የኢትዮጵያ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ሉሲዎቹ በኡጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የመጀመሪያው የሴካፋ ውድድር ላይ ተካፋይ በመሆን ሲወዳደሩ ቢቆዩም እንደተጠበቁት ግን ዋንጫውን ማንሳት አልቻሉም፤ የሉሲዎቹ የእዚህ ውድድር ተሳትፎም አዘጋጇን ሀገር ኡጋንዳን 4-1 በማሸነፍ ሊጠናቀቅ ችሏል፤ ለሉሲዎቹ ዛሬ በተደረገው ጨዋታ የድሉን ግቦች ያስቆጠሩት ሀትሪክ በመስራት ረሂማ ዘርጋ እና ሎዛ አበራ ደግሞ ቀሪውን በማስቆጠር ነው፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዘንድሮ ተሳትፎአቸው በምድባቸውም ባደረጉት ጨዋታ ሩዋንዳን ሎዛ አበራ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦችና መስከረም ካንኮ ባገባችው አንድ ግብ 3ለ2 አሸንፈው ከታንዛኒያ ጋር ደግሞ ያለግብ አቻ የተለያዩ ሲሆን ለፍፃሜ ለማለፍ እሁድ ዕለት ከኬኒያ አቻቸው ጋር ባደረጉት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ደግሞ ሎዛ አበራ በድጋሚ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች 3ለ2 በሆነ ውጤት መሸነፋቸው በአፍሪካ አህጉር በእግር ኳሱ ካላቸው ጅማሮና ጥንካሬ አንፃር እንደዚሁም በቡዙዎች ከሚሰጣቸው ከፍተኛ ግምት አንፃር የሴካፋን ዋንጫ የማግኘት ህልማቸውና ተስፋቸው ሊያከትም መቻሉ ሁሉንም ሊያሳዝን መቻሉ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን በኬኒያ በግማሸ ፍፃሜ ተሸንፈው ከወደቁ በኋላ የመጨረሻ የሚባለውን ጨዋታቸውን ለደረጃ በዛሬው እለት ከአዘጋጇ አገር ኡጋንዳ ጋርም አድርገው 4-1 ማሸነፋቸው ከፍፃሜው የኬኒያ እና የታንዛኒያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ጨዋታ በኋላ የነሐስ ሜዳሊያ የሚያሸልማቸው ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዛሬ ለደረጃ የገጠመውንና ያሸነፈውን የኡጋንዳ የሴቶች ብሄራዊ ቡድንን ከእዚህ ቀደም ማለትም ከ15 ዓመታት በፊት በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ተገናኝተን የነበረ ሲሆን ያኔም የኢትዮጵያ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን በሜዳው 2ለ0 በማሸነፍና ካምፓላ ላይ ደግሞ 2ለ2 ከተለያየ በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ይታወሳል፡፡
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ተሳትፎው ሶስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን ቡድኑ አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት በውድድሩ ላይ ስላደረጋቸው ፍልሚያዎች የጨዋታ ፊልሞችን ፈልጎ ይዞ በመምጣት በጨዋታው ዙሪያ ስለነበረን ጠንካራ እና ደካማ ጎን በመነጋገር ባለሙያዎችን በመጋበዝ ከእዚህ ቀደም የነበሩትን መሸፋፈኖች ወደኋላ አስቀርተን ያለምንም መሸፋፈን ጥልቅ ውይይት ሊደረግበት ይገባል፤ ያን ስናደርግም እግር ኳሱ ላይ ለውጥ ይመጣል፡፡
ሉሲዎቹ በሰላም ወደ ሀገራችሁ ግቡ