኔ ብ/ቡድን ውስጥ
ቦታ አላቸው፡፡”
ከ10 ዓመት ላላነሰ ጊዜ ከሀገሪቱ እግር
ኳስና ከፕሪምየር ሊጉ በመራቁ ለሊጉም፣
ተጨዋቾቹንም አያውቃቸውም፤ ለብ/
ቡድኑ ኃላፊነት መብቃት የለበትም በሚል
ስለሚቀርብበት አስተያየት?
“ትክክል ነው፤ ከዚህ አስተያየት ጋር ፀብ
የለኝም፡፡ እንደውም አስተያየቱን ትክክል
ነው ብዬ እደግፋለሁ፡፡ በመደበኛ አሰልጣኝነት
ስራዬን የምሰራው በየመን በመሆኑ ለሀገሪቱ
ሊግ በጣም ቅርብ ነኝ የሚል ጉንጭ አልፋ
ክርክር ማድረግ አልፈልግም፡፡ እውነታው
ይሄ ቢሆንም ግን እዚህ ጋ አንድ ጥያቄ
ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት
ለብ/ቡድን ተመድበው ሲሰሩ የነበሩ የውጪ
አሰልጣኞች እኮ ብ/ቡድኑንና ሊጉን ተወውና
ሀገሪቷን እንኳን ከካርታ ውጪ የማያውቋት
ናቸው፤ እነሱ እንኳን መጥተው ሰርተዋል፡
፡ እነ ባሬቶ፣ ኤፌም ኡኑራ ወደዚህ
ከመምጣታቸው በፊት ሊጉንም ተጨዋቾቹንም
ሀገሪቷንም አያውቋትም፡፡ እኔ ወደ የመን
ከመሄዴ በፊት በሀገሬ ሊግና ብ/ቡድን ውስጥ
ሰርቻለሁ፤ ውጤትም ከሙያ ጓደኞቼ ጋር
በመሆን አስመዝግቤያለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን
በካፍ ኤሊት ኢንስትራክተርነቴ ወደ ሀገሬ
እየመጣሁ የብ/ቡድኑን አጨዋወት መነሻ
እያደረኩ የተለያዩ ስልጠናዎችን እሰጣለሁ፤
በዚህ ምክንያትም የእግር ኳሱን የዕለት ተዕለት
እንቅስቃሴ በተለያየ መንገድ እከታተላለሁ፡፡
የትኛውም ሀገር የውጪ አሰልጣኝ ሲቀጥር
አሰልጣኙ ከሀገር ውስጥ አሰልጣኞች፣
ከቴክኒክ ዳይሬክተር ጋር በመተባባር ነው
የሚሰራው፡፡ ከእኔ ጋር አብረው በኮቺንግ
ስታፍ ውስጥ የተካተቱት ረዳቶቼ ፋሲል፣
ሙሉጌታና ውብሸት በፕሪምየር ሊጉ ውስጥ
በትልቅ ክለብ ደረጃ በመስራት ላይ የሚገኙ
አሰልጣኞች ናቸው፤ እነዚህ አሰልጣኞች
ሊጉን በቅርበት ስለሚያውቁት በእኔ
የሚፈጠረውን ክፍተት በቀላሉ በቅርበት
ስለሚያውቁት በእኔ የሚፈጠረውን ክፍተት
በቀላሉ ይሞላሉ፡፡ አሁንም 34 ተጨዋቾችን
የመረጥነው ከእነሱና ከተለያዩ የሊጉ ታላላቅ
አሰልጣኞችጋር በመነጋገር ነው፡፡ በዚህ
አጋጣሚ የወቅቱ ሻምፒዮን የጅማ አሰልጣኝ
ገ/መድህን ኃይሌ፣ ውበቱ አባተ፣ ስዩም
ከበደንና ፀጋዬን በዚህ አጋጠሚ ለትብብራቸው
ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ በቀጣይ ሊጉን
እያየን ተጨዋቾችን እየፈተሽን ከተለያዩ
የስፖርት አጋሮች የሚደርሱንን ግብአቶች
በማካተት ቀዳዳውን እያጠፋን እንሄዳለን፡፡”
በረዳት አሰልጣኝነት የመረጥካቸው
አሰልጣኞች ልትረዳቸው ወይስ እንዲረዱህ?
በምንመስፈርት መረጥካቸው? በሚል
ስለቀረበለት ጥያቄ
“ትክክል ነው በተደጋጋሚ የምክትል
አሰልጣኝነት ምርጫ ላይ በጥንቃቄ
መታየት እንዳለበት ሲነገር ቆይቷል፤
ምክትል አሰልጣኝ ኮን ከመደርደር ወይም
እንዲጦር የሚመጣ አሰልጣኝ ተደርጎ
ሲቆጠር እሰማለሁ፤ አያለሁ፡፡ እነዚህን
ሶስት አሰልጣኞች አብረውኝ በረዳትነት
እንዲሰሩ የመረጥኩበት በርካታ ምክንያቶች
አሉኝ፡፡ አንደኛውና ዋናው ፋሲልም፣
ሙሉጌታና ውብሸት ሶስቱም ለፕሪምየር ሊጉ
ለተጨዋቾችም በጣም ቅርብ ናቸው፡፡ ማን?
ምንድነው? የሚለውን በቅርበት ያውቃሉ፡
፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ በክለብም፣ በብ/ቡድንም
በመጫወት፣ በማሰልጠን ትልቅ ታሪክና
ስብዕና ያላቸው አሁን ባለው ትውልድም
እንደ አርአያ እንደሞዴል የሚታዩ ናቸው፡
፡ በፕሪምየር ሊግ ውስጥ ባሉ ትላልቅ
ክለቦች ውስጥ የሰሩና ዘመናዊውን ፉትቦል
በቅርበት በመከታተል ማደግ የሚፈልጉም
ናቸው፡፡ ተጨዋቾችን ማፍራት ብቻ ሳይሆን
እንደ ኤሊት ኢንስትራክተርነቴ ለሀገሪቷ
ነገ ሊጠቅሙ የሚችሉ አሰለጣኞችን
ለረዳትነት ለመምረጥ ችያለሁ፡፡ ከእነዚህ
መሠረታዊ ምክንያቶች በመነሳት በረዳትነት
የመረጥኳቸው አሰልጣኞች የሚረዱ ሳይሆን
እኔንም ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲረዱ
የተመረጡ መሆናቸው መግለፅ እወዳለሁ…”
በሀገሪቱ ከፍተኛ የግብ ጠባቂና የአጥቂ
ችግር መኖሩ ያሰጋዋል?
“ሁላችንም የተጨዋቾች ምርጫ
ስናደርግ እንደ ትልቅ ክፍተት ያየነው
ችግር ይሄው ነው፡፡ ከ16 የሊጉ ክለቦች
10ሩ የውጪ ሀገር በረኞች ናቸው፡፡ ከቀሩት
ስድስት ግብ ጠባቂዎች ውስጥ ነው የተሻሉ
ናቸው ብለን ያመንባቸውን የመረጥናቸው፡፡
በግብ ጠባቂም በአጥቂ ላይም ጠንካራ ስራ
መስራት ያስፈልጋል፡፡ አጥቂን በተመለከተ
ብትወስድ የሀገሪቱ የግብ አግቢ ክብርን
የወሰዱትና አብዛኛውን ግቦች ያስገቡት
የውጪ አጥቂዎች ናቸው፡፡ በአጥቂ በኩል
እነሱን ተከትሎ የተሻለ ተሳትፎ አሳይተዋል
የተባሉ አጥቂዎችን በንፅፅር መርጠናል፡
፡ እነሱን በብ/ቡድን የተሻለ ስራን እንዲሰሩ
ከመደበኛው ልምምድ በተጨማሪ ልዩ
ልምድ በመስጠት ለማብቃት የምንጥር ነው
የሚሆነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ
የሀገሪቱ ችግር ስለመሆኑ ተጨማሪ ምርምር
የሚያስፈልገው አይሆንም፡፡”
ካለፉት የብ/ቡድን አሰልጣኞች ምን
ትምህርት ወስዷል…?
“ሁሉም በፊት ከነበሩት ከስኬታቸውም
ይሁን ከውድቀታቸው ከጥንካሬያቸውም
ይሁን ከድክመታቸው የሚማረው ይኖራል፡
፡ እኔም ከእነዚህ ነገሮች የምወስደው ወይም
የምማረው ብዙ ነገር አለ፡፡ ከብዙ ነገሮች
ጋር ተያይዘ የምንፈልገውን ያህል ውጤት
ማግኘት ባንችልም የአቅማቸውን ሁሉ
አድርገዋልና የሰሩትን ስራ ሁሉ አከብራለሁ፤
የተመዘገበውንም የተሰራውንም ሁሉ በፀጋ
እቀበላለሁ እነሱ ለዛሬ ስራችን ትልቅ እርሾ
ትተውናልና፡፡ በዚህ የተነሳ የምማረው ብዙ
ነገር ይኖራል፤ አሁን ያለውን ደግሞ እንደ
አዲስ ምዕራፍ የምጀምረው ይሆናል፡፡”
የኢትዮጵያ ብ/ቡድን የወቅቱ ትልቁ
ውጤት ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ
ያለፈበት ነው፡፡ ይሄንን ሪከርድ የማሻሻል
ወይም የመጋራት ሃባብ አለው…?
“የምትጠይቀኝ እንደ አሰልጣኝነቴ
ፍላጎቴን ከሆነ መልሴ አዎን ነው የሚሆነው፤
በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ሀገራችንን
ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመለሰ ትልቅ ውጤት
አለ፤ ከተሳካልኝና አምላክ ከረዳኝ ሰርቼ
ይሄንን ሪከርድ የመስበር ካልሆነም የመጋራት
ትልቅ ምኞት አለኝ፡፡ ማንኛውም አሰልጣኝ
ትልቁ ግቡ በአህጉሪቱ ውድድር ላይ መገኘት
ከመሆኑ አንፃር እንደ ፍላጎቴ የዚህን መሰል
ወርቃማ ታሪክ አካልና ከተቻለ ርቆ መሄድ
ምኞቴ ነው ብሎ ማሰብ ጤነኝነትም ነው
ለእኔ…፡፡”
የኢትዮጵያ ብ/ቡድን አሁን ትክክለኛውን
ወደ ውጤት የሚወስደውን ሰው አግኝቷል
ብሎ መናገር ይቻላል…?
“ይሄ ጥያቄ አሁን መልስ ያገኛል ብዬ
አላስብም፤ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጠው
አብርሃም ሳይሆን የመደቡኝ ሰዎችና
ውጤቱ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ትክክለኛውን ሰው
ማግኘት አለማግኘቱ ከስራ በኋላ ብናየው ነው
የምመርጠው፡፡”
ቀጣዩን የአፍሪካ ዋንጫ ያልማል?
ወይስ የማለፍ ዕድላችን ተማጧል?
“የማለፉ ዕድላችን ተሟጦ ካለቀማ
ለምን እንወዳደራለን? ለምን ገንዘብ፣ ጊዜ
እናባክናለን? ከምደባችን አላፊ የሚሆነው ቡድን
ባለመታወቁ ያለንን ዕድል እስከመጨረሻው
አሟጠን እንጠቀማለን፡፡ ለእኔ ለአፍሪካ ዋንጫ
የማለፍ ዕድሉ የተዘጋ ምዕራፍ ባለመሆኑ
ጠንክረን ሰርተን የማይቻል የሚመስለውን
ለመቻል እንሞክራለን፡፡ ለተስፋ መቁረጥ እጅ
ሰጥተን የምናደርገው ነገር አይኖርም፡፡ እግረ
መንገዳችንን ግን ሀገራችን ላይ ለሚዘጋጀው
የቻን ውድድር ጠንካራ ቡድን መስራቱ ላይ
ትኩረት ሰጥተን እንንቀሳቀሳለን፡፡”
ከተመልካች ከሚዲያ የሚሰነዘሩበትን
ሙገሳዎችና ትችቶች እንዴት ነው
የሚያስተናግደው?
“ትችትም ሙገሳም የእግር ኳስ መገ
ለጫ ባህሪዎች ናቸው… ሁለቱንም በፀጋ
እቀበላለሁ…”
ከኤርትራ ጋር ስለሚደረገው የወዳጅነት
ጨዋታ
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
ለኤርትራ አቻው የወዳጅነት ጨዋታ ጥያቄ
አቅርቧል፤ ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ
ተሰጥቶታል፤ ግን እስክንዘጋጅ ጠብቁን
ስላሉ እየጠበቅን ነው፡፡ የሁለቱ ሀገሮች
የወዳጅነት ጨዋታ ብዙ ትርጉም ያለው
ነው፡፡ የመጀመሪያው ትልቁ ከውድድር
በላይ የሆነ ሌላው የሰላም ማወጂያ የሰላም
ዋንጫ ውድድር መሆኑ ነው፡፡ ኤርትራውያን
በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይ በ3ኛው
የአፍሪካ ዋንጫ ትልቅ አስተዋፅኦ የነበራቸው
ባለውለተኞች በመሆናቸው የእነሱም ታሪክ
የሚታወስበት ሰላምን፣ ወንድማማችነትን፣
አንድነትን የሚያበስር ከወዳጅነት ጨዋታም
በላይ የሆነ ጨዋታ ነው፡፡ ሌላው ከሴራሊዮን
ጨዋታ በፊት የቡድናችንን የተጨዋቾቻችንን
መልክ ምን እንደሚመስል የምናይበት የተለየ
ቦታ የምንሰጠው ውድድር ነው፡፡
አብርሃም ሰውን ማስከፋት አይወድም፤
ሁሉንም ማስደሰት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር
የባህሪ ለውጥ የማምጣት ሀሳብ አለው?
በሚል ስለቀረበለት ጥያቄ…?
“በዚህ በኩል ምንም የማመጣው የባህሪ
ለውጥ የለም፤ አሁን የደረስኩበት ደረጃ
ያደረሰኝ አሁን ያለው ባህሪዬ ነው፡፡ አሁን
ባለኝ ባህሪዬ ፌል ያደረኩት ነገር የለም፡፡
ጉምሩክ፣ ኒያላ፣ ወንጂ፣ መድን፣ ኢትዮጵያ
ቡናና የመንም ሄጄ በኦሎምፒክና በዋናው
ብ/ቡድን ሳሰለጥን ስኬታማ ነበርኩ… ፌል
ያረኩበት ሁኔታ የለም፤ ምክንያቱም ስራዬን
በአግባቡ ስለሰራሁ ብቻ ነው፡፡ እውነት ነው
አብርሃም ሰውን ማስቀየም አይፈልግም በሚል
ተደጋግሞ የሚነሳ ነገር አለ፤ እውነት ነው፡፡
አሁንም ቢሆን ሰውን ማስቀየም አልፈልግም፤
ነገር ግን ሰውን ለማስደሰት ወይም
ላለማስቀየም ብዬ ስራዬንም እንደማልበድል
በግልፅ መታወቅ አለበት፡፡ ሰው ለማስቀየም
ብዬም ስራዬን አልበድልም፡፡”
በየመን ትልቅ ስኬትን ያገኘኸው
የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ነህ፤የየመን ስኬት
ለአፍሪካ ውድድር ወይም ለኢትዮጵያ ብ/
ቡድን የሚሰጠው የተለየ ጥቅም አለው…?
ውድድሩም አህጉሩም የተለያየ ከመሆኑ
አንፃር…?
“ጠቀሜታ የለውም አልልም፤በተለይ
እንደ አሰልጣኝነቴ ብዙ ትርፍ አግኝቼበታለሁ፡
፡ እውቀትም ልምድም ከፍተኛ የራስ
መተማመንን የእግር ኳስ ምስጢሮችን
የማገኝበትን ታላላቅ ትምህርቶችንና
መድረኮችን አስገኝቶልኛል፡፡ የሀገሬን ብ/
ቡድን ለማሰልጠን ስመጣ ባለኝ ላይ
እነዚህን ሁሉ ጨምሬ ነው፡፡ የተለየ የእግር
ኳስ ባህልና በተለይ ቻሌንጆችን እንዴት
መቋቋም እንደሚቻል በቻሌንጆች ውስጥ
እንዴት ስኬታማ ሆኖ መውጣት እንደሚቻል
ተምሬበታለሁ፡፡ ከሀገሬና ከአፍሪካ እግር ኳስ
ያገኘሁትን በማጣመር ከግል ክብር ዝናና
የተለያዩ ጥቅሞች ውጪ እነዚህን ትርፎች
አግኝቼበታለሁ፡፡ ለሀገሬም ለአፍሪካም ው
ድድር በሚስማማ መልኩ እጠቀምበታለሁ፡፡”
የኢትዮጵያ ብ/ቡድን በመያዝ ሶስተኛው
ኢንስትራክተር በመሆን ከታላላቆቹ
ኢንስትራክተሮች መንግስቱና ካሣሁን ተካ
ተርታ ስለመሰለፉ?
“ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁና
ኢንስትራክተር ካሣሁን ተካ እኔ አሁን
ለምገኝበት ደረጃ ያደረሱ የሀገር ባለውለተኞች
ናቸው፡፡ እነሱ ጋር ደርሻለው ወይም
እነሱን ተክቻለሁ ማለት ከባድ ብቻ
ሳይሆን ድፍረትም ነው፡፡ ለእኔ 2ቱም
ኢንስትራክተሮች ለቅ/ጊዮርጊስ፣ ለብ/ቡድን
የተጫወቱ ብ/ቡድኑንም ቅ/ጊዮርጊስንም
በማሰልጠን የራሳቸውን ታሪክ በደማቁ
ያፃፉ ናቸው፡፡ በኢንስትራክተርነታቸውም
በሀገር ውስጥና በውጪ ብዙ ሙያተኞችን
አፍርተዋል፡፡ በዚህ ደረጃ ያለፉን ታላላቅ
ሰዎች መተካት በእኔ አቅም ተክቻቸዋለሁ
ከማለት ይልቅ ተከትያቸዋለሁ ተከተልኳቸው
ተብሎ ቢቀመጥ ይበልጥ ሃሳቤን በትክክል
ይገልፀዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ዛሬ እዚህ
ለመድረሴ አሻራቸውን ያሳረፉብኝ በርካቶች
ናቸው፡፡ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ብ/
ቡድን ውስጥ አብረን ስንሰራ በሀገር ደረጃ
ውጤትን ያጣጣምኩት ከእሱ ጋር ነው፡፡
ዛኒዚባርና ሩዋንዳ ላይ በሀገር ደረጃ መስራትና
ውጤታማ መሆን ምን እንደሚመስል ቁልፉን
የሰጠኝ የሙያ አባቴ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ
ኢት.ቡና ውስጥ ለአንድ ዓመት ስሰራ ስዩም
አባተ የሜዳውን ምስጢር ያስተማረኝ ሰው
ነውና ትልቅ ክብር አለኝ፡፡
ከአስራት ኃይሌ ጋር አብሬው ባልሰራም
በተለያየ ጊዜ በኢንስትራክተርነት ትልቅ ደረጃ
እንድደርስ ከውጪ ሀገር ያስመጣቸውን
መፅሐፎችና የስልጠና ቪዲዮዎችን ሳይሰስት
በመስጠት በመምከር ትልቅ ድጋፍ ያደረገልኝ
የሙያ አባቴ ነው፡፡ አሁን በሕይወት ባይኖርም
የመብራት ኃይል አሰልጣኝ የነበረው ጋሽ
ሐጎስ ደስታ በእግር ኳስ ትልቅ አሰልጣኝ
መሆን ከፈለክ ከዘመኑ ጋር መሄድና ማንበብ
እንዳለብኝ ጆሮዬን ቆንጥጦ ያስተማረኝ
በመሆኑ ለእነዚህ ታላላቅ ሰዎች ምስጋና
ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡