በመሸሻ በልዴ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በግብ ጠባቂነት ሙያ ላይ በመሰማራት ድንቅና ምርጥ
ብቃታቸውን አሳይተው ካለፉ የቀድሞው ተጨዋቾች መካከል ስሙ በተለየ ሁኔታ
የሚጠቀሰውና የአሁን ሰአት ላይ ደግሞ በመድን ክለብ ውስጥ በግብ ጠባቂነት እያገለገለ
የሚገኘው በለጠ ወዳጆ የእግር ኳስን በክለብ ደረጃ ለም/ጦር፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪ፣
ለኤሌክትሪክ፣ ለሳሚት፣ ለሙገር፣ ለኢትዮጵያ መድን፣ ለኢትዮጵያ ቡና፣ ለትራንስ
ኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለረጅም አመታት ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን
በመጨረሻም ኳስን ላቆም በማልፈልግበት ሁኔታ ከኳሱ ተለይቼ ወደ አሰልጣኝነት ሙያ
ገባሁ በሚል ዛሬ ወደተሰማራበት አሰልጣኝነት ለመምጣት እንደቻለ ይናገራል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ሲጫወት የምናውቀው በለጠ በግብ
ጠባቂነቱ ብቃት ጥሩ ከመሆኑ በተጨማሪ ኳስን በእግሩም ይዞ ከተከላካዮች ጋር ተቀባብሎም
በመጫወት ይደነቅ የነበረ ሲሆን በአማካይ ስፍራም ላይ በተለይ ደ/ዘይት ላይ ይካሄድ
በነበረው የጤና ቡድኖች ውድድር ላይ የላቀ ብቃቱን ማሳየቱ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የምናውቀው በለጠ ወዳጆ ከእግር ኳሱ ሙያ ውጪ በአሁን
ሰአት ቤተሰብም መስርቶ የሚኖር ሲሆን ከባለቤቱ ወሰን ደጀኔ ያፈራቸው የ15 አመት እድሜ
ያላት ቤተልንና የ13 አመት እድሜ ያላትን ምህረትአብ በለጠ ወዳጆን ሊያፈራ ችለል፡፡
የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣም በዛሬው እትሙ ከእዚህ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጨዋች ጋር
በOldies bot Goodies አምዱ እንግዳ አድርጎት ያቀረበው ሲሆን ተጨዋቹም ምላሹን
በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡
በእግር ኳስ በጣም የተደሰትክበት ቀን፡
- ማሰታውቂያ -
– የእግር ኳስ ሕይወት ውስጥ ከፍ ያለ
ደስታ እንዳለ ሁሉ ሀዘንም ቢኖርም በእኔ
የተጨዋችነት ዘመኔ ላይ ግን ብዙውን ወቅት
ያሳለፍኩት በደስታ ነው፤ ከእነዚያ መካከል
ደግሞ ከደስታም የበለጠ ደስታ አለና ለእኔ
ከሁሉም በላይ በጣም የቦረቅኩበት ጊዜ
ቢኖር የም/ጦርና የኤሌክትሪክ ተጨዋች
በነበርኩባቸው ጊዜያቶች የአገሪቱን ትላልቅ
የሚባሉ ዋንጫዎችን በ1980 ዎቹ
የመጀመሪያዎቹ ዓመታቶች ቅዱስ ጊዮርጊስን
በማሸነፍ ያነሳንበትንና በ1990 ላይ ደግሞ
የኤሌክትሪክ ተጨዋች ሆኜ የፕሪምየር
ሊጉን ዋንጫ ያገኘሁበትን ጊዜያት በእኔ የኳስ
ሕይወት ውስጥ ምርጥ የነበረ የደስታ ወቅት
ነበርና እነዚያ የማይረሱ ናቸው፤ ሌላም
አንድ የረሳሁት የደስታም ጊዜ አለና እሱንም
ልጨምርና የጥያቄውን ምላሽ ላጠናቅቅ፤
ይኸውም በአንድ ወቅት ላይ እኔ የመድን ግብ
ጠባቂ እያለው ክለባችን ከሊጉ ላለመውረድ
ይጫወት ነበር፤ ግጥሚያችንን የምናደርገው
ደግሞ መቀሌ ላይ በአሰልጣኝ ገ/መድህን
ሃይሌ ከሚመራው ከትራንስ ኢትዮጵያ ጋር
ነበር፤ ቡድናችን ያንን ጨዋታ ከተሸነፈ
ይወርዳል፤ የወቅቱ አልቢትር መቶ አለቃ
ጥላሁን ጉደታ ነበርና እኛ ላይ ፔናሊቲ
ሰጠብን ያንን ፔናሊቲም ገርሱ ሸመና መተና
ሳተው፤ እኛ ደግሞ አንድ ግብ አስቆጥረንና
ትራንስን በማሸነፍ ከመውረድ የተረፍንበት
ጊዜ ሌላው የተደሰትኩበት ቀኔ ነው፡፡
-በእግር ኳስ በጣም ያዘነበትና ልቡ
የተሰበረበት ቀን፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ
ተጨዋች ሆነህም አሰልጣኝ ሆነህም ሽንፈት
ሲያጋጥምህ በጣም ያሳዝናል፡፡ የአንድ ወቅት
ላይ ታድያ አሁንም ድረስ እኔ ከውስጤ ፈፅሞ
በማላወጣው ሁኔታ ከደረሱብን ሽንፈቶች
መካከል በጣም ያዘንኩትና ልቤም የተሰበረበት
ቀን ቢኖር በአሰልጣኛችን ስዩም አባተ ይመራ
በነበረው ምርጡ የብሄራዊ ቡድን ውስጥ በእኔ
ስህተት በመጨረሻና ማገገም በማንችልበት
ደቂቃ ላይ በሩዋንዳዎች ግብ ተቆጥሮብን
የተሸነፍንበትና ለዋንጫ ሳናልፍ የቀረንበትን
ጨዋታ መቼም ቢሆን አልረሳውም፤
በጨዋታው በመሸነፋችን የተናደድኩትም ያ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጥሩና ምርጥ
ቡድን ስለነበር ነው፤ በጊዜው ዋንጫውን
ማንሳትም ይችል ነበር፤ የግማሽ ፍፃሜ
ጨዋታው ላይ ታዲያ በእኔ የእግር ቁጥጥር ስር
የነበረችው ኳስ ግጥሚያው ወደመጠናቀቅያው
ሰዓት ሲቃረብ ለተከላካያችን አንዋር ሲራጅ
አቀብላለሁ ብዬ ነው ኳሷ በማጠሯ በፓስ
ስህተት የእነሱ ተጨዋች ኳሷን ኢንተር
ሴፕት አድርጎ በማግኘት ሊያስቆጥራትና
ሊያሸንፉን የቻሉትና ምንም አይነት ደቂቃ
በሌለበት ሰአት ግብ ስለተቆጠረብን በጣም ነው
ላዘን የቻልኩት፡፡
–እግር ኳስ ተጨዋች ባይሆን ኖሮ በምን
ሙያ እናገኘው ነበር ፡-በሹፍርናው ሙያ
ከድሮ ጀምሮ በጣም ጎበዝ ነኝ፤ የ4ኛ መንጃ
ፈቃድም አለኝ፤ አምስተኛ እንዲኖረኝም
ጀምሬ ነው ያቆምኩት፡፡ በሙያው ኳስን
በምጫወትበት ክለብ ውስጥ ሁሉም ነው
ከቀድሞ ጊዜ አንስቶም የመንጃ ፍቃዱን
በየጊዜው አወጣም ስለነበር ኳሱን ባልጫወት
ሁሉ በእዚያ ሙያ ላይ እገኝ ነበር፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ግብ፡-ብዙዎች
የግብ ጠባቂ ስለሆንኩ ብቻ እኔ ላይ ስለተቆጠረ
ምርጥ ግብ እንጂ እንዴት ምርጥ ግብ
ሊኖረው ይችላል ብለው ጥያቄ ሊያነሱ ይችሉ
ይሆናል፤ በጣም የሚገርመው ግን በምንም
ይሁን በምን እኔ ያስቆጠርኩት ምርጥ ግብ
ግን አለኝ፡፡ ይህችም ግቤ በአንድ ወቅት ላይ
የኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ እያለሁ ከኢትዮጵያ
ንግድ ባንክ ጋር ስንጫወት ያገባኋት ምርጥና
ተደናቂ የፍፁም ቅጣት ምት ናት፤ የሁለታችን
ጨዋታ በጊዜው ወሳኝና የጥሎ ማለፍ ጨዋታ
ነበር፡፡ ያን ወቅትም ላይ በአምስት አምስት
የመለያ ምት ስንለያይ ብዙ ጊዜ የእኛ ቡድን
ውስጥ ኤልያስ ጁሀር ከሌለ የፍፁም ቅጣት
ምትን የምመታው እኔ ነኝ ያን እለትም
እንድመታ ተደርጌያለሁ ከእኔ በፊት ግን
የመምታቱ ተራው የባንኮች ሆነና የእነሱ ግብ
ጠባቂ ተስፋዬ አድማሱ /ኦስትሪች/ የፍፁም
ቅጣት ምት በመምታት የተካነ ነበርና እኛ ላይ
መትቶ አስቆጠረ ያኔም እኔ ፊሽካ ሳይነፋ ነው
የመታው የሚል ነገርን በመናገሬና ዳኛውም
ያንን ስላወቀ ምቱ እንዲደገም በማስደረግ
ያንን ኳስ እኔ አዳንኩት፤ የመምታቱም ተራ
የእኔ ሆኖና ምርጥ ግብ በማስቆጠር ቡድኔን
ለአሸናፊነት አበቃሁትና እሷን ግቤን በጣም
አደንቃታለሁ፡፡
–በጨዋታ ዘመኑ የተቆጠረበት ምርጥ
ግብ፡- አዎን፤ አለች፡፡ የግብ ጠባቂ እስከሆንክ
ድረስ ምርጥ ግብ ይቆጠርብካል፡፡ እኔም ላይ
እስከዛሬ ከገቡብኝ ግቦች ውስጥ በምርጥነቷ
ቀዳሚውን ቦታ የምሰጣትና እኔ ላይ ተቆጥራ
አቻ የማላገኝለት ግብ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር
እየተጫወትን ሳለ ጳውሎስ ጌታቸው /ማንጎ/
ያስቆጠረብኝን ነው፤ ግቧ ምርጥ ስለነበረችም
ለግቧ አድናቆት በመስጠትና በመገረምም
ለማጨብጨብ ችያለሁ፡፡ በወቅቱ ታድያ
ማጨብጨቤን ተንተርሶም ግቡ የተቆጠረበት
ሁኔታ አውቆ ነው በሚል በሌላ ነገር
ሊተረጎምብኝም ችሏል፡፡
–በተጨዋችነት ዘመኑ የተሻለ ቦታ
የሚሰጠው ምርጥ ጨዋታ፡-የእኔ የእግር
ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ምርጥ ጨዋታ
ብዬ የምጠቅሰው ም/ጦር ውስጥ በነበረኩበት
ሰአት ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር
ያደረግናቸውን ግጥሚያዎች በሙሉ ነው
ሁሌም ከእነሱ ጋር ስንጫወት እኛም እነሱም
በብዙ ደጋፊዎቻችን ታጅበን የምናደርገው
ጨዋታ ስለሆነ የድጋፍ ድምቀቱ እንደዚሁም
እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ አንዳችን
በአንዳችን ላለመሸነፍና ጨዋታውንም በድል
ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት የምናደርግበት
ጨዋታ ስለነበር እነዚያን ጨዋታዎች
ሁሉም ስሜቴን የሚገዙ ናቸውና ምንጊዜም
ሳደንቃቸው እኖራለሁ፡፡
-የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ አሰልጣኝ፡- ብዙ
ጥሩ ጥሩ አሰልጣኞች ቢኖሩም ለእኔ ግን
እነዚህ ሶስቱን በልዩ ቦታ ነው የማስቀምጣቸው
እነሱም ኢንስትራከተር ካሳሁን ተካ፣ አሰልጣኝ
ስዩም አባተና ነፍሳቸውን ይማረው ማስተር
ቴክኒሽያን ሀጎስ ደስታ በሚሰጡት ስልጠና
በሚሰሩት ቡድንና የተጨዋችን የብቃት ደረጃ
በሚገባ በማወቅ በልዩ ሁኔታ ሙያውን
የተካኑ ናቸውና ለእነሱ የምርጥነቱን ቅድሚያ
እሰጣለሁ፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ተጨዋች፡
–በእኛ ጊዜ ብዙ ናቸው፤ ማንን ጠርተህ
ማንን ትተዋለህ እከሌም ለማለት ትቸገራለህ፡
፡ አስብው እስኪ ሙሉጌታ ከበደ፣ ሚሊዮን
በጋሻው፣ሙሉአለም እጅጉ፣ ነፍሱ ይማረው
ታሪኩ መንጀታ፣ ካሳዬ አራጌ፣ ኤልያስ
ጁሀር፣ አሰግድ ተስፋዬ እያልክ ትቀጥላለህ፡
፡ ኸረ ሌላም ብዙ አሉ ግን የግድ አንድ
ተጨዋች ጥራ የሚል ጥያቄ ብቻ ከቀረበልኝ
ሙልጌታ ከበደ ለየት የሚል ተጨዋች ነው፡፡
-በጨዋታ ዘመኑ ያስቸገረው ተጨዋች፡
– የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በግብ
ጠባቂነት ስጫወት ብዙ ጊዜ እኔን እንዳልቸገር
የሚያደርጉኝ ምርጥ ተከላካዮች በም/
ጦር በነበርኩበት ሰአት እነ ደረጄ በላይ፣
ዘውዱ /ማሙዬ/ እና በሃይሉን የመሳሰሉት
በኤሌክትሪክ ደግሞ እነ ተስፋዬ ታደሰ /
ተስፊቲ/ ሲሳይ ተሰማ፣ መስፍን /ፒስ/
የመሳሰሉ ተጨዋቾች ስላሉ ያንን ያህል በጎላ
መልኩ የሚያስቸግረኝ ተጨዋች ባይገጥመኝም
የኤሌክትሪክ ክለብ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ግን
የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አሰግድ ተስፋዩ
ነፍሱ ይማረውና ኳስን ባላሰብኩበት ሰአት
ላይ ግብ ያገባብኝ ስለነበር ለእኔ እሱ ነው
ያስቸገረኝ፤ ሌላው ኤልያስ ጁሃር የአንድ
ቡድን ተጨዋች ስለነበርን ሌሎችን ያስቸግር
እንጂ እኔን ብዙ አያስቸግረኝም ምንአልባት
የእኛ ተቃራኒ ቢሆን ግን ያስቸግረኝ ነበር፡፡
–በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ አብሮት
ባለመጫወቱ የሚቆጨው፡-ይኖራል ብለህ ነው
ብዙዎቹን በክለብ ደረጃ፣ በአዲስ አበባ ምርጥና
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አብሬያቸው
ልጫወት ችያለሁና አልተጫወትኩም ብዬ
የምቆጭበት ተጨዋች ማንም የለም፡፡
–በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ማየትና
መስማት የማይፈልገው፡-የአዲስ አበባ
ስቴድየም ላይም ሆነ በሌሎች የክልል
ከተማ ሜዳዎች ላይ አንድአንድ የስፖርት
አፍቃሪዎች የተጨዋቾችን ስም እየተጣሩ
የሚሳደቡበትን ሁኔታ እንደዚሁም ደግሞ
የአንድ ክለብ ደጋፊዎች ከሌላው ክለብ
ደጋፊዎች ጋር መሸናነፍ ያለና የሚኖር ሆኖ
ሳለ እርስ በርስ ያለምክንያት ሲጣሉና አጓጉል
ስድቦችንም ሲሰዳደቡ መስማት እንደዚሁም
ደግሞ የእግር ኳስ ተጨዋቾችም የዳኝነት
ውሳኔን አምኖ ካለመቀበል ደጋፊዎችን ለፀብ
የሚያነሳሱበት ድርጊቶችን ሲፈፅሙ እንደ
አሰልጣኝነቴ ቦታው ላይ ሆኜ ማየትንም
መስማትንም ፈፅሞ አልፈልግም እዚያ ቦታ
ላይ ጥሩ ነገርን መመልከትም ብቻ ነው
የምፈልገው፡፡
–በለጠ ወዳጆ ራሱን በ3 በተመረጡ
ቃላቶት ሲገልፅ፡-ስለራሴ ከምናገር ሌሎች
ሰዎች ስለእኔ ብዙ ቢሉ ብመርጥም በል
ከተባልኩ ግን ዝምተኛ ነኝ፣ ማድመጥን
እፈልጋለሁ፣ መናገር ያለብኝን በግልፅና ፊት
ለፊት እናገራለሁ፡፡
–በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ይመራ በነበረው
የ1995ቱ የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ
ላይ የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ እያለህ
ስለተቆጠረብህ ተደጋጋሚ ግቦችና ግቦቹ
የተቆጠሩበት መንገድ ቡና ከሚከተለው
የጨዋታ ፍልስፍና ጋር የተያያዘ ነው ስለ
መባሉ፡- የኢትዮጵያ ቡና ክለብን በካሳዬ
አራጌ አሰልጣኝነት ተጠርቼ ስኳዱን ስቀላቀል
እንሰራ የነበረው ልምምድ ጥሩና ያማረም
ነበር፤ ኳስን መሰረት ያደረገም እንቅስቃሴም
ነበር እንከተል የነበረው፤ ሆኖም ግን እኔ
በአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ጨዋታ ላይ
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት 5-0 ልንሸነፍ
ብንችልም በቡድናችን ላይ የተቆጠረብን ግብን
ግን ከጨዋታው ታክቲክ ጋር በማያያዝ
የሽንፈቱ ምክንያት ያ እንደሆነ አስበው
የሚናገሩ ሰዎች ካሉ ያ ስህተት ነው፤ የቅዱስ
ጊዮርጊስ ክለብ ያንን ጨዋታ ያሸነፈን
የእግር ኳስ ላይ በሚያጋጥም አይነት ሽንፈት
ነው፤ ከእዚያ ውጪ የሆነ እንቅስቃሴንም
ብንከተል እኮ ኳስ ነውና ሊያሸንፉን ይችላሉ፤
እኛም በጨዋታው ብናሸንፍ እኮ ብዙ
ሊባልልን እንደሚችል እናውቀውም ነበርና
አባባሉን ፈፅሞ አልቀበለውም፤ በእግር
ኳሱ ዓለም እኮ ብዙ ነገርን ተመልክተናል
ብራዚል ራሷ ባስተናገደችው የአለም ዋንጫ
ጀርመንን ገጥማ 7 ግብ ተቆጥሮባት መሸነፏ
ይታወሳል፤ እንማንቸስተር ሲቲ የመሳሰሉ
ክለቦችም በርካታ ግቦች በተጋጣሚያቸው
ላይ አስቆጥረው ሲያሸንፉም አይተናልና
የእኛን ሽንፈት ያኔ ካሳዬ አራጌ ከሚከተለው
አጨዋወት ጋር እኔ ፈፅም አላገናኘሁም
በወቅቱ እንደውም ብዙ የእሱ አጨዋወት
ተቃራኒ ሆነውና አጨዋወቱንም በመጥፎ
ጎኑ በማሰብ የማይደግፉ የነበሩ አሰልጣኞችና
የሰዎችም አመለካከት ስለነበር ያ የጨዋታ
ፍልስፍና ከጅማሬው አኳያ ሌሎች
ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ሆኖ ሳለ ሊበረታታ
ሲገባው መወገዙ ተገቢም አልነበረምና እኛ
ያኔ የተሸነፍነው በእግር ኳሱ በሚያጋጥም
አይነት ሁኔታ ነው፡፡
-ከኢትዮጵያ ቡና ለመልቀቁ የዚያ
ጨዋታ ሽንፈት ምክንያት ነው ስለመባሉ፡
-የኢትዮጵያ ቡና ክለብን በ1995ቱ የክረምት
ወራት የዝውውር መስኮት በመቀላቀል
ከደብረ ዘይቱ የዝግጅት ጊዜ አንስቶ ክለቡ
ውስጥ በአጠቃላይ የቆየሁት ለ3 ወር
ለሚደርስ ጊዜ ነው፤ የአሸናፊዎች አሸናፊ
ጨዋታ ላይም ከተሳተፍኩ በኋላም ለተወሰነ
ጊዜም ቆይቼ ነበር ሆኖም ግን በቅዱስ
ጊዮርጊስ ከተሸነፍን በኋላ የክለቡ አስተዳደርና
አመራሮች ጋር ያሉት ሁኔታዎች ከእግር
ኳሱ መርህ ጋር አብረው የማይሄዱና በተለይ
ደግሞ ብዙ ክለቦችም ጋር ስጫወት ያየሁት
ስለሆነ ለሲኒየር /ነባር/ ተጨዋቾች ያለው
አመለካከት ያንን ያህል ስለሆነ ብቻም ነው
ከክለቡ እንድለቅ የተደረግኩት እንጂ በእዚያ
ጨዋታ ሽንፈት አይደለም እኔ ከቡና እንድለቅ
የተደረግኩት፡፡
–በእግር ኳስ ጨዋታ አጥብቆ የሚጠላው፡
-የእግር ኳስ ውስጥ ተጨዋችም ሆንኩ
አሰልጣኝ መቀበል ባትችል በጣም እንኳን
የሚያስጠላው ነገር ሽንፈት ነው ያንን
የሚወድ ሰውም አይኖርም፡፡
–እግር ኳስ ተጨዋች ሆኖ በማለፉ ምን
ትርፍ አግኝቷል፡-ከህዝብ የተገኘ ፍቅርንና
እውቅናን በዋናነት አግኝቻለሁ፤ በእዚያ
ሙያ ባልሰማራ ኖሮ ዛሬ እኔን ማን ያቀኝ
ነበር? እናንተስ ስላወቃችሁኝ አይደለም
አስታውሳችሁ የእኔን የእግር ኳስ ህይወት
አስመልክቶ ቃለ-ምልልስ የሰራችሁኝ
ስለዚህም የእግር ኳስ ዋናው ትርፉ ይሄ
ነውና ያንን እድል በማገኘቴ በጣም ነው ደስ
ያለኝ፡፡
–በእግር ኳሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈለው
ትልቁ ደመወዝ፡-የም/ጦር ተጨዋች እያለው
ያገኘሁት የኪስ ገንዘብ ነበር የምንለው 20
ብር ነበር፤ አንድ አንዴም ከኪስ ገንዘቡ
ተጨምሮም እስከ 50 ብር ይሰጠንም ነበርና
ያንን ብር መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡
–አሁን የአንድ ተጨዋች ደመወዝ በወር
166 ሺህ ብር አካባቢ ደርሷል፤ ይሄንን
ደመወዝ ከእሱ ዘመን ጋር አነፃፅሮ ምነው
በዚህ ዘመን ተጨዋች በሆንኩ ይላል?፡
-በፍፁም እንደዚያ ብዬም ፈፅሞ አስቤም
አላውቅም ምክንያቱም እዚህ ምድር ላይ
ስትኖር ህይወት አለ እኮ ፈጣሪ እስከፈቀደልህ
ድረስ ወይ ትኖራለህ ወይ ታልፋለህ የአሁኑ
ጊዜ እግር ኳስ ተጨዋቾች እኮ ያንን ያህል
ክፍያ እያገኙ ያሉት አንዱ የኳስ ሂደት
ስለሆነ ነውና ክፍያውን ማግኘታቸው ጥሩ
ነው፤ ይገባቸዋልም፤ የእግር ኳሱ ላይ ከእኛ
በፊትም የነበሩት ኳስ ተጨዋቾች እኮ ከነፃ
አገልግሎት ጀምሮ የተጫወቱበት አጋጣሚ
ነበር፡፡ ወደፊት የሚመጣው ትውልድ ደግሞ
ከአሁኑ የበለጠ ክፍያ ማግኘቱም አይቀሬ ነውና
ያንን አድንቀን በመቀበል ግን ልናስተላልፈው
የምንፈልገው መልዕክትም ሊኖር ይገባል፡
፡ የእግር ኳስ ተጨዋቹ ለሚከፈለው ክፍያ
መጫወቱ እንጀራው እስከሆነ ድረስ ጠንክሮ
በመስራት ለሙያውም ሆነ ለክለቡ ብሎም
ለአገሩ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ሁሉ በመክፈል
ጥሩና አበረታች የሆነ ብቃቱን በሜዳ ላይ
ሊያሳይ ይገባዋል፡፡ ለስራው ክብርም ሊሰጥ
ይገባል፡፡ የአገሪቱ አሰልጣኞችም ቢሆኑ
በደሞዝ ክፍያው አሁን ጥሩ ተጠቃሚ
ስለሆኑም በእውነት ላይ ተመርኩዘው
በመስራት በሙያው ራሳችንን ለማሳደግና
በመማርም እውቀታችንን ልናሳድግና የሀገሪቱ
እግር ኳስ ከፍ እንዲል ብዙ ልንሰራ ይገባናልና
እኛ ጥሩ ስንሆንም ነው ተጨዋቾቹም የበለጠ
ጥሩ የሚሆኑትና እዚያ ላይ ትኩረት ተደርጎ
ሊሰራበት ይገባል፡፡
-የእግር ኳስ ተጨዋች ሆኖ በማለፉ
ስለሚሰማው ስሜት፡-በጣም ደስተኛ ሆኜ
ነው ያለፍኩት፤ ኳስን እኮ ገና ስትጫወትባት
ጀምሮ ነው ስሜቷን የምታውቀው፤ ልጅ ሆኜ
ስፈጠር በኳሱ እዚህ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ
ብዬ ሳይሆን መጫወት የጀምርኩት በኳሱ
ለመርካትም ስል ነውና ኳስ ተጨዋች ልሆን
መቻሌን በጣም ነው የወደድኩት፡፡
–የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ላይ
እሰር ቤት ገብተሃል ስለመባሉ፡-አዎን፤
የም/ጦር ተጨዋች እያለሁ በተደጋጋሚ
እስር ቤት ገብቼ የታሰርኩበት አጋጣሚ
አለ፤ የታሰርኩትም በእዚያን ወቅት ኳስን
እጫወት በነበረበት ወቅት አልፎ አልፎ
ከካምፕ እንወጣና ለመዝናናት ስንል አጥር
ዘለን እንወጣ ስለነበርና የእኛ ክለብ ም/ጦር
ደግሞ የሚሊቴሪ ቡድን ስለሆነ በዲስፕሊን
ላይ ያለው እርምጃ ጠንካራ ስለነበር በእዚያ
ድርጊታችን እኔን ጨምሮ አምስትና ስድስት
የምንደርስ ተጨዋቾች የታሰርንበት ጊዜ
ነበር፤ ክለባችን እኛ ላይ ክትትል ያደርግ
የነበረው በወቅቱ መሸነፍና አቻ መውጣት
ፈፅሞ አይፈልግም ስለነበር ነው፤ ለእዚያም
ከካምፕ እንድንርቅ አይፈለግም ነበርና እኛ
አልፎ አልፎ ያንን ትእዛዝ ስናልፍ ተይዘን
እስር ቤት እንገባ ነበርና ያ እስር በተደጋጋሚ
አጋጥሞኛል፡፡
-የም/ጦር ክለብ ውስጥ የእስር ውሳኔ
ሲገጥማቸው ይቀጡት ስለነበረው፡-የም/ጦር
ተጨዋች እያለንና ስንታሰር በጊዜው እኛ
ላይ የሚደርስብን ቅጣት በጠዋት በበርሜል
በተሞላ ቀዝቃዛ ውስጥ ነበር የምንነከረው፤
ከዚያ ደግሞ በሰርቪስ ወደ ልምምድ ሜዳም
እንሄድና የቁጭ ብድግም ምንም እንኳን
የስፖርት ልምምድ ቢሆንም እንደ ቅጣት
ተቆጥሮብን ለረጅም ሰአታት እስኪደክመን
ድረስ እንሰራም ነበር፡፡
–አግኝተህ ማጣት የማትፈልገው፡- ፈጣሪ
ይመስገን አግኝቼ ያጣሁት ነገር የለም፤
ጤናዬን ቤተሰቦቼንና የኢትዮጵያ ህዝብን
አግኝቻለሁ፡፡
–በአሁን ሰአት ስለተሰማራህበት ሙያ፡
–የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በተጨዋችነት
ሙያ እንዳሳለፍኩ ሁሉ በአሁን ሰአት ላይ
ደግሞ በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት በማገልገል
የአገሬን እግር ኳስ ከፍ ያለ ደረጃ ለማድረስ
ጠንክሬ እየሰራሁ ነው፤ በግብ ጠባቂነቱ
ሙያ እስካሁን ድረስ በመከላከያ ክለብ
ውስጥ ለ6 አመታት ቆይቼ አስልፌያለሁ፡
፡ በወልድያ ከተማና በሰበታም እንዲሁ
ሰርቼ አሳልፌያለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግም
የኢትዮጵያ መድን ግብ ጠባቂ አሰልጣኝ
ሆኜ እየሰራሁ ነውና ለእዚህም ፈጣሪዬን
በምወደው ሙያ ላይ ስላቆየኝ ማመስገን
እፈልጋለሁ፡፡