በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረጉ 4ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል ሁሉም ጨዋታዎች ክልል ላይ የሚደረጉ ነው የሚሆነው።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ወልዋሎ አ.ዩ.
ድሬ ላይ 9:00 ሲል የሚጀምረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በውጤት ቀውስ ውስጥ እንደመገኘታቸው የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ የሚደረግ በመሆኑ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ ያደርገዋል። ማድረግ ከሚገባው 14ጨዋታዎች 13ጨዋታዎችን ያደረገው ድሬዳዋ ከተማ በተከታታይ የጣላቸው ነጥቦች ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንዲገኝ አድርጎታል። ወልዋሎ አ.ዩ. ከአሰልጣኝ ብርሀኔ ገ/እግዚአብሔር ስንብት በኋላ እንደ አጀማመሩ መሆን ተስኖት የነበረ ቢሆንም በ14ኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ላይ ያስመዘገበው የ1-0 ውጤት ደረጃውን ወደ 10ኛ እንዲያሻሽል ረድቶታል። ድሬዳዋ ከተማ በ10ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ወልዋሎ አ.ዩ. በአንፃሩ በ16 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
አዳማ ከ ጅማ አባጅፋር
በሌላ የሊጉ የ9:00 ጨዋታ አዳማ ላይ የሳምንቱ ትልቅ ጨዋታ በኦሮምያ ደርቢ አዳማ ከተማ ከ ጅማ አባጅፋር የሚጫወቱ ይሆናል። በሊጉ ጅማሬ የነበረበትን ድክመት በማሻሻል 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለው ጅማ አባጅፋር በ14ኛው ሳምንት ሽንፈት ያላስተናገደውን መሪውን ደደቢትን ከሜዳው ውጪ ተጉዞ 2-1 በማሸነፍ ጣፋጭ 3ነጥቦች ማስመዝገብ ችሏል። ሆኖም ግን ዛሬ ወደ አዳማ ተጉዞ የሚያደርገው ጨዋታ ቀላል ይሆንለታል ተብሎ አይጠበቅም። ለዚህም ዋና ምክንያት ሊሆን የሚችለው አዳማ ከተማ ሜዳው ላይ ያለው ጥንካሬ እና ወቅታዊ ብቃቱ ጥሩ ሆኖ መገኘቱ የተገኔ ነጋሽን ቡድን ጠንካራ ያሰኘዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ ቡድኖች በ1 ግብ ክፍያ ብቻ ተበላልጠው በእኩል 21ነጥቦች 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ መገኘታቸው ጨዋታውን በጉጉት እንዲጠበቅ ያደርገዋል።
ሲዳማ ቡና ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ
ይርጋለም ላይ የሚደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ2 የተለያየ የውጤት ጉዞ ላይ የሚገኙ ቡድኖች እንደመሆናቸው ዛሬ የሚመዘገበው ውጤት ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ መናገር ይቻላል። ሲዳማ ቡና ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖት አንድ ጊዜ ከፍ አንድ ጊዜ ደግሞ ዝቅ እያለ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአንፃሩ በውጤት ቀውስ ውስጥ ሆኖ ድል ማስመዝገብ ከተሳነው ሰነባብቷል። በዚህም ማግኘት ከሚገባው 36ነጥቦች 9ኙን ብቻ አሳክቶ የሊጉ ግርጌ ላይ ሊቀመጥ ችሏል። ሲዳማ ቡና በበኩሉ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ በ8 ነጥቦች ከፍ ብሎ በ17 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ፋሲል ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ
- ማሰታውቂያ -
አዞዎቹ ነገ ወደ ጎንደር ተጉዘው የአንደኛ ዙር የመጨረሻ የኢትዮጵያ ፕርምየር ሊግ ጨዋታቸውን ከ ፋሲል ከተማ አቻቸው ጋር የሚያደርጉ ሲሆን በ14ኛው ሳምንት አርባምንጭ በአለልኝ አዘነ ብቸኛ ግብ ሜዳው ላይ ድሬዳዋ ከተማን ሲያሸንፍ ፋሲል ከተማ በአንፃሩ ወደ አ/አ ተጉዞ በኢትዮጵያ ቡና 3-2 በሆነ ጨዋታ መሸነፉ ይታወሳል፡፡ ፋሲል ከተማ በሊጉ ከመሪው ደደቢት በ6ነጥቦች በመራቅ በ19ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ በ13ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አዞዎቹ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ከወራጅ ቀጠናው ሙሉ ለሙሉ ወጥተው የሊጉን የመጀመሪያ ዙር የመጨረስ እድል ይኖራቸዋል።