“ የእግር ኳሱ የተጨዋችነት ዘመኔ በደስታ የተሞላ
ነው፤ በርካታ ስኬቶችን በሀገር ውስጥ ባለገኝም
በየመን ሊግ ማጣጣሜ አሁንም ድረስ ያስደስተኛል”
– “በፈንጂ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኝ በሕይወት
- ማሰታውቂያ -
መትረፌ አምላኬን እንዳመሰግን አድርጎኛል”
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመኑ ላይ በክለብ ደረጃ ለኢትኮ፣ ለአዳማ
ከተማ ለኢትዮጵያ ቡናና በየመን ሊግም ለአልአህሊ ተጫውቶ ያሳለፈው ተደናቂው
ምርጡ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ብርሃኑ ቃሲም በብዙዎች የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች
አጠራርም በሚታወቅበት የቅፅል ስሙ “ብሬ መድሃኒቴ” የተጨዋችነት ዘመኑ ላይ
በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ተጨዋች ሆኖ ያሳለፈ ሲሆን የአሁን ሰአት ላይ ኳስን
ካቆመ በኋላ ወደ ግል ህይወቱ በማምራት የራሱን የስፖርት ትጥቅ ቤት ከመክፈት ባሸገር
በመስኖ ስራም ላይ ተሰማርቶ ህይወቱን እየመራ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደረጃ
ለአዳማ ከተማና ለኢትዮጵያ ቡና ክለቦች ተጫውቶ ያሳለው ብርሃኑ ቃሲም ኳስ ከቆመ በኋላ
ወደፊት ከሙያው ላለመራቅ ሲል ወደ አሰልጣኝነቱም የመምጣት ከፍ ያለ ፍላጎት እንዳለው
እየገለፀ ሲሆን ተጨዋቹን የቀድሞው የእግር ኳስ ተጨዋቾችን በምናስታውስበት የOldies
but Goodies አምድ ላይ የዛሬው እንግዳ አድርገነው አቅርበነዋልና፤ ተከታተሉት:
-ስለትውልድ ስፍራውና እድገቱ፡-
የትውልድ ስፍራዬ ዝዋይ /ባቱ/ ነው፤ ዝዋይን
በኳሱ ደረጃ ስለእውቅናዋ ብዙም ባልገልፃትም
ለኑሮ በጣም ምርጥ የሆነችና የሐይቅም ሀገር
ነች፤ እዚያም ነው የተመራኩት፤ ከህፃንነቴ
እድሜዬም ጀምሮ የእግር ኳስን እንደብዙዎቹ
የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾችም ነው የጨርቅ
ኳስን በማንከባለል መጫወት የጀመርኩትና
የአስተዳደጌ ሁኔታዬ ይህን የመሰለና
በአብዛኛውም ከኳስ ጋርም የተያያዘም ነው፡፡
–የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ
በምን ሙያ ላይ ትገኝ እንደነበርና ወደ ኳሱ
በመግባትህ በቤተሰብህ አካባቢ ስለነበረው
አመለካከት፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ለመሆን
ነበር በወቅቱ የተፈጠርኩት ከእዚያ ውጪ
ስለምንም ነገር አስቤም ሆነ ተጨንቄም
አላውቅምና የእጣ ፈንታ ጉዳይ ሆኖ ነው
በጣም የማፈቅረውና ከልቤ የምወደውም
የእግር ኳስ ተጨዋች ለመሆን የቻልኩት፤
የእግር ኳስ ተጨዋችነት ውስጥ በመግባቴ
ከልጅነቴ ጀምሮ እንደቡዙዎቹ ተጨዋቾች
ፈቃዱ ባይኖርም እኔ ላይ ግን ምንም አይነት
ጫና አልነበረብኝምና ለእዚያም ነው ኳሱን
በጥሩ ሁኔታም ልጫወት የቻልኩት፡፡
–ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነት ሕይወት
በምን መልኩ እንደገባ፡- የኢትዮጵያ እግር
ኳስ የተጨዋችነት ሕይወት ውስጥ ገብቼ
የምወደውን ኳስን ለመጫወት የቻልኩት
በቅድሚያ የትውልድ ክልሌ ዝዋይ ላይ ልጅ
ሆኜ ለኢትኮ ታዳጊ ቡድን በኃላም ለዋናው
ቡድኑ አድጌ በመጫወት ነው ፡ ፡
በመቀጠልም በክልል ጨዋታ ላይ ለዞኑ ምርጥ
የኦሮሚያ ክልል በሚያዘጋጀው ውድድር ላይ
የምስራቅ ሸዋን ወክዬ በመጫወት ነው፤
ከእዚያም ውድድሩ ላይ ባሳየሁት ጥሩ የሆነ
ብቃት ለአዳማ ከተማ ክለብ ተመረጥኩና
ገባሁ ይሄም ነው የእኔ የእግር ኳስ ጨዋታ
አጀማመር፡፡
–በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ በጣም
የተደሰተበት ቀን፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ውስጥ በተጨዋችነት ዘመኔ በመምጣት
ከፍተኛ ደስታን ከተጎናፀፍኩባቸው ጊዜያቶች
መካከል ሁሌም የቅድሚያ ደረጃን የምሰጠው
የ999ዎቹ የጅማሬ ዓመታቶች ላይ የአዳማ
ከተማን ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ
ያስገባንበትን ወቅት ሲሆን ሌላው ደግሞ
የድሬዳዋ ከተማ ላይ በተካሄደው የእዚሁ
ውድድር ላይ እኔም ባለቀ ሰዓት የም/ባቡር
ላይ ያስቆጠርኳት የማሸነፊያ ግብ ነበረችኝና
እነዚያ ሁሌም ያስደስቱኛል፡፡
-በእግር ኳስ በጣም ያዘነበትና ልቡ
የተሰበረበት ቀን፡- የእግር ኳስን ስጫወት
በጣም ካዘንኩባቸው ጊዜያቶች መካከል
መቼም ቢሆን የማልረሳው የአዳማ ከተማ
ክለብ ከ4 ዓመታት በፊት ከፕሪምየር ሊጉ
የወረደ ወቅት ነው፤ የእዚያን ጊዜ በቡድኑ
ውስጥ ለክለቡ ውጤት ማጣት ብዙ ጥሩ
ያልነበሩ ጉዳዮችም ታይተዋልና ያኔ ክለቡን
በጣም ከመውደዴ የተነሳ ቡድኑ ሲወርድ
ልቤም በሀዘን ተሰብሯልና ይህንን ወቅት
ፈፅሞ አልረሳውም፡፡
-የአዳማ ከተማ ተጨዋቾች ላይ በአንድ
ወቅት ስለደረሰው የፈንጂ አደጋና እሱም
የእዚያ አደጋ ቁስለኛ ሆኖ ስለማሳለፉ፡-
ጊዜው 18 ዓመታት ያለፈውና የ1992 ዓ.ም
ላይ ይመስለኛል፤ በእኛ የአዳማ ከተማ 6 እና
7 የምንደርስ ተጨዋቾች ላይ የፈንጂው አደጋ
የደረሰው፤ ቦታው የአዳማ ፖስታ ቤት አካባቢ
አሰብ ሆቴል ጋር ነበር ድንገት እኛ ተጨዋቾች
ሻይ ቡና እያልን ሳለ በወቅቱ የመነሻው
ምክንያት ያኔ ብዙ ነገር ቢባልም አሁንም
ድረስ ፈፅሞ በማናውቀው ሁኔታ ግን ፈንጂው
ፈንድቶ በእኔ፣ በግብ ጠባቂያችን ሱራፌል፣
በዳንኤል ተክሉ፣ በመስፍን ጌታቸው /ትንሼ/፣
የጅማ ልጅ በሆነው የቡድናችን ተጨዋች
በመሐመድ ላይ ነው ጉዳቱ የደረሰው፤ ከእኛ
ጋር ያኔ ከነበሩት ተጨዋቾች መካከል ይታገሱ
ብቻ ነው ከአደጋው አምልጦ የተረፈው፤ ያን
ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሼ ሁኔታውን አሁን
ድረስ ሳስታውሰው በጣም ነው የማዝነው፤
የእዚያን ወቅት አደጋው እኔን ለ6 ወር ያህል
ከፈነዳው ፈንጂ ውስጥ የወጡ 3 ፍንጥርጣሪ
ቁርጥራጭ ብረቶች ሆዴ ውስጥ ገብተው
በኦፕራሲዮን ነበር የወጣልኝና ያኔ ሁላችንም
በፈጣሪ ፈቃድ ከሞት የተረፍንበትም ጊዜ
ስለነበር የአደጋውን ከፍተኛነት አሁንም ድረስ
ፈፅሞ አልረሳውም፡፡
-ብርሃኑ የእግር ኳስን ከማን ጋር
ሲጫወት ይመቸዋል፤ ማን ከጎኑስ ጋር
እንዲኖር ነበር የሚፈልገው፡- የኢትዮጵያ እግር
ኳስ ውስጥ ከአጠገቤ ሲጫወት የቅድሚያ
ደረጃን ሰጥቼው በጣም የሚመቸኝ ተጨዋች
ቢኖር የአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ እያለሁ
በችሎታው በጣም አደንቀው የነበረው መስፍን
ጌታቸው /ትንሼ/ ነበር፤ ሌሎች ተጨዋቾችም
በመቀጠል አሉ፤ ከእነዚሁም መካከል ከባንኮች
ክለብ በመምጣት ቡድናችንን የተቀላቀለው
አለማየሁ ደስታና ሌላው ተጨዋች ሰብስቤ
ደፋርም ለእኔ ከጎኔ ሆነው እንዲጫወቱ
የምፈልጋቸው ምርጥ ተጨዋቾች ነበሩና
እነሱ ናቸው ዋንኛ ምርጫዎቼ፡፡
-በጨዋታ ዘመኑ ስለሚያደንቀው
ተጨዋች፡- ነፍሱን ይማረውና የእግር ኳስን
ሊያቆም ሲል ትንሽ የደረስኩበት፣ በጣም
በሚወዱትም የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች
ዘንድ ‘‘አሴ አሴ ጎል” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት
ሲዘመርለት የነበረው አሰግድ ተስፋዬ ጂረስ
ለእኔ እሱን ሲጫወት ከተመለከትኩበት ጊዜ
ጀምሮ በጣም የማደንቀው ተጨዋች ነውና
እሱ ነው ምርጫዬ፤ አሰግድ የአጥቂው
ስፍራ ላይ ጎል እንዴት ማስቆጠር እንዳለበት
አሳምሮና አህምሮውንም አሰርቶ በተግባርም
የሚያውልም ተጨዋች ነበርና የእሱ በጣም
አድናቂው ሆኜም ነበር የእግር ኳስን
ስጫወት የነበርኩት፡፡
-የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ የሚለው
አሰልጣኝ፡- የእግር ኳስን ስትጫወት ስለምርጥ
አሰልጣኞች የራስህን ሚዛን በማስቀመጥ
የምታደንቀው የራስህ የሆነ ምክንያት አለህ፤
ያም በመሆኑም እኔም የእግር ኳስ ተጨዋች
ሆኜ ብቅ ስል ካሰለጠኑኝ አሰልጣኞች ውስጥ
የመጀመሪያውን ስፍራ ሰጥቼው የማደንቀው
አሰልጣኝ ቢኖር በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ
ስጫወት በኃላፊነት የመራኝን አሰልጣኝ
ብርሃኔ ገ/እግዚአብሄር ነው፤ ብርሃኔ
የሙያው ቆይታ ላይ ከጥሩ ስልጠናው ባሻገር
የእግር ኳስ ተጨዋቾች በምንም መልኩ
እንዳይጨናነቁ የሚያደርግበትና የልምምድ
አሰጣጡንም ከኳስ ጋር በተያያዘ ለተጨዋቾች
በሚመች መልኩም የፕሮፌሽናል መንገድን
በመከተል ያሰለጥን አሰልጣኝ ስለነበር እሱ
በጣም የሚመቸኝና የማደንቀው አሰልጣኝ
ነበር፡፡
-ከባህር ማዶ የሚያደንቀው ተጨዋች፡
– ኦ! ብራዚላዊው የቀድሞው የአጥቂ ስፍራ
ተጨዋች ሮናልዶ ሉዊስ ናዛሪዮ ዴሊማ ለእኔ
የሁልጊዜም ምርጡ ተጨዋች ነው፤ አሁን
ላይ ኳስ ካቆመ ጊዜያቶችን ቢያስቆጥርም
እሱን ወደፊትም ሳደንቀው እኖራለሁ፡፡
-ከባህር ማዶ በአሰለጣጠኑ ቀልቡ
የወደደው አሰልጣኝ፡- አሁን ላይ ፔፕ
ጋርድዮላን፤ ለእሱ ልዩ አድናቆትም ነው
ያለኝ፡፡
-ለብርሃኑ የዓለማችን ምርጡ ክለብ፡-
ሪያል ማድሪድ ነዋ!
–ብርሃኑ ራሱን በ3 በተመረጡ ቃላቶች
ሲገልፅ፡- ምላሹን ለመስጠት ከባድ ጥያቄ
ቢሆንም ግን የግድ ልመልስ፤ ሁሌም ነገሮችን
አድበስብሶ ማለፍ አይመቸኝምና ፊት ለፊት
ነው የምናገረው፣ ከሰዎች ጋር እግባባለሁ፣
የማህበራዊ ኑሮም በጣም የሚመቸኝ አይነት
ሰው ነኝ፡፡
–የእግር ኳስ ተጨዋች ሆነህ በማለፍህ
ምን ትርፍ አግኝተሃል፡- በገንዘብ ደረጃ
ያንን ያህል ዳጎስ ያለና ብዙ የሚባል ብር
ባላገኝም ከገንዘቡ የበለጠ ግን ትልቅ ነገርን
በእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወቴ ለማግኘት
ስለቻልኩ በእዚህ በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡
፡ የሰው ፍቅር ከገንዘብ ይበልጣል፤ የሰው
ፍቅርና አድናቆትም ነው እኔን ለእውቅናና
ለከፍተኛም ደረጃ ያበቃኝ እንዲሁም ምርጥ
የሆነ ቤተሰብንም እንድመሰርት ያስቻለኝና
በእዚህ ባገኘሁት የሰው ፍቅር እውቅናና ዝና
ሁሌም ደስተኛ ነኝ፡፡
-የጨዋታ ዘመኑ ምርጡ ግብ፡- የድሬዳዋ
ከተማ ላይ ከምድር ባቡር ጋር ባደረግነው
ጨዋታ ወቅት ነበር 2-2 የነበርንበት ሰዓት
ላይ ከመሃል ሜዳ በቀጥታ ኳስዋን በመምታት
በጥሩ ሁኔታ ግቧን ያስቆጠርኳት፤ ያቺ ግብ
ክለባችንን አዳማ ከተማንም ለድል ያበቃች
የማሸነፊያ ጎልም ነበረች፤ በእዚያ ወቅት ላይ
ግቧን በማስቆጠሬም በሴኖትራክ ወደ ድሬዳዋ
በመጓዝ ሲያበረታቱን የነበሩትን የቡድናችን
ደጋፊዎችም ጮቤ ያስረገጠጭ አንድአንዶቹም
ደስታቸውን ከመቆጣጠር ባለፈ መልኩም
አሸዋ እስከመቃም የደረሱበት ሁኔታም
ስለነበር የእኔ የምንጊዜውም ምርጧ ግቤ ያቺ
ነበረችና እሷን መቼም ቢሆን አልረሳትም፡፡
-በጨዋታ ዘመኑ ሲያስቸግረው የነበረው
ተጨዋች፡- የኤሌክትሪኩን አፈወርቅ ኪሮስ
ፈፅሞ አልረሳውም፡፡ እሱን ሁሌም የፕሪምየር
ሊጉ ጨዋታዎችን ላይ እኛ አዳማዎችና እነሱ
ስንጫወት ከስር ከስሬ በመከተል እኔን ማርክ
የሚያደርግ እየመሰለ ዳኛ ሳያየው በጉልበቱ
በተደጋጋሚ ጡንቻዬ ላይ ይመታኝ ስለነበር
እሱ በጣም ያስቸግረኝ ነበር፡፡ የአንድ ወቅት
ጨዋታ ላይ እንደውም በተለይ እሱ ሲመታኝ
መጫወት አቅቶኝ የወጣሁበት ግጥሚያም
ነበርና ያንን ጊዜ በጣም የማስታውሰው ነው፡፡
-አብረኸው ባለመጫወትህ የሚቆጭህ
ተጨዋች፡- ብዙ ጊዜ ዮርዳኖስ አባይ ጋር
በክለብ ደረጃ እዚህም ሆነ የመን በነበርንበት
ጊዜ ከእሱ ጋር መጫወትን አጥብቄ እፈልግ
የነበረ ቢሆንም ያንን ባለማሳካቴ በጣም
ይቆጨኛል፤ ከዮርዳኖስ ጋር በታዳጊና
በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ግን የተገናኘንበት
ወቅት ነበር፡፡ ከእሱ ጋር ብዙ ጊዜ በክለብ
ደረጃ ተቃራኒ ሆነን ነው የተጫወትነው፤
ሌላው ፈፅሞ በምንም ደረጃና መልኩ አብሬው
ያልተጫወትኩት ተጨዋች እና መጫወት
እየፈለግኩ ያላገኘሁት ተጨዋች ቢኖር
የቅዱስ ጊዮርጊሱ የቀድሞው የአማካይ ስፍራ
ተጨዋች ሙሉ አለም ረጋሳ ነው፡፡ ከሙሉ
አለም ጋር የአዳማ ከተማ ተጨዋች ሆኜም
የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች ሆኜም በጣም
ተቃራኒና ባላንጣ ፈፅሞ በማንስማማ ቡድን
ውስጥም ተቀናቃኝ በሆነ መልኩ ነው እሱን
ላገኘው የቻልኩትና ከእሱ ጋር በአንድ ላይ
ብጫወት ኖሮ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡
–የአዳማ ከተማ ተጨዋች ሆነህ በማለፍህ
ዛሬ ላይ ምን ይሰማሃል፡- የአዳማ ከተማ
ክለብ የእግር ኳስ ተጨዋችነት ቆይታዬ
ለእኔ ረጅመን ጊዜ ያሳለፍኩበትና አሁንም
ድረስ በጣምም የምወደውም የቀድሞ
ክለቤም ስለሆነ እዚያ የነበረኝ ጊዜ በጣም
ጥሩ የነበረ ነው፤ እዚህ አገር ላይ ሳለው
የተጨዋችነት ዘመኔ ላይ ብዙ ክለቦች ውስጥ
ገብቼ አልተጫወትኩም፡፡ ኢትዮጵያ ቡና
ገብቼ ብቻም ነው ለአንድ አመት ያህል ብቻ
የተጫወትኩትና የፉትቦል ህይወቴ በአብዛኛው
ያለቀው በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ ነው፡፡
ስለዚህም በክለቡ ተጫውቼ በማለፌ በጣም
ደስተኛ ነኝ፡፡
–የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥም ሆነህ
የየመን እግር ኳስ ውስጥ ተጫውቶ በማለፉ
በዋናነት ስለተሰማው አስደሰች ስሜት፡-
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥም ሆነ በየመን
የተጨዋችነት ዘመኔ ብቅ ብዬ መጫወት
ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ የእኔ ትልቅ የደስታ
ጊዜያቶች ብዬ የምጠቅሳቸዉ ነገሮች ሁሌም
በምጫወትባቸው ክለቦች ውስጥ የቋሚ
ተሰላፊ ሆኜ ልጫወት መቻሌና ክለቦቹን
በጥሩ ሁኔታ ያገለገልኩኝ መሆኔን ነው፤
የእግር ኳሱ ላይ ተጠባባቂ ተጨዋች ሆኜ
ስላላለፍኩም መቼም እንዳልከፋ አድርጎኛል፡
፡ የእዚያ ስሜት አሁንም ኳስ አቁሜ ሁሉ
አብሮኝ ያለ ጉዳይ ነው፡፡
–የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ገብቶ
ስለመጫወቱና የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ
አንድም ጊዜ ከተጫወተባቸው ክለቦች
ጋር ያላነሳ ስለመሆኑ፡- የኢትዮጵያ ቡና
ክለብ ውስጥ ለአንድ ዓመት ቢሆንም ገብቼ
የተጫወትኩበት ወቅት ለእኔ አሁንም ድረስ
አይረሳኝም ምርጥና ፍቅር የሆነ ጊዜንም
ነው ያሳለፍኩት፤ ቡና ገብተህ ስትጫወት
ሁሌ በተለይ ትልቁን ደስታ የሚፈጥሩልህ
ደጋፊዎቹ ናቸው እነሱን ለማስደሰትም ብለህ
ነው የምትጫወተው፤ ቡና ጋር ስትጫወት
ከሌላው ይለያል፤ ለአሰልጣኝ ለኮሚቴ ብለህ
ኳስን አትጫወትም ለራስህ እና ዝናንም
ለማግኘትም ነው የምትጫወተውና እኔ ጥሩ
ጊዜን ነው ያሳለፍኩት፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ
በተጨዋችነት ዘመኔ የተጫወትኩት እኔን
ለከፍተኛ እውቅናና ዝና ላበቃኝ የአዳማ
ከተማና ለአንድ ዓመት ያህል ደግሞ ለቡና
ነበር በእነዚህ ክለብ ቆይታዎቼም የሊጉን
ዋንጫ ልናነሳ የምንችልበት እድሎችንም
ለማግኘት ከጫፍ ደርሰን ያጣንባቸው
ጊዜያቶች አሉ የመጀመሪያው በአሰልጣኝ
ወንድማገኝ ከበደ የሃላፊነት ዘመን ቡድናችን
ሲሰለጥን በሁሉም ነገር ጥሩ ሆነን በጥቃቅን
የራሳችን ችግሮች የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት
ያልቻልንበትና በኋላም የሶስተኛ ደረጃን
በመያዝ ሊጉን ያጠናቀቅንበት ሲሆን ሌላው
ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናን በተቀላቀልኩበት
የ1996ቱ የፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ
ክለባችን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲጫወትና
2-2 ሲለያይ በጣም የማደንቀውና ትልቅ
ክብርም የምሰጠው ኢንተርናሽናል አልቢትር
ኃይለመላክ ተሰማ ለእኔ በትክክል የእነሱ
የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት
ተፈፅሞብኝ የፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለን
በእዚያ ጨዋታ ምን አልባት የፍፁም ቅጣት
ምቱ ተሰጥቶን ቢሆን ኖሮ ያን ግብ ብናገባ
የሊጉን ዋንጫ የምናነሳበት እድሉ ሊኖረን
የሚችልበት ሁኔታው ነበረና ያን አልረሳውም፡
፡ እንደዚሁም ደግሞ የክለባችን ውስጥም
በነበሩት አንዳንድ ችግሮችም የሊጉን ዋንጫ
ያጣንበትና ያንን ዋንጫም በስተመጨረሻም
የሐዋሳ ከተማ ክለብ እንዲያነሳ የተደረገበት
ጊዜ ነበርና ይህንን ወቅት መቼም ቢሆን
የማልረሳውና ሁሌም ቢሆን የሚቆጨኝም
ነው፡፡
–ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተከፈለው ደምወዝ፡
– የኢትኮ ክለብ ተጨዋች እያለሁ ከቢ ቡድኑ
ወደ ዋናው ቡድን ሳድግ ያገኘሁት የ200 ብር
ነው፡፡
-ለመጀመሪያ ጊዜ ደምወዙን ሲያገኝ
ስለተሰማው ስሜት፡- ያኔ ለመጀመሪያ
ጊዜ የ200 ብር ደምወዝ ሲከፈለኝ ለእኔ
ብዙ ትርጉም ነበረው፤ ብሩም ዋጋ ነበረው
ብሩንም ለእናቴ በመስጠትም ነው ቤተሰቦቼን
በወቅቱ የረዳሁበት፤ ከእዚያን ጊዜ አንስቶም
ነው የማገኛቸውን ጥቅማ ጥቅሞች ለእነሱ
በመስጠት መርዳትን የጀመርኩት፡፡
–ዛሬ ለአንድ ተጨዋች ከ200 ሺህ ብር
በላይ የሚከፈልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፤ ዛሬ
ላይ ሆነህ ምነው በዚህ ዘመን ተጨዋች
በሆንኩ ብለህ ትመኛለህ፡- በፍፁም እንደዚህ
ብዬ አልመኝም፡፡ ሁሉም ነገር ከጊዜው
ጋር አብሮ የሚሄድ ነውና ያንን ነው ልል
የምችለው፤ እንደምኞት ቢሆንማ ኖሮ የአለም
ዋንጫን አሁን ላይ መጫወትም እፈልጋለሁ
እል ነበርና ሁኔታዎች ሁሉ ከሰአቱ ጋር
አብረው የሚሄዱ ናቸው፤ ፉትቦልን ደግሞ
አሁን ላይ በምን ደረጃ እንዳለህ ታውቃለህ፤
ተጨዋቾች እያገኙት ያለው ክፍያ ጥሩ ነው
የሚያገኙት ክፍያም የእግር ኳሱን ያነቃቃል
ስራዎችን በጣም ተበረታታው እንዲሰሩም
ያደርጋል፤ ያም ሆኖ ግን አሁን ላይ
የእግር ኳሱ ላይ ከሚከፈለው ክፍያ አኳያ
ስታየው ብዙ ለውጦች እየታዩ ያሉ
አይመስለኝም፤ ይሄ ደግሞ ሊሆን
የቻለው የእግር ኳሱ ከመነሻው
ከስሩ ሊስተካከል ባለመቻሉ ነው፡
፡ ከእዚያ መነሻነትም ሁሉም ጋር
የእግር ኳሱ ላይ የሚያታዩት
ችግሮችና ነገሮች መስተካከል
ይገባቸዋል፡፡ የክፍያው ሁኔታ
ከእግር ኳሱ እድገት ጋር አብሮ
የሚሄድ ቢሆንም ጥሩና የተሻለ
ነው እንደውም እኮ የክፍያውም
ሁኔታ የእኛ አገር ላይ ስለሆነ
እንጂ ብሩ ብዙ ሆኖ አይደለምና
እንደክፍያው ሁሉ የእግር ኳሱም
ላይ አይነተኛ ለውጥ ቢመጣ በጣም
ነው ደስ የሚለኝ፡፡
–ስለ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነት
የየመን ቆይታው፡- የኢትዮጵያ
እግር ኳስ የተጨዋችነት ዘመን
ቆይታዬን በማጠናቀቅ የፕሮፌሽናል
ተጨዋችነትን በየመን ላይ
ሳከናውን ጥሩ ወቅትን ነው
ያሳለፍኩት በእዚያ አገር ቆይታዬም ላይ
ሁለት ጊዜ የአገሪቱን የሊግ ዋንጫ፣ ሁለት
ጊዜ የጥሎ ማለፉን ዋንጫን ከማግኘትና አንድ
ጊዜም የአገሪቱ የኮከብ ግብ አግቢነትን ክብርም
በማግኘት የእግር ኳስን የስኬት ድሎች
ላጣጥም ችያለው፤ ከእዚህ ባሻገር በኤሽያ
ቻምፒዮንስ ሊግም የመጫወት እድልን
ያገኘሁበትም ጊዜ ስለነበር እነዚህ ሁሉ የእኔ
የደስታ ጊዜና ወቅቶች ናቸው፤ አሁንም ድረስ
እነዚያ ወቅቶች በትልቅ ደረጃ የሊግ ዋንጫን
ያነሳሁባቸው ጊዜያቶችም ነበሩና ሁሌም
ስደሰትባቸውም እኖራለሁ፡
–በቅፅል ስሙ ‘‘ብሬ መድኃኒቴ” ተብሎ
ስለሚጠራበት ስያሜና ማን እንዳወጣለት፡-
የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች ናቸው ይህንን ስም
ያወጡልኝ ብሬ መድሃኒቴ ሊሉኝ የቻሉትም
ክለቡ በሚያደርገው ጨዋታ ላይ ለአንድ
በሽታ የፈውስ መድሃኒት እንደሚገኝለት ሁሉ
እኔም ለክለቤ በወሳኝ ወቅትና ጨዋታዎች ላይ
እነሱ ሲጨናነቁ ጥሩ እጫወትና ጎልም አገባ
ስለነበር ፈውስ ስለሆንኩላቸው ነው በስሙ
ሊዘፍኑልኝ የቻሉት፤ በስያሜው ሲጠሩኝም
ልዩ ስሜትም ይፈጠርብኝም ነበር፤ እኔ
ክለቡን ከተቀላቀልኩበት የታዳጊነት እድሜዬና
ጊዜዬ አንስቶ በችሎታዬ ሲያደንቁኝና
ሲወዱኝ አሁንም ድረስ በማስታወስም ስሜን
የሚጠሩበት ሁኔታም ስላለ ለእነሱ ያለኝ
ክብር ከፍተኛ ነው፡፡ ሁሌም ሳደንቃቸውም
እኖራለሁ፡፡
–ስለባለውለተኛ ስፖርተኞች ምን
የምትለው ነገር አለ፡- የባለውለተኛ ስፖርተኞች
ለእዚህች አገር በክለብም ሆነ በብሄራዊ ቡድን
ደረጃ ለእዚች ሀገር ስላከናወኑትና ስለፈፀሙት
ብዙ ነገሮች ብዙዎቻችን በሚገባ እናውቃለን፤
ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሰዎች ዛሬ ላይ ከአቅም
ማጣት ጋር ተያይዞ ተረስተውና በየሜዳው
ወድቀው የቀሩ አሉና ያን ስታይ ስሜትን
ይነካል፡፡ አንዳንዴ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ
ከትልልቅ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመነጋገርም
የምናሳልፍበትም ወቅትም አለና የእነሱን
ሁኔታ ስትሰማው ሳይሆን ስታየው በጣም
ነው የምታዝነው፤ እነዚህ ባለውለተኞች ችላ
ባይባሉ በጣም ጥሩ ነው፤ የሚመለከታቸው
አካላቶችም በፍጥነት ለእነዚሀ መሰል ሰዎች
በመድረስ አንድ ነገርን ሊያደርጉለቸው ቢችሉ
በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡
–የ2 ቁጥር ማልያን ስለማድረጉ ምስጢር፡
– የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ስጫወት
የሁለት ቁጥር ማልያን ያደረግኩት የእግር
ኳስ ተጨዋችነቱ ላይ በመሃል ሜዳ ችሎታው
አደንቀው የነበረውና እኔንም ለመጀመሪያ ጊዜ
በትልቅ ደረጃ እንድጫወት ከስር በማሳደግ
አጫውቶኝ የነበረው የአሁኑ የቡራዩ አሰልጣኝ
አብዲ ቡሌ ይለብሰው ስለነበር ነው፤ ከእዚያ
መነሳሳትም ነው ቁጥሩን ያደረግኩት የአዳማ
ከተማ ክለብ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስገባ
2 ቁጥር ስላልነበር ከፊቱ ሁለት ቁጥር ብቻ
ስለነበር 20 ቁጥር የለበስኩበትም አጋጣሚም
አለ፤ በሀዋላ ላይ ግን 2 ቁጥር ተገኘልኝና
እሱን እስከመጨረሻ ድረስ አደርግኩት፡፡
–በጥሩና በድንቅ የእግር ኳስ ተጨዋችነቱ
የምናውቀው ብርሃኑ ቃሲም ኳስን መጫወት
ካቆመ በኋላ አሁን በምን ሙያ ላይ ተሰማርቶ
ይገኛል፤ ኳስንስ በምን ምክንያት አቆመ፡
– የእግር ኳስ ተጨዋችነቴን ያቆምኩት
ተጎድቼ፣ በቅቶኝና ፈልጌ ሳይሆን በአንዳንድ
ለእግር ኳሱ እንቅፋት በሆኑ ነገሮች እና
በራሴም የግል የሆኑ ጉዳዮች ነው እንጂ
ኳስን እንደቀድሞው መጫወት እችል ነበር፡
፡ ያም ሆኖ ኳሱን አቆምኩና ወደራሴ የግል
የሆነ ስራ ገባሁኝ የአሁን ሰአት ላይም የራሴ
የሆነ የስፖርት ትጥቅ ቤት መሸጫ ኖሮኝ
ስራን እየሰራሁ ነው፤ ከእዚያ ውጪም
የእርሻ የመስኖ ስራንም በመስራት ላይም
ነኝና በእዚሁ ስራ የቤተሰቦቼንም የራሴንም
ህይወት በጥሩ ሁኔታ እየመራሁም ነው፡፡
–ብርሃኑ ወደ አሰልጣኝነቱ ለመምጣት
ስላለው ፍላጎት፡- አዎን በጣም ከምወደው
የእግር ኳስ ሙያ ባልርቅ በጣም ነው ደስ
የሚለኝ፤ ለእዚያም አሁንም ድረስ የአዳማ
ከተማ ላይ የሚገኙት የቡድኑ ደጋፊዎችና
እንደ እነሱ የሚወዱኝ ሌሎች አካላቶች
ለምን ወደ ክለቡ ጠጋ ጠጋ ብለህ በሙያ
ለማገልገል አትመለስም እያሉም አሁንም
ድረስ ይጠይቁኛል ሆኖም ግን የራሴን የሆኑ
ጉዳዮችን ወደማስተካከል ሁኔታ ላይ ስለነበርኩ
ያንን ነግሬያቸው አሁን ስለጨረስኩ ክለቡን
ለማገልገል መምጣት እፈልጋለው እንግዲህ
ምርጫቸው የሚሆነው የእነሱ ነው፡፡
–የአሰልጣኝነት ኮርስን ስለመውሰዱ፡-
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ለአዳማ ከተማ
ክለብ ተጫውቼ ካበቃሁ በኋላ የአሰልጣኝነት
የመጀመሪያ ኮርስን ወስጃለሁ፡፡ አሁን ደግሞ
የሁለተኛ ኮርስ የሚሰጥበት ጊዜ ስለተቃረበ
ያንን ወስጄ ወደሙያው በመምጣት
በተጨዋችነት ዘመኔ የነበረኝን ልምድ ለአሁኑ
ጊዜ ተጨዋቾች ማካፈል እፈልጋለሁ፤ የእግር
ኳሱን ስትጫወት ማሳካት እፈልጋለሁ፡፡
ስለትዳር ሕይወቱ፡- የትዳር ሕይወትን
የመሰረትኩት የእግር ኳስ ተጨዋች ሆኜ
ነው፤ ለ14 ዓመታት ያህልም ከባለቤቴ
ሰሚያ ሁሴን ጋር ትዳሬን በጥሩ ሁኔታ
አጣጥሜ በመጓዝ አሁንም ድረስ በጥሩ
ሁኔታ እየኖርንም ነው፤ በእዚሁ የትዳር ጊዜ
ቆይታችንም ከባለቤቴ ሶስት ልጆችን ማለትም
የ13 ዓመት የ10 ዓመትና የ3 ዓመት ዕድሜ
ያላቸው አሮን ብርሃኑ ሀማር ብርሃኑና ራያን
ብርሃኑ የሚባሉ ልጆችንም አፍርተናልና
በእዚሁ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
–ቀረ የምትለው ነገር፡- የኢትዮጵያ እግር
ኳስ ላይ ኳሱን ተጫውቼ ሳሳልፍና እስካቆም
ድረስ ምርጥ የሆኑ የደስታ ጊዜያቶችን
አሳፌያለሁ፡፡ በእዚህ ሁሌም አምላኬን
አመሰግነዋለሁ፡፡ የእኔ የእግር ኳስ ህይወት
እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከጎኔ በመሆን ጥሩ
አስተዋፅኦ ላደረጉልኝ አካላቶች እና ለቤተሰቦቼ
በተለይ ደግሞ ለእኔ ከአጠገቤ ባለመጥፋት
አስፈላጊውን እንክብካቤ ታደርግልኝ
ለነበረችውና አሁንም አብራኝ ላለችው ሁሉ
ነገሬም ለሆነችው ውዷ ባለቤቴም ከፍተኛ
ምስጋናዬን ለማቅረብም እፈልጋለሁ፡፡
–በመጨረሻ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ላይ የአሁን ሰአት ላይ ለውጥን ለማምጣት
የተለያዩ አካዳሚዎችና የስልጠና ሁኔታዎች
በማመቻቸት የታዳጊ ወጣቶች ላይ ስራ
ለመስራት እንቅስቃሴዎች ሊጀመሩ ችለዋል፡፡
የእግር ኳሱ ላይ ለውጥ የሚመጣውም እዚያ
ላይ ሲሰራም ነው ተብሎም እየተነገረ ና
እየሰማን ነው፡፡ ለእኔ ግን ያ ብቻ ትክክለኛው
ምላሽ ነው አልልም በመጀመሪያ እዚያ ስልጠና
ውስጥ ከመገባቱ በፊት አሰልጣኞቹ ራሳቸው
በደንብ ሊማሩና ዘመናዊ በሆነ ሁኔታም
የእግር ኳስን ሊሰለጥኑም ይገባል፤ የስልጠና
አስፈላጊው እውቀቱ ሁሉ ሊኖራቸውም
ይገባልና ያለ እዚህ ሁኔታ ለውጥ ፈፅሞ
አይመጣም፡፡