በ8ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ 7ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል ሶዶ ስታዲየም ላይ ወላይታ ድቻ ከስሑል ሽረ ያገናኘው ጨዋታ ይጠቀሳል። በዚህ ጨዋታም ስሑል ሽረ 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ከጨዋታው በኋላም አሰልጣኞቹ አስተያየት የሰጡ ሲሆን የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ገ/ክርስቶስ ቢራራ ዛሬ ያከናወኑት ጨዋታ በወላይታ ድቻ አሰልጣኝነት የመጨረሻ ጨዋታቸው እንደሆነ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ “በክለቡ የቦርድ ሀላፊዎች ውሳኔ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ በወላይታ ድቻ አሰልጣኝነቴ አልቀጥልም።” ብለዋል። አሰልጣኙ አክለውም “በባለስልጣናቱ የሁለት ጨዋታ እድል ተሰጥቶኝ ነበር። እሱ በመጠናቀቁ ስራዬን ልለቅ ነው።” ብለዋል።