ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪም ደሳለኝ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ፣CAF/ ፕሬዘዳንት አህመድ አህመድን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
ፕሬዘዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ የአፍሪካን እግር ኳስ ህዳሴን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅንጅት መሥራት ገልጸዋል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ በፍጠነት እያደገች በመሆኑና ፌዴሽኑም እግር ኳስ ከጨዋታነት በተጨማሪ የልማት አቀጣጣይና የአፍሪካ ወጣቶችን ኑሮ ማሻሻያ መሳሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ካለው ፍላጎት አንጻር ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናን መጫወት ይጠበቅባታል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ መንግሥት ለስፖርት ልማቱ በሰጠው ትኩረት መደመማቸውን የገለጹት የካፍ ፕሬዚዳንት እየተገነቡ ያሉ ስተዲየሞችና የስፖርት አካዳሚያዎች የጥረቱ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ካፍን/CAF/ በመምራት ለእግር ኳሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ታላቅ ኢትዮጵያዊና የአፍሪካ ልጅ መሆናቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ የሚገነባው የስልጠና ማዕከል በእሳቸው ስም እንዲሰየም ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ካፍ በሚያዘጋጃቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ውይይቶችና ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያ ተሳታፊ አለባትም ብለዋል የካፍ ፕሬዚዳንቱ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪም በበኩላቸው ኮንፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከካፍና ከፊፋ ጋር በመተባበር በዘርፉ አገራችን የሚገባት ሚና እንዲትጫወት በሚያደርገው ጥረት መንግሥት ማድረግ የሚችለውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የካፍ መስራች እንደመሆኗ መጠን በሚፈለገው መጠን መሆኗ የጠቆሙት ጠቅላይሚኒስትሩ ፤ ወደ ነበራት የመሪነት ቦታ ለመመለስ ጠንክራ እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራችን በአፍሪካ እግር ኳስን ካስተዋወቁት ጥቂት አገሮች አንዷ መሆኑን ገልጸው የተለያዩ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማስተናገድ የረዥም ጊዜ ልምድ ያላት እንደመሆኗ የተለያዩ ውድድሮችን በማስተናገድ አገራችን ብሎም አፍሪካን ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው የምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ አካዳሚ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ካፍ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ እምነታቸው መሆኑን የገነጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ፕሬዚዳንት ለሥራው የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል፡፡
ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ካፍን/CAF/ በመምራት ለእግር ኳሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው እውቅና የሚገባቸው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ከዚህ አኳያ መንግሥት ከኮንፌዴሽኑ ጋር በመተባበር ተገቢ እውቅና እንዲያገኙ የሚችለው ጥረት እንደሚያደርግም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡